ድሬ ለምን የሰው ሞት ሞተች? – ያሬድ ይልማ

ፈቅዳችሁ ጆሮ የምትሰጡኝ ከሆነ፡ አቦ ከሳምንታት የስንፍና፡ አዚም በኋላ፤ ሲቆጠቅጠኝ የቆየውን በሞራል ውክልና የተቀበልኩትን እሮሮ ጀባ ልበላችሁ…ካንደበት በወጡ ቃላት ባይሆንም፡ ከአራት የሰፈሬ ልጆች፡ አይኖች ውስጥ በሰኮንዶች ቅፅበት፡ ያስተዋልኩት የገፅ ላይ እውነት፡ ነው፡፡ የከተብኳቸውም፡ ቃላት፤ ከሰፈሬ ልጆች፡ ልሴ-ተተኪና፡ መሰለ ኡኒ ጠብሻን አይኖች፡ ውስጥ የተረዳሁትን የሂራር መልእክት፡ ነው፡፡

ከትውውቅ ሓሳብ አስቀደምኩ፡ይቅርታ፤ እንተዋወቃ፤ የድሬዳዋ ልጆች ከሚባሉት ነኝ፤ ልክ እንደ ሁለቱ የሰፈሬ ልጆች፡ መሴ ኡኒና ልሴ ተተኪ፤ በእድሜ እራሴን ለመግለፅ ያክል፡ የነ ልሳን ተተኪ፡ የደርዘን አመታት ታናሻቸው ነኝ፡፡ እንደውም መሴ ኡኒ ከዚያም በላይ ይርቀኛል፡፡

የዛሬ ፤ መሴና ልሴን ያገኘኋቸው እለት፡ አብረን ቆመን፡ ላየ እንግዳ፡ ታዛቢ፡ ግን ቁመና ሁለንተናቸው፡ ታናናሾቼ ይመስሉት ነበር፡፡ ለነገሩ ሰፈር ያገኘኋቸው ታናናሾቼ፡ ደግሞ፡ ግርጅፍጅፍ ብለው፡ ታላላቆቼ ስለሚመስሉ፡ ለማስረዳት ግራ አጋቢ ነው፡፡

ድሬዳዋ!!!… አዬ ድሬዳዋ… !

ድሮ ድሮ ለሚያውቃት እንደኔ ድጋሚ ከአመታት በኋላ ቢያያት፤ መጀመሪያ የሚለውን ቃል የሚመስለኝ፤ ”የድሬዳዋ…. የት ሄደ፡ደሟ” እሚል ነው የሚመስለኝ፡፡በከረረ ነገር፡ ዙሩን አከረርኩት አይደል…. ይታወቀኛል፡፡ ብዙሃኑ ደግሞ በምናቡ የሚያውቃት ድሬ፡ ”አቦ ጭንቅ አንወድም”… የሚሉትን የድሬ ልጆችን ስእል፡ ስለሆነ፡ ይብቃኝ፡፡

መሴ ኡኒን ላስተዋውቃችሁ፤ ድሮ ሰፈር ውስጥ ስለስሙ አሰያየም የማስታውሰውን ብነግራችሁ ጥሩ መግቢያ፡ ይመስለኛል፡፡

ዋ! ድሬዳዋ ምርጥ ነበረች፤ ብዙዎች ሲተርኩ እንደሰማሁትና በተለይ ደግሞ ”አባቴ በየአጋጣሚው፡ እንደነገረኝ”፡፡  መሰለ የኛ ሰፈር፡ (ነምበርዋን) ነዋሪ በሆነበት ዘመን፤በድሬዳዋ እነ ኮተኒ፤ እና ባቡር ከአገር ውጪ ደግሞ እነ ኬኒ ዳግሊሽንና ኢያን ራሽ እንዲሁም ጆን ባርነስን ይዞ ገናና የነበረውን  ሊቨርፑልን ደጋፊ ለነበረው አባቴ ለወጣትነት የእግር ኳስ ፍቅርና፡ ስሜቱ፡ ድሬዳዋ በመኖሩ ካተረፋቸው፡ ትሩፋቶቹ፡ በቪኤችኤስ የተቀዱ የየሳምንቱን የሊቨርፑል ጨዋታዎች ከሶስት ቀናት በኋላ በኦተራይ ከጅቡቲ ነዋሪ ጓደኛው ዳዉድ ፡ ተልከውለት የሚኮሞኩምበት ወቅት፤ የክርስቶስ ት/ቤት ፍሬ የሆነው ጳውሎስ ኞኞ በጋዜጠኝነት ችሎታው አባቴን እና ድሬዎችን፡ ያኮራበት፡ እነአሊቢራህ የፈነዱበት፤ እነጀማል ረጎራ፡ በብስክሌት ስፖርት የነገሱበት፡ እንዲሁም ሲዘረዘረሩ ቢውሉ አያሌ ጥሩ ነገር በድሬ የሞላበት፡ ዘመን ነበር፡፡

ይህ ዘመን ለመሰለ በቀድሞ ሰፈሩ አዲስ ከተማ የልጅነት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ኋላ ቤተሰቦቹ ሰፈር ቀይረው ወደ ነምበርዋን ሲገቡ፡ ተማሪ ሆኖ ብስራተ ገብርኤል ት/ቤት ተመዘገበ ፡፡ ግልፅ ምስል ለመስጠት ያክል፡ ብዙዎች የድሬዳዋውን ብስራተ ገብርኤል ት/ቤትን፡ በደረጃው፡ ከአዲስ አበባው፡ሴንጆሴፍ ት/ቤት ጋር ያመሳስሉታል፡፡

መሰለ ብስራተ ገብርኤል ት/ቤት፡ ሲገባ ለእንግሊዘኛ ትምህርት ገና ስለነበር እና ሌሎቹ መማር ጀምረው ስለነበር ፤  የእንግሊዘኛ መምህሩ አንድ ”one” የእንግሊዘኛ ቃል ብላክ ቦርድ ላይ ፅፎ፡ ፈቃደኛ አንባቢ ብሎ ሲጠይቅ፡ ለትምህርት ቤት አዲስ የሆነው መሰለ ፡ የድፍረት ደመነፍሱን አምኖ እጁን አወጣ፡፡ መሴ እኔ ላንብብ ብሎ ሲፈቀድለት፤ የተጠየቀችውን ”one” የምትለውን የእንግሊዘኛ፡ ቃል፡ መሴ እንደመሰለው፡ በጥድፊያ….፤ ”ቲቸር – ኡኒ!…” ብሎ አነበበና፡ የብስራተ ገብርኤል ት/ቤት አጀማመሩ የክፍል ተማሬው በሳቅ እንዲቀበለው ምክንያት፡ ሆነ፤ ኋላም፡ የቀሪው ዘመኑ መጠሪያ ቅፅል ስሙ ”መሴ ኡኒ” ሆኖ ቀረ፡፡ መሴ ቅፅል ስሙን እንግዲህ፡ እንደዚህ አገኘ፡፡

ከአመታት የአዲስ አበባ ኑሮ በኋላ፤ ጊዜ ተሳክቶ እና ሁኔታዎች ሞልተውልኝ እናቴን ላያት፡ ከድሬዳዋ ኤርፖርት ያመጣኝ ባጃጅ፡ ቤታችን አካባቢ እንዳወረደኝ ነበር መሴ ኡኒንና፡ ልሳን ተተኪና ዳግም፡ ያገኘኋቸው፡ ፡፡ ትንሽ ቀምቀም አድርገው ሞቅ ያላቸው፡ መሴንና ልሴን ሞቅ ያለ ሰላምታ እንደተለዋወጥን፡ በአጠቃላይ ሁኔታቸው የምንዱባንነት ፡ ገፅታ፡ መደንገጤ እንዳይታወቅ፤….

”መሴ አቦ ድሬ እንዴት ነው ሳ” ስል ፡ መሴ በቅፅበት፤ ሃይ ኩቢቲ አልሰማህም እስካሁን፤

…“ሃይ ድሬዳዋ፡ ደም አንሷት፡ እኮ ድልጮራ ገብታ በጉሉኮስ ነው ያለችው” አለኝ፡፡

…ፌዝ ነው፤ ግን አልሳቅኩም፡ እነሱም አልሳቁም ነበር፡፡ ወይ ይህንን ፌዝ ብዙ ግዜ ብለውት የቀልድነት፡ ጣእሙ ጠፍቷቸዋል፤ ወይ እንደ እውነት ተቀብለውት ይሁን አላውቅም፡ ፊታቸው ፈገግታ ቢስ ነበር፡፡ በዛው ቅፅበት ለአፍታ ፊታቸውን በአትኩሮት አየሁት፡፡

የነመሴ አራት አይኖች፡ ውስጥ ያየሁት ታዲያ ምን መሰላችሁ፤ ድሮ አይቼ የማላውቀውን፡ ሌላ ደስ የማይል እውነት ነበር፡፡

በሰነባበቱ ውብ የዘፈን ግጥሞች የተገለፀችውን ድሬን፤ አሊያም፡ ሁልጊዜ በፍሰሃ፡ ተሞልቶ፡ አብሽር ድሬዎች፡ ጭንቅ አናውቅም፡ በሚል ብሂል የህዝቧ መፈክር፡ ታውቃ፡ የምትናፈቀውን ድሬንም አልነበረም፤ ያቺ…በብዙ የአገሪቱ ነዋሪ፡ ምናብ ውስጥ፡በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ፡ ነዋሪ፡ የጉብኝት ትልም (በኪየስት ሊስት)፡ አናት ላይ የምትቀመጠዋን ከተማ ….”ፈርሃኑ” ነዋሪዋን ሳይሆን፡ በኑሮ ትግል ዝለት ውስጥ የቆሙ፡ ቁመናና ንግግራቸው፡ ሁሉ ወዝ የሌለው፤  የምንዱባን መንፈስ የወረሳቸው፡ ድሬዎችን ነበር፡፡

የዛሬን አያድርገውና፤ ድሬዳዋ የከተማነት ቡቃያዋ የታየው፡ ለጋሱ ደምስሯ፡ የባቡር ሀዲዱ፡ ከተሜዋን ድሬን ፡ ቀድሞ ገዚራ በመድረሱ ነበር፡፡ በቀላል አማርኛ፡ ውቧ ድሬዳዋ የተፈጠረችው፡ ከአራትመቶ ሃምሳ ኪሎሜትር በላይ የሚረዝመው፡ ህይወት ሰጪ፡ የባቡር መስመር ከጅቡቲ ”ዲሬ-ዳዋ ” በመድረሱ ነበር የምስራቋ እንቁ ፍንትው ያለችው፡፡

ከብዙ አመታት በፊት ታዲያ፡ ይህ አንጋፋ የደም ስሯ (ባቡሩ) ተቋረጠ፡፡ እስካሁንም ፤ ድሬዳዋን ሳይሰናበታት የውሀ ሽታ እንደሆነ ቀርቷል፡፡ ከዛን ግዜ አንስቶ፡ ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆን ህዝብ፡ ለሃያና ሰላሳ አመታት የሰራበትን የስራ ልምድ እንደያዘ፡ (እንደ አስኳላ ዲግሪ አውቅና ሊሰጠው እና በሞያነት ሊያዝ ባይችልም) ሲለፉበት ለኖሩ ሁሉ፡ ትዝታውን ብቻ፡ ጥሪት፡ አውርሷቸው፤ ሃሰን ጆግ፤ ኦተራይ፤ እና ፋልቱ፡ የኮትሮባንድ ነጋዴዎች፡ መናኻሪያ ስለሆነ ተባለና ተቋረጠ፡፡

ለዛ ሁሉ የድሬዳዋ ህዝብ፡ እንዲሁም እንደምወዳት እናቴ ቢጤዎች ታዲያ፡ የባቡሩ፡ መቋረጥ ምክንያት፡ ጭራሽ ትርጉም የማይሰጥ መልስ ሆኖ እንደዘለቀ፡ ይኀው ድሬዳዋም ለአመታት በዘለቀ ህመም፡ የከተማ ጣር ወዝ አልባ አርጎ አስቀርቷታል፡፡ ለዚህ ነው ድልጮራ በግሉኮስ ነው ያለችው ተብላ የተፌዘባት፡፡

እነ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሉሳን እንካችሁ ያለች፤…  የነዶ/ር ጌታቸው ቦሎድያ፡ አበርክታ ፤ ፕ/ሮ አስራት ወልደየስ፡ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞን፡ የመሳሰሉ የተራራ ያክል የገዘፈ አንፀባራቂ ማንነት፡ በጉያዋ የቀፈቀፈች… ከቋንቋ ከፍ የሚል፡ የስሜት መንፈስን ከኦሮምኛና አደሪኛ ዜማዎቹ ውስጥ ድሬዳዋ አስታጥቃው፡ ለሙሉ ኢትዮጵያዊያን ፍልቅልቅ እንቁነቱን በድምፁ ውበት ያሳየውን አሊቢራህን ያበረከተች ድሬዳዋ፤ ለዘመናት የዘለቀ፡ የስልጣኔ ከተምበሪ (መግቢያ) የሆነችው ድሬ፤ ከአሸዋ ሜዳዎች ፍትጊያ የፈለቁ፡ ልዩ ክህሎትን ተላብሰው ታሪክ የፃፉ፡ የእግር ኳስ ተጫዋቾችና፤ ብስክሌተኞች፤ ደግመው ደጋግመው የድል ችቦን ያነገቡና፡ የተቀባበሉ ኢትዮጵያዊያንን ያፈራች ድሬዳዋ፤…..  ዛሬ ማህፀኗ እያፈራ አይደለም፡፡ በአንፃሩ ግን፤ ቀን ቢጨልምም የሙጥኝ አገሬ ድሬን ትቼ የት ልሂድ ያሉትን፡ እንደ እነ መሴ ኡኒ መሳይ ልጆቿን፤ ጭርንቁስ መልኳን አልብሳቸዋለች፡፡

ድሬዳዋ ከመሄዴ ከሳምንታተ ቀድሞ ያነበብኩት፡ የድሬ መልክን እኔንና ብዙዎችን በመፅሐፉ ፡ ሁለንተና እንደ አስቃኘው፤ ታላቅ ሰው (አፈንዲ ሙተቂ) ቃላት – እንደ ”ያ ኡመተ ፈናን ያ ኡመተ ቀሽቲ ዲሬዳዋ” ትረካ ሳይሆን፤…..  ወዝ አይናቸው የቦዘዘ፡ ሁለንተናቸው፡ የበደነ ሰዎችን ነው፡ ድሬ ላይ ያየሁት፡፡

ድሬዳዋ ያ ለጋስ ደምስሯ ቢቋረጥም፤ ከመቶ አመት በላይ ውብ ሆኖ ግርማ የለገሳት የገዚራ ጥላዎቿ ቢጠወልጉም፤ የተሳሉ ያክል የሚስቡት ሰፈሮቿ፡ (ኮኔል፤ መጋላ፤ ደቻቱ፤ ቀፊራ፤ እና ገንደዲፖ…)  ወዘናቸው ቢወይብም፤ በአስገራሚ ብቃት ትውልድን ሲያንፁ፡ የነበሩ መምህራኖች፡ ታጭቀው የኖሩት ትምህርት ቤቶቿ ( እነ ኖትረዳም ፡ ብስራተ ገብርኤል፡ ክርስቶስ፡ አቡነ እንድርያስ፡ አሊያንስና… ሌሎች ሁሉ) ኦና ቢሆኑም፤ በሀረርጌ ልዩ ፀጋ ውርስ መሰረት፡ የዳበረው ማህበራዊ እሴታዊ መስተጋብር ተኮትኩቶ የሰውን ደስታ መሻት፤ ባህል አድርገው ይኖሩባት የነበሩ ልጆቿ፡ የፋሽንና የሙዚቃ ቀበኛ ና ዘበናዮች መላቅጡ እስኪጠፋባቸው፤ ፈናን አንዳልነበሩ ጤባ እስኪባሉ የኑሮ ሸክም ከብዶ ያደጉበትን የመካፈል ውብ ባህል መከወኛ መላውን ድሬዳዋ ብትነፍጋቸው በእልፍ አእላፍ፡ ገዚራና ሌሎች ሰፈሮቿን ጥለው ቢተሙም፤ ለነመሴ ኡኒ ግን፡ አንድ ነገር ከድሬ ገበታ አልቀረም፤ ጫት!… ጫት፡ በሽበሽ ነው፡፡

እውነት የሆነውን መካድ ስለማያስፈልግ፡ የሞራል ግዴታም ስለሚሰማኝ ነው፡፡ አሁንም፡ ጫት እንደጉድ አለ፡፡ ይጥቀም አይጥቀም የሚል አስተያየት ባልሰጥም ጫት በአቅርቦትም በአይነትም ተበራክቶ፡ይገኛል፡፡ ሳሂቤን ኢብሮን ዋቢ ላድርግና፡ ጫት ከበዛ ደም ማነስ ማስከተሉ፡ እሙን ነውና!!!  እውነትም ድሬ ደም አንሷታል ብል ስላቅ አይደለም፡ ሃቅ እንጂ፡፡እኔም ባጭሩ የተቋጨውን የድሬ ዚያራዬ እንዳስተማረኝ፡ የነዋሪውን የገቢ ምንጮች አንዲያው በግርድፉ ለመዳሰስ ያክል፤ የድሬዳዋ ወጣት እኩሌታው ገቢ የለውም ማለት ይቻላል፤ አዚጋ… እኩሌታ ማለት ስንት ነበር!…. እሱን እባካችሁ እናንተው አስሉልኝና ደግፉኝ….. ከተሳሳትኩ ግን አፉ በሉኝና ልቀጥል፡፡

በተጨባጭ ደፍሮ መናገር የሚቻለው ሌላው የአብዛኛው ህዝብ መተዳደሪያና የስራ ዘርፍ ባጃጅ መንዳት ሳይሆን አይቀርም፤ ቀላል የማይባሉ የድሬ ልጆች ደግሞ በዱቄትና ሲሚንቶ ፋብሪካ እንዲሁም በፓሊስነት እየሰሩ እንዳሉ አይቻለሁ፤ ቁጥራቸው ያን ያክል ባይጋነንም ብዙ የእድሜ እኩያዎቼና አብረውኝ የተማሩ ድሬዎች በመናሃሪያ ካሪዎች ሆነዋል (የተሳፋሪ ደላላ፡ አሊያም የተራ አስከባሪ አይነት ስራ ማለት ነው)፡፡ ከሞላ ጎደል የነመሴ ፊተ ላይ የያነበብኩትን እሮሮን ለማስረዳት ሞክሬያለሁ፤ በትክክል ስሜቴን ግለፅ ካላችሁኝ ግን፡ ያየኋቸው አንዳንድ የከተማዋ እንቅስቃሴዎች፡ ተስፋ እና ግርታን በአንድ ግዜ ከድሬዳዋ አየር ላይ አቀላቅለው፡ አይቼያለሁ፡፡ ወደ ሸገር መመለሻዬ ወቅት ላይ ነፋስ አምጥቶ ከጆሮዬ ሹክ ካለኝ መርዶ ጋር ይያያዛል፤

ያ!… የድሬዳዋ ምልክት ውበት የልጅነቴ ትዝታዎች ሁሉ ባክግራውንድ፤ ከመቶ አመታት በፊት ያኔ የድሬዳዋ ውብ ከተማ ቡቃያነት መጀመሪያ መካነ-ፅንስ… ከዚራ፤… ለምወዳት ቤቴ ድሬዳዋ የአመታት ጣር መባቻ፤ ግብአተ መሬት መፈፀሚያ ሊሆን ነው የሚል ጉድ ሰማሁና የመሴ ኡኒን ፌዝ ለእውነት የቀረበ ትንቢታዊ ሟርት ሆኖ አገኘሁት!

ግን እውነትነቱን ያለምንም ሌላ ማረጋገጭ ባውቅም ፡ ለስሜቴ ስል ግን አሁንም ማመን አልፈልግም፡፡……..

አለበለዚያ፡ እውነት ሆኖ የከዚራ ቤቶች ከመቶ አመት በላይ ተጠብቀው ኖረው፡ ድንገት፡ ዛሬ ላይ ሲታዩ በሞገስ ገጥመው ጥላ የሆኑት ዛፎች የያዙት ቦታ ስፋት ፤ እጥረት በሚሰበክበት ወቅት ደግሞም ከልማት አንፃር ብክነት ነው ተባለ፡፡

ከምእተ አመት የዘለለ እድሜቸው፡ ከቅርስነት ይልቅ፡ ጉድፍ ከመሰለማ ምን ማለት መሰላችሁ፤ የአሊቢራህ የአስቴር አወቀና ጋሽ መሐሙድ ዘፈኖች ብቻ ገዚራን ሊያሳዩ የሚችሉ ቀሪ ቅርስ ሆነው ዋጋቸው ይንራል፡፡ ህዝበ-አዳም ድሬንና ገዚራ ጥላዋን ለማየት ያለምሽ ቅዠታም ሁሉ፡ ህልምሽን ለማሳካት፡ እማኝ፡ ተራኪ፡ የሚሆኑት፡ ዜማዎቹ ብቻ ይሆናሉ፡፡

ያ!… የድሬዳዋ ምልክት፡ ውበት፡ የልጅነቴ ትዝታዎች፤ የምወደውን፡ ብስክሌት፡ ብዙ እሁዶች ላይ፡ ያየሁበት፡ የትዝታዎቼ፡ ሁሉ ባክግራውንድ፤ ከመቶ አመት በፊት፡ ያኔ፡ የድሬ ውበት፡ ቡቃያው፡ የተኮተኮተበት፡ መካነ-ፅንስ… ከዚራ፤ለምወዳት ቤቴ ድሬዳዋ የአመታት ጣር፡ መባቻ፤ ግብአተ መሬት መፈፀሚያ ሊሆን ነው የሚል ጉድ የዛሬ አመት ገደማ፡ ሰማሁና፡ የመሴ ኡኒን ፌዝ፡ ለእውነት የቀረበ፡ ትንቢታዊ ሟርት ሆኖ አገኘሁት!

የመሴ ኡኒ ሟርት እውን ከሆነ አንድ ነገር መልስ ያገኛል፤ ከዘመናት በፊት የተቆረጠው የድሬዳዋ የደምስር ድሬን በበቀለችበት ከዚራ አንደኛዋን ከምጧ መካን ድልጮራ ሆስፒታል አቅራቢያ፡ ከከዚራ ዛፍ ጥላዎቿ ስር አፈር ተመልሶባት፡ ደረት ደቅተን፡ አንደኛችንን፡ እርማችንን እናወጣለን፡፡

በቅን የልማት ራእይ ትልም ስም እቅዳቸውን በህዝቡ ፊት ያቀረቡትም፤ ከሂርና እስከ አለማያ ድረስ ካሉ የኦሮምያ ስፍራ ወጥተው ዝቅ ባለው የትምህርት ደረጃቸው ምክንያት ሲቪል ሰርቪስ የሚባል የመከነ ትውልድን እንዴት ማፍራት ይቻላል በሚል ጥያቄ መነሻ ምላሽነት ካሪኩለሙን የቀረፀ ስፍራ ላይ ብቻ በተማሩ ሰዎች እንድትመራ የተደረገችው ውቧ ድሬዳዋ ውስጥ ይቀር የነበረውን አስገራሚ ኢትዮጵያዊነት ገድለው በድሬዳዋ መቃብር ላይ የመጨረሻውን ሚስማር ቸንክረው ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ተልእኮን ይዞ ከጫካ ለወጣው የወያኔ መንግስት ታማኝ ሎሌነታቸውን ያስመሰክሩና ይሸለማሉ፡፡

ወደየያዙትም፡ ከዚራ የሌለችበት አዲስ ድሬዳዋን ያለማሉ ማለት ነው፡፡ …….ለነገሩ፡ የባቡር ጣቢያውም እኮ መልካጀብዱ አካባቢ ነው ያለው፡ ለቀደመው የድሬዳዋ ነዋሪ ራቅ ይላል፡፡ ለምን እዛ ድረስ ማሸሽ እንዳስፈለገ ባላውቅም፡ ለአዲሶቹ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ሰፈሮች ጉያ ስር እንደሆነ ግን አይቻለው፡፡ ዋቢ ለመጥቀስ ያክል አዲስ የተመሰረተው፡አወዳይ ሰፈር አንዱ ነው፡፡

ምን ትላላችሁ….. እኔ…… የሰይጣን ጆሮ ይደፈን ብያለሁ፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ ለአስራምናምን አመታት የዘለቀ ውርጅብኝ ድሬዳዋን ለምን ሲያላጋት ኖረ ብዬ ስጠይቅ፡ ትንሽም ቢሆን ለእውነት የቀረበ የመሰለኝና ያሳመነኝ ምክንያት አርእስት እንዲሆን አደረግኩት፡፡

ማለቂያ ከሌለው የአውሬው የወያኔ አገዛዝ የሸፍጥ ክምር መሃከል አንዲት እንቁ እየተንቦገበገች ትበራ ነበር፤ ይቺ እንቁ ድሬዳዋ ናት፡፡  ድሬዳዋ ከተማ ሳለች የሰው ሞት እንድትሞት የተደረገችው፡ ያንን አውሬው የማይወደውን፡ ዛሬ ለጥያቄ እስከመቅረብ ግርታ እግር ስር የወደቀውን ፡ ኢትዮጵያዊነት የምንለውን፤  ጌጣችንን ድሬ በመልኳና በህዝቧ ውህደት አጊጣበት ትታይበት ስለነበረች ነበር፡፡ እረ ጎራው ሲባል እየፎነነ የሚከተውን፤ አይደለም ለአድርባይ ወንበዴ፡ ብርቱ ክንድ ላለው ለጣልያን ጡጫ አይኑን ያልጨፈነ፤ ጥርሱን እንደነከሰ ሃያላንን እንደ ሸክላ ስሪት ቀለጣጥሞ ፤ እሳት በመንሽ እየረጨ ዶጋ አመድ ያደረገ አንድነት የሚርመሰመስባት የውህደት ምድር ስለነበረች ነው ከተማ ሆና እንደ ሰው ደሟ ፈሶ፡ ወዟ ገርጥቶ እንድትጣል የተደረገችው፡፡

ከበሽታም እጅግ ኋላ ቀር፤ በአራዳ ቋንቋ ( “በፋራ በሽታ”) መንበረ-ፀባኦት ፤ ደደቢት ጥምቀታቸው ላይ እንደቆረቡ የተያዙበት የአውሬው በሽታ፤ የመከፋፈልን፡ የብሄርተኝነትን እና ዘረኝነት በህገ-መንግስት ከትቦ በሽታውን እያስታመመ ለሚሰብክ ግዞተኛው ወያኔ፤ ድሬዳዋ ማርከሻው ነበረችና፤ አውሬው ወዲያው አጠፋት፡፡ ከምን ዘር እንደተወለዱ የማይገዳቸው፤ የአባት የእናታቸውን ዘር ሳያውቁ ቁልቢ ገብሬል በትሳስና በሃምሌ ተምመው በእግር የሚጓዙ፤ በእንቁጣጣሽ በኢድ፡ ፍራንክና ስጦታ ለልጆቻቸው ሳያዳሉ እየሰጡ፡ በአሊቢራህ ሙዚቃ ሽር የሚሉ፡ ዘመናዊ ዜጋ ነዋሪዎችን እንደማግኔት ትስብ የነበረችው ድሬዳዋ፤ የአውሬው መርዛም የዘረኝነት ልክፍት ማርከሻ ፀበሉ ስለነበረች፤ የሰው ሞት ተፈረዶባት ተፈጨሰች!፡፡

በልማት ራእይ ትልም ስም ፤ የወያኔን አጥፊ እቅድ፡ ለአመታት በድህነት ፍላፃ ተመትቶ አቅሙን ጨርሶ በድህነት በሚኖረው የድሬዳዋ ህዝብ ፊት የሚያቀርቡት፤ ከሂርና እስከ አለማያ ድረስ ካሉ የኦሮምያ ስፍራ ተመርጥው ፤ የድሬዳዋ መስተዳደር መሪዎች፤ መጀመሪያ የባቡር ጣቢያ እምብርት የሆነችውን ከዚራን የባቡር ጣቢያውን እምብርትነት አሳጥተው ባቡር ሃዲዱ ለነባሩ ነዋሪ ሳይሆን ፤ ከአወዳይ አለማያና፡ ከተለያዩ የሶማሌ ከተሞችና መንደሮች የሁለት መቶ ሺህ ብር የባንክ ስቴትመንትና የአወዳይ መታወቂያ ብቻ እያሳዩ ለሚመጡ ሰዎች ከድሬዳዋ ጥግ ፤ መልካ ጀብዱ አካባቢ ሄደው እንዲሰፍሩ የተደረጉ ነዋሪዎች በር ላይ የአዲሱ የባቡር ጣቢያ እንዲያርፍ አደረግው ጀመሩ፡፡ ከዚያ አመታት ጠብቀው ደግሞ ከዚራ ይፍረስ አሉ፡፡ እነኚህ ድሬዳዋን እንዲመሩ የሚመለመሉ የድንጋይ ማምረቻው ምርቶች፡ ናቸው፡፡

እነ አሰድን የመሰሉ ዝቅ ባለው የትምህርት ደረጃቸው ምክንያት ሲቪል ሰርቪስ የሚባል የመከነ ትውልድን እንዴት ማፍራት ይቻላል በሚል ጥያቄ መነሻ ምላሽነት ካሪኩለሙን የቀረፀ ስፍራ ላይ ብቻ በተማሩ ሰዎች እንድትመራ የተደረገችው ውቧ ድሬዳዋ ውስጥ ይቀር የነበረውን አስገራሚ ኢትዮጵያዊነት ገድለው በድሬዳዋ መቃብር ላይ የመጨረሻውን ሚስማር ቸንክረው ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ተልእኮን ይዞ ከጫካ ለወጣው የወያኔ መንግስት ታማኝ ሎሌነታቸውን ያስመሰክሩና ይሸለማሉ፡፡

ይህንን ለማረጋገጥ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ እና አቶ አሰድ ዛይድ የድሬዳዋን መሬት በሚዘገንን መልኩ በገሃድ ሸንሽነው ቸብችበው ካበቁ በኋላ በላቀ ሹመት የወያኔ መንግስት ስልጣን ሰጥቶ አዘዋውሯቸዋል፡፡ ይህ ነው ዋናው ምክንያት ድሬዳዋ፤ ይህ ነው ከባቡር መስመሯ የሚያገኙትን ጥሪት ለድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ በፍቅር ሲያካፍሉ የነበሩትን እና ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ሲቀልቡ የነበሩትን የድሬ ነዋሪዎችን በሌላ ቋንቋ፡ ኢትዮጵያዊነትን ከዘረኝነት ከፍ አድርገው ያሳዩ የነበሩ ህዝቦችን ይዛ የነበረችው እንቁ ፡ድሬዳዋን የሰው ሞት  እንድትሞት የሰዉዋት ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ነው፡፡

 

ያሬድ ይልማ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.