በደሴ ግዳጅ ከሕዝብ ጋር አንጣላም ያሉ ሚሊሻዎችና ፖሊሶች መሣሪያ ሊገፈፉ ነው፤

 ዓባይን በእግር የሚሻገሩ ሰዎችን ለመከልከል የተለቀቀው ግድብ ጉዳት አደረሰ፤

ሚዚያ 2 ቀን 2009 ዓ.ም፤ በደሴና አካባቢው ያሉ የታጠቁ ሚሊሻዎች ራቅ ወደ አሉ አካባቢዎች ለተልዕኮ አንሔድም በማለታቸው ትጥቃቸውን እንዲያስረክቡ ታዘዋል፡፡ ዛሬ ጠዋት አካባቢ ከደሴ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ሚሊሻዎች ያስታጠቀን ሕዝብ በመሆኑ መሣሪያ አንመልስም በማለታቸው ከአስተዳደር አካላት ጋር ፍጥጫ ተፈጥሯል፡፡ በደሴ ከተማ የሲቪል ፖሊሶች ታማኝ አይደላችሁም በሚል ግምገማ መሣሪያ እንዳይዙ ታግደዋል፡፡ ከሰሞኑ መሣሪያ የተከለከሉት ፖሊሶች እገዳው እስከመቼ ድረስ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነገር የለም፡፡

በተያያዘ የደሴ ከተማ ነጋዴዎች ሥራ ባለመሥራታችን ግብር ልንከፍል አይገባም የሚል ተቃውሞ አንስተዋል፤ መምህራን በበኩላቸው አመጻቸውን አጠናክረው እንደቀጠሉ ሰምተናል፡፡
በሌላ በኩል በዓባይ ድልድይ ምክንያት ከሁለት ተከፍላ የሰነበተች የባሕር ዳር ከተማ ለዜጎቿ ስቃይ ሆናለች ተብሏል፡፡ ድልድዩ በመዘጋቱ ምክንያት የዓባይን ወንዝ በዋና እንዲሁም ድንጋይ ባለበት አካባቢ ደግሞ በእግር ለመሻገር መፍትሔ ያደረጉት የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የጨርጨራ ግድብ ተከፍቶ ጉዳት አድርሷል ተብሏል፡፡ በዋና እና በእግር የሚሻሩ ሰዎችን ለመከልከል የተለቀቀው ግድብ ምክንያት በቀበሌ 10 እና 11 የዓባይ ወንዝ አጠገብ የጓሮ አትክልቶች ተጠራርገው ተወስደዋል ብለውናል እማኞቻችን፡፡ ከወንዙ ዳር አንድ ኪሜ ርቀት ላይ ያለ የአትክልት ቦታ ድረስ ጉዳት አድርሷል ያሉት ምንጮች በድንገት የተለቀቀው ግድብ ከባሕር ዳር ራቅ ብለው ባሉ ገበሬዎች ማሣ ላይና የሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.