አፄ ሱስንዮስን ማነው ማንነት የሚለግሳቸው? – አንዱዓለም ተፈራ – የእስከመቼ አዘጋጅ

ረቡ፣ ሚያዝያ ፬ ቀን ፳ ፻ ፱ ዓመተ ምህረት

የነበረን መተረክ እንጂ፤ ጠምዝዞ በመለወጥ ያልነበረ ማድረግ አይቻልም።

አሁን ላለንበት የፖለቲካ ቀውስ ተጠያቂዎቹ እኛው ያሁኖቹ ነን። አሁን ያለንበትን የፖለቲካ ሀቅ ለመቀየር፤ ኃላፊዎቹ፤ የአሁኖቹ እኛው ነን። የትናንቱ ሀቅ፤ ትናንት በነበረው ሁኔታ የተሸመቀቀ ስለሆነ፤ ያንን ተረድቶ፤ ዛሬ ያለበትን ሁኔታ እንዳለ እንዲቀጥል ማድረግ፤ የገዥዎች ጥረት ነው። ይሄንን ለመቀየር መጣር ደግሞ፤ የታጋዮች ግዴታ ነው። በዚህ ስብጥር ሂደት፤ ወደ ኋላ ተመልሶ፤ አንድም ተጠያቂነትን ለቀድሞዎቹ መሥጠት፤ አለያም ደግሞ፤ ያልነበረን እንደነበረ፤ የነበረን ደግሞ እንዳልነበረ በማድረግ፤ ወደዚያ እንዳንመለስ ዓይነት ሙገታ ሲቀርብ ይታያል። በጥቅሉ፤ ይህ ሁሉ ጥረት፤ “እኔ ምንም ኃላፊነት የለብኝም!” ብሎ፤ የቀድሞዎቹን ለሁሉም ነገር ተጠያቂ በማድረግ፤ ለማምለጥ የሚደረግ የዛሬ ግብዞች ሩጫ ነው። ታሪክን መረዳት እንጂ፤ ጠምዝዞ ለመለወጥ የሚደረግ ጥረት፤ የታጋዮች ተግባር አይደለም። እስኪ በዚህ ግባት፤ የአፄ ሱስንዮስን ማንነት እና ሌሎች ለሳቸው ሊለጥፉባቸው የሚከጅሉትን ቀለም እንመለከት።

በቅድሚያ፤ ታሪካችንን የምናገኘው በሁለት መንገድ ሰፍሮ ነው። የመጀመሪያው በግዕዝ ከተጻፉትና፤ በግለሰቦች እጅም ሆነ በደብራት ከሚገኙ የብራና ጽሑፍት ነው። ሌላው ደግሞ፤ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው፤ እኒሁኑ መጽሐፍት አገላብጠውና አስተርጉመው፤ ለራሳቸው ምርምር በሚረዳቸው መንገድ በዘገቡ የውጪ ጎብኝዎች፤ ወይንም የታሪክ ተመራማሪዎች ነው። ባንደኛውም ሆነ በሁለተኛው መንገድ የምናገኘው ታሪካችን፤ አሁን ላለነበት ሁኔታ ተጠያቂ አይደለም። ነገር ግን፤ ያንን ተረድተን፤ ያንን አውቀን፤ እኛ አሁን ያለንበት ሁኔታ የራሳችን ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን፤ ትምህርት ለመውሰድ ይረዳን ዘንድ፤ በትክክል ማወቁ፤ የግድ ነው። አሁንም፤ የነበረን መተረክ እንጂ፤ ጠምዝዞ ያልነበረ ማድረግ አይቻልም።

የኢትዮጵያን የነገስታት ታሪክ በዘመናዊ መልክ ጽፈው ካገኘኋቸው ኢትዮጵያዊያን ውስጥ፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የመጀመሪያው ናቸው። ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የጻፉት፤

ዋዜማ።

በማግስቱ የኢትዮጵያን ነገስታት

የታሪክ በዓል ለማክበር፤

የሚለው በ ፲ ፺ ፻ ፳ ፩ ዓመተ ምህረት የመጀመሪያ ዕትሙ፤ በ ፳ ፻ ፩ ዓመተ ምህረት ደግሞ፤ የልጅ ልጃቸው አቶ ሽመልስ ይልማ ያሳተሙት መጽሐፍ፤ መረጃዬ ነው።

በዚህ መጽሐፍ ገጽ ፶ ፬ የሚጀምረው ምዕራፍ ፮፤ በኢትዮጵያ የነገሡትን ነገሥታት፤ ከአፄ ይኩኖ አምላክ ( የክርስትና ስማቸው፤ ተስፋ እየሱስ )  እስከ ጎንደሩ ንጉሥ አፄ ሠርፀ ድንግል ድረስ ዝርዝራቸውን ያቀርባሉ። አፄ ይኩኖ አምላክ፤ ከዛጔ ነገሥታት ተደብቀው ይኖሩ የነበሩ፤ የቀዳማዊው የሚኒልክ ተወላጅ ናቸው። አፄ ይኩኖ አምላክ እሰከ ዛጔው ንጉሥ ነዓኩተለዓብ ድረስ በድብቅ ቆይተው፤ በኋላ በአቡነ ተክለሃይማኖት ጣልቃ ገብነት፤ የሚኒልክን ትውልድ በሥልጣን ላይ ለማውጣት ባደረጉት ጥረት፤ ተሳክቶላቸው፤ ለመንገሥ በቅተዋል። ይህን ሁሉ ሂደት፤ አሁን በዚህ ወቅት የምንገኝ ሰዎች፤ አሁን ባለን ግንዛቤ መቀበሉ ያዳግተናል። ነገር ግን፤ መረዳት ያለብን፤ የዚህ ወቅትና የኛ ወቅት የተለያየ መሆኑን ነው። የተለያየ ማለት ደግሞ፤ በግንዛቤም ጭምር ነው።

ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በዚህ ዝርዝራቸው፤ ከአፄ ይኩኖ አምላክ በቀጥታ የሚወለዱት ፳ ፬ ኛው ንጉሥ አፄ ልብነ ድንግል ናቸው፤ ብለው አስፍረዋል። አፄ ልብነ ድንግል በነበረው የፖለቲካ ሀቅ፤ የአፋርና የሶማሌ ወገኖቻቸውን አሰባስበው በዘመቱባቸው በአህመድ ኢብን ኢብራሂም ( በተለምዶ ግራኝ መሐመድ ) ተገደው፤ ግዛታቸውን ከሸዋ ነቅለው ወደ አማራው አገር ወስደዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴም ይሄንኑ ታሪክ፤

A History of

Modern Ethiopia

1855 – 1991

በሚለው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዕትማቸው፤ የአፄ ይኩኖ አምላክን አነጋገስ፤ ከብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ለየት ባለ መንገድ፤ በመቅድማቸው በገጽ ፰ እና ፱ ላይ ይሄንኑ አስፍረዋል።

ለዚህ ጽሑፍ፤ እኒሁ ሁለቱ ማስረጃዎች፤ ከሞላ ጎደል ሌሎች ያካተቱትን አጠቃለው ስለሚይዙ በቂ ናቸው። ሆኖም ግን ይሄንኑ ታሪክ ለማመሳከር፤ ሌሎች ከዚሁ ትረካ ጋር አንድነት ያላቸው ጹሑፍት መኖራቸውን ከወዲሁ እገልጻለሁ።

እዚህ ላይ አንድ ሀቅ ማስፈር እፈልጋለሁ። ምንም እንኳን አሁን በኛ ጊዜ ቦታ ባይኖረውም፤ በዚያ ወቅትም ሆነ እስከዛሬ ድረስ፤ ነገሥታት በተለያየ ሁኔታ፤ ከተለያዩ ወገኖች፤ መጋባታቸውና መዋለዳቸው ሀቅ ነው። ሆኖም ግን፤ ጋብቻ የሚፈጽሙት፤ ለነበሩበት የፖለቲካ ሁኔታ መጠቀሚያ ለመግዛት እንጂ፤ ዘራችንን ለመቀየጥ ወይንም ማንነታቸውን ለመለወጥ፤ ስሌት አግብተው አልነበረም። እናም ከሌላ ወገን ሲያገቡ፤ ያ ወገን በግዛታቸው ተጠቃሎ እንዲገብርላቸው ነበር። እናም፤ አብዛኛው ነገሥታት፤ ከሌላ ወገን ሚስቶችን በማምጣት ተጋብተዋል። በዚህም ግዛታቸውን አስፍተዋል። ጠብ አብርደዋል። ተቀናቃኞቻቸውን አምክነዋል። የንግሥና የትውልድ ቆጠራቸውን በነገሡት አባቶቻቸው ስበዋል። በዚህም፤ የአብዛኛዎቻቸውን እናቶች ካለማወቃችን ባሻገር፤ የእናቶቻቸው ትውልድ፤ ባፈ ታሪክ በተለወሰ ልቁጥ ተሸክፏል።

ወደ አፄ ልብነ ድንግል ስንመለስ፤ አጠቃላይ የንግሥና ዘመናቸው፤ ከ ፲ ፭ ፻ እስከ ፲ ፭ ፻ ፴ ድረስ ለሰላሳ ዓመት ሲሆን፤ ልጃቸው አፄ ገላውዲዎስ፥ ፲ ፱ ዓመት ነግሠዋል። በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ግጭት፤ ቱርኮች አህመድ ኢብን ኢብራሂምን ሲረዱ፤ ፖርቹጋሎች ደግሞ ንጉሡን ይረዱ ነበርና፤ አፄ ገላውዲዎስን፤ ፖርቹጋሎች አወናብደው፤ የእኩልነት ግዛት ስጠን ሲሏቸው፤ ከፈለጋችሁ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ መኖር ትችላላችሁ። ከዚህ ሌላ ግን አባቴ ምንም ውለታ አልገባላችሁም፤ በማለት፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ፤ አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀዩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ እንጂ፤ የፖርቹጋል መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ፤ በኢትዮጵያ መሬት እንዳይያዝ ብለው አዘዋቸዋል። የአፄ ገላውዲዎስ ልጅ፤ አፄ ሚናስ ናቸው። አፄ ሚናስ፤ ወደ ሸዋ ከመመለስ ይልቅ፤ በጎንደር እንደነገሡ ቀሩ። ልጃቸው አፄ ሠርጸ ድንግል መንግሥታቸውን በጎንደር ስላደረጉ፤ የጎንደር መንግሥት በሳቸው እንደተጀመረ ይነገራል።

እንግዲህ ወደ ጽሑፌ ርዕስ ስመለሰ፤ አፄ ሠርፀ ድንግል አፄ ያዕቆብን ይወልዳሉ። አፄ ያዕቆብ ደግሞ አፄ ሱስንዮስን ይወልዳሉ። አፄ ሱስንዮስ የዝነኛው የአፄ ፋሲል አባት ናቸው። ከአራት አምስት ወራት በፊት ከዶከተር ኃይሌ ላሬቦ ጋር ባደረግሁት ልውውጥ፤ የዚህ የአፄ ሱስንዮስን የትውልድ ጉዳይ አንስተን ነበር። እሳቸው፤

እንግዴህ ስለአፄው ከሆነ፣ እኔ እንደማውቀው እሳቸው ማለትም አፄው ( አፄ ሱስንዮስን ማለታቸው ነው – የኔ ) ራሳቸው በቀጥታ ከደቡብ ብሔረሰብ አይወለዱም። ከደቡብ ብሔረ ሰብ ዝምድናቸው በምንዝላታቸው ማለትም በዐምስተኛ አባታቸው ሊሆን ይችላል። የአፄ ናዖድ እናት ወይንም የአፄ በዕደማርያም ባለቤት ንግሥት ሮምኔ [ሮማነወርቅ] ትውልዳቸው ከአዳል ወይንም ከሐዲያ ነው የሚል ዜና አለ። ግን ርግጠኝነቱ ያጠያይቃል።”  ( መመንዘል = ማክበድ  – የኔ )

ብለውኛል።

እዚህ ላይ፤  አፄ ናዖድ à አፄ ልብነ ድንግልን à አፄ ገላውዲዎስን à አፄ ሚናስን à አፄ ሠርፀ ድንግልን à አፄ ያዕቆብን à አፄ ዘድንግልን è ከዚህ በኋላ አፄ ሱስንዮስ የተከተሉ መሆናቸውን ላሰምርበት እፈልጋለሁ። ( አምስተኛ ሳይሆን በቀጥታ ከቆጠርነው ሰባተኛ መሆኑ ነው። በተጨማሪ፤ ከአፄ በዕደማርያም የተከተሉት አፄ እስክንድር ሲሆኑ፣ ከአፄ እስከንድር ደግሞ አፄ አምደ ጽዮን ተከትለዋል። አፄ ናዖድ ከዚያ ነው የቀጠሉት። ነገር ግን፤ ይሄን ብልም፤ የወንድማማቾች መከታተል ሊኖር ስለሚችል፤ ዝርዝሩን ላለማንዛዛት ብየ ስለተውኩት ነው፤ ቆጠራው ሊለያይ ይችላል። ) አፄ ሱስንዮስ፤ በንግሠታቸው፤ ፍጹም አማራ ናቸው ማለት ነው።

መረጃ ይሆን ዘንድ፤ የአፄ ሱስንዮስን ከኦሮሞነት ጋር የመያያዝ ግንዛቤን ሊያስከትል የሚችል ሁኔታን ግልጽ ላድርግ። አፄ ሱስንዮስ፤ አቤቱ በተባሉበት በወጣትነታቸው ወቅት፤ ከቤተመንግሥት ሸሽተው፤ ወደ ኦሮሞዎች ዘንድ ሄደው በዚያ አድገዋል። እናም ለመጎልበት፤ የአማራና የኦሮሞ ጦር አሰባስበዋል። በኋላ ደል ካደረጉና፤ ከቤተክህነት እየራቁ ሲሄዱ፤ የአማራ ባላባቶችንና የቤተክህነትን ጉልበት ለማዳከም፤ ዕውቅ የሆኑ የኦሮሞ ደጋፊዎቻቸውን ከደቡብ አምጥተው፤ በጎጃም፣ በቤጌምድርና በመላው አማራ ግዛታቸው አስፍረዋል። ያ ብቻ ሳይሆን፤ መሬትና ጥሪት አድለዋቸዋል። ሹመትም ሠጥተዋቸዋል። የወሰዱት መሬት፤ ከቤተክህነት መሬትም ጭመር ነበር። ይህ የቤተክህነት ሰዎችን ቅሬታ አብዝቶባቸዋል። በርግጥ ከፖርቹጋሎች ጋር የነበራቸው ግንኙነትና መኮትለካቸውን ተከትሎ፤ ደንቢያ ላይ የራሳቸውን ቤተክርስትያን እንዲያቋቁሙ ቦታ ሠጥተው፤ በደንቀዝ ቤተ መንግሥታቸው የካቶሊኩን ፖርቹጋላዊ ቄስ፤ ፔሮ ፓይዝን ማስፈራቸው፤ ለተከተለው ውድቀት ዳርጓቸዋል።

አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ። አፄ ሱስንዮስ ያገቧቸው ወልደ ሰዓላ ( ሌላም የንግሥና ስማቸው ሥልጣን ሰገድ ) የሚባሉ ባላባት ናቸው። እሳቸው ወደ ጎንደር የመጡት ከመርሃቤቴ ነው። በጎንደር እነ ፋሲልን፣ ገላውዲዎስን፣ ወለተ ገብርዔልን እና ሌሎችንም ወልደው፤ የሃይማኖት ንትርኩ ስላልጣማቸው፤ በ፲፮፻፲ ወደ ቆማ ወረዱ። ከዚያ የቆማ ፋሲለደስን መሥርተው፤ በዚያው በ፲፮፻፶፫ ዓመተ ምህረት አድፈው፤ እዚያው አስከሬናቸው አርፏል። አፈ ታሪኩ፤ እኒህን ንግሥተ ነገሥት ሥልጣን ሰገድን፤ የወለጋ ኦሮሞ ባላባት ዘር አለባቸው ይላል። እንግዲህ ይህ አፈ ታሪክ ነው። ነገሥታት የንግሥና ትውልድ ሐረጋቸውን የሚቆጥሩት በወንድ ትውልዳቸው ነው። እናም በወቅቱ በነበረው ሂሳብ፤ አፈ ታሪክነቱ እንዳለ ሆኖ፤ አፄ ፋሲልን ኦሮም አያደጋቸውም።

እንግዲህ አፄ ሱስንዮስ፤ ከአማራነታቸው በስተቀር፤ በጽሑፍ የሰፈረ ምንም ማስረጃ የለም ማለት ነው። ታዲያ ማነው ለሳቸው የማንነት ምልክት ሊሠጣቸው የተነሳ? ማምለጫ ይሆናል በማለት፤ “ይባላል!” “ሌሎች ያላሉ!” ወይንም “የሚባል ነገር አለ!” በማለት፤ ጥርጣሬን ሆን ብሎ ለማስገባት የሚደረግ ጥረት አለ። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን እንድናስተውል እፈልጋለሁ። የመጀመሪያው፤ ወሬው በማን ተናፈሰ የሚለው ሲሆን? ሁለተኛው ደግሞ፤ ወሬው ለምን ተናፈሰ የሚለው ነው።

ይህ እንዳለ ሆኖ፤ አሁን ወሬው ለምን ተናፈሰ? ይህ ከበጎም በጎ ካልሆነ ዓላማ ሊራገብ ይችላል። በጎ የምለው፤ በቅንነት ነገሥታቱ ሁሉ የኢትዮጵያ ነበሩና፤ በመካከላችን፤ ገዥ ብሔርና ተገዥ ብሔር የሚባል የለም ከሚል ነው፤ ብዬ እገምታለሁ። ነገሮችን በቅን መንፈስ ማየት እፈልጋለሁ። ይህ ካልሆነ፤ ትርጉሙ ለኔ በጠጠረ መንገድ፤ ነገሥታትን ለማሳነስ፣ ታሪክን ለመጠምዘዝና፤ አገር ለማናጋት ይሆናል እላለሁ።

ወሬው በማን ተናፈሰ? ይህም ቢሆን ሁለት ምንጮች አሉት ይመስለኛል። የመጀመሪያው፤ እባካችሁ አንድ ነን። የቀድሞዎቹ ይሄን የኛን ንትርክ አላገናዘቡትም። እናንተ ዝም ብላችሁ ስላሁኑ ተጨነቁ። ከሚል ከቅንነት የሚያስቡ ግለሰቦች ናቸው እላለሁ። ሌላው ምንጭ ግን፤ አማራውን ታሪክና እMነት ለማሣጣትና ለተንኮል ነው እላለሁ። በዚህም ሆነ በዚያ መንገድ፤ ይህ አላስፈላጊ ትረካ ባሁኑ ሰዓት ወደ አደባባይ መውጣቱ፤ ክፍተትን ለማብዛት ካልሆነ በስተቀር፤ በትግሉ ዘንድ አስተዋፅዖ የለውም። አሁን አማራው የሕልውና ጥያቄ አፋጦት፤ ማንነቱን፣ ታሪኩን፣ ቋንቋውን፣ ባህሉን ለማስመርና ሕልውናውን ለመጠበቅ በሚያደርገው ትግል፤ አዘናጊ ነው እላለሁ።

ይህ ታሪክ ለኔ ልዩ ትርጉም አለው። ስለራሴም የሚናገር ክፍል ስላለበት፤ በቀጥታ ከልጅነት ጀምሮ ያጠናሁትን የጠየቀ ጉዳይ ነው። እናም የትም ቦታ ማስረጃ አቅርቤ ልነጋገርበት የምችለውና የሚገባ ግዳጄ ነው።

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.