ፋሲል ከነማ ( ዓፄዎቹ )የስፖርት ቡድን ብቻ ሳይሆን የነፃነት አርማ ነው – ዘነበ ዘ ቂርቆስ

እግር ኳስ በመላው አለም ተወዳጅ ስፖርት ነው በተለይ ኢትዮጵያውያን ለእግር ኳስ ያለን አመለካከት እጅግ በጣም የላቀ ነው እንኳን በአገራችን ኢትዬጵያ ውስጥ የሚደረጉት ውድድር ይቅርና በሌሎች አለማት የሚደረጉትን ውድድሮች በንቃት በመከታተል የሚወዳደረን የለም በተለይ ደግሞ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ መከታተል ብቻ ሳይሆን ቡድንም ኖሮት በከፍተኛ ሁኔታ ይደግፋል ። ለማንኛውም ይህን ያክል ካልኩ ወደተነሳሁበት ዋናው ጉዳዬ የፋሲል ከነማ ቡድን ትንሽ ልበል ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአንጋፋነታቸው የሚታወቁ ጥቂት የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የቅዱስ ጊዮርጊስ ብድንና የኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በደጋፊዎቻቸው ብዛት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው እኔም ከነዚህ ቡድኖች አንዱ የሆነው የቡና ቡድን ደጋፊ ነበርኩኝ አሁንም ከምኖርበት አገር ሆኜ የቡድኔን ውጤት ከአገር ቤት ካሉት ደጋፊዎች እከታተላለሁ ። እናም እነዚህ ቡድኖች በሚጫወቱበት ወቅት ስቴድየሙም ይሁን ሶሺያል ሚዲያው ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ሞቅ ደመቅ ይላል ። አሁን አሁን ግን ከነዚህ ቡድኖች ሌላ በተጨማሪ አንድ ቡድን በመላው ኢትዮጵያ አድናቆትንና ፍቅርን እያገኘ የደጋፊዎችም ቁጥር ከምንጊዜውም በላይ እየጨመረ ይገኛል ከነዚህም አዳዲስ ደጋፊዎች መካከል እኔና እኔን መሰል ኢትዮጵያውያኖች ዋነኞቹ ነን ይህ ቡድን በሰሜኑ አገራችን የሚገኘው የጎንደሩ ፋሲል ከነማ ( ዓፄዎቹ )ቡድን ነው ።

የፋሲል ከነማ ( ዓፄዎቹ )ቡድን መች እንደተመሰረተ መረጃው ባይኖረኝም ቡድኑ ግን ከተመሰረተ ረጅም እድሜ እንደሌለው እርግጠኛ ነኝ ሆኖም ግን ቡድኑ በአሁኑ ሰዓት በደጋፊዎች ብዛት አገሪቷ ውስጥ ካሉት ቡድኖች ግንባር ቀደምትነት ደረጃ ይዟል ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም ይህም የሆነበት ምክንያት በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ እግር አፍቃሪም ይሁኑ በሌሎችም እግር ኳስ ወዳድ ባልሆኑት ዘንድ ጭምር ቡድኑ እጅግ በጣም ተወዳጅ አድርጓታል ምክንያቱም ቡድኑ የኢትዮጵያውያን የነፃነት አርማ ተደርጐ ስለሚወደስ ጭምር ነው ። በተለይ ቡድኑ ከከተማው ውጭ በተለያዩ ከተሞች በእንግድነት በሚሄዱባቸው ከተሞች በአጠቃላይ በደጋፊ ብዛት ወደር የማይገኝለት ቡድን ሆኗል ህዝቡ ቡድኑን ከመደገፍ ባሻገር ለጎንደር ህዝብ ያለውን አጋርነት የሚያሳይበት መንገድ መሆኑና ቡድኑ በሚጫወትበት ወቅት የሚሰሙት የድጋፍ መዝሙሮች እጅግ ወኔ ቀስቃሽ በመሆናቸው ምክንያት ህዝቡ የበለጠ እንዲወደው አድርጎታል ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ቡድኑ ከሌሎች ከተሞች ከሚመጡ የሌላ ቡድን ደጋፊ ጋር የሚያሳየው የአብሮነት ስሜት በመላው ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንዲወደድ አድርጎታል ።

ታዲያ ይህ ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘው ቡድን በወያኔ አፓርታይድ ስርዓት እጅግ ክፉኛ በመጠላቱ ምክንያት ቡድኑን በተቀነባበረ ሁኔታ በጎንደር ህዝብና በመላው ኢትዮጵያዊው ዘንድ ለማስጠላት የተቀነባበረ ዘመቻ ተከፍቶበታል ። ለዚህም ይረዳው ዘንድ በጎንደርና በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ የሚጠላው የዳሽን ቢራ ስፖንሰር እንዲሆን ሆን ተብሎ ተደርጓል ። ይህም የተደረገበት ምክንያት የቡድኑን ደጋፊዎች ለማራቅ እና ቡድኑ እየያዘ የመጣውን ተቀባይነት ለማሳጣት ብሎም የነፃነት አርማነቱን መግፈፍ ነው ።

ስለሆነም በመላው አለም የሚገኘው የፋሲል ከነማ ቡድን ደጋፊ የሆነ በሙሉ ይህንን ሴራ ጠንቅቀን ልንረዳው ይገባል ። አላማው ከላይ እንደገለፅኩት የነፃነት አርማውን መግፈፍና ደጋፊውን ማመናመን ነው ስለሆነም ሁላችንም ለቡድኑ ያለንን ድጋፍ ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ በማጠናከር እንዲሁ ደግሞ ለስፖንሰሩ ያለንን ጥላቻ በሌላው በኩል ከሜዳ ውጭ በማጠናከር ልንገፋበት ይገባል ። ይህም ማለት በጎንደር ማንም ሰው ከዚህ በፊት ከሚያደርገው በበለጠ የዚህ ቢራ ተጠቃሚ አለመሆንና በጨዋታው ሰአት ግን የቡድኑን ተጫዋቾች ላለመረበሽ ያለምንም ተቃውሞ ለቡድኑ ያለንን አጋርነት ማሳየትና ማንኛውም የዳሽን ቢራ ያለበትን አርማ ባለመያዝ ድጋፋችንን በመቀጠል የተቀነባበረብንን ሴራ ማክሸፍ ይጠበቅብናል ። በሌላው በኩል የተጫዋቾቹን ሞራል መጠበቅ ከሁሉም ደጋፊ የሚጠበቅ ነው ተጫዋቾቹን ዳሽን ቢራ ወደፊት ስፖንሰር ሊያሰራቸው ይችላልና እነርሱን እንደምንረዳቸው አስቀድመን እንድናሳውቃቸው ይገባል እላለሁ ።

ፋሲል ከነማ ( ዓፄዎቹ )የእግር ኳስ ቡድን ብቻ ሳይሆን የነፃነት አርማችን ነው ። አሁንም ድጋፋችንን የበለጠ አጠናክረን እንቀጥላለን ።

ዘነበ ዘ ቂርቆስ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.