የቀኔኔሳ የዝምታ ጩኸት – ኄኖክ የሺጥላ

ይኽንን ፎት ስመለከት በቀነኔሳ ውስጥ የታፈነው የ ዝምታ ጩኸት ተሰማኝ ። ከቁስ በረከት ከፍ ባለ የሰውን ልጅ ሰው የሚያደርገው ለአምሳያው መጨነቁ ፥ መቆርቆሩ ፥ እና መቆሙ ብቻ ሳይሆን ከፍ ሲሉም እንደ ክርስቶስ ራሱን ለሌሎች መስጠት መቻሉ እነሆነ እያሰብኩ ፥ በዚች ቅፅበት እየሮጠ የታሰረውን ቀነኔሳ ሳይ ከልቤ አዘንሁ።

በፈይሳ እና በቀነኔሳ መኃከል ያለው ልዩነት ፥ ኢትዮጵያው ውስጥ ያለውን ጨቋኝ ስርዓት የመደገፍ እና ያለመደገፍ ፥ የስርዓቱን በደል የመረዳት እና ያለ መረዳት ፥ የድሃ ገበሬዎች መሬት ያለ አግባብ በኢንቨስትመንት ስም እንደሚቀማ ( ወይም እንደሚነጠቅ ) የማወቅ እና ያለማወቅ ፥ ተመሪዎች ደብተራቸውን እንደያዙ በአደባባይ በመንግስት ታጣቂዎች ስለመገደላቸው እኩል መረጃ የማግኘት እና ያለማግኘት ፥ የመንግስት ሰራተኞች በፖለቲካ አቋማቸው የስራ ቅጥር ኮንትራታቸው የመቀጠሉን እና ያለ መቀጠሉን ፥ ጠሃፊያ ፥ ጦማሪያን ፥ ጋዤጠኞች ፥ የእምነት አባቶች ፥ እናቶች ፥ እህቶች እና ወንድሞች ስለ አገራቸው ጉዳይ መንግስት ከሚያስበው በተለየ ስላሰቡ በማሰባቸው ታስረው መገረፋቸውን ፥ የድንጋይ ጠጠር ላይ በጉልበታቸው እንዲሄዱ መደረጋቸውን ፥ እንደ ዜጋ መከበር ሳይሆን መዋረዳቸውን የማወቅ እና ያለማወቅ ልዩነት አይደለም ፥ በፈይሳ እና በቀነኔሳ መኀከል ያለው ልዩነት ሰው የመሆን እና ያለመሆን ቀላል የሚመስል ግን አንኳር የሆነ ትልቅ ልዩነት ነው ። ከቀነኔሳ ውስጥ የሸመቀው « ምን ገዶኝ » እና በፈይሳ ውስጥ የሰረፀው « የአገሬ ጉዳይ እኔንም ያገባኛልም ይገባኛልም » ባይነት መሰረታዊ ልዩነት በሃሳብ አንድ ያለመሆን ወይም የተለያዩ የፖለቲካ ግንዛቤዎችን የማስተናገድ ውጤት ሳይሆን እንደ እንደ እንስሳ ለመኖር የመፍቀድ እና ያለመፍቀድ ልዩነት ውጤት ነው !

ጥያቄው የቀነኔሳ እጆች እንደ ወንድሙ ፈይሳ ወዳ ላይ እንዲነሱ ስንት ሰው ይገደል ነው ? ስንት የአሞቦ እና የአለማያ ልጆች ይሙቱ ነው ? ስንተ የወለጋ ወጣት የጥይት እራት ሲሆን ነው ቀነኔሳዊያን እጃቸውን ወደ ሰማይ አንስተው « እኔም የአገሬ ጉዳይ ያገባኛል !» ሉሉን የሚችሉት ነው ! ? የቀነኔሳ እና መሰል የአገር ልጆች እጅ ከህዝቡ ልቦና ጋር እንዲስማማ በአገር ደረጃስ ምን ያህል እንዋረድ ?

የሆነው ሆኖ ይኽንን ፎት ስመለከት በቀነኔሳ ውስጥ የታፈነው ድምፅ ከፈይሳ እጅ በላይ ወደላይ ተነስቶ ሲጮኽ ይሰማኛል !

ኄኖክ የሺጥላ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.