እርስ በርስ የመረጋገም ልክፍት ፣ ግትርነት ፣ መንገኝነት ፣ ጊዜን አለማወቅ ቅጣቱ ብዙ ነው – ምንሊክ ሳልሳዊ

ይህችን የንቃት እውነት እንዋጣት። እንደፈልጉ ያሾሩሃል አንድ ጊዜ በዘር ፤ አንድ ጊዜ በሃይማኖት እየመጡ ይንጡሃል። ለምን ብለህ ራስህን ለመጠየቅ ሞራሉ የለህም።አጀንዳ መፍጠር አትችልም በፈጠሩት አጀንዳ እንደፈለጉ በንፋሳቸው ያነፍሱሃል። ወደ ፈለጉት ይጠልዙና ጎል ይከቱሀል። እርስ በርስም ትባላለህ።እነሱ ስራቸውን ይሰራሉ። የባከነው የለውጥ ሃይል አንተ ነህ። በፍጹም ባለህበት መርገጥና ከኋላህ ያለውን ሳታይ የፊጥ የተጋረደብህ ስለሆንክ ተስፋ ቢስነት ተጋግሮብሀል። መንቃት ያንተ ድርሻ ነው።መምከር ደግሞ የራሳቸው ጠላቶች ካልሆኑ ካለፈው የተማሩ ሰዎች ግዴታ ነው። እርስ በርስ የመረጋገም ልክፍት ፣ ግትርነት ፣ መንገኝነት ፣ ጊዜን አለማወቅ ቅጣቱ ብዙ ነው።

በስሜታዊነት፣ በዕልህና በግትርነት የትም አንደርስም፡፡ ግትርነት ለማመዛዘን እድል አይሰጥም፡፡ ግራ ቀኝ ለማየት ጊዜ አይሰጥም፡፡ የአብዛኞቻችን ዓይነተኛ ችግር ከስሜታዊነት የሚመነጭ ኃይለኛ ግትርነት ነው፡፡ ግትርነት እያለ ዲሞክራሲ ይፋፋል ማለት ደግሞ ዘበት ነው፡፡ ከግትርነት በላይ ቃል ቢኖር እንጠቀምበት ነበር፡፡ሌላ ብዙ ቅፅል፣ ብዙ ጭራና ቀንድ እየቀጠልን ለግትርነታችን ምክኑ ያ ነው እንበል እንጂ አብረን ያደግነውን ግትርነት የሚያክል ባላንጣ የለንም፡፡

እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል ማለት፤ ግትርነት ነው፡፡ ጠላቴ ያለበት አንድ ጥግ፣ እኔ ያለሁት ሌላ ፅንፍ፣ ብሎ መፈጠምም ግትርነት ነው፡፡ ሀብትን ማከማቸት አልጠግብ ማለትና ምንም ጥቅም ላይ ባላውለውም በእኔ እጅ ይሁን፤ ማለትም ግትርነት ነው። ሀብት ሲሰበስብ ከርሞ ሳይጠቀምበት የሚቀር በርሀብ ይሞታል፡፡ በአንፃሩ ሁሌ በማባከን መለከፍም ግትርነት አለበት፡፡ “አባካኝነት ለድህነት ይዳርጋል፡፡ ድህነት፤ ዕውነተኛ ድህነት፣ ሞት ነው” የኦዞ ዘፈን የሚለውንም ልብ ይሏል፡፡ በሀገራችን ጉዳይ ግልፅ በግልፅ እንነጋገር ሲባል በፍፁም እምቢኝ ብሎ ድርቅ ማለትም ግትርነት ነው፡፡ እርስ በርስ የመረጋገም ልክፍትም ግትርነት ነው ፡፡ ፊት ለፊት በመወያየት የጋራ መፍትሄ ማምጣት ያዋጣናል፡፡ የሆነውን ለመሸፋፈን ከመሞከር በግልፅ ማፈንዳት ወደፍሬ ያደርሰናል!

ለግልፅነትም፣ ለተጠያቂነትም፣ የሁሉ እናት – ክፍል ለሆነው ዲሞክራሲም፤ ዞሮ ዞሮ መጠቅለያው ጊዜ ነው፡፡ ለጊዜ በመገዛት ጊዜን መግዛት ነው ጥበቡ፡፡ ጊዜን ካወቁ እንዲሉ ስኬት ቅርብ ነው፡፡ መቼ ማፈግፈግ እንዳለብህ ዕወቅ – ጊዜው አልበሰለምና። መቼ አጥብቀህ መምታት እንዳለብህ ዕወቅ – ካረፈድክ ትጠቃለህና፤ ፡፡ የመጨረሻዋን ደቂቃ ተጠቅምባት፡፡ ጊዜን አለማወቅ ቅጣቱ ብዙ ነው። #ምንሊክ ሳልሳዊ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.