ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬን መጽሀፌን ለማጣጣል ሙከራ አድርገዋልና ሲሉ ይቅርታ እንዲጠየቁ መግለጫ ሰጡ

ይድረስ ለሀገሬ የኢትዮጽያ ህዝቦች በያላችሁበት
———————————————————
 (ከልጃችሁና ወንድማችሁ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)
*****************************************
 አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ እኔን ለማዋረድና ስለ ኢትዮጽያውያን የዘር ትስስር የሚያስረዳውን “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የተሰኘውን መጽሀፌን ለማጣጣል ያደረገውን ሙከራ ዐይታችሁአል። ይህ ግለሰብ፥ ለውይይት ጋብዞኝ፥ ከጋዜጠኝነት ሙያና ስነ ምግባር ውጪ የጎንዮሽ ተልእኮ ይዞ ቀርቦ፥ የቴሌቪዥኑን ጣቢያ  ወደፍርድ ቤት ሙግት ለውጦ መንፈሳዊ ወከባና ስቃይ (psychological torture) አድርሶብኝ የጥያቄ ማእበላት እየደራረበብኝ፥ ልመልስ ስሞክር መልሴን ፈርቶ እንደ አፈነኝ አስተውላችኋል።  የሚገርማችሁ ነገር አቶ ቶዎድሮስ በእግር በፈረስ አስፈልጎኝ ነበር ያገኘኝ። እኔ ለተለመደው ጋዜጠኛ ጥያቄ መስሎኝና ዛሬ ስለ እሱ ማንነት የማውቀውን ያኔ ባለማወቄ፥ ቃለመጠይቁን ለመቸር ፈቀድኩ። እሱ ለካስ ሌላ ተልእኮ ይዞ አስልቶ፥ አውጠንጥኖና አድፍጦ ይጠብቀኝ ኖሮአል።  ባላሰብኩት ስልት ሊያዋርደኝና
የብዙ ጊዜ ምርምር አካሂጄ ላቤን አንጠፍጥፌ የከተብኩትን፥ የኢትዮጵያን ህዝብ ትልቅነትና አድነት የሚያንጸባርቀውን የፍቅርና የሰላም ድርሰቴን ዋጋ ሊያሳጣው ሞከረ። እኔም ቁጣዬን እና የብስጭት አጻፋዬን በክቡሩ የኢዮጵያ ህዝብ ፊት ላለማሳየትና ላለመመለስ በትእግስት ችዬ ፕሮግራሙን ጨረስኩ። አቶ ቴዎድሮስን ህዝብ ይቅርታ ጠይቅ ቢለውም እስከ አሁን በትእቢት ዝም ብሎአል። እሁን በርካታዎቻችሁን  እናንተን እግዜር ዐሳይቶአችሁ ፕሮፌሰር ፍቅሬንስ ለምን ይቅርታ አይጠይቅም አላችሁ። ለእኔም በግሌ አንተን ለምን እስከአሁን ይቅርታ አልጠየቀም፤ ብላችሁ ጻፋችሁልኝ።
 አዎን እኔስ እድሜልኬን ለኢትዮጵያ አንድነት የቆምኩ ወንድማችሁ አይደለሁምን? አሁንስ ከጎሰኝነት ጎጥ ወጥቼ የኢትዮጵያዊነትን ፋና ከፍ አድጌ አንቦግቡጌ እያበራሁ ወደፊት በቁርጠኝነት የምራመድ የታላላቆቹ የእነኢትዮጵና የእነ ደሸት ዝርያ አይደለሁምን? አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ በኔ ላይ ያደረሰው በደል አቶ ቴዎድሮስ ካሳሁን ላይ ካደረሰው ይበልጣል እንጂ ያንሳልን? ለኔስ የሚሟገትልኝ ወገን የለኝምን? እናንተስ በኔ ላይ ታዳላላችሁን? እኔስ ወንድማችሁና ልጃችሁ አይደለሁምን? እኔ ተዋርጄ አቶቴዎድሮስ ይቅርታ ሳይጠይቀኝ እናንተ በድል አድራጊነት ስሜት ወደየቤታችሁ ገብታችሁ በእኔ ላይ በራችሁን ትቀረቅራላችሁን? እሱ እኔንስ ይቅርታ መጠየቅ አይገባውምን? ፍርዱን ለህሊናችሁ ትቼዋለሁ።
ወንድማችሁና ልጃችሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.