የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግህ ያን ያህል አስፈላጊነው?

 

“ጥሩ የአካል ብቃት እንዲኖርህ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ። በየቀኑ ለ30 ደቂቃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አድርግ። ካንሰር እንዳይዝህ ከአልኮል ራቅ። የልብ ሕመምን ለመከላከል አልኮል ጠጣ። ከዚህም ከዚያም በሚሰጡህ ምክሮች ግራ ተጋብተህ ታውቃለህ? አንድ ቀን አንድ ነገር ሲነገር ከቆየ በኋላ ወዲያው በሳምንቱ ከዚያ ነገር ሙሉ በሙሉ ተቃራኒ የሆነ ነገር ይነገራል። . . . ሳይንቲስቶች በአንድ ነገር ሊስማሙ የማይችሉት ለምንድን ነው? ቡና አንድ ሳምንት በጣም ጎጂ እንደሆነ ሲነገር ቆይቶ በሚቀጥለው ሳምንት ምንም ጉዳት እንደሌለው የሚነገረው ለምንድን ነው?”

ባርባራ ብሬም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የስፖርት ጥናቶች ፕሮፌሰር

የሕክምና ባለሞያዎች አብዛኛውን ጊዜ በአመጋገብና በአካል ብቃት ጉዳዮች ላይ ይወዛገባሉ። ብዙ ሰዎች ጤናን በተመለከተ እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ አታድርግ በሚሉ መረጃዎች ብዛት ግራ ይጋባሉ። ይሁን እንጂ መጠነኛ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግን አስፈላጊነት በተመለከተ በሳይንቲስቶች መካከል አጠቃላይ የሆነ ስምምነት ያለ ይመስላል። ስለዚህ ጥሩ ጤንነት እንዲኖርህ የምትፈልግ ከሆነ አዘውትረህየአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አለብህ!

በቂ የሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ በዛሬው ጊዜ በተለይ በኢንዱስትሪ በበለጸጉ አገሮች ከባድ ችግር ሆኗል። በእነዚህ አገሮች ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ለበርካታ ትውልዶች እንደ ግብርና፣ አደን ወይም ግንባታ የመሳሰሉትን አድካሚ የጉልበት ሥራዎች ይሠሩ ነበር። እነዚህ አባቶቻችን ኑሯቸውን ለማሸነፍ የሚፈጁት የጉልበት መጠን በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ዕድሜያቸውን እስከማሳጠር ይደርስ እንደነበረ አይካድም። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው “በጥንቷ ግሪክና ሮም የሰዎች አማካይ ዕድሜ ከ28 ዓመት አይበልጥም ነበር።” በአንጻሩ ግን በ20ኛው መቶ ዘመን መጨረሻ ላይ ባደጉ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች አማካይ ዕድሜ 74 ዓመት ደርሷል። ይህን የሚያክል ለውጥ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው?

ቴክኖሎጂ በረከት ነው ወይስ እርግማን?

በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች የተሻለ ጤንነትና ዕድሜ አላቸው። ይህ ሊሆን የቻለው በከፊል፣ ቴክኖሎጂ ባስገኘው ለውጥ ምክንያት ነው። በዘመናችን የተፈለሰፉ መሣሪያዎች ሥራችንን የምናከናውንበትን መንገድ ስለለወጡ ብዙ አድካሚ ሥራዎች ቀላል ሆነዋል። የሕክምናው መስክ በሽታን ለማሸነፍ በሚደረገው ጥረት ትልቅ እድገት በማሳየቱ የብዙ ሰዎች ጤንነት ተሻሽሏል። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ተፈጥሯል።

ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የጤንነት መሻሻል ያስገኝ እንጂ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች አብዛኛውን ሕይወታቸውን ቁጭ ብለው እንዲያሳልፉ አስተዋጽኦ አድርጓል። የአሜሪካ የልብ ማኅበር ኢንተርናሽናልካርዲዮቫስኩላር ዲዚዝ ስታቲስቲክስ በሚል ርዕስ ባወጣው ሪፖርት “የኢኮኖሚ እድገት፣ የከተሞችና የኢንዱስትሪ መስፋፋት እንዲሁም ግሎባላይዜሽን ለልብ ሕመም መስፋፋት አመቺ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ እንዲፈጠር አድርገዋል” ብሏል። ይኸው ሪፖርት ለልብ ሕመም ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል “ብዙ እንቅስቃሴ አለማድረግና ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ” በዋነኝነት እንደሚጠቀሱ ገልጿል።

ከሃምሳ ዓመት በፊት በበርካታ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ላባቸውን እያንጠፈጠፉ ከበሬና ከሞፈር ጋር ይታገሉ፣ በእግራቸው ረጅም መንገድ ተጉዘው ጉዳያቸውን ያከናውኑ፣ ማታ ማታ ደግሞ በቤታቸውና በአጥር ግቢያቸው ውስጥ የሚገኙ ነገሮችን ይጠግኑ ነበር። የእነዚህ ሰዎች የልጅ ልጆች የሚኖሩበት ሁኔታ ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነው። የዘመናችን ሠራተኛ አብዛኛውን የሥራ ሰዓት የሚያሳልፈው ከኮምፒውተር ፊት ወንበር ላይ ተቀምጦ ሲሆን ከቦታ ቦታ የሚጓጓዘው በመኪና፣ ምሽቱንም የሚያሳልፈው ቴሌቪዥን ፊት ተቀምጦ ነው።

አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው በቀደሙት ዘመናት ዛፎችን ሲቆርጥና ሲያጓጉዝ የሚውል አንድ ስዊድናዊ ዛፍ ቆራጭ በቀን 7,000 ካሎሪ ያቃጥል የነበረ ሲሆን አሁን ግን ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎችን በሙሉ የተራቀቁ መሣሪያዎች ሲያከናውኑ ቆሞ ሲያይ ይውላል። ከዓለም አውራ ጎዳናዎች መካከል አብዛኞቹ በአንድ ወቅት የሚገነቡትም ሆነ የሚጠገኑት አካፋና ዶማ በያዙ ሰዎች ነበር። አሁን ግን ኋላ ቀር በሆኑ አገሮች እንኳ ሳይቀር የቁፋሮውንና አፈር የመዛቁን ሥራ የሚያከናውኑት ከባድ መሣሪያዎች ናቸው።

በአንዳንድ የቻይና አካባቢዎች ለመጓጓዣነት ተመራጭ የነበረው ብስክሌት በትናንሽ ሞተር ብስክሌቶች በመተካት ላይ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ሰዎች ከሚያደርጓቸው ጉዞዎች 25 በመቶ የሚሆኑት ከ1.5 ኪሎ ሜትር የማይበልጡ ሲሆን ከእነዚህ አጫጭር ጉዞዎች 75 በመቶ የሚሆኑት የሚደረጉት በመኪና ነው።

በተጨማሪም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመቀመጫቸው ሳይነሱ የሚውሉ ልጆችንም አፍርቷል። አንድ ጥናት እንዳመለከተው የቪዲዮ ጨዋታዎች “ይበልጥ አስደሳችና እውን እየመሰሉ በሄዱ መጠን ልጆች . . . ቪዲዮ መጫወቻቸው ላይ አንጋጠው የሚውሉበት ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።” ቴሌቪዥን ማየትንና ለልጆች ተብለው የሚዘጋጁ ሌላ ዓይነት መዝናኛዎችን በተመለከተም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

አብዛኛውን ጊዜ ቁጭ ብሎ ማሳለፍ የሚያስከትለው አደጋ

ጉልበት የሚጠይቅ ሥራ በከፍተኛ መጠን መቀነሱ ከአካል፣ ከአእምሮና ከስሜት ጋር የተያያዘ ብዙ የጤና መቃወሶችን አስከትሏል። ለምሳሌ በብሪታንያ የሚገኝ አንድ የጤና ድርጅት የሚከተለውን ዘግቧል:- “በቂ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ልጆች ለራሳቸው ያላቸው ግምት ዝቅተኛ ሲሆን የበለጠ ፍርሐትና ጭንቀት ይሰማቸዋል። በተጨማሪም እነዚህ ልጆች የዕፅና የትንባሆ ሱሰኛ የመሆን ዕድላቸው በቂ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ልጆች በጣም የሠፋ ነው። ቁጭ ብለው የሚውሉ ሠራተኞች ወዲያ ወዲህ ከሚንቀሳቀሱ ሠራተኞች የበለጠ ከሥራ ገበታቸው ይቀራሉ። በቂ እንቅስቃሴ ሳያደርጉ የኖሩ ሰዎች ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ደግሞ የዕለት ተዕለት ኑሯቸው የሚጠይቀውን አቅምና እንደልብ የመንቀሳቀስ ችሎታ እንኳ ያጣሉ። በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ሰው እጅ ላይ ለመውደቅ ይገደዳሉ፣ የአእምሯቸውም ጤንነት ይቃወሳል።”

የካናዳ የአካል ብቃትና የአኗኗር ስልት ምርምር ተቋም ፕሬዚዳንት የሆኑት ኮራ ክሬግ “ካናዳውያን በሥራ ቦታቸው ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከቀድሞው በጣም ያነሰ ነው። . . . በአጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው በጣም ቀንሷል” ብለዋል። የካናዳው ግሎብ ኤንድ ሜይል ጋዜጣ “አርባ ስምንት በመቶ የሚያክሉ ካናዳውያን የክብደታቸው መጠን ከፍተኛ ሲሆን 15 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በጣም ወፍራሞች የሚባሉ ናቸው” ብሏል። ጋዜጣው በማከል በካናዳ ለአቅመ አዳም ከደረሱ ሰዎች መካከል 59 በመቶ የሚሆኑት ተቀምጠው የሚውሉ እንደሆኑ ገልጿል። በፊንላንድ የኩዎፒዮ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ማቲ ኡሲቱፓ “በመላው ዓለም ውፍረትና ቁጭ ብሎ መዋል እየተስፋፋ በመምጣቱ ምክንያት በአብዛኛው ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ዓይነት የስኳር በሽታ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መጥቷል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

በሆንግ ኮንግ በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት 35 ዓመትና ከዚያ በላይ ከሆናቸው ሰዎች መካከል ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለሞት የሚዳረጉት በቂ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር በተያያዘ ችግር ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል። የሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ በሆኑት በፕሮፌሰር ታይ-ሂንግ ላም የሚመራ ቡድን ያደረገውና በ2004 አናልስ ኦቭ ኤፒድሚዮሎጂ በተባለ መጽሔት ላይ የወጣው ጥናት በሆንግ ኮንግ በሚኖሩ ቻይናውያን ላይ “በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ የሚያስከትለው የጤና ጉዳት ትንባሆ ማጨስ ከሚያስከትለው ጉዳት ይበልጣል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ተመራማሪዎቹ በቀረው የቻይና ክፍልም “በዚህ ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሚመጣ” ተንብየዋል።

ታዲያ ይህ ጭንቀታቸው ተገቢ ነው? በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ ትንባሆ ከማጨስ እንኳን የበለጠ በጤንነታችን ላይ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል? ብዙ የማይንቀሳቀሱ ሰዎች ብዙ ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች ጋር ሲወዳደሩ በደም ግፊት መጨመር፣ በልብ ሕመም፣ በአጥንት መሸርሸር ችግር፣ በአንዳንድ የካንሰር ዓይነቶችና በውፍረት የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል።*

 ዎል ስትሪት ጆርናል “በሁሉም የዓለማችን ክፍሎች፣ በቂ ምግብ የማግኘት ችግር ባለባቸው አካባቢዎች እንኳ ሳይቀር ከመጠን በላይ ወፍራም የሆኑ ሰዎች ቁጥር በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የተስፋፋውን የውፍረት ወረርሽኝ በዋነኝነት ያባባሰው ከፍተኛ የካሎሪ መጠን ያላቸውን ምግቦች የመመገብ ልማድና በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ አንድ ላይ መዳመራቸው ነው” ሲል ዘግቧል። በስቶክሆልም፣ ስዊድን በሚገኘው በካሮሊንስካ ተቋም ከጤና ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ባሕርያት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ስቴፋን ሮስነር “በዓለም ውስጥ ከመጠን በላይ ውፍረት የማይጨምርበት አንድም አገር የለም” እስከማለት ደርሰዋል።

ዓለም አቀፍ ችግር

ዘወትር መጠነኛ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ለደኅንነታችን አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አካላዊ እንቅስቃሴ በበቂ መጠን አለማድረግ ስለሚያስከትለው አደጋ ብዙ ቢነገርም ከዓለማችን ነዋሪ በጣም ሠፊ የሆነው ክፍል አሁንም በቂ የሰውነት እንቅስቃሴ አያደርግም። የዓለም የልብ ሕመም ፌዴሬሽን ከዓለም ሕዝቦች መካከል ከ60 እስከ 85 በመቶ የሚሆነው ክፍል፣ “በተለይ ልጃገረዶችና ሴቶች ለጤንነት ጥቅም በሚያስገኝ መጠን አካላዊ እንቅስቃሴ” እንደማያደርጉ ያምናል። ይኸው ድርጅት “ከሁለት ሦስተኛ የማያንሱ ልጆች ለጤናቸው በሚበጅ መጠን አካላዊ እንቅስቃሴ አያደርጉም” ይላል። በዩናይትድ ስቴትስ ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት በአብዛኛው ተቀምጠው የሚውሉ ሲሆን ከ12 እስከ 21 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል ግማሽ ያህል የሚሆኑት ጠንከር ያለ አካላዊ እንቅስቃሴ አያደርጉም።

ብዙ አካላዊ እንቅስቃሴ የማይጠይቅ አኗኗር መስፋፋቱን በተመለከተ በ15 የአውሮፓ አገሮች የተደረገ አንድ ጥናት በቂ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሰዎች ብዛት በስዊድን ካለው 43 በመቶው በፖርቱጋል ካለው ደግሞ 87 በመቶው እንደሚሆን አረጋግጧል። በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል 70 በመቶ የሚያክሉ ነዋሪዎች በቂ እንቅስቃሴ አያደርጉም። የዓለም ጤና ድርጅት “በመላው ዓለም የተደረጉ የጤና ቅኝቶች ያስገኙት ውጤት በአስደናቂ ሁኔታ ተመሳሳይ ነው” ይላል። ስለዚህ በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በቂ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ምክንያቶች የሚሞቱ መሆናቸው ሊያስደንቀን አይገባም።

ይህ አዝማሚያ በጣም አስደንጋጭ እንደሆነ በመላው ዓለም የሚኖሩ የሕክምና ባለሞያዎች ያምናሉ። በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ መንግሥታዊ ድርጅቶች መጠነኛ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ለሕዝብ ለማስተማር የሚያስችላቸው የተለያየ ዘመቻ ጀምረዋል። አውስትራሊያ፣ ጃፓንና ዩናይትድ ስቴትስ እስከ 2010 ድረስ ዜጎቻቸው በሚያደርጉት አካላዊ እንቅስቃሴ መጠን ላይ 10 በመቶ ጭማሪ ለማድረግ ተነስተዋል። ስኮትላንድ እስከ 2020 ድረስ ለአካለ መጠን የደረሱ ነዋሪዎቿ በሚያደርጉት አካላዊ እንቅስቃሴ ረገድ የ50 በመቶ ጭማሪ ለማምጣት እቅድ አውጥታለች። ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘ ሪፖርት እንደሚያመለክተው “የዜጎቻቸውን አካላዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ የሚያስችላቸውን ብሔራዊ ፕሮግራም ከነደፉ አገሮች መካከል ሜክሲኮ፣ ብራዚል፣ ጃማይካ፣ ኒው ዚላንድ፣ ፊንላንድ፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ሞሮኮ፣ ቬትናም፣ ደቡብ አፍሪካና ስሎቬንያ ይገኛሉ።”

መንግሥታትና የጤና ተቋሞች ምንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ የየግል ጤንነታችንን የመንከባከቡ ኃላፊነት የሚወድቀው በየራሳችን ላይ ነው። ‘በበቂ መጠን እንቀሳቀሳለሁ? ሰውነቴ የሚያስፈልገውን ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እያደረግኩ ነው? ካልሆነስ በቂ እንቅስቃሴ እንዳላደርግ ያገደኝን የአኗኗር ስልት እንዴት መለወጥ እችላለሁ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። የሚቀጥለው ርዕስ የአካላዊ እንቅስቃሴህን መጠን ከፍ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ ይጠቁማል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ ለሕይወት አስጊ በሆኑ አንዳንድ በሽታዎች የመያዝ ዕድልን በእጅጉ ይጨምራል። ለምሳሌ የአሜሪካ ልብ ሕመም ማኅበር እንደሚለው በበቂ መጠን አለመንቀሳቀስ “በልብ በሽታ የመያዝን ዕድል በእጥፍ ሲያሳድግ የደም ግፊት መጨመር በሚያስከትለው ችግር የመጠቃት ዕድልን ደግሞ በ30 በመቶ ያሳድጋል። በተጨማሪም በልብ ምትና በደም ዝውውር ችግር የመሞትን እንዲሁም በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስን አጋጣሚ በእጥፍ ከፍ ያደርጋል።”

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ የሚያስከትለው ኪሣራ

  ብዙ መንግሥታትና የጤና ተቋማት በቂ እንቅስቃሴ አለማድረግ በማኅበረሰቡ ላይ ያሳደረው የወጪ ጫና በጣም አሳስቧቸዋል።

● አውስትራሊያ – በዚህች አገር በቂ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ የጤና ችግሮች የሚወጣው ወጪ በዓመት 377 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይገመታል።

● ካናዳ – የዓለም የልብ ሕመም ፌዴሬሽን እንደሚለው ከሆነ ካናዳ “በቂ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ተዛማጅነት አላቸው” ለሚባሉ የጤና ችግሮች ያወጣችው ወጪ በአንድ ዓመት ብቻ 2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል።

● ዩናይትድ ስቴትስ – ዩናይትድ ስቴትስ በ2000 በቂ እንቅስቃሴ ካለማድረግ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ላላቸው የሕክምና ወጪዎች ያወጣችው ገንዘብ 76 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ልጆች በቂ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል

  በቅርብ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት አዘውትረው በቂ እንቅስቃሴ የማያደርጉ ልጆች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው። በቂ እንቅስቃሴ ያለማድረግ ችግር ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ልጆች ላይ ጎልቶ ይታያል። ልጆች እያደጉ በሄዱ መጠን የሚያደርጉት እንቅስቃሴም እየቀነሰ የሚሄድ ይመስላል። ልጆች አዘውትረው በቂ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ከሚያገኟቸው ጥቅሞች ውስጥ የሚከተሉት ይገኛሉ።

● አጥንቶቻቸውና ጡንቻዎቻቸው ከመዳበራቸውም በላይ ጤናማ የሆኑ መገጣጠሚያዎች ይኖሯቸዋል

● ከመጠን በላይ ክብደት አይጨምሩም ወይም አይወፍሩም

● ከደም ግፊት መጨመር ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ችግሮች ማስወገድ ወይም ማዘግየት ይችላሉ

● ከዕድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ዓይነት የስኳር በሽታ መከላከል ይችላሉ

● ለራሳቸው ያላቸው ግምት ከመጨመሩም በላይ የስጋትና የጭንቀት ስሜት ይቀንስላቸዋል

● እንቅስቃሴ የበዛበት ኑሮ መልመዳቸው ትልቅ በሚሆኑበት ጊዜ ቁጭ ብሎ መዋል እንዳይወዱ ያደርጋቸዋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የተሻለ ጤና ለአረጋውያን

  ዕድሜህ እየጨመረ በሄደ መጠን መጠነኛ ከሆነ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራም የምታገኘው ጥቅም ይጨምራል ይባላል። ቢሆንም ብዙ አረጋውያን ጉዳት ይደርስብኛል ወይም እታመማለሁ በሚል ፍርሐት አካላዊ እንቅስቃሴ ከማድረግ ወደኋላ ይላሉ። እርግጥ ነው፣ አረጋውያን ከበድ ያለ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረጋቸው በፊት ሐኪም ማማከር ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ አካላዊ እንቅስቃሴ የአረጋውያንን ሕይወት የተሻለ ሊያደርግ እንደሚችል ባለሞያዎቹ ያምናሉ። አረጋውያን አዘውትረው አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ከሆነ:-

● አእምሯቸው ይበልጥ ንቁ ይሆናል

● ሚዛን የመጠበቅና የመተጣጠፍ ችሎታቸው ይጨምራል

● ስሜታዊ ጤንነት ይኖራቸዋል

● ከጉዳት ወይም ከሕመም ፈጥነው ያገግማሉ

● ጨጓራቸውና አንጀታቸው እንዲሁም ጉበታቸው ሥራውን በተሻለ ሁኔታ ያከናውናል

● የሚመገቡት ምግብ በጥሩ ሁኔታ ከሰውነታቸው ጋር ይዋሃዳል

● በሽታ የመከላከል አቅማቸው ይጨምራል

● አጥንታቸው ይጠነክራል

● የተሻለ አቅም ይኖራቸዋል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.