የቴዲ አፍሮ ደጋፊዎቹም ተችዎቹም ለትክክለኛ አስተያየት እድል አልሰጡም! – ሰርጸ ደስታ

ነገሩን ያበላሹት ቀድመው ተችዎቹ መሰሉኝ ከዛ ሌላኛን ጽንፍ ይዘው ደጋፊዎች የጦርነት ያህል መዋጋት ጀመሩ፡፡ ቴዎድሮስ ጸጋዬን ብዙ ነገሩን እወድለታለሁ፡፡ አንዳንዴ ግን ያበዛዋል፡፡ የሰውም ሀሳብ መስማት ቢችል ጥሩ ነው፡፡ ቴዲ አፍሮን ቴዎድሮስና ዳኝነት የተቹበት ሁኔታ የግል ችግር ከቴዲ አፍሮ ጋር ያላቸው ነው የሚያስመስለው፡፡ የቴዲ አፍሮን ደጋፊዎችም ያስቆጣው ይሄው መሠለኝ፡፡ ብዙ ደጋፊዎች እንደውም ከጠበቀኩት በላይ ተረጋግተው ለእነ ቴዎድሮስ ጸጋዬ መልስ ሰጥተዋል፡፡ እንደተባለውም ገና ከአልበሙ ሽፋን ጀምረው እነ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ሲሰጡት የነበረው አስተያየት እነሱ በኋላ ላይ ሊያስተባብሉበት ቴዲን ለማነጽ የሚረዳ ነው ቢሉትም ለአድማጭ የሚሰጠው ሥሜት የግል ችግር እንዳለባቸው ነው፡፡ ሂሳቸው ነገሮችን ይሄ እንዲህ ቢሆን የተሻለ ነበር እዚህ ጋር አበላሽቶታልና በመሳሰሉት ሁኔታዎችን እያሳዩ ከሥሜታዊነት በፀዳ ቢሆን እንዳሉትም ቴዲን ሊያንጸው ይችላል፡፡ እነሱ ግን በቀጥታ ቴዲን ለመቃወም የአለሙ ነው ያሰመሰለባቸው፡፡ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ጥበብን እንዴት እንደሚያያት አላውቅም ግን ቴዲን ወቅታዊ የሆኑ ነገሮችን እያነሳ መዝፈኑን የጥበብ ሰው ባሕሪ አደለም ይላል፡፡ እኔ ደግሞ እንደሚገባኝ የጥበብ ሰው ማለት ወሳኝና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በጥበብ መግለጹ ነው፡፡ አሮጌውማ ተረትና ታሪክ ይናገሩት፡፡ ቴዲ አፍሮንም በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅ ያደረገው ወቅታዊ የሆነ የሕዝብን ሥነልቦና የሚገዛ ሥራው ነው፡፡ ጥበብ ማለት እኮ ይሄ ነው፡፡ ቀነኒሳ የሚለውን ዘፈኑን የሰማን ጊዜ ሁላችንም ተደምመናል፡፡ መቼም እንቁዎቹ ሯጮቻችን ያን ታሪካዊ ሩጫ ከመሮጣቸው በፊት ሰርቶት አይደለም ግን ቴዲ እንወረደ ነው የትራኩን ትዕይንት የተጠበበበት ብል ይሻላል፡፡ ከቴዴ ቀነኒሳ በፊት በቀነኒሳና ኃይሌ መካከል የሆነ መቃረን አለ የሚል በሰፊው የተናፈሰ ወሬ ነበር፡፡ ያ ወሬ ከሩጫው በኋላ በከፋ ሁኔታ በቀጠለ ነበር፡፡ ቀነኒሳ ሀይሌን አሸነፈው በሚል ማለት ነው፡፡ ቴዲ ነው ይሄን ክፉ ወሬ ወሀ የከለሰበት፡፡ ጭራሽ የማንረሳው የሯጮቻችንን ፍቅር ያስነበበበት፡፡ ዛሬም ድረስ ከኔዜማውና ከእነሁለመናው የማንረሳው ትውስታችን ሁኖ ያ የእንቁ ሯጮቻችንን የትራክ ላይ ትዕይነት ዛሬም እናየዋለን፡፡ ይሄን ያደረገው የወቅታዊ ነገሮችን የሚያነሳው ቴዲ ነው፡፡ ማንም ይሄን ሲያድርግ አላየንም፡፡ ሌላው ዳላስ፣ ሼመንደፈር፣ ባልደራስ፣ ለነገሩ ይቅርብኝ ስንቱን ለዘረዝር ነው፡፡ ቃላቶቹ ራሳቸው ለሕዝብ የታወቁት በቴዲ ምክነያት ነው፡፡ እኔ በበኩሌ ሼመንደፈር፣ ባልደራስ ምናምን የሚባሉ ቃላቶችን አላውቃቸውም ነበር፡፡ ባይገርምሽ እጅግ የምወድለት ዜማው ነው፡፡ የወቅታዊ ነገር ሳላነሳ የማላልፈው ሌላው ያስተሰርያል ነው፡፡ ጆሮ ያለው ቢኖር ቴዲ ለሕዝብም ለፖለቲከኞቻችንም ጥሩ መካሪ ነበር፡፡ ቴዲ በፍቅር ዘፈን አይታወቅም ብል ይሻለኛል፡፡ ሼመንደፈርን እንዳትለኝ ሼመንደፈር ጾታዊ ፍቅር ሳይሆን ማሕበረሰባዊ ፍቅርን ነው የሚያወድሰውና፡፡ አንዳንድ ነጠላ ዜማዎቹ ላይ አሉ መሰለኝ፡፡ ግን ትዝ አይሉኝም፡፡

ቴዲ ሁሌም ሕዝብን ለማቀራረብ፣ የሀገር ወዳድነት ፍቅርና ቁጭት ያለበት ለመሆኑ ግጥሞቹና ዛማዎቹ ያሳብቃሉ፡፡ ባይሆን ኖሮ ልግጠምህ ቢል እንኳን አይሆንለትም ነበር፡፡ ሰው የማይወደውን ነገር ሊጠበብበት አይችልምና፡፡ አሁንም ቢሆን አልበሙን ኢትዮጵያ ያለበት ምክነያት ለብዙዎቻችን ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ይቆጨዋል፣ ያመዋል፣ ብዙ ብሏል፡፡ በኢትዮጵያዊነቱ ምክነያት ብዙ ደርሶበታል፡፡ የእድል ነገር ሆኖ ባለቤቱም እንደዛው ናት ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ አምለሰትን ብዙ በመድረክ ባላውቃትም ኢትዮጵያዊ መሆኗን መስዋዕት ከፍላበታለች ብል ይቀለኛል፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ እያለ የሚደነፋው ሁሉ ሲያረግዝ ልጁን የአሜሪካ ወይም የካናዳ ዜጋ ለማድረግ ስንቱ ሊወልድ ሰሜን አሜሪካ እንደሚሄድ እናውቃለን፡፡ አምለሰት አደረገቸው የተባለው ደግሞ ተቃራኒውን ነው፡፡ ለመወለድ ከሰሜን አሜሪካ ኢትየጵያ የሄደች ልዩ ሴት፡፡ ልጇ ሌላ ዜጋ እንዳይሆን! ኢትዮጵያዊ እንዲሆን! ይች ሴት በመጻፈ ምሳሌ መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት የተባለላትን ሴት ታስታውሰኛለች፡፡ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ይህን ቤተሰብ ልበለው የሚመሰለው ካለም ምን ያህል እንደሆነ አላውቅም፡፡ አዎ ይህ ቤተሰብ (ቴዲና አምለሰት ልጆቻቸውን ማለቴ ነው) ሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ስለአገሩ ያገባዋል፡፡ እኔ ይህን ቤተሰብ የምገነዘበው እንዲህ ነው፡፡ እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ ብዬ ስለማምን ቴዲን እተቸዋለሁ፡፡ የሚተችበት ካለ፡፡

ኢትዮጵያ የሚለው አሁን የወጣው ነጠላ ዜማ እኔም የቀረዋል ከሚሉት ነኝ፡፡ ለብ በሉ ቴዲን ከላይ በገለጽኩት ሁኔታ ከተረዳሁት ምን እንደምጠብቅ ገምቱ፡፡ ቴዎደሮስ ጸጋዬ የግል ቂም አይነት ትችት ባያደርገው ኖሮ በጥሩ ሁኔታ የዜማውን ስህተትና በዚህ መልኩ ቢሻሻል ቢላ ባማረለት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ዜማ ዜማውም ግጥሙም እኔንም እንደጠበቀኩት አልሆነልኝም፡፡ ውበት አንሶታል፡፡ ግጥሙ ቴዲ የሚገጥማቸው አይነት አደለም፡፡ ለምሳሌ የሰሎሞን ዕፅ  የሚለው ቃል ትክክል አደለም፡፡ ሰሎሞን በጥበቡ እንጂ በተክል አናውቀውም፡፡ ባንዲራውንም ከቀስተደመናው ጋር ያያዘበት ስንኙ በተለመደ አይነት አድርጎታል፡፡ እስኪ ወደኋላ ሄዳችሁ ሞናሊዛ የሚለውን ዜማ ሥሙ፡፡ እንዴት ስዕላዊ መጎናጸፊያ እንደሰጠው፡፡ ቴዲ ስለኢትዮጵያ ለመዝፈን እጅግ ስለሚጓጓ ይመስላል፡፡ ለነገሮች በጣም ከተጨነቁ አንዳንዴ አምቢ ይላል፡፡  ከግጥም ውጭ ዜማው ችግር አለበት የምለው ተራ ዜማ አደረገው፡፡ ሲገባም ዘው ነው ያለው፡፡ መግቢያ የለውም፡፡ ያስተሰርያል የሚለው ዘፈኑ ትንሽ መግቢያ ነበረው፡፡ ሼመንደፈርም መሰለኝ፡፡ ሌሎች ብዙ የራሱ ምርጥ መጊቢያ የነበራቸው ዜማዎች አሉ፡፡ በዚህ ነጠላ ዜማው በፍጥነት የሆነ ሳክሲፎን የሚመስል ድምጽ ነው ሲጮሕ የሰማንው፡፡ ከነጭርሱም የትንፋሽ መሳሪያ ሳይኖርበት መግቢያው በለሆሳስ የሆነ ደራም፣ ሌሎች የሚያነቃችሉና ከአገርኛው ክራርን የሚጠቀም መግቢያ ያለውን ዜማ ቢያስብ ፍጹም የተለየ ድባብ ያለው ዘፈን በዚሁ ግጥም ሊያሰማን ይችል ነበር፡፡ ይህ ራሱ ጋር አለ እንዴት እንዳልመጣት አላውቅም፡፡ ከመግቢያውም አልፎ ተራ የለመድንውን አይነት ድምጽ ባልሰማን ነበር፡፡ ለነገሩ ለጠቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው እንጂ እንዲህ ቀላል እንዳልሆንም አውቃለሁ፡፡ ለግጥምም ሆነ ዜማ በምንገጥምበት ወይም በምናዜምበት ወቅት ያለው ጊዜያዊ ሁኔታችን ወሳኝ ነው፡፡ ተመስጦ ማለቴ ነው፡፡ በተለይ ከውጭ ያለን ድምጽ ማቀናበር የሚያስችል፡፡ ኢትዮጵያን እንደገና ቢዘፍናት ደስተና ነኝ፡፡ ደግሞ ይችላል፡፡ ከአስፈለገ ግጥምም ዜማም እናዋጣለን፡፡ ኢትዮጵያ ከሞለው ይልቅ ጎጃም ኖራ ማሬ የሚለው ጥሩ ውበት አለው፡፡

ከዚህ በላይ ቢሆን ብለን የየራሳችንን ተመኘን እንጂ እንደህም ሆኖ ዘፈኑ ዛሬ ኢትዮጵያውነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈተና ውስጥ በገባበት ሁኔታ ጥሩ መቀስቀሻ ሆኗል፡፡ እውነት ነው ለብዙዎቻችን የምናስባትን ኢትዮጵያን እንዳናይ ኢትዮጵያዊነታችንን ሊያስጥሉን ጠላቶቻችን በዝተዋል፡፡ እርግጥ በዛው ልክ ኢትዮጵያዊነቱን በዘልማድ የኖረበት ሁሉ አሁን እየባነነ ነው፡፡ የቴዲን ዘፈን በመደገፍ ከሰጡ አንዳንድ ሰዎችም የምንሰማው ይሄንን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነታችን ጠምቶናል፡፡ ናፍቆናል፡፡ ተውን እኛ እንሰማዋለን አንደምንም ቢዘፈን ኢትዮጵያዊነታችንን የሚያስታውሰንን ዘፈን እኛ እንፈልገዋለን የሚለው የአንዳንዶች አስተያየት ልብ ይነካል፡፡ እኔም ቴዲን ከአለው አቅም አንጻር ከዚህ የረቀቀ ዘፈን ለኢትዮጵያ ስለተመኘሁ እንጂ የሆነውም ቢሆን ቴዲ ሥራውን ከሌሎች ጋር በማወዳደር አደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለእሱ ምን እንደሆነ የምረዳው ስለመሰለኝ፡፡ እውነት ነው ኢትዮጵያዊነት ውስጣችን እየተንተክተከ ያለን አለን፡፡ ችግሩ ደግሞ ማወቅ የማይገባንን ሁሉ ማወቃችን ጭምር ነው፡፡ አንዳንዱን ራሳችን ጎርጉረን ነው ያወቅንው ሌላው ግን ራሱ መጥቶ ነው ሹክ የሚለን፡፡ ግን ለማን እንነግረዋለን፡፡ ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ አደለም ግን ሌሎች (ፈላስፎቹን ማለቴ ነው) ስለእኔው ኢትዮጵያ የሚሉትንና የሚያስቡትን አደምጣለሁ፡፡ አብዛኛው ሌላው ግን የሚያወን በረሀባችን፣ በትርምሳችን፣ በኋላ ቀርነታችን ነው፡፡ ማንነታችን ለነገሩ እኛ ላንሆን እንችላለን ብቻ ጥንታዊውያኑ ኢትዮጵያውያን እነማን ነበሩ፡፡ ኢሬቻና እንቁጣጣሽ ከኖሕ የመጡ ናቸው ይላል እውቀት፡፡ ኢትዮጵያውያን ዘምንን ሰከንድ ባነሰ ስሌት ነበር የሚቆጥሩት ይላል ታሪካቸው፡፡ አንድ አመት 365 ቀን 6 ሰዓት 2 ደቂቃ 0.4 ሰከንድ(ቅጽበት) ይልና በ600 ዓመት የቺ የሰኮንድ ሽርፍራፊ 1 ቀን ትሆናለች በዛ ዘመን ጳጉሜ 7 ቀን ትሆናለች፡፡ ሰማያትን (ከዋክብትን የሚመራመሩ ነበሩ ይልላ ታሪካቸው፡፡ ጥንታውያን የግሪክ ታሪክ ጸሐፊዎችም ይህንን እውነት ነበር የሚናገሩት፡፡ እኛ ግን የኮከብ ቆጣሪ ጠንቋይ እንጂ የኮከብ ተመራማሪ ጠቢብ አናይባትም፡፡ የጥበብ ነገር ለእኛ ተረት ነው፡፡ አክሱምና ላሊበላ ድንጋዮቹ ቆመው ሲፋረዱን ውሸት ናቸው ብለን እርሳችንን በክህደት አሳምነን እንኖራን፡፡ እነዚህን ጥንታዊያኖቹ አልሰሯቸውም ሌሎች መጥተው ሰረተውላቸው ነው ባለመቻል ባርነት ራሳችንን ያስገዛን፡፡ ቴዲን በሌላ ሥራው ኢትዮጵያን እንዲዘፍናት እየጠኩት፡፡ ሠላም እላለሁ፡፡

 

እግዚአብሔር ኢትየጵያዊነትን ዳግም ይመልስ!

 

አሜን!

 

ሰርጸ ደስታ

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.