እስቲ ዶሴው ይውጣ! የማን? የ “ያ ትውልድ”- አቻምየለህ ታምሩ ( ክፍል ፪)

እስቲ ዶሴው ይውጣ  . . .

ኢሕአፓ የሚባለው የያ ትውልድ አገር አፍራሽ ድርጅት ከሰሞኑ በኔ ላይ ሲዘምት ሰነበተ አሉ። ዘመቻው በሬድዮ የታጀበ ጸረ አቻምየለህ ቅስቀሳ እንደነበር የኢሕአፓን ሬዲዮ የማዳመጥ ትዕግስቱ ያላቸው ወዳጆቼ ነገሩኝ። ኢሕአፓ በኔ ላይ ሲዘምት የሰነበተው በተለያየ ወቅት በሰጠኋቸው ቃለ መጠይቆች “ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከተመሰረቱት የያ ትውልድ ጸረ ዐማራ ድርጅት መካከል ኢህአፓ አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው” በማለቴ ነበር።

አዎ! ይህ የተናገርሁት ምንም አይነት ስህተት የለበትም። ኢሕአፓ ጸረ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተመሰረተ የኢትዮጵያ ጠላቶች የትሮይን ፈረስ ነበር። ለዚህ ደግሞ ማረጋገጫው የራሱ የኢሕአፓ ፕሮግራም ነው። ኢሕአፓ የታገለው “በፖሊሲ የታገዘ ነበር” ያለውን አማራ የማድረግ ጭቆና ታግሎ በመጣል የብሔሮችን መብት እስከ መገንጠል ተግባራዊ ለማድረግ ነበር።

የኢሕአፓ የትግል ውጤቶች ሁለት ናቸው። አንደኛው የኤርትራ መገንጠልና አገር መሆን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የነፍስ ልጁ የሆነው ፋሽስት ወያኔ ስልጣን መያዝ ነው። የኢሕአፓ እናቱ ማርታ መብርሀቱ ኑራ ባታይም ኢሕአፓ የታገለለትን የትግል ፍሬ ሻዕብያ አውሮፕላን ጠልፎ ካርቱም ያስኮበለለውና ከኢሕአፓ አባቶች አንዱ የሆነው እያሱ አለማየሁ የኤርትራን አገር መሆን በሕይወት ቆይቶ በአይኑ ለማየት ታድሏል።

“ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቆርበት አንጥፉልኝ ይላል” እንደሚባለው ኤርትራን ለማስገንጠልና ኢትዮጵያን ለመበታተን የታገለው ኢሕአፓ ለኢትዮጵያ ነጻነትና ለዲሞክራሲ ሲል ያፈሰሰው አንድ ጠብታ ደም ያለው ይመስል፤ በአፈ ቀላጤዎቹ በነ ክፍሉ ታደሰና በባቢሌ ቶላ [እያሱ አለማየሁ] አማካኝነት ኢትዮጵያን ያጠፏትን የኢሕአፓ ፋኖዎች “ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲና ሰላም ለማምጣት ሲሉ የወደቁ ሰማዕታት” አድርገው በማቅረብ በምጸት ሊገድሉን በደረቁ ይላጩናል።

ኢሕአፖውያን ያላወቁት ነገር ቢኖር ሀያ አንደኛውን መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማሰባቸው ነው። ዛሬ ላይ የደረስንበት ዘመን እንደ ሀያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ስድሳዎቹና ሰባዎቹ አመታት የሌለ ታሪክ ፈጥሮ የሚዋሽበት ዘመን አይደለም። የምንኖርበት ዘመን የመረጃና ማስረጃ ፍሰትና አቅርቦትን ስላቃለለው ፋሽስት ጥሊያን ጀምሮ የተወውን ረጅሙን የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ በዐማራ የበላይነት ፈርጃችሁ ኢትዮጵያን በጎሳና በመንደር ለመበታተን፣ ዐማራን ለማጥፋትና ኤርትራን ለማስገልጠል የታገላችሁበትን ጥቁር ታሪክ አይናችሁን በጨው በማጠብ “ያ ትውልድ”፤ “ኢትዮጵያ ሆይ!”፤ “የትውልድ እልቂት” ወዘተ የሚሉ የቅጥፈት ድርሰቶችን በመደረት “ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ታግለናል” እያላችሁ ያላመረታችሁትን ሸቀጥ ገበያ በማቅረብ ለመፏለል ብትሞክሩ ትርፉ ትዝብትና ውርደት ብቻ ነው።

ዛሬ ላይ ዶሴያችሁ ወጥቶ የታገላችሁት አላማ ሲገለጥ፤ የታገላችሁት ኢትዮጵያን ለማፍረስ፣ አማራን ለማጥፋት፣ ኤርትራን ለማስገንጠልና ሌሎችንም “ጭቁን” ያላችኋቸውን “ብሔሮች” የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል መብት ለማጎናጸፍ መሆኑ ታውቋል። እነዚህን የኢህአፓ የትግል ምሰሶዎችን የያዘው ታሪካችሁ ቀለም በጥብጣችሁ፣ ብራና ፍቃችሁ፣ ብዕር ቀርፃችሁ፣ጉባኤ ዘርግታችሁና ትምህርት አስፋፍታችሁ ከድርጅታችሁ ምስረታ ጀምሮ በጻፋችኋቸው ዶሴዎች ተዘርዝሮ በየ ላይበራሪው ይገኛሉ። ዘመኑ የማይዋሽበት ሆኗል! እኔ በቃ ለመጠይቅ ያነሳኋቸው የትግላችሁ አላማዎች ኢህአፓ ከምስረታው ጀምሮ በደማቅ ቀለም ጽፎ ሕያው ያደረጋቸው የትግል ምሰሶዎቹ ናቸው።

ከታች በታተመው የኢሕአፓ ዶሴ እንደሚታየው “የኢሕአፓ የማያወላውል አቋም የኤርትራን ሕዝቦች የራሳቸውን እድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል” እንደሆነ በግልጽ ተቀምጧል። የወያኔ አላማም ተመሳሳይ ነበር። ኢሕአፓ መልኩን በመስታውት እያየ ወያኔን የሚያወግዝበት የሞራል የበላይነት ሊኖረው አይችልም፤ ሁለቱም የታገሉት አንድን ጠላት [አማራን] እና ለአንድ አላማ [ኢትዮጵያን ለመበታተን] ነውና!

EPRP Manifesto

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.