የጋምቤላ ኪዳነ ምሕረት የወርቅ ታቦት የደረሰበት ጠፋ፤ “የኮማንድ ፖስት አባል ነኝ” የሚሉት የሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንዳይጠየቁ ተፈሩ

ሐራ ዘተዋሕዶ

  • ጽላቱ በመንበሩ ላይ አለመኖሩን የሚያረጋግጥ የቪዲዮ ምስል በካህናቱ ተቀርጿል
  • በአፋጣኝ እንዲጣራና እንዲመረምር፣ ምእመናኑ መንበረ ፓትርያርኩን ተማፅነዋል
  • በምርመራና ማጣራቱ፣ ጽላቱን ከጥንቱ የሚያውቁ ካህናት እንዲካተቱ ተጠቁሟል፤

ዋና ሥራ አስኪያጁ፡-

  • “ጸሎት ላድርግበት” በሚል፣ ሌላ የወርቅ ጽላት ከመዘክር እንዲወጣ ወትውተው ነበር
  • ከሌሎች 2 ሓላፊዎች ጋራ፣ “የኮማንድ ፖስት አባል ነን” ስለሚሉ እንዳይጠየቁ ተፈሩ
  • “ጥያቄአችንን በቀጥታ ለሀ/ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እንዳናቀርብ ያሳስሩናል”/ምእመናኑ/

*                    *                 *

(አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፺፰፣ ቅዳሜ፣ መጋቢት ፳፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.)

በጋምቤላ እና ደቡብ ሱዳን አህጉረ ስብከት መንበረ ጵጵስና የምትገኘው፣ የሐመረ ኖኅ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ካቴድራል፣ ዕድሜ ጠገብ ታቦት፣ የደረሰበት አለመታወቁን የከተማው ምእመናን የተናገሩ ሲኾን፤ በአቋራጭ መክበር በሚፈልጉ ስግብግቦች እጅ ሳይገባ አፋጣኝ ማጣራትና ምርመራ እንዲካሔድላቸው መንበረ ፓትርያርኩን ጠየቁ፡፡

ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ትእዛዝ፣ በ1941 ዓ.ም. መታነጿንና ንጉሠ ነገሥቱ ሙሉ በሙሉ በወርቅ የተለበጠ የኪዳነ ምሕረት ታቦት እንዲገባ ካስደረጉ በኋላ፣ ሥርዓተ እምነታቸውን ሲፈጽሙባትና ሲማፀኑባት እንደኖሩ ምእመናኑ ጠቅሰው፣ ከየካቲት 24 ቀን ጀምሮ ግን፣ ታቦቱ በመንበሩ ላይ እንደሌለ ከካቴድራሉ ካህናት መስማታቸውን ተናግረዋል፡፡

ታቦቱ፣ በመንበሩ ላይ አለመኖሩን በመጀመሪያ ያረጋገጡት የካቴድራሉ አስተዳዳሪ እንደነበሩና ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ቄሰ ገበዙን እንደጠየቋቸው ያወሱት ምእመናኑ፣ ቄሰ ገበዙ፥ “እኔን ለምን ትጠይቁኛላችሁ? ሥራ አስኪያጁን ጠይቁ፤” የሚል ምላሽ በመስጠታቸው፣ “ኹኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎብናል፤” ብለዋል፡፡ይኹንና የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ በቀጥታ እንዳይጠይቁ የሚያሰጋቸው ነገር መኖሩን ነው፣ ምእመናኑ የሚናገሩት፡፡ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት ንጉሤ፣ ከሀገረ ስብከቱ የስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊና ከፕሮቶኮል ሹማቸው ጋራ፣ “የኮማንድ ፖስት አባል ነን” እያሉ እንደሚያስፈራሩ የጠቆሙት ምእመናኑ፣ “የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን ተጠቅመው ያሳስሩናል፤” ብለው እንደሚሰጉና ሁከት እንዳይቀሰቀስ ፍርሃት እንዳደረባቸው አልሸሸጉም፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከወራት በፊት፣ “ጸሎት አደርግበታለኹ፤ አምጣልኝ” እያሉ በካቴድራሉ ቤተ መዘክር ያለውን ሌላ የወርቅ ጽሌ እንዲያወጣላቸው ሓላፊውን ሲወተውቱ የነበሩ መኾናቸው የጥርጣሬአቸውን አቅጣጫ እንዳጠናከረላቸው ምእመናኑ አስረድተዋል፡፡

“ለምነን ያላፈርንባት፤ ችግራችንን ፈጥና የምትሰማን የኪዳነ ምሕረት ታቦት ጠፍታ እንዴት ዝም እንላለን፤ ብለን በአንድ ቦታ ተሰብስበን ከተመካከርን በኋላ በትዕግሥትና በሥርዓት ለሚመለከተው የበላይ አካል ማመልከትን መርጠናል፤” ያሉት ምእመናኑ፣ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት፣ ባለፈው መጋቢት 13 እና 14 ቀን፣ ጉዳዩን ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና ለፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት ማቅረባቸውን አስታውቀዋል፡፡

ሙሉ በሙሉ ከወርቅ የተሠራው ታቦት፣ የሀገርም ቅርስ መኾኑን ምእመናኑ ጠቁመው፣ በአቋራጭ የመክበር ምኞት በተጠናወታቸው ስግብግቦች እጅ ሳይገባ፣ በመንበረ ፓትርያርኩ መሪነት አስቸኳይ ማጣራትና ምርምራ እንዲካሔድላቸው ተማፅነዋል፤ ጽላቱ የሚቀመጥበት መንበር ባዶ መኾኑን የሚያሳይ በወቅቱ በካህናት የተቀረፀ የቪዲዮ ምስል በአባሪነት ማቅረባቸውን ገልጸው፣ ጽላቱ በመንበሩ ላይ ተገኘ ቢባል እንኳ፣ ዕድሜ ጠገቡ ጽላት ራሱ መኾኑን ለይተው በሚያውቁ ካህናት ታይቶ መረጋገጥ እንደሚኖርበት ጨምረው አሳስበዋል፡፡

ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ፣ የሀገረ ስብከቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ በእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡

አህጉረ ስብከቱን በዋና ሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት መጋቤ አእላፍ ቆሞስ አባ ተክለ ሃይማኖት፣ በክልሉ ከተመደቡበት ከመጋቢት ወር 1999 ዓ.ም. ወዲኽ፣ ቀደም ሲል 17 ብቻ የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ወደ 53 ማደጉንና በደቡብ ሱዳን ጭምር መታነፃቸው ተገልጧል፡፡ይህም፣ የዋና ሥራ አስኪያጁን ሐዋርያዊ ትጋት ያመለክታል ቢባልም፣ በአብያተ ክርስቲያናቱ አገልግሎት ቀጣይነትና አያያዝ ረገድ ከፍተኛ ጥያቄዎች መነሣታቸው አልቀረም፡፡ ለአብነት ያኽል፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የማይደፈረውን በመድፈር የደቡብ ሱዳንን(Upper Nile states) ባለሥልጣናት አሳምነውና መሬት ተረክበው ስድስት አብያተ ክርስቲያናትን መሥራታቸው በሪፖርት ለጠቅላይ ጽ/ቤቱ ተገልጿል፡፡

በመጨረሻው የጋምቤላ ክልል ድንበር፣ ኩኩሪ ቀበሌ ተሠርቶ የነበረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን

እውነታው ግን፣ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚወሰዱ ጽላት፣ ከጦርነቱ በኋላ የት እንደገቡ አለመታወቁ ነው፡፡ በግለሰብ ቤት ተሰብስበው እንደነበርና ኪራዩ በወቅቱ ባለመከፈሉ፣ በአከራዩ፥ አውጡልን፤ ሲባል እንደነበር፣ ወደ ስፍራው የሚመላሱ ነጋድያን ቢናገሩም፣ ርግጡ ግን እስከ አኹን አልተገለጸም፡፡ በጋምቤላ ክልል ድንበር ላይ፣ ኩኩሪ ቀበሌ የተሠራው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ዛሬ፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ መኖሪያ ቤት ኾኖ መታየቱ ሌላው አሳዛኝ ክሥተት ነው፡፡

በመጨረሻው የጋምቤላ ክልል ድንበር፣ ኩኩሪ ቀበሌ ተሠርቶ የነበረው የቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን፤ ዛሬ ጽላቱ ወጥቶ የአካባቢ ማኅበረሰብ መኖሪያ ቤት ኾኗል

በእነኝኽና በሌሎችም፣ አንዳችም ተጠያቂነት የሌለበት የዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ዓምባገነናዊ አመራርና አጠራጣሪ የእምነት አቋም አኳያ ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን መሠረት ያደረጉ፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን መሠረታዊ መፍትሔ የሚሹ በርካታ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች፣ ከአገልጋዮችና ከምእመናን በየጊዜው ወደ ማዕከል እየጎረፉ ይገኛሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.