ጥጋብ የትም አያደርስም #ግርማ_ካሳ

 

በሰሜን ጎንደር በተለያዩ ቦታዎች የተኩስ ልውውጦች መደረጋቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች እየወጡ ነው። ከፋኝ በሚል ስም የሚንቀሳቀሱት በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈው የጎቤ መልኬ ወታደሮችና በሌሎች የጎበዝ አለቆች የሚመሩ የአማራ ተጋድሎ ታጣቂዎች ሲሆኑ፣ በዋናነት ከአገዛዙ ጋር እየተፋለሙ ያሉት ብዙ የወያኔ ወታደሮች እንደተገደሉም እየሰማን ነው።

ግንቦት ሰባት በአስመራ በኩል የሚያደርገው ትግል የትም ስላላደረሰው፣ በአማራው ክልል በራሳቸው ተደራጅተው በጎበዝ አለቆች ከሚመሩት አንድንድ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ለመመስረት እየሞከረ እንደሆነም ለማወቅ ችያለሁ። እነዚህ ድርጅቶች የፈጸሙትን ጥቃት ነው፣ በተያያዥነት፣ ኢሳት በአንዳንድ ቦታዎች ግንቦት ሰባት ጥቃት ፈጸመ ብሎ የዘገበው። እንጂ፣ ከኤርትራ የመጡ የግንቦት ሰባት ወታደሮች የፈጸሙት ምንም አይነት ጥቃት እንደሌለ አረጋግጫለሁ። ኤርትራ ያለው ነገር ያበቃለት ነገር ነው !!!!!!!!

እንደዉም ግንቦቶች አሁን ያለዉን ሁኔታ ማመኑ አሳፍሯቸው ነው እንጂ፣ ከወዲሁ እኮ ቀስ በቀስ ዳር ዳር እያሉን እው። ለማንኛውም እየተንሸራተቱም ቢሆን ፊታቸውን ከሻእቢያ ማንሳታቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው። ሻእቢያ ለራሱ ሕዝብ ያልሆነ ለተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጭራሽ ሊሆን አይችልም። ከጅምሩም አልሰሙንም እንጅ ይሄንኑ ነበር ስንንገራቸው የነበረው።

ግንቦት ሰባት እኔ አደረኩት ቢልም ባይልም፣ ግንቦት ሰባት ኖረም አልኖረም፣ በአገራችን ነገሮች ስር እየሰደዱ፣ ሕዝቡ አምሯል። ነገሩ እየከበደ መሆኑን ፣ ስልጣን ላይ ያሉ የተረዱት አልመሰለኝም። ሕወሃቶች ይመስለኛል ጎንደር በጦርነት ብትጥለቀለቅ ግድ የሚሰጣቸው አይመስለኝም። ይመስለኛል “እኛ ጋር እስካልደረሱ ድረስ፣ ብአዴኖችን፣ ኦህዴዶች…. እየላክን እርስ በርስ ይፋጁ። የሚወድመው እና የሚጎዳው፣ ተንደላቀን የምንኖርባቸው መቀሌና አዲስ አበባ፣ እኛ የምንዝናናባቸው ላንጋኖና ሶደሬ ..እስካልሆነ ድረስ፣ ደባርቅ ፣ ወገራ፣ ጋይንት …. ቢወድም እነርሱ ነው የሚጎዱት። በዚያ ያለው የገበሬው ማሳ ቢቅጣል የራሱ ጉዳይ ። ምን ጨነቀን ?” ብለው የሚያስቡ ነው የሚመስለኝ። ልክ ያኔ መንግስቱ ሃይለማሪያም ትግራይ እንደፈለገች ትሁን ብሎ ለወያኔ ትግራይን ለቆ እንደወጣው። አስታወሳለሁ ” መጠኔ መግዣ እንኳን የላቸውም” ብሎ፣ ከትግራይ አልፈው የትም የሚሄዱ አልመሰለዉም ነበር። ግን እንዳሰበው አልነሆነም። ትግራይን አልፈውም አዲስ አበባ ከበቡለት። እርሱም እንደ አጼ ቴዎድሮስ ራሴን እገድላለሁ ብሎ እንዳልፎከረ ፈርጥጦ ጠፋ።

አሁንም ህወሃቶች በጥጋብ ተነፍተው ባላሰቡት ጊዜ ጉድ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያወቁት አልመስለኝም። እነርሱ ከተሰነይ ወታደር ተነቃንቆ፣ ተከዜን ተሻግሮ እንዲመጣ ነው የሚጠብቁት። አይደለም፣ በጎንደር ያለው የትጥቅ ትግል ከኤርትራ በመጡ ታጣቂዎች የተጀመረ አይደለም። ዝም ብለው “ኤርትራ፣ ኤርትራ፣ ግንቦት ሰባት ግንቦት ሰባት .” ይላሉ እንጅ በደንብ ያውቁታል ትግሉ የሕዝብ ትግል እንደሆነ። በማናቸውም ጊዜ በሸዋ፣ በወሎ፣ በአዲስ አበባ ሳይቀር የታጠቁ ሃይሎች ሊነሱ ይችላሉ። ማን ያውቃል ይሄን ጊዜ ነገሮች ዉስጥ ውስጡን እየበሰሉም ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ በጎንደር እየተፋፋመ ያለውን የትጥቅ ትግል እንደ ማስጠንቀቂያ ወስደዉት፣ በቀላሉ ወደ ሌሎች ቦታዎች መዛመቱ እንደማይቀር ተረድተው፣ በቶሎ ማሻሻያዎችን ቢያደረጉ መልካም ነው እላለሁ። ይሄ ልመና አይደለም። ይሄ ማስጠንቀቂያ ነው። ጥጋብ የትም አያደርስም። ትሁት ሆኖ፣ የሕዝብን ጥያቄ ማክበሩ ይበጃል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.