ኢትዮጵያ የተያዘችባቸው ካንሰሮች – ያየያየ ይልማ

በአለም የጤና ድርጅት ፍቺ መሰረት ካንሰር ፤ በዛ ያሉ ጤናማ ያልሆኑ የሴሎች እድገት ሲሆን ፤ (Cancer is a group of diseases involving abnormal cell growth with the potential to invade or spread to other parts of the body.) ይህም ጤናማ ያልሆነ የሴሎች መባዛት ሌላውን እና ጤናማ የሆነውን የሰውን አካል የመበከል አቅምና አዝማሚያ ሲኖረው ነው ካንሰር የሚሰኘው፡፡ ታዲያ ይህ አለምን እና ህዝቦቿን እያስጨነቀ ያለ በሽታ ፤ ኢትዮጵያዊያን እንደ ግለሰብ በህዝቧ ላይ የተከሰተውን የበሽታውን መኖር ለመዘርዘር ሳይሆን ኢትዮጵያም እንደሃገር በዛ ያሉ ካንሰርን የሚሳዩ ምልክቶችን ማሳየት በመጀመሯ ፤ ኢትዮጵያን ካንሰር እንዳጠቃት ምልክቶቹን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ የዘረኝነትን ስብከት እና ከልክ በላይ የተራገበ ብሄርተኝነትን እንድታራምድ፣ ህዝቦቿ ይህንን ቁንፅል አመለካከት አሜን ብለው እንዲቀበሉ ከህገ መንግስት ሰነድ እስከ የየግለሰብ መታወቂያ ድረስ አንድ አገር ያደረጓት ብልቶቿ ተፈልቅቀው እንዲለዩ፣ የተደረገባት አዲስ አገር ከሆነች እነሆ ሃያ አመት አለፈ፡፡ ይህ አላስፈላጊ የኋልዮሽ ሽምጥ መጋለብ ከተጀመረ ግዜ ጀምሮ አስገራሚ ብዙ እባጮች ኢትዮጵያ ላይ እና ኢትዮጵዊያን ላይ ታይቷል፡፡ እነኚህ እንደ ሃገር ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ የሚታዩት ፣ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊ፣ እና ማህበረሰባዊ መስተጋብሮችን የሚያካልሉ እና በዋነኝነት በአመለካከት ላይ የሚገለፁ፣ አገራዊ ቀውስን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩቱ፣ እባጭና ጉድፎች ናቸው አንድ በአንድ ተደማምረው፣ በሂደት አገሪቷን እንደ ሰው እያቆሰሉ፣ ቁስሏንም እያሸተቱና እያመረቀዙ፣ ብለውም እያበሰበሱ፣ አካሏን ሙት የሚደርጉት፡፡

ኢትዮጵያ በዚህ ካንሰር በመያዟ ምክንያት በአገሪቷ ላይ የሚታየው የጎጥ ፖለቲካ፣ በመንግስት ዘር በትኖ ለቃሚነት ፋና የሚመራው አርቲፊሻል ገፅታ የተላበሰው የሃገር ኢኮኖሚ እና ዘግናኝ በሚባል ደረጃ እንዲቀጥል ተደርጎ ያለው ኢፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ዋነኛ እውነታዎቹ የሆኑለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ህፀፆችን፣ ለጊዜው ወደ ጎን ትቼ ማተኮር የምፈልገው በሌላኛው የካንሰር ምልክት እና የዚህ ፅሁፍ መነሻ ፤ ሙስና ላይ ይሆናል፡፡

ይህ አጭር ፅሁፍም፣  የአገሪቱ አንድ ክፍል በሆነችው አዲስ አበባ ፣ እየተደረገ ባለ በአንድ ተጨባጭ  እውነት ላይ የሚመሰረት ይሆናል፡፡ ለዚህ ፅሁፍ እንዲሆን የሚቀርበው እውነት መነሻው ኢትዮጵን እንደ ካንሰር ጤናማ ያልሆኑ ብክለቶች ፣ እዚም እዛም እየታዩ እንደ ሃገር ከፍተኛ አደጋ የደቀኑባትን እጅግ በጣም የበዙ ችግሮች በዚህ አችር ፅሁፍ ለመዳሰስ አይሞክርም፡፡

ነገር ግን በታሪካችን በየትኛውም ወቅት ቢሆን አይተን የማናውቀውን የንዋይ ፍቅርን ፤ ምስጋና ለወያኔ ይግባና ፣ ሁለንተናዊ የሆነ የአንድ ዜጋ ዝቅጠት (በእኩይ ስራ የሚያተርፉትን ብቻ)፣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ላይ (ከመዲናዋ አዲስ አበባ ምሳሌ) አንድ አነስተኛ መንደር ላይ እየተከሰተ ያለን እውነት በማጋለጥ ፣ በአንፃሩ ደግሞ ከፍ ያሉት የሙስና አሻጥሮች እና የዚህ ሁሉ ሸፍጥ ጣጣው እንዴት ህዝቡን ፣ ብሎም ኢትዮጵን እንደ አገር ምን በደል እያደረሰባት እንዳለ በጥቂቱ ለማሳየት እና የዜግነት ሞራላዊ ግዴታን ለመወጣት፣ ብሎም እነኚህን ክፋቶች ለመታገል ማወቁ የመጀመሪ መፍትሄ ይሆናል በሚል ቅንነት ላይ በመመስረት ነው፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለጋራ መኖሪያነት ከተሰሩና እጅግ ብዙ ህዝብ ከሚኖርባቸው ሰፈሮች ውስጥ ፣ በቄራ አካባቢ የሚገኙትን ሁለቱን ትልልቅ የጋራ መኖሪ ኮንዶሚኒየም ቤቶችን የሚመለከት ይሆናል የሙስና ሚና እንዴት የእንዳንዱን በነዚህ የጋራ መኖሪ ቤቶች ያሉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ህይወት እንዴት እንደለያየው ያሳያል፡፡ እነኚህ በቄራ አካባቢ ያሉት የኮንዶሚኒየም ሰፈሮች የየራሳቸው መለያ ስያሜ አላቸው፤ አንደኛው ጎተራ ኮንዶሚኒየም፣ ሌላኛው ደግሞ መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ተብለው ይጠራሉ፡፡ በመካከላቸው ያለው ቄራ ሲሆን ከቄራ ሁለቱም አንድ የታክሲ ፌርማታ ርቀት ላይ አንዳቸው ከሌላኛው ተቀምጠው የሚገኙ እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአዲስ አበባ ህዝብ የሚኖርባቸው፣ የደመቁ የጋራ መኖሪዎች ናቸው፡፡

የጎተራ ኮንዶሚኒየም

በጎተራ ኮንዶሚኒየም ከሰማንያ በመቶ በላይ የቤት ባለቤቶች ትግሬዎች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ከመከላከያ ሰራዊት አንስቶ በተለያዩ የመንግስት ስራ ላይ ቀድመው ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ተመርጠው የቤት ባለቤት የሆኑበት አስገራሚ የጋራ መኖሪ ግቢ ነው፡፡ ተከራዮቹ ግን ከሁሉም የማህበረሰብ የተውጣጡ እና እጅግ ዳጎስ ያለ ገቢ ያላቸው ንጥጥ ከተሜዎች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አለበለዚያ ፣ የወር ደሞዝን በአንድ ገበታ አገልግሎት ለሚያስከፍሉ አገልግሎት ሰጪዎች ማን እየከፈለ ሊችለው ነው፣ ምንም ሳይመስላቸው ዩሴን ቦልትን (የወቅቱ የኢትዮጵ መቶብር ቅጥል ስም ነው፡፡) ጎተራ ላይ ከሚበትኑቱ የወያኔ ግት መጣጮች በስተቀር፡፡

ታዲያ በዚህ አስገራሚ ስፍራ እንደ ቀድሞዋ ሃያል አገር እንግሊዝ፣ በጎተራ ኮንዶሚኒየምም ፀሃይ አትጠልቅም፡፡ ከሱፐር ማርኬት እስከ ክሊኒክና ሆስፒታል፣ ከበርገርና ፒዛ ቤት እስከ ቁርጥና ጥብስ ቤቶች፣ ከፀጉር ቤት እስከ ባንክ ቤት ፣ አንድ ከተማ ውስጥ ተበታትኖ የሚገኝ አገልግሎት ሁሉ፣ በጎተራ ኮንዶሚኒየም በሚያስገርም የምርጫ ብዛት ተቸምችሞ በአንድ ስፍራ ይገኛል፡፡

የባለስልጣን፡ የኮንትራክተር እና የዌኔ ግት መጣጮች ያስቀመጧቸው እንስቶች፣ ከመኖሪያው እኩል መሸታ ቤቶች የሚገኝበት ጎተራ ኮንዶሚኒየም ሁለቱ አስከፊ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋነኛ ችግሮች አይመለከታቸውም፣ ነዋሪዎቹ አዲስ አበባ ውስጥ እየኖሩ ይህንን የአዲስ አበባ ህዝብን ችግር መኖሩንም የረሱ ሰዎች በብዛት ለማግኘት ጎተራ ኮንዶሚኒየም ተወዳዳሪ የሌለው ስፍራ ነው፡፡ ይህ እንዴት እንደሆነ ስጠይቅ ያገኘሁት ምላሽ በጥቅልሉ ይህ ነው፡፡ በዋነኝነት የትግሬ ቤት ባለቤቶች የሚገኙበት ጠንካራ የጋራ መኖሪያ ኮሚቴ ስላለው ነው፡፡

የመብራ ሃይል ኮንዶሚኒየም

ውሃና መብራ እስከ ጭራሹንም ጠፍቶ እንደማያውቅ ስሰማማ ማመን ነው ያቃተኝ፤ ምክንያቴ ደግሞ በአንድ የታክሲ ፌርማታ ያክል የሚርቀው መብራ ሃይል ኮንዶሚኒየም ላይ ያለውን የውሃና የመብራ ችግር በመኖርም ጭምር ስለማውቀው ነበር፡፡ መብራት መሰረታዊ ነገር በመሆኑ ለምን እንደዚህ ኑሮን በሚያቃውስ መንገድ የአዲስ አበባ መብራት ሃይል እንደሚያቋርጠው የሁላችንም እንቆቅልሽ ስለሆነ የመብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም (ከጎተራ ኮንዶሚኒየም በስተቀር) ብቻውን ተነጥሎ ስለዚህ መብራት ችግር ማውራቱ ይቅርና ስለ አስገራሚው የመብራ ሃይል ኮንዶሚኒየም ችግር ላመልክት፡፡

መብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ውሃ ይቋረጣል ሳይሆን፣ የሚመጣበት ለሊት እንደ አመት በአል የመዘከር ያክል ነው ጥቂት ነው፡፡ ቀን ውሃ መጥቶ ሳይቋረጥ ለተወሰኑ ሰአታት እንኳን ከቆየ፣ ነዋሪው ልክ እንደ ተአምር ስለውሃ መምጣት በስልክ እየተጯጯኸ ሲደዋወል፣ ከስራው አቋርጦ እየመጣ ሲተራመስ ማየት የማይቀር ነው፤ ምክንያቱም ይህ ክስተት ሁል ጊዜ የሚታይ ስላልሆነ፡፡ የመብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች፣ በሳምንት አንድ ግፋ ቢል ሁለት ቀን ለአንድ ሰአት ያክል፣ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት ላይ በምፅዋት የሚለቀቅ ውሃን ተጠቅሞ የሚኖር ፣ በከፍተኛ የቧንቧ ውሃ ችግር እጅግ ለአመታ እየተሰቃየ ያለ የአዲስ አበባ ህዝብ ነው፡፡ እረ ለመሆኑ ለምንድን ነው በኮሚቴዎች አማካኝነት ይህ ቸግር ለሚመለከተው አካል እንዲታወቅ ተደርጎ መፍትሄ የማይበጅለት ብዬ ስጠይቅ፣ ዋነኛው ችግር ታዲያ ይኸው አይደል እንዴ! በብዙ ሺህ ከሚቆጠረው ከህዝቡ ችግር የሚያተርፉ፣ ከስቃዩ እና ከምሬቱ ደስታ የሚጠጡ የዘቀጡ የመንግስት አላፊዎች አይደሉ እንዴ ይህ እንዲሆን ጠንክረው እየሰሩ ያሉት ብለው አፍረጥርጠው አስገራሚውን የጋራ መኖሪ ቤቶችን በውሃ ችግር የሚፈጠር አስገራሚ የሙስና ቢዝነስ ነገሩኝ፡፡

ውሃው እንዲለቀቅላቸው ነዋሪዎች ተሰብስበው ቁጥር ስፍር ለሌለው ጊዜ ከታች እስከላይ ለሚመለከተው ሁሉ ለአራ አመታ አቤት ቢሉ መፍትሄ ሳይበጅለት የኖረው የኮንዶሚኒየሙ ነዋሪ፣ ከቤት ኪራዩ ቀጥሎ የሚያወጣው ከፍተኛው ገንዘብ ለግዢ ውሃ በመሆኑ እና፣ ይህንን የግዢ ውሃ ገቢ የሚካፈሉት የመንግስት ሃላፊዎች በመሆናቸው ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡ የመብራት ሃል ኮንዶሚኒየምን ከብበው ያሉ ነባር የቄራ መደበኛ መኖሪያ ቤቶች አሉ፤ ከእነዚህ ቤቶች የተመረጡት ውሃቸው ሳይቋረጥ እንዲፈስ የውሃ ልማት ሙሰኛች ይህንን ሁኔታ እንዳለ እንዲቀጥል ያደርጋሉ፤ እጅግ ግዙፉን የኮንዶሚኒየም ግቢን ያጥለቀለቁ፣ በዚሁ የሸፍጥ ስራ የጭነት መኪኖች ሳይቀር የገዙ ውሃ ቀጂዎች፣ በመብራት ሃይል ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ እንደ አሸን ፈስሰው፡ ውሃ እንዲቀዳለት የሚፈልግ ሰው ከአንድ እስከ አስር ጀሪካን የውሃ ግዢ ትእዛዝ በስልክ እየተቀበሉ፡ እነሱው ከተከራዩትና ከውሃ ልማት አላፊዎች ጋር ጥቅም በሚካፈሉባቸው ቤቶች ሞልተው ከሚያከማቿቸው ባለ ሰላሳ ሊትር ጀረኪናዎች እንደ ትእዛዙ ልክ አንድ ጀሪካን በሰላሳ ብር እየቸበቸቡ፡ ምስኪኑን የኮንዶሚኒየም ነዋሪ ህዝብን ኑሮ አስከፊ እንዳደረጉት ይኸው እስከዛሬዋ እለት ድረስ በግፍ ይኖራሉ፡፡

ይህ ኢትዮጵያን እንደ አገር ከያዛት የዝቅጠት ካንሰር ማሳያ ምልክቶች አንዱና እጅግ ታናሹ እንጂ ፈፅሞ ትልቁ አይደለም፡፡ በቀጣይ የኢምፔርያል ሆቴልን በሚመለከት ተመሳሳይ እውነታን እናያለን፡፡ ሰላም!!!

ያየያየ ይልማ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.