በመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቀረበ የእርቀ ሰላም ጥያቄ – በዶ/ር ሶሎሞን ጉግሳ

April 9, 2017

“ማንም። እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?”  ፩ኛ የዮሐንስ መልዕክት ም. ፬ ቁ. ፳.

ውድ የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ የእትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በሻርለት እና ይህን ጽሁፍ ለምታነቡ ኢትዮጵያውያን በሙሉ፤

እንደምን ሰነበታችሁ።

የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በሻርለት ኖርዝ ካሮላይና ከተመሰረተ ፲፯ አመታት በላይ አስቆጥሯል። የቤተክርስቲያኑ ታሪክ እንደሚያስረዳው በነዚህ ዓመታት ውስጥ አራት ግዝያት ያኽል ከፍተኛ ሊባሉ የሚችሉ እና በዚሁም ሳቢያ ምዕመኑ በተፈጠረው የአስተሳሰብ ልዩነት ጎራ ለይቶ የተተራማመሰበት ነበር ማለት ይቻላል።ከነዚህ አራት አበይት ክስተቶች ሦስቱ በልዩነት ከቤተክርስቲያኑ የተለዩ ምዕመናን የየራሳቸውን ቤተክርስቲያን በማቋቋም የተደመደሙ ነበሩ። አራተኛው ግን የነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት በሚመስል መልኩ በመካሰስ ላለፉት ሦስት ዓመታት በጣም ፈታኝ ከመሆንም አልፎ በግለሰብ እና በቤተሰብ ላይ ትልቅ እንግልትን ያስከተለ ነበር። ከሳሹም ተከሳሹም ችግር የደረሰበትም ያልደረሰበትም ሁሉም “ከእብድ ገላጋይ” በማበር ራሱን ያብከነከነበት ጊዜ ነበር ያሳለፍነው። በሌሎች የአሜሪካ ግዛትም ይሁን በሌላው ክፍለ ዓለማት እንደሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በሰላምም ይሁን በጸብ ከመለያየትና የራስን የአምልኮ ቦታ (ለጊዜውም ቢሆን ከሚስማሙ ወንድምና እህቶች ጋር) ከመመስረት በባሰ መልኩ ምርጫ እንኳን ያሳጣ ነበር ማለት እችላለሁ።

በዚህ ማስታወሻዬ ያሳለፍነውን ታሪክ መዘርዘር አንባቢውንም ማሰልቸት በአሁኑም ወቅት አስፈላጊነቱ ስላልታዬኝ አንኳር አንኳሩን ብቻ አስረዳለሁ። በዚህ አቀራረቤ አንዳንድ ጉዳዮች ተጨማሪ ትንተና እንደሚያስፈልጋቸው ­­በአንባቢው ፍላጎት ካየሁ  ተከታታይ ጽሑፍ ለማቅረብ ወይም በቀጥታ ለመነጋገርም የሚፈለግ ግለሰብ ወይም አካል ካለም በሀሳቡ ላይ ተመርኩዞ ለመነጋገርም ፈቃደኛነቴን አስቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ።

የቤተክርስቲያናችን አራተኛው አለመግባባት መነሻ፤

ማንኛውም በአሜሪካ በቦርድ በሚተዳደር ቤተክርስቲያን አሰራር መሰረት የሚመራው የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያናችን አብረውን በመንፈሳዊ አስተዳዳሪነት አገልጋይ የነበሩትን መነኩሴ ሲያሰናብት የሰበካ ጉባኤው የቤተክርስቲያኑን መተዳደሪያ ደንብ በመከተል ነበር። ለውሳኔም የነበረው አስገዳጅ እና ጭብጥ ሃሳብም ለቤተክርስቲያናችን ብቁና የሚጠበቅባቸውን ቤተክርስቲያን የመጠበቅና የማስጠበቅ አግልግሎት ያለመስጠታቸው ብሎም ሁሉንም ምዕመን እንደ አባት በእኩል መንፈስ ማስተዳደር ባለመቻላቸው ነበር። ያም ሆኖ የሰበካ ጉበኤው አባትነታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ሌላ ቦታ እስከሚያገኙ ድረስ እንዲረዳቸው ብሎ $3000.00 ለግሶ ነበር። ሆኖም ባለመስማማታቸው እና ባስቸኳይ ወደ ጠበቃ ሄደው ከመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አገልግሎት መሰናበታቸው ተገቢ አለመሆኑን እና የሰበካ ጉባኤውም በአስቸኳይ ከሃላፊነት እንዲወርድ የሚጠይቅ ደብዳቤ ይዘው በመምጣት በጉልበት ለማስፈጸም ሲሞክሩ ሁኔታዎች ተቀያየሩ። ከዚያም አልፎ ተርፎ በሳቸው መገለል ምክኒያት ሁኔታውን በመወያየት መፍታት ሳይሆን እሳቸው በቀደዱት መንገድ የቤተክርስቲያኑ አባላት የሆኑት ካልሆኑት ጋር ተቀናጅተው ባጠቃላይ 23 ግለሰቦች (ሦስቱ የሰበካ ጉባኤ አባላት) የተገለሉትን መነኩሴ መነሻ በማድረግ የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያንን እና በሰበካ ጉበኤ የምንገኘውን ፱ ሰዎች March 27, 2014 የጀመሩት ክስ ይኸው በሦስት ዓመቱ (March 16, 2017) በኖርዝ ካሮላይና ጠቅላይ ፍርድ ቤት (NC Supreme Court) ውሳኔ ሊጠናቀቅ ችሏል። በዚህ ባሳለፍነው ሦስት አመታት ውስጥ በግሌም ሆነ ከሰበካ ጉበኤ ጋር በመሆን ለመፍታት ጥረት ባደርግም የተለያየ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች ዝምድናን እና/ወይም የትውልድ አካባቢን መሰረት አድርጎ በተሰባሰበ የውስጥም የውጭም ሃይል በመነሳቱ የሚፈለገውን እርቀ ሰላም ማምጣት አልተቻለም።

የእርቀ ሰላም ሙከራዎች፤

የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንን እና የሚያስተዳድሩትን የሰበካ ጉባኤ አባላት ክስ እንዲቆም እና ወንድምና እህት የሆንን የአንድ አገር ሰዎች ሰላም እና ፍቅራችን እንዲመለስ ለማድረግ ከየአቅጣጫው ብዙ ተሞክሯል። ሙከራዎቹን በሙሉ በየሶስት ወሩ ስናደርግ በቆየነው የአባላት አጠቃላይ ስብሰባም ላይ ሆነ በየሰንበቱ በአውደ ምህረቱ እየተገኘን ስናስታውቅ ቆይተናል። ለአብነት ያኽል በ 6/15/14፣ 1/11/15፣ 3/8/15፣ 8/23/15፣ 12/27/15፣ 3/27/16፣ 7/10/16 እና በ 10/30/16 በተካሄዱት የአጠቃላይ አባላት ስብሰባ ላይ ሰለ እርቅና እና ሰላም የቤተክርስቲያኑ ሰበካ ጉበኤ በሰፊው ዘግቦታል። በግልም ሆነ በቡድን በመነሳሳት የተሞከሩ የእርቀ ሰላም ሂደቶችን ጨምሮ ከአስር ጊዜያት በላይ ተሞክሯል። ከዚህ በታች የገለጽኳቸው ግን አንኳር የሚባሉትን ሰባቱን ነው።

፩ኛ/ በስደት ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ባመለከትነው መሰረት ብፁዕ አቡነ ዲሞጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (የቀድሞው ቆሞስ አባ ጽጌድንግል) እና መላከ ገነት ገዛኸኝ ተመድበው ለእኔ ግልጽ ባልሆነ መንገድ ነገር ግን በወቅቱ መላከ ገነት ገዛኸኝ እንዴት የሀገር ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ በሌሉበት እኛ መምጣት እንችላለን? ብለው በጠየቁኝ ምክኒያት ይመስላል ስይመጡ ቀሩ:: በወቅቱ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ እንደ አባትነታቸው ልጆቻቸውን በእኩል መንፈስ በመመልከት ነገሩን ለማዬት ከመሞከር ይልቅ ከመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን አገልግሎት ለተወገዱ መነኩሴ ለአባ ገብረማርያም እና ለከሳሾች በመቆማቸው እምነቱን ስላጣን ነበር ለስደተኛው እና ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶሳችን ያመለከትነው እና ጉዳዩንም ለማየት አስታራቂ አባቶች የተመደቡት።

፪ኛ/ የመጀመሪያ ጠበቆቻችን በነበሩት በ Mr. Julian እና በ Ms. Snead አማካኝነት በ Mrs Sara Krumer በኩል የተካሄደው የ April 10, 2015 (የስቅለት ዕለት) የእርቅ ጥረት ለመጀመሪያ ጊዜ ጮራን የፈነጠቀ ነበር። ሆኖም ቀኑን በሙሉ ስንደራደር ቆይተን በመጨረሻ ከሳሽ ወገኖቻችን ከኛ ተሻሽሎ የቀረበውን ሃሳብ አንቀበልም ብለው ድርድሩን ካልተጨማሪ ውይይት አቋርጠው ወጥተዋል። ዋናው የተለያየንበት ጉዳይ የ 2013 ማሻሻያ ደንብን የመቀበልና ያለመቀብል ጉዳይ ነበር።  በቤተክርስቲያናችን በኩል የ 2013 ማሻሻያ ደንብ ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ዋነኛው በስደት ያሉትን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዎስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያን እና እሳቸው የሚመሩትን ቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበልንበት ነበር። ነገር ግን ከሳሾች አንዱና ዋናው የክሳቸው ጭብጥ ይህን ማሻሻያ ደንብ እውቅና አለመስጠት ስለነበር አልተስማማንም። እዚህ ላይ አንድ ነገር ጠቆም አድርጌ ማለፍ እፈልጋለሁ። የስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ አባል የሆኑት የሀገረ ስብከታችን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ  ከቤተክርስቲያናችን አገልግሎት የታገዱትን አባ ገብረማርያምን እና ከከሳሾችን የወገኑት ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስን የሚቀበለውን የ 2013 ማሻሻያ ድንብን የሚቃወሙትን ማለት ነው ። በእውነት ይህ ወገናዊነት እምነቱ ላይ የተመሰረተ ነውን? ፍርዱን ለአንባቢው።

፫ኛ/ የፕሮቴስታንት ዕምነት ተከታይ ሦስት ወንድሞቻችን በጋራ ያደረጉት ጥረት በእውነቱ ሁለተኛው ትልቅ ተስፋ የታየበት ነበር። ይህ እርቀ ሰላም በ May 12, 2015 ተጀምሮ የቤተክርስቲያናችን የሰበካ ጉበኤ አባላትን እና ከሳሾችን ፊት ለፊት በ June 14, 2015 አገናኝቶ ለመጀመሪያ ጊዜ በባህላችን ወግና ስርአት እርቀ ሰላም እንዲወርድ ያስተቃቀፈን ነበር። ነገር ግን ቤተክርስቲያናችን የሥላሴ በዓልን በደመቀ መልኩ ለማክበር ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጳጳሳትን ሲመድብልን ከሳሽ ወገኖቻችን ከአባ ገብረማርያም ጋር በመሆን በጋራ ለሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት ጳጳሳት ለምን ይመጣሉ ጥያቄ ትልቅ አምባጓሮ ተፈጥሮ ይኸኛውም እርቀ ሰላም ሊጨናገፍ ችሏል።

፬ኛ/ ይህ ሽምግልና በብፁዕ አቡነ ሉቃስ የሚመራ ሆኖ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስን እና ዶ/ር ቀሲስ አንዱአለም እንደዚሁም በሕጋዊ ቅዱስ ሲኖዶስ ስር ከተዋቀረው የቤተክርስቲያናት አንድነት ማህበር ዶ/ር አምባቸውን እና አቶ ምርጫውን ያካተተ ነበር። በእውነት ለመናገር የሰበካ ጉበኤው ባለው ጽኑ የእርቅ ፍላጎት የተነሳ በሥላሴ ዋዜማ በ July 10, 2015 እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ከአባቶች ጋር ያደረገው ስብሰባ፣ በበነገታው July 11, 2015 በሥላሴ በዓል እለት ከተወሰኑ የከሳሾች አባላት እና ከአባ ገብረማርያም ሃይሉ ጋር በዶ/ር ቀሲስ አንዱአለም ስብሳቢነት የመነጋገሪያ አጀንዳችንን ለመቅረጽ ያደርግነው ጥረት ነበር። ሆኖም በ July 12, 2015 ከሳሾች ሁለት ተወካይ ግለሰቦች ልከው በአባቶች መነጋገር እንደማይፈልጉ መግለጻቸው ከዚያም አልፎ ተርፎ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ እስከ ሚመለሱበት July 13, 2015 ድረሰ ያደረጉት ጥረት በሙሉ ሳይሳካ መቅረቱ በእውነት ልብ የሚሰብር ነበር።

፭ኛ/ አሁንም ለእርቅ እና ለሰላም ባለኝ ጽኑ ዕምነት ለሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ አመልክቼ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ (የቀድሞው ቆሞስ አባ ጽጌድንግል) እና መምህር ፍሬሰው አነጋግረውኝ ትልቅ ተስፋ አድርጌ ነበር። ነገር ግን አባቶች ያቀረቡትን ማለሳለሻ መንገድም ሆነ እኛን እና ከሳሾች ወገኖቻችንን የማነጋገር ዕቅድ አልተሳካም። ምክኒያቱም ከሳሾች ጉዳዩን በሕግ አግባብ እንጨረሰዋለን ብለው ለአባቶች በሰጡት መልስ ነበር። አባቶችም እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን እንዲጠብቅ እንጸልያለን እናንተም በጸሎት ተግታችሁ እርቀ ሰላሙን እግዚአብሔር እንድያድለን ተመኝተውልን ተሰናብተውኛል።

፮ኛ/አሁንም ጥረቴን ባለማቋረጥ ከዚህ በፊት ከጴንጤዎች ወንድሞቻችን ጋር በነበረው እርቀ ሰላም የተሳተፈና ከከሳሾች ጋር የሚገናኝ ግለሰብ ጋር በሌላ በሶስተኛ ወገን ባደረግኩት ግንኙነት አሁንም እንደገና የእርቅ በሩ እንዲከፈት ሆነ። የሰበካ ጉባኤው እና ከሳሾች ይህ ከከሳሾች ጋር በሚገናኘው ግለሰብ ሰብሳቢነት በ 6/19/16 በጣም በጋለ ስሜት ተነጋግረናል።ልዩነታችንንም ሆነ አንድነታችንን ገለጽለጽ አድርገን ስለተነጋገርን በእውነት እያንዳንዳችን ምን እንደምንፈልግ የታወቀበት በአይነቱ የመጀመሪያ የሚባል ነበር ብል ማጋነን አይደለም። በወቅቱ የነበረውን ስብሰባ ያሳረግነው ቅድመ ድርድሩን ለመቋጨት አንድ ተጨማሪ ስብሰባ ማድርግ ሲሆን የሚመቸንንም ቀን ለሰብሳቢው በአንድ ሳምንት ውስጥ ማሳወቅ ነበር። እኛ የሰበካ ጉባኤ አባላት የሚመቸንን ቀን ቆርጠን ስናሳውቅ ከሳሾች ባለማሳወቃቸው ብሎም በነበረን ስብሰባ ላይ የነበሩትን ክርክሮች ምክኒያት በማድረግ የትም አይደርስም የሚል አባባል በሰብሳቢው በኩል ስላስነገሩን ይህም ጥሩ ጅምር ከሸፈ።

፯ኛ/ ይህ የመጨረሻው ጥረት ደግሞ በ 10/30/16 ከቀሩት የቤተክርስቲያን አባላት ጋር ያደረግነው ስብሰባ ነበር። ለአባላቱ የቀረበው የእርቀ ሰላሙ ጥያቄ በረብሻ እና እኛን (በተለይ እኔን) ቢያንስ ላለፉት ፫ ዓመታት ብዙ ሸክም ተሸክመን ቤተክርስቲያናችን እንዳይዘጋ ጥረት ያደረግነውን አገልጋዮች እንዳናያችሁ፣ እናንተ ቤተክርስቲያኑን ስላዳከማችሁ ምርጫ ብቻ አካሂዳችሁ ጥፉ የተባልንበት ስብሰባ ነበር። ሃላፊነታችንን ለማስተላለፍ ድሮም ቢሆን ተቃውመን አናውቅም። ይኸው ዛሬ በኛ ላይ ጣታቸውን የቀሰሩት “አባላት” ይህን ቤተክርስቲያን ሳታረጋጉ መውረድ የለባችሁም ስላሉን እንጂ በሰውኛ ካየነው ከልፋት በስተቀር ምንም ጥቅም የሌለውን ስልጣን ፈልገነው አልነበረም። ቤተክርስቲያናችንን እንድማንኛውም ተቆርቋሪ አባል ከመከላከል ውጭም ፍላጎት እንዳልነበረን ያሳለፍነውን ጊዜ ዘወር ብሎ ማዬት ተገቢ ነበር። ስለዚህ ባጭሩ ከስርዓት ውጭ በረብሻ መልክ ቢሆንም በእለቱ እርቅ እና ሰላም አንፈልግም ተብሎ ተደመደመ። ይህ የከሸፈው ጥረት ከታች ወረድ ብዬ እንደምገልጸው በተገኘው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ መሰረት ከከሳሾች አራት ግለሰቦች ከምዕመናን ደግሞ ከ፲፪ የማያንሱ ምዕመናን በጠየቁት የእርቀ ሰላም ጥያቄ መሰረት ነበር። ሆኖም ከላይ “የውስጥም የውጭም ሃይል በመነሳቱ የሚፈለገውን እርቀ ሰላም ማምጣት አልተቻለም” በሚል ጠቅለል ባለ መልኩ ከሽፏል ማለት ይሻላል። ዝርዝሩ አሳዛኝ ታሪክም ስላለው አልፌዋለሁ።

የፍርድ ቤት ውሳኔ፤

ቤተክርስቲያናችን እና የሰበካ ጉባኤ ፱ አባላት ክስን በተመለከተ ብዙ ውጣ ውረድ ብናሳልፍም አበይት የምላቸውን ብቻ በቀናትና በዓመታት ቅደም ተከተል (Chronological order) እንደሚከተለው እዘረዝረዋለሁ። ለሕዝብ ፍጆታ (public consumption) የዋሉትን ሊንኩን በመጫን ለማንበብ ይቻላል።

  • የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴና ዘጠኝ የሰበካ ጉባኤ አባላት Animaw Azige et al v. Holy Trinity Ethiopian Orthodox Tewahdo Church, et al file number 14-CvS-5590 በመክለምበርግ ካውንቲ March 27, 2014 ክስ ቀረበባቸው፤
  • ከሳሾች በአንድ በኩል ከላይ በተጠቀሰው መልኩ ከሰው በሌላ መልኩ ደግሞ ለ NC Consumer Protection Division ባስገቡት ማመልከቻ መሰረት በ July 16, 2014 በጽሁፍ ተጠይቀን አስፈላጊውን መልስ ስለሰጠን በዚህ በኩል የሄዱበት ስሞታ የትም አልደረሰም፤
  • November 5, 2014 በነበረው ችሎት ከሳሾች የነበራቸውን ጠበቃ ከ Ohio ባስመጡት ተክተው ከአንድ ቀን በፊት የነበራቸውን ክስ ያዋጣል በሚሉት መንገድ አስተካክለው በማስገባታቸው ቀጠሮ ተሰጥቶ ተለያየን፤
  • Decenber 9, 2014 በዋለው ችሎት ጉዳዩን ያዩት ዳኛ (Judge Robert C. Ervin Superior Court, Mecklenburg County) በውስጡ ስላለው ዝርዝር ጉዳይ ሃሳብ ሳይሰጡበት የከሳሾች ስሞታ በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው ሲወስን የቤተክርስቲያኑ የክሱ ማሰረዣ ጥያቄ ውድቅ ተደረገ፤
  • ቤተክርስቲያናችን ግን በነበረው ጽኑ የወንድማማችነት ከዚያም ባለፈ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችን በሚያስገድደን መሰረት የውስጣችን የቤተክርስቲያን አባላት አለመግባባት መፈታት ያለበት በቤተክርስቲያን እንጂ በዓለማዊ ፍርድ ቤት እንዳልሆነ አበክሮ እና ዘርዝሮ ይግባኝ አለ። ይግባኙን መሰረት በማድረግ በ September 6, 2016 የከፍተኛው ፍርድ ቤት (NC Superior Court of Appeals) በሦስት ዳኞች በሙሉ ድምጽ በ Decenber 9, 2014 የነበረውን ውሳኔ ሻሩት። ይህ ውሳኔ የከሳሾችን ስሞታ ማዬት ፍርደ ቤት በቤተክርስቲያን እምነት ላይ ገብቶ እንዲፈርድ ስለሚያስገድድ ይህንን ማድረግ ደግሞ የአሜሪካን ሕገ መንግስት መጻረር ስለሚሆን ፍርድ ቤት ስሞታውን ማዬት የለበትም የሚል ነበር። https://appellate.nccourts.org/opinions/?c=2&pdf=33730 ውሳኔውም በአንድ ወቅት ቤተክርስቲያኑን በሚያስተች መልኩ ዘግቦ የነበረው የከተማው ዋነኛ ጋዜጣ (Charlotte Observer) ሳይቀር ዘግቦትም ነበር። http://www.charlotteobserver.com/news/politics-government/article100218712.html
  • በየጊዜው ስለ እርቀ ሰላም እንደማሳስበው ሁሉ አሁንም ከዚህ ውሳኔ በኋላ በኢትዮጵያ አቆጣጠር መስከረም ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም. በቤተክርስቲያኑ ዓውደ ምህረት ላይ ቆሜ እርቀ ሰላም እንዲወርድ ጠይቄ ነበር። ሆኖም ከላይ በጥቅሉ (ዝርዝር ሳያስፈልገው) በገለጽኩት መሰረት ሳይሳካ በመቅረቱ ከሳሾችም ይግባኛቸውን ለኖርዝ ካሮላይና የመጨረሻው የፍርድ ቤት አካል ለሆነው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቀረቡ።
  • በተለይ ከ 10/30/16 በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ያለው መተራመስ እየተባባሰ በመምጣቱ እንኳን እርቀ ሰላም ከከሳሾች ወገኖች ጋር ለመፍጠር ቀርቶ ቤተክርስቲያናችንን እና ሰበካ ጉባኤውን “እንከላከላለን” የምንለው እርስ በራሳችን መደማመጥ ስላልቻልን በግሌ የወሰድኩት አቁም ቢኖር ራሴን ለተወሰኑ ግዚያትም ቢሆን ከቤተክርስቲያኑ ገለል አድርጌ የመጨረሻውን የአለማዊ ፍርድ ቤትን መጠባበቅ ነበር። እግዚአብሔር ግን ታጋሽ የሆነ የፍቅር አምላክ ነውና በዚህ ክስ ምክኒያት በየትኛውም ወገን ያለነውን መረጋጋት እንድናገኝ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት የሚጠበቀውን ውሳኔ ከአምስት ወራት ጊዜ በኋላ እንድንሰማው ፈቃዱ ሆነ። የኖርዝ ካሮላይና የጠቅላይ ፍርድ ቤት (NC Supreme Court) የከሳሾችን ይግባኝ ሰረዞ የከፍተኛ ፍርድ ቤት (NC Superior Court of Appeals) ውሳኔ እንዲጸና አደረገ። https://appellate.nccourts.org/orders.php?t=P&court=1&id=322803&pdf=1&a=0&docket=1&dev=1

በክሱ መራዘም ምክኒያት ራሳችንን ጎዳን፤

የቤተክርስቲያናችን የሰበካ ጉበኤ የመተዳደሪያ ደንባችን በሚያዘው መሰረት የመንፈሳዊ አስተዳዳሪ መነኩሴ ከተገለሉ በኋላ ራሳቸውን መነኩሴውን ጨምሮ ሌሎቹም ወንድምና እህቶች እንዲሁም ቤተክርስቲያኑን እንከላከላለን የምንል በሙሉ ቀስ በቀስ ወደ አእምሮአችን ተመልሰን እርቀ ሰላም ከማውረድ ይልቅ በሆነውም ባልሆነውም ምክኒያት በየጊዜው የተገኙትን የእርቀ ሰላም በሮች ክርችም እያደረግን መዝጋቱን ተያያዝነው።

በተለይ በ September 6, 2016 የ NC Superior Court of Appeals ለቤተክርስቲያኑ በፈረደበት ወቅት በቤተክርስቲያኑ ዓውደ ምህረት ላይ ቆሜ አሸናፊና ተሸናፊ የለም የሚያስፈልገን አጠቃላይ እርቀ ሰላም ነው ብዬ በተናገርኩበት ወቅት ልክ ቤተክርስቲያን እንደማያውቅ እምነት የለሽ አሸንፈናል እንጂ ለምንድነው ያላሸነፍነው? በሚል አንዳንዶቹ የቤተክርስቲያኑን ሳይሆን የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ ሰውን ለመቀስቀሻ ተጠቀሙበት። ከዚያም አልፎ ከከሳሾችም የተወሰኑ ከምዕመናንም የተወሰኑ መጥተውም ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ የሰበካ ጉባኤውን ቢጠይቁ ግቢ ውስጥ “አምባጓሮ” ተነስቶም ነበር። ያ ከየት እንደመጣ ብዙ ሰው ያልተገነዘበው የውስጥ ተቃውሞ October 30, 2016 ባካሄድነው የቤተክርስቲያናችን አጠቃላይ ጉባኤም ተደገመ። ስለእርቅ ባነሳ እርቅ አንፈልግም አንተንም ልናይህ አንፈልግም ተባለ። አልፎ ተርፎም በኔ ላይ የስድብ ጋጋታ፣ እንዲህ አይደረግም ብለው የተናገሩትንም ሆነ ሳያስቡ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩት ሁሉ ቤተሰብን እንደሁም ጓደኝነትን ሁሉ በሚያፈራርስ መልኩ በዙ ችግር እንዳለፈ በጣም የቅርብ ጊዜ መጥፎ ትዝታ ነው። በዚህ ሂደት ያሳለፍነውን የምጠይቀው ጥያቄ አለኝ። ለመሆኑ ስንሰራ የነበረውን ረጋ ብለን አስበነው እናውቃለን? ምን ያህል እግዚአብሔር ታጋሽ እንደሆነና ስንት ጊዜ እድሉን እንደሰጠንስ ለአንድፍታም ቢሆን በህሊናችን ውልብ ብሎ ያውቃል? ለዚህ ነው አሁንም ታጋሽ የሆነው የሰማዩ አምላካችን እግዚአብሔር ሌላ እድል የሰጠን። ይህ እድል አሁንም እንዳለፈው “አሸንፋናል” መባል አለበት ተብሎ መደናቆራችንን መቀጠል ሳይሆን ዕድሉን ባግባቡ መጠቀም አለብን ባይ ነኝ። ፍርድ ቤት የግድ ለአንዱ ወገን ስለሚፈርድ ባልተግባቡት ወገኖች መካከል ዘላቂ ሰላምና እርቅን ሊያመጣ አይችልም። እርቅና ሰላምን ለማምጣት መጣር ያለብን እኛው የአንድ አገር ልጆች ነን።

ባጠቃላይ ሲታይ የክሱ መራዘም ቤተክርስቲያናችን ከከሳሾች ጋር ባለው አለመግባባት ብቻ ሳይሆን ገና ከመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት “የእብድ ገላጋይ ዱላ ያቀብላል” እንዲሉ ከሳሾች ወንድምና እህቶችም ሆኑ ቤተክርስቲያናችንን እንከላከላለን ብለው የሚያስቡ ወንድምና እህቶች እንደዚሁ በሚቀበሉት ምክር ማለት እችላለሁ አሁን ላለንበት የተዳከመ ሁኔታ ላይ ደርሰናል። በመሰረቱ ግን ሲታይ ምክር ማንም ሊሰነዝር ይችላል ነገር ግን ውሳኔ ምንግዜም የራስ ነው። በዚህም ምክኒያት ድክመቱ ዞሮ ዞሮ በማንኛውም ወገን ለመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቆመናል ብለን የምናስበው በሙሉ ነን ባይ ነኝ። ለሁላችንም ትምህርት ይሆን ዘንድ በዚህ ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት ያየኋቸውን መሰረታዊ የአካሄድ ችግሮችን እንደሚከተለው አቀርበዋለሁ።

፩ኛ/ ከመነሻው ቤተክርስቲያንን ወደ ዓለማዊ ፍርድ ቤት ከመውሰድ በፊት ያለመግባባቱን በንግግር ለመፍታት መሞከር ተገቢ ነበር። ከክሱም በኋላ ሆነ በፊት የቤተክርስቲያናችንን ችግር ለመፍታት የምንሞክረው በዝምድናና በጓደኝነት ነው። ለዚህም ነው ክሱ ላይ እያለን እንኳን ቤተክርስቲያናችንን “እንከላከላለን” ብለን የቀረነው እንኳን መግባባት ያልቻልነው። ይልቁንም ወደ ተመሳሳይ አዙሪት የገባን ይመስላል። ይህን ለመገንዘብ አሁን “ተመረጡ” ተብሎ ያየናቸውን የሰበካ ጉባኤ አባላት ብናይ የቤተክርስቲያኑን መተዳደሩያ ደንብ ያልተከተለ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ እይታ እንኳ መልክ የሌለው (ፍረንጆቹ bad optics ይሉታል) መሆኑ አግራሞትን ይጨምራል። ታዲያ ይህ ለሌላ ችግር መዘጋጀት የሚመስል አካሄድ ምን ይሉታል? በዚሁ ከቀጠልንስ ማብቂያውስ የት ይሆን? በዚህ መንገድስ እየሰራን ቤተክርስቲያን መመላለሳችን በረከት እናገኛለንስ ብለን ማሰብ ራስን ማታለል አይመስልምን?

፪ኛ/ በቤተክርስቲያናችን ክስ ምክኒያት በመሃከላችን ያለው አለመግባባት እስካልተፈታ ድረስ የቤተክርስቲያናችን ዋና የገቢ ምንጭ የነበረው የስቴዲዮም የሥራ ዕድል ከ 2015 ጀምሮ እንደማይቀጥል ባሰሪዎቻችን ሲነገረን የቤተክርስቲያናችንን ወጪ 50% በላይ የሚሸፍነው ገቢ ሲቋረጥ ሁላችንም አዝነን ነበር። የሚገርመው ግን ይህ ገቢ ሲቋረጥ ከዚህ በፊት በአንድ አባላችን ጠቋሚነት ሥራ ይገኝበታል የተባለውን ካምፓኒ በማነጋገር የተወሰኑ ቀናት PNC music Pavilion በተባለው ቦታ ከሰራን በኋላ ለዓመት ኮንትራት ዕድሉን ሲሰጡን እኛው ቤተክርቲያናችንን “እንከባከባለን” የምንለው ባለመግባባት ስራውን አንፈልግም ብለን ደመደምን። በጉልበታችን እየሰራን ለቤተክርስቲያናችን ገቢ ይሁን ያሉትን አባላት ሁሉ በቤተክርስቲያኑ ስም መስራት አትችሉም ብለን የቤተክርስቲያናችንን ገቢ እኛው ዘጋነው። ታዲያ ይህ አካሄድ አዋቂነት ነበር ትላላችሁ? እንዲዚሁ በራችንንም ዘግተን ገቢ የሚያስገኝ ነገር ሁሉ አንፈልግም ብለን በጣም በተወሰኑ አባላት በወርሃዊ መዋጮ መቀጠል እንችላለን?

የመፍትሄ ሃሳብ፤

ይህ በኖርዝ ካሮላይና በሻርለት ከተማ ከተቋቋመ ከ ፲፯ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን ውስጥ በእግዚአብሔር ፈቃድ ልጆች ወልደን አሳድገን ለቁም ነገር ያበቃን አሁንም ኑሮአችንን እንዲባርክልን ወደፊትም ለምንመሰርተው ቤተሰብ ጸጋውን እንዲያላብሰን ለኢትዮጵያ አገራችን እና ለሕዝባችን ምህረትን ባጠቃላይ በእያንዳንዳችን ሕይዎት ሰላም እና ፍቅርን እንዲያድለን የምንጸልይበት ብዙ የሥላሴ ልጆች አለን። በመሆኑም ተረጋግተን እና ሰከን ብለን ማሰብ ይኖርብናል።

በኔ አስተሳሰብ ኑሮ አስተማሪ ነው ብዬ ስለማምን ወድቀን መነሳት እንችላለን ብዬ ከልቤ አምናለሁ። በየግላችን የደረሰብን ብዙ ነገር አለ ብለን ማሰቡ ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ልባችንን ለማደነደን ብቻ ነው የሚረዳው። ስለዚህ ሁሉንም ለቸሩ ፈጣሪያችን በመስጠት ሁላችንም ለእርቅ እንድንዘጋጅ ያስፈልጋል የሚል ጽኑ ዕምነት አለኝ። ­­­ስለዚህ አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ እንደገና እርቀ ሰለም በቤተክርስቲያናችን እንዲወርድ በሥላሴ ስም እጠይቃለሁ። ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት እርቁ አጠቃላይ እንጂ ቡድናዊ እርቅ እንዲሆን ፍላጎት የለኝም። ተገቢም ነው ብዬ አላምንም። ይሁን እንኳን ብለን ባለመረዳት ብንቀጥልበት የሚጸና እርቅ አይሆንም። ከአሁን ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ይህ ቤተክርስቲያን ቢያንስ ላለፉት ስድስትና ሰባት አመታት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ውዝግብ ውስጥ ገብተን የተበታተንን ወንድምና እህቶችን የሚያካትት አጠቃላይ እርቅ አስፈላጊ ነው ባይ ነኝ። ይህን ለማድረግ ደግሞ ያሳለፍነውን ተሞክሮአችንን እንኳን ባንጠቀም በዝናም ሆነ በውስጡ ባላፍንበት የምናውቀውን ኢትዮጵያዊነታችንን ብንይዝ በቂ ነው እላለሁ። ስለዚህ ሁላችንም የነበረንን የመጠላላት መንገድ አስወግደን ለእርቅ እንድንዘጋጅ በድጋሚ በሥላሴ ስም እጠይቃችኋለሁ። በእርቀ ሰላሙ ሃሳብ ከተስማማን ይህን እርቀ ሰላም ማን ያካሂደዋል የሚል ጭንቀት ሊኖርብን ይችላል። መልሱ ቀላል ነው። የሚያስፈልገው የሁላችንም የልብ መነሳሳት ነው። እኔ በበኩሌ ዛሬውኑ ለሚደረግ አጠቃላይ እርቅ ዝግጁ ነኝ። ከዚህ አካባቢ እርቁን ሊያካሂድ የሚችሉ የሉም እንኳን ቢባል ከሌላ ቦታ በእድሜአቸውም ሆነ በአስተሳሰባችው የከበሩ ብዙ ኢትዮጵያዊ ወገኖች ስላሉ እነሱን ማነጋገር ሁሉ ይቻላል። ጉዳዩ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ያጣናቸውን ወይም የተሰወሩብንን የኢትዮጵያዊነት እሴቶቻችንን የማስመለስ እንጂ ከአንፍጫ እርቀት በላይ በማያስኬድ የአስተሳሰብ ድህነት ላይ ሙጭኝ ማለት አይደለም።

የእርቀ ሰላሙ ሂደት ዝርዝር ሲጀመር የሚታይ ቢሆንም ለመንደርደሪያ ሊጠቅም ይችላል ብዬ ያሰብኳቸውን ላካፍል።

፩ኛ/እስካሁን ድረስ በውጭም በውስጥም የሚካሄደውን መጎነታተል እንደማይጠቅም ተረድተን ከሳሾች ወንድሞችና እህቶቻችንን እጃችን ዘርግተን ይቅር ለእግዚአብሔር በማለት ቢያንስ ከመካሰሳችን በፊት ወደነበርንበት ብንመለስ፤

፪ኛ/ እስከአሁን የተጓዝንበት መንገድ እንደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልምዳችን ብዙ የሚያወላዳ እንደማይሆን ተገንዝበን በሰላም እና በፍቅር ተመልሰን ቤተክርስቲያናችንን ከምንኖርበት አገር ሕገ ደንብ ጋር በማጣጣም ማገልገል እና በመንፈሳዊ በኩል ደግሞ ለአባቶች አስፈላጊውን ክብር በመስጠት በመንፈሳዊ መንገድ እንዲመሩን እድሉን መስጠት፤

፫ኛ/በዚህ በክሱ ምክኒያትም ይሁን በተለያየ ምክኒያት ከመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን በሻርለት የቀሩብንን ወንድሞችና እህቶች የሚጋብዝ ጥሪ በአስቸኳይ ብናሰራጭ፤ ሁል ጊዜ አስተሳሰባችን ሰፊና ፍጹም ታጋሽ መሆን ጥቅም አለውና።

አጠቃላይ አስተያየት፤

በመሰረቱ በየሰንበቱ በየአውደ ምህረቱ ላይ የሚሰጠው ቃለ ሕይወት ወደ ውስጣችን ዘልቆ ስብዕናችንን የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ለዚህ አንዳረግም ነበር። መቸም ሰው በመሆናችን ራሳችንን በነጻነት ለመግለጽ በምናደርገው መፍጨርጨር በመሃከላችን ጸብ እንኳ ቢፈጠር ቢቻል እራሳችን ባስቸኳይ ተነጋግረን ብንፈታው ካልሆነም በኢትዮጵያዊ የችግር አፍታት ስልት ሽማግሌም በገባበት ነበር። ነገር ግን እንዳለመታደል ሆኖ በስደተኛውና ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶሳችንም ቢሆን በውስጡ ያለው አንዳንድ አለመግባባት የአንድን አብያተ ክርስቲያን ጉዳይ በመንፈሳዊ መልክ መፍታት አለመቻሉ ትንሽ ቅር ያሰኛል። ማንም አማኝ እንደሚረዳው የወንድሞችና እህቶች አንድነትና ፍቅር ከዓለማዊ ፍርድ ቤት አይጠበቅምና አሁንም ቢሆን ከቅዱስ ሲኖዶሱ ብዙ እንጠብቃለን። በተለያዩ  ምዕመናንን በሚያካትት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉበኤ ላይ ተገኝቼ በተደጋጋሚ እንደሰማሁት እንደግድግዳ ደግፎ ጣሪያውን (ቅዱስ ሲኖዶሱን) የሚሸከመው ምዕመኑ ነውና በኛ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ችግር ባለባቸው ሁሉ በመድረስ ምዕመኑን ማጽናናት ይጠበቅበታል።

ሌላው ማሳሰቢያዬ ግን አንዳንድ ጉዳዩን ከሁሉም ወገን ሳይሰሙ ከአንድ በኩል ብቻ በሚናፈስ አሉባልታ ከመረበሽም አልፈው ከርቀት ሆነው ስለአንድ የቤተክርስቲያን የውስጥ አሰራር ፍርድ መስጠት ብሎም በግለሰብ ላይ ያነጣጠረ ትችትን በጭፍኑ መሰንዘር ለኔ በጣም አስደንጋጭ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ምክኒያቱም እነዚህን የምላቸውን ግለሰቦች ለወደፊት የኢትዮጵያ ሁኔታ ሲስተካከል ሊመሩን ይችላሉ ብዬ የማስባቸው ዓይነት መሆናቸውና እንዲህ ዓይነት ፈርደ ገምድል አስተሳሰብ ሳይባቸው ስጋቴ ስለሚጨምር ነውና ልብ ሊሉ ይገባል። ይህን አስተያየት የሰጠሁት ከምላቸው ግለሰቦች ጋር ለወደፊት በግል የመነጋገር ፍላጎት እንዳለኝ እንዲገነዘቡት ከወዲሁ እንዲያውቁት ለማድረግ እንጂ ሌሎች እንደሚያደርጉት በዚህ ባደባባይ ለመነታረክ ፈልጌ አይደለም። ምናልባት ሃሳቤን ሳቀርብ ሃይለ ቃል ተጠቅሜ ከሆነ አንባቢውንም ሆነ በዚህ በቤተክርስቲያናችን ጉዳይ የሚነካቸውን በሙሉ ይቅርታችሁን እየጠየኩ የእርቀ ሰላም ሂደቱ ተሳክቶ መካነ ብርሃን ቅድስትሥላሴ ቤተክርስቲያንን የምንል በሙሉ የአንድነትና የፍቅር ታሪካችንን መልሰን ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲኮራብን እየተመኘሁ ጉዳዬን እዚህ ላይ እቋጫለሁ።

ጸሐፊውን በኢሜይል ማግኘት ከፈለጉ solkoki11@gmail.com

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.