የአህዮች ሥጋ ለውጭ ገበያ በመቅረቡ የሀገራችን ምጣኔ ሀብት ሊሽመደመድ ነው! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

በተለይ ከተሜው አህያን ሲያስባት ጥቅም ያላት እንስሳ መስላ አትታየውም፡፡ ከዚህም የተነሣ ይመስለኛል አህያ የሚለውን ቃል ከባድ ስድብ መስደቢያ አድርጎ ይጠቀምበታል፡፡ ከዚህ ቀደም አባ ገብረሐና የዐፄ ቴዎድሮስ አገልጋይ ከነበረው ብላት ሐድጎ ጋር በነበራቸው ቁርሾ የተነሣ ሐድጎን አድጎ (አህዮ) እያሉ፡፡ ትግሬ የሚለውን የዘሩን መጠሪያም ተግሬ (መረገጫዬ፣ አገልጋዬ፣ ባሪያዬ) እያሉ እየተረጎሙ ይሰድቡት ስለነበረ ስድቡ ከግለሰብ መስደቢያነት ወደ ብሔረሰብ መስደቢያነት መሸጋገሩን፣ ብላታ ሐድጎም አባ ገብረሐናን ለዐፄ ቴዎድሮስ ደጋግሞ ከሶ አባገብረሐና ሊታረሙ ባለመቻላቸው ዐፄ ቴዎድሮስ የፍትሐ ነገሥት ዋና ባለሥልጣናቸውን አባ ገብረሐናን ክፉኛ አስገርፈው ከሀገር እንዲባረሩ እንዳደረጓቸውና አባ ገብረሐናም ወደ ትግሬ ተሰደው እንደነበር፣ ትግሮችም ጉዳዩን ያውቁ ስለነበረ “አንተማ አንድ ጊዜ አህያ! አንድ ጊዜ ባሪያ! እያልክ የምታንቋሽሸን አይደለህ!” እየተባሉ ጥርስ ተነክሶባቸው ትግሮቹ በአባገብረሐና ላይ ጨክነው ስለነበር አባገብረሐና የሚልሱት የሚቀምሱት አጥተው በስደታቸው ወቅት ከባድ የችጋርና የፈተና ወቅት አሳልፈው እንደነበረ መጻፌ ይታወሳል፡፡ አህያ የዚህን ያህል እርባናቢስ ተደርጋ ተቆጥራ ስሟ ከበድ ያለ ስድብ መስደቢያ ሆኖ አገልግሏል እያገለገለም ይገኛል፡፡

ነገር ግን አህያ እንደምናስባት ከንቱ እንስሳ ሳትሆን ለሀገራችን ምጣኔ ሀብት የጀርባ አጥንት ለሆነው ግብርና የጀርባ አጥንት የሆነች እንስሳ ናት፡፡ አህያ ለአርሶ አደሩ የግብርናውን ምርት ከማሳው እስከ ጎተራው ከጎተራውም ወደ ገበያ በማጓጓዝ ብቸኛ የምርት መጓጓዣ አገለግሎት የምትሰጥ እንስሳ ነች፡፡ ለአርብቶ አደሩ ደግሞ የጭነትና የመጓጓዣ አገልግሎት የምትሰጠው ግመል ናት፡፡ አህያ እርባታዋ አዝጋሚና እንደሌሎቹ የቤት እንስሳት እንደ ላም፣ በግ፣ ፍየል ፈጣን ባለመሆኑ ቁጥሯ አነስተኛና የተገደበ እንዲሆን ግድ ስላለ የጥቅሟን ያህል እንደልብ የምትገኝ እንዳትሆን አድርጓታል፡፡ ከዚህ ተፈጥሯዊ ችግር በተጨማሪ እሷን የሚያጠቃ በሽታ በመኖሩ ህልውናዋ እራሱ ለአደጋ እንደተጋለጠ ከ5 ዓመታት በፊት አሁን ስማቸውን የማላስታውሳቸው በሸገር ራዲዮ (ነጋሪተ ወግ) የቀረቡ በአህያ ላይ ጥልቅ ጥናት ያደረጉና ይሄንን የአህያን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ከነበሩ ዶ/ር (ሊ/ጠ) ጥናት ከተገለጠ ዓመታት ተቆጥሯል፡፡ የአህያ ችግር ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ቁጥሯ የሀገሪቱ ግብርና የሚፈልጋትን ያህል ባለመሆኗና አነስተኛ በመሆኑ የተነሣ ገበሬው ያሉትን አህዮች እየተዋዋሰ ከአቅማቸው በላይ የሚያሠራቸው በመሆኑ በአህዮቹ ላይ የሚያጋጥመው ተደራራቢ ተደጋጋሚ አካላዊ ጉዳት ሌላው ችግር ነው፡፡

እንግዲህ በእነኝህ ችግሮች ምክንያት ቁጥሯ ግብርናው በሚፈልገው መጠን ላይ ልትሆን ያልቻለችውንና እየተመናመነች የመጣችውን፣ ለአርሶ አደሩ አገልግሎቷን የሚተካ ሌላ እንስሳ የሌላትን ጠቃሚ እንስሳ ቄራ አስገብቶ ሥጋዋን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ምን ያህል ድንቁርና እንደሆነ ለመገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ነገሩ ለቻይኖቹ “ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር ይቆረጣል!” እንደሚባለው ነው የሆነላቸው፡፡ በአስተውሎት ከተመለከትነው ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ ቻይኖቹ እኛን እራሳችንን በልተው መጠቀም እንደሚፈልጉ የሚያሳይ እጅግ ጭካኔና ራስወዳድነት የተሞላበት ተግባር ነው እየፈጸሙብን ያሉት፡፡

ሥጋቱን የሚያጎላው ሌላው ምክንያት ደግሞ ገበሬው አህያ እጅግ የምትጠቅመው መሆኑንና የማትተካ፣ ያለእሷ ምንም ሊያደርገው የሚችለው ነገር የሌለ መሆኑን ቢያውቅም ባለበት የቤት ጣሪያ አስነቅሎ የሚያሸጥ የማዳበሪያ ዕዳና ችግር ምክንያት አህያውን እንዲሸጥ በሚቀርብለት አማላይ ዋጋ እየተደለለ ለመሸጥ የሚገደድ መሆኑና በዚህም ምክንያት አህያ ከአብዛኛው ገበሬ እጅ ከመጥፋት አንሥቶ ባጠቃላይም ከሀገራችን እስከመጥፋት ልንደርስ እንደምትችልና በዚህም ግብርናው አከርካሪው ሊሠበር የሚችል መሆኑ፡፡ ግብርናው ተመታ ማለት ደግሞ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብትም ተሽመደመደ ማለት መሆኑ መታወቅ ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ክፉ የሚመኙልንና የሚጥሩብንም ተሳካላቸው ማለት ነው፡፡ ባንዳው፣ አህያው እንዳልል አህያ የዚህን ያህል ጠቃሚ ሆነች! ደንቆሮው ልበላ! እንዲሁም የደደቢት ልጅ ደደቡ፣ ቅጥረኛው ወያኔም የሚፈልገው ይሄንን አይደል? ባይሆን ኖሮ የአህዮች ቁጥር ለእኛ ለራሱ ለምትሰጠን አገልግሎት በቂ እንዳልሆነች እየታወቀ፣ አገልግሎቷ የማይተካ መሆኑ እየታወቀ እንኳንና ላልረባ ዋጋ ሽያጩ ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገባ ቢሆንም እንኳ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑ እየተወቀ እንዴት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ይወሰናል? ነው ወይስ ወደ ቻይኖቹ የአህያ ቄራ የሚገባው የሞተ አህያ ብቻ ነው? እንዲያ ቢሆንም እንኳ ራሱ ጅቦቻችንና መሰል አራዊት የሚበሉትን አጥተው በሰውና በከብቶች ላይ ሊፈጥሩት ከሚችሉት የደኅንነት ሥጋትና አደጋ አኳያ ፈጽሞ ሊፈቀድ አይገባም!

እንዲያው ነገሩን እንድታውቀው ብየ ነው እንጅ ይሄንን ማስገንዘቤ አንተስ እንኳን አህያህን አንተን እራስህን ቄራ እያጋዘ አወራርዶ ቢሸጥህ እራስህን ለማዳን፣ ህልውናህን ለመታደግ አንዳች ነገር ታደርጋለህ ብየ ተስፋ ማድረግ እጅግ ይቸግረኛል፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.