መጀመሪያ ባለስልጣኖቹ የአህያ ስጋ መብላትን በደንብ እንደተለማመዱ ግንዛቤ ይያዝበት – ሸንቁጥ አየለ

 

ወያኔ የአህያ ስጋ በቻይና ነጋዴዎች በኩል ኤክስፖርት እንዲደረግ ሲፈቅድ የኢትዮጵያ ህዝብ መንፈሱ እንደ ሚበሳጭ : ልቡ እንደሚያዝን: የመዋረድ ስሜት እንደሚሰማዉና ተስፋ መቁረጥ እንደሚንጸባረቅ በደንብ ያዉቃል::የኢትዮጵያ ህዝብ እስላሙም ሆነ ክርስቲያኑ ወይም ሌላ እምነት ያለዉ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የባህል እና የመንፈሳዊ መሰረቱ ይሄን ነገር አጥብቆ የሚጽዬፈ እንደሆነ ያዉቃል::ሆኖም ወያኔ ሆን ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብን መንፈሳዊ መሰረተ ለማዋረድ ብሎም የባህል እሴቱን ወደ አልቦ ለመክተት ማንኛዉንም የጸረ ኢትዮጵያዊነት ስነልቦና የዉጭ ባህል እያመጣ ኢትዮጵያ ህዝብ መሃል ይደፋል::በዚህም ህዝቡን ተስፋ እንዲቆርጥ: ከመንፈሳዊነት እንዲላቀቅ: ባህል የሌላዉ ህዝብ እንዲሆን : ስነልቦናዉ የተሳከረ እና ግራ የተጋባ እንዲሆን የመደላድል አዉድማዉን ይጥላል::

ኢትዮጵያዊነት የጋራ መገለጫ እሴቶች እና የጋራ ዉህድ መንፈሳዊ መሰረቶች እንዳሉት ብሎም እነዚህ ህዝባዊ መሰረቶች ህዝቡን እንዳስተሳሰሩት የሚያዉቀዉ ወያኔ ይሄን መሰረት መናድ እንዳለበት የወሰነዉ ጫካ ሆኖ ነዉ:: የዘራዉ የጎሳ ልዩነት: የሀይማኖት የእርስ በርስ መቃቃር: የታሪክ መቆሳሰል እና አለመተማመን ጭብጥ ብሎም የኢትዮጵያዊነት ህላዌን የመካድ ጥልቅ እርሾ የመጨረሻዉን ፍሬ የሚያፈራለት በኢንቨስትመንት እና በኢኮኖሚ ልማት ስም ኢትዮጵያዉያን ያላቸዉ መሰረታዊ የመንፈሳዊ: የባህል እና የስነልቦና እሴት ሁሉ ለመጨረሻ ጊዜ ተዋርዶ ሲበጣጠስ እንደሆነ አስልቶ የተነሳዉ ወያኔ ምናልባትም ወደፊት የሰዉ ልጅ ኩላሊት መገበያያ ማዕከል በገሃድ በሀገሪቱ እንዲኖር ሊፈቅድና ኢትዮጵያዊነት የመጨረሻዉ የባዶነት ስሜት ዉስጥ ጠልቆ እንዲገባ ሊያደርግ እንደሚችል ይታወቃል:: ለነገሩ ምን የቀረ ነገር አለ? ግን ብዙ የቀረ የኢትዮጵያዊነት እርሾ አለ::ወያኔ የማያዬዉ ::እኛ ኢትዮጵያዊያኖቹ ግን የምናዬዉ !

በነገራችን ላይ ከጥቂት አመታት በፊት ከተወሰኑ የወያኔ ባለስልጣኖች አንደበት በገሃድ የሚሰማ ንግግር ነበር::ይሄዉም ቻይና በሚሄዱበት ጊዜ አብዛኞች የአህያ ስጋ እየበሉ እንደመጡ በኩራት ይናገሩ ነበር::የፈረስ ስጋም በላን ሲሉ የተደመጡ ነበሩ:: ይሄን እኔ እራሴ በጆሮዬ ሁሉ ሰምቼ ዘግንኖኛል:: እንዴዉም በአንድ የግል ጋዜጣ ላይ “ባህል እና የአመራር ስልት” የሚል አንድ ጽሁፍ አቅርቤ ነበር::እናም መጀመሪያ ባለስልጣኖቹ የአህያ እና የፈረስ ስጋ መብላትን በደንብ እንደተለማመዱ ግንዛቤ ይያዝበት::

የብልጽግና ጽንሰ ሀሳብ ሊቃዉንቱ በስፋት አብራርተዉ እንደ ገለጹት ሁል አቀፍ ብልጽግና (holistic development) በአንዲት ሀገር ዉስጥ ሊኖር የሚችለዉ ባህልን: መንፈሳዊነትን: ማህበራዊ መሰረትን: ህግን እና ፍትህን: ተቋማትን: ታሪክን: ስነልቦናን: ኢኮኖሚን: ፖለቲካን: አካባቢን : የሰዉ ሀብት ብልጽግናን እንዲሁም ሌሎችንም ተያያዥ ጉዳዮችን ሁሉ ያካተተ እና ግንዛቤ ዉስጥ ያስገባ የተሳለጠ የብልጽግና ፖሊሲ እና እስትራቴጅ ሲኖር ብቻ ነዉ ::ወያኔ ይሄን በደንብ ያዉቃል::ግን እርሱ ግቡ ኢትዮጵያን ማበልጽግ ሳይሆን ራዕይዉ ኢትዮጵያን ወደ አልቦነት ደረጃ በማዉረድ የዘቀጠ ማህበረሰብ የሚኖርባት ለአገዛዝ የምትመች የጎሳ ስብስብ የሆነች ስመ ሀገር ማድረግ ነዉ::እሱ ያለ ተቀናቃኝ እየጨፈረ እንዲኖር መሆኑ ነዉ::

የዝንጀሮን ቅኔ እዚህ ማጣቀሱ ግን መልካም ነዉ:-

የእግዜርን ነገር ምኑን አዉቀሽዉ :

ወይ እኔ እበላዉ አንቺ አርመሽዉ !

እናዳለች ዝንጀሮ ይሄ ሁሉ ደባዉ እራሱን የሚያጠፋ ብሎም ምናልባትም ደግሞ ኢትዮጵያዉያንን ባልታሰበ ሚስጥራዊ ኩነት የሚያስተሳስር እልህን የሚያጭር እርሾ ሆኖ ሊወጣ ይችል ይሆናል::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.