የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ እየፈጠሩ የሚያወሩትን ከመከተል መሠረቱን ቢያውቅ! – ሰርጸ ደስታ

ዛሬ ላይ ብዙ ምሁራን ነን የሚሉ ግለሰቦች ያልታሰበ፣ የልተፈጸመ ታሪክ እየጻፉና እየተናገሩ ትውልድን ከትክክለኛ መረጃ በማሳትና በማምከን የባዘነ ሲያደርጉት እናያለን፡፡ እነዚህ ምሁራን ነን ባዮች የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን መሆናቸው ካልሆነ በብዙ መልኩ የምሁርነትን ስነምግባርና ለምሁርነት የሚያበቃ በመረጃ ላይ የተመሰረተ መረጃን ወይ ያልቻሉ ናቸው ወይም ደግሞ የራሳቸው አላማ ስላላቸው ሆን ብለው ትውልድን ከትክክለኛው መረጃ ያወጡታል፡፡ በዚህም በማሕበረሰብ ደረጃ ሳይቀር የተሳሳተ መንገድ እንዲከተል ያደርጋሉ፡፡ ባልተፈጠረና ባልታሰበም ታሪክ ምሁር ነን በሚሉ ግለሰቦች ሳቢያ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ አነሰም በዛም እየተጎዳ ነው፡፡ ከሁሉ በከፋ ሁኔታ የተጎዳው ግን ግን የኦሮሞ ሕዝብ በተለይም ደግሞ የቁመቤው ትውልድ ነው፡፡ አብዛኛው የዚህ ትውልድ መሠረታዊ ማንነቱን ጥሎ ሌሎች በመገቡት የተሳሳተ መረጃ እየተመራ ከመሠመር ወጥቶ እናየዋን፡፡ የሚነገሩት ታሪኮች ሁሉ ጥላቻ በሌሎች ላይ እንዲኖረው ሆኖ አእምሮ የተለጎመ ሆኗል፡፡ እንደ ጠላት የሚያየው ዛሬ እየገደሉት ያሉትን ገዳዮቹን ሳይሆን ክብርና ወኔ ሊሆኑት የሚችሉትን የቀደሙ ጀግኖች አባቶቹንና ለኦሮሞ ሕዝብ ክብር ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸውን መሪዎችና ግለሰቦች ነው፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክና ሥርዓት አሟልቶና አጣርቶ ከጻፉትና ባለውለታ ሊሆኑ የሚገባቸው ግን በዛሬው በተሳሳተ መረጃ አእምሮው የታወረው  የኦሮሞው ተውልድ ዘንድ እንደ ጠላት ከሚታዩት አንዱ የታሪክ ጸሐፊው አባ ባሕሬ ናቸው፡፡ የአባ ባሕሬን መጽሐፍ በትክክል አግኝተው ያነበቡት በጸሐፊው ጥልቅ የምርምርና የጽሑፍ ችሎት እጅግ ይደነቃሉ፡፡ በአባ ባሕሬ “ዜናሁ ለጋላ” የሚለው መጽሐፍ እጅግ ከተደመሙትና ከሚያደንቁት አንዱ ደግሞ በዘመናችን የኦሮሞን ገዳ ሥርዓት በጥልቀት ያጠኑት ፕ/ር አስመሮም ለገሰ ናቸው፡፡ እንደ አስመሮም ለገሰ ከአባ ባሕሬ በላይ የኦሮሞን ገዳ ሥርዓት ጠንቅቆ የመዘገበ የለም፡፡ አባ ባሕሬ የዘጠኝ ገዳዎች ማለትም 72 ዓመት ሙሉ ሂደት እየተከታተሉ በጥልቀት ታሪኩን መዝግበው ዛሬም ድረሰ በሰነድ እንዲኖር ያደረጉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ምሁር ነን የሚሉ አባ ባሕሬንን መጽሐፍ ይዘቱን ይቅርና ርዕሱን እንኳን የማያውቁት አባ ባሕሬን የኦሮሞን ሕዝብ ከባሕር ወጣ ብለዋል ብለው ሲናገሩ በድፍረት ነው፡፡ ማንም ሰው ቢያስበው አባ ባሕሬን 72 ዓመት ሙሉ የገዳን ሥርዓት እየተከታተሉ ነው የመዘገቡት፡፡ የጻፉትም መጽሀፍ ትልቅ መዝገብ እንጂ በአንድ ቃል የሚለካ አደለም፡፡ ከባሕር ወጣ ብለዋል ብለው የሚናገሩት ሁሉ የአባ ባሕሬንን መጽሐፍ አንብበው ሳይሆን በወሬ የሰሙትን ነው፡፡ 72 ዓመት ሙሉ ትኩረት ሰጥተው ተከታትለው ሥርዓቱንነና ታሪኩን የጻፉለጽን ሕዝብ እንዲህ ዛሬ እነዳገኙ ከየትም ወፍ ዘራሽ  ወሬ እየዘሩ ምሁር ተብዬዎች ንግግር አደለም፡፡ የኦሮሞን ሕዝብ ሥርዓትና ታሪክ በትክክል ለማወቅና ለመረዳት ከአባ ባሕሬ መጻፍ በላይ ምንም አይነት መዝገብ የለም፡፡ መቼም ይሄ ትውልድ የታወረ በመሆኑ እንዴት ጋላ ብለው ይጽፋሉ ማለቱ አይቀርም፡፡ እውነታው በዛን ወቅት ጋላ የሚለውን አጠራር አባ ባሕሬ የሰየሙት ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ ዛሬ ኦሮሞ ተብሎ ሥማቸው የተቀየረው ሕዝብ ራሳቸው ለአባ ባሕሬ የነገሯቸውን መጠሪያ ነው፡፡ በዛን ወቅት ኦሮሞ የሚባል ቃል አልነበረም፡፡  ጋላ የሚለው ቃልም እንደ ጥሩ ያልሆነ ሥያሜ እየሆነ የመጣው በኃለሥላሴ ጊዜ እንጂ ከዛ በፊት ምንም የተለይ የሕዝብን ክብር ለማሳነስ የሚውል ሥም አደለም፡፡ በፈረንሳዮቹ ወንድም አማቾች አባዲዎች በጉድሩ (ወለጋ) ኦሮሞ የሚል ሥም በመጠቀም የዛን አካባቢ ሕዝብ ሥም ጽፈዋል ተብሎ የሚነገረው ዘመን የቅርብ ጊዜ ነው፡፡ ይህን  ጉዳይ ማንሳቴ አሁንም የአባ ባሕሬ መጽሀፍ ዜናሁ ለጋላ ስለሚል ያልተፈጠረን ታሪክ መናገር ሱስ የሆነባቸው ሌላ የተሳሳተ ታሪክ እንዳይሰሩበት ነው፡፡ https://www.youtube.com/watch?v=1ZqDFvRMVmc

ሌላው የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው በተለይም አማራና ትግሬ ከሚባው ሕዝብ የተለየ ሆኖ ራሱን ሀበሻ ማለትን ይፀየፍና ሐበሽነትን ለትግሬና አማራ የሰጣል፡፡ ሲለውም አማራና ትግሬ ሴማዊ ኦሮሞና ሌሎች ደቡብ ሱማሌ ምናምን ኩሽ ይላል፡፡ በእርግጥ የዚህ ታሪክ መነሻው በትምሕርት ቤትም ሲሰጥ የኖረው የሴሜቲክ ኩሽቲክ ምናምን ቋንቋ በሚል የተከፋፈለው ሂደት ነው፡፡ እውነታው ሴሜቲክና ኩሽቲክ የተባሉት የቋንቋ ምድቦች ሁለቱም አፍሮኤዢያቲክ ተብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ በእርግጥም ሐበሻ ከሚላ ሕዝብ ጋር ይየያዛል፡፡ ሐበሽ የሚለው ቃል የተለያየ ትርጉም ቢሰጠውም የተደባለቀ ሕዝብ የሚለው ብዙዎች ያምኑበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም ደግሞ የሴሜቲክና ኩሽቲክ ቋንቋ ምድብ የሚታወቁት አሁን በአለው ሳይንሳዊ የመለዘር(ጀኔቲክስ) ጥናት መሠረት ፍጹም የማይለያዩ ሕዝቦች እንደሆኑ የሚያሳይ የሳይንሳዊ ሪፖርት ከዚህ በፊት ለአንባብያን ጋብዤ ነበር፡፡ ችግሩ የሚያነብ የለም፡፡ ሑሉም ተናጋሪ ነው፡፡ በእርግጥም ታሪክ እየፈጠረ ማውራት የለመደ ማንበብ አያስፈልገውም፡፡ በድጋሜ ያንኑ ጹሑፍ እጋብዛለሁ፡፡ http://www.cell.com/ajhg/pdf/S0002-9297(12)00271-6.pdf  ምሁር ነን የምትሉ ሁሉ እባካችሁ አንብቡት፡፡ የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ ይዘትን ምን እንደሆነ አላውቅም፡፡ ስላላነበብኩት፡፡ ኦሮሞና አማራ በዘር አንድ ናቸው ከሆነ ግን ዋነኛ ጭብጣቸው በሊንኩ የምታገኙት በታወቀ የሳይንስ መጼሔት የወጣው ጽሑፍ ይሄንኑ ነው እንደወረደ የሚናገረው፡፡ ይህ ጽሁፍ የኦሮሞና አማራን የዘር አንድነት ብቻም ሳይሆን ትግሬ፣ አፋር ሱማሌ፣ ወላይታ ምናምን የአንድ ዘር ግንድ እንዳላቸው ከመናገሩም በላይ እንዴት ከኢትዮጵያ ተነስተው እስከታንዛኒያ የደረሱ ሕዝቦች እንዳሉ የሚያሳይ ገሀድ ነው፡፡ የኬንያውን ማሳይና፣ የታንዛኒያውን ሰንዳዌ ሕዝብ በግልጽ የኢትዮጵያውያን ዘሮች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ ግብጾች በተወሰነ፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ የአለም ሕዝብ ሁሉ ደም የተከማቸባት አገር እንደሆነችም ይመሰክራል፡፡ ይህ ነው ሐበሽነት፡፡

ሌላው ከማስተዋል ማጣት የሚመጣ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመልክ አንዱ ከአንዱ እንደማይለይ በግልጽ እየታየ በዘር የተለያየን ነን ብሎ ራሲን ወደ ሆነ ሰፈር እያስጡ የሚነገረው ንግግር ነው፡፡ ታሪካችንም እኮ በግልጽ ይነግረናል፡፡ ቢያንስ ብዙ ዛሬ ኦሮምኛና አማርኛ የሚናገሩ ሕዝቦች በአንድ ወቅት ሌላ ቋንቋ ተናጋሪ እንደነበሩ እናውቃለን፡፡ ጋፋት፣ ዳሞት ምናምን የሚባሉ ቋንቋዎች በደርግ ጊዜ እንደነበሩ አናውቅ ነበር፡፡ ዛሬ እንዲህ የሚባል ሕዝብ የለም፡፡ ይህ እንግዲህ አስተውሉ በጣም በቅርብ በእኛው እድሜ ማለት ነው፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የሳይንሳዊ ጥናት ውጤት ግን ለእኔ ሌላ ታሪክ ነው ያጫረብኝ፡፡ እንደሚገባኝ ከክርስትናም ከእስልምናም በፊት ብዙው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰማይ አምላክ የሚያምን ነበር፡፡ በሰሜኑ የኦሪት እምነት ተከታይ እንደነበር በግልጽ ይነገራል፡፡ ሆኖም ይሄ እምነት በሁሉም ሕዝቦች ዘንድ በአንድ ወቅት እንደነበር ዛሬ ድረስ የዘለቀው ባህላዊ ድርጊታቸው ይመሰክራል፡፡ በተለይም በኦሮሞ ሕዝብ ኢሬቻ እየተባለ የሚጠራው አምልኳዊ ሥርዓት በቀጥታ የኦሪት ሥርዓት እንደነበር የሚያመላክት እውነት አለ፡፡ ማስተዋል ከቻላችሁ የኦሮሞ ሕዝብ በበባሕል የሚያመልከው ዋቄፈታን ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታ የሰማይ አምላክ ማለት ነው፡፡ ዋቃ ማለት በኦሮምኛ ሰማይ ወይም እግዚአብሔር ማለት ነው፡፡ በብዙ አገሮች እንደምናየው ራሱ በሰራው ጣዖት ያመልካል እንጂ በሰማይ አምላክ የሚያምን ሕዝብ እስከማውቀው የለም፡፡ ይህ የሚያሳየን ቢያንስ ዛሬ ኦሮሞ የተባለው ሕዝብ ጥንቱንም የኦሪት እምነት ተከታይ እንደሆነ ነው፡፡ ይሄንኑ የሚያጠናክረው በብዙዎች ዘንድ እንደ ባዕድ አምልኮ የሚታየው የኢሬቻ ሥርዓት ነው፡፡ አስተውላችሁ ከሆነ የኢሬቻ በዓል የሚከበረው በመስከረም ነው፡፡ ይህ ወር በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስቲያን እንቁጣጣሽ የተባለው በዓል የሚከበርበት ነው፡፡ እንደእውነቱ የእንቁጣጣሽን ሀይማኖታዊ መሠረት የሚገናኘው ከክርስትና ጋር ሳይሆን ከኦሪታዊ ሥርዓት ጋር ነው፡፡ አከባበሩም ኢሬቻ ከተባለው የኦሮሞ ሕዝብ ሥርዓት ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ለሁለቱም ለእንቁጣጣሽም ለኢሬቻም ልዩ መለያቸው ቄጤማ ወይም ለምልም ሳር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እንቁጣጣሽ ከኖህ የጥፋት ውሐ መቀነስ ጋር የተያያዘና የጭንቅ ጊዜ አለፈ በሚል የምስጋና ማቅረቢያ ነው፡፡ በኢሬቻም የሚደረገው ይሄው ነው፡፡ እኔ የታሪክ ምሁር አደለሁም፡፡ እዚህ ላይም ይህን ጉዳይ ያንሳሁት ማስተዋል እንዲኖረን እንጂ ነው የሚል ድምዳሜም ለመስጠት አደለም፡፡ የታሪክ ምሁራን ዋና ሥራቸው እንዲህ ያሉ ሥርዓትን መነሻቸውን መመራመርና መድረስ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው እንኳን እንዲህ ያልታወቀውን ተመራምሮ መድረስ ይቅርና ሌሎች ትመራምረው በሥርዓት መዝግበውት ያለውን ታሪክ አንብቦ ትክክለኛ መረጃ ከመስጠት ይልቅ ከምናብ እየወለዱ የሚጽፉ የታሪክ ምሁራን ናቸው ያሉን፡፡ ስለ ኢሬቻ ታሪካዊ አመጣጥ ማንም የሚነግረን የለም፡፡ ዛሬ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሁሉ ምንነቱንና እንዴት እንደመጣ ሳያውቅ ነው የሚከተለው፡፡ ገዳንም ሌሎች ጻፉት እንጂ እንዴት እንደመጣ ታሪካዊ ሂደቱ በኦሮሞ ምሁራን ዘንድ እንደሚያወሩለት አይታወቅም፡፡

በመጨረሻም ብዙ የኦሮሞ ምሁራን ነን የሚሉ ሕዝቡን ታሪክ አልባና ማንነት አልባ በማድረግ አደሕይተውታል፡፡ እነሱ ራሳቸውን ምሁር ለማድረግ እንጂ ስለሕዝቡ ታሪክ ጉዳያቸው አደለም፡፡ ምሁርነታቸውን ለመግለጽ የማይነግሩን ማዕረግ የላቸውም፡፡ አንዳንዶች ያልተመረቁበትን ዲግሪ ሳይቀር እየጨምሩ ሲናገሩ አያፍሩም፡፡ ሌሎች ደግሞ በእከሌ ዩኒቨርሲቲ የፒ ኤች ዲ ምናምን እጩ ምንትስ ምንትስ በሚባል ዘርፍ ይሉንና ራሳቸውን መጀመሪያ ይቆልላሉ፡፡ ይህ ምሁርነት አደለም፡፡ በፍልስፍና እንዲሕ ያሉ ቃላትን ከንግግር በፊት መጠቀም ከፍተኛ ሕጸጽ (ፋላሲ) ነው፡፡ ፋላሲ ኦፍ አደ ሁሚነም ይባላል፡፡ ሌሎች የሆነ የፈረንጅ ሥምና የሆን ፈረንጅ የጻፈውን ፅሑፍ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል እንዲህ ብሏል ይላሉ፡፡ አሳዛኙ ነገር የጠቀሱት ጉዳየት በሚጠቅሱት ጽሑፍ ውስጥ ያለመገኘቱ ብቻም ሳይሆን ከእነጭርሱ የሚባል ጽሁፍም ላይኖር ይችላል፡፡ በቃ በእነሱ የታወቀ የፈረንጅ ሥም በመጥቀስ ራስን ምሁር ማድረግ ይቻላል፡፡ ፅሁፍም ካለው በጥልቀት አንብቦ ከመረዳት ሳይሆን ወይ የሆነ ቦታ አንዱ ሲያወራ የሰሙትን ነው መልሰው የሚያወሩት፡፡ ይህ ደግሞ ፋላሲ ኦፍ አድ ፖፕለም ይባላል፡፡ በታወቁ ሰውች ሥም ሀሰት መናገር ማለት ነው፡፡ እንደ እውነቱ ጥልቁን የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ የጻፉትን የአባ ባሕሬን መጻፍ ሳያነብ ፈረንጅ በጨረፍታ ያያትን ታሪክ መናገር በራሱ ከፈረንጅ አምላኪነትና ከአባ ባሕሬን ጋር ይያያዛል ብለው የሚያስቡትን ሕዝብ ከመጥላት በቀር ምን ምክነያት እንዳለው እኔን አይገባኝም፡፡

ይህን ሁሉ ብዬ በዛው ልክ ብዙ ጥረት እያደረጉ ያሉ የኦሮሞ ምሁራንና አክቲቪስቶች እንዳሉ አልዘነጋም፡፡ ለእኔ እንደነ ፕ/ር መረራ ጉዲና የመሳሰሉት ምሁራን ብዙ እንደለፉ አሁንም ለሕዝብ መሥዋዕት እስከመሆን ተሰልፈው እናያቸዋለን፡፡ የእነ መረራ ፍልስፍና ግን ታሪክን እየፈጠሩ በሚያወሩ ምሁር ነን ተብዬዎች ወሬ አድማጭ ሊያገኝ አልቻለም፡፡ አሁንም እላለሁ፡፡ የኦሮሞ ምሁራን ልብ በመሳሳት ከሆነ ራሳችሁን ማይት ብትችሉ፡፡ ሕዝቡን የምትጠቀሙበት ዘዴያችሁ ግን ከሆነ ምን ይደረጋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በቅርብ የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ደጋፊ ከአገኙ መልካም ነገርን ሊያሳዩን የሚችሉ ሰው እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡ ብዙዎች ሥነቶች ለዘመናት ያቦኩትንና ያበላሹትን በአንድ ሌሌት ለማ መፍትሄ እንዲያበጁለት አትጠብቁ፡፡ ቢያንስ ለማ በንግግራቸው የምናየው በራስ የመተማመን ሥሜት አለ፡፡ ሁሉም ከተባበራቸው ጨዋታውን ሁሉ ሊቀይሩ የሚችሉ ሰው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዶች ሕዝብን ለመሳብ ሲናገሩ የደመጣሉ፡፡ የለማ ንግግር ግን ቁጭትም፣ የማንነት ሥሜትም እንዳለበት እናያለን፡፡ በአዲስ አበባ ኦሮሞ ታወር መሥራት እንደ ልዩ የልማት ዕቅድ የተወሰደበት ነገር ግን አሳዝኖኛል፡፡ ምክነያቴ የኦሮሞን ሕዝብ አዲስ አበባ ኦሮሞ ታወር የሚል ሕጻ መሥራት በሚል መደለል እንችላለን የሚል ሥሜት ስላነበብኩበት ነው፡፡ አንድ ተናጋሪ ከተናገሩት”ፊንፊኔ ጂዱቲ ኦሮሞ ታወር ኢጃሩ በርባና፣ ቢይ ኩን ከን ኦሮሞቲ ኦሮሞን ቢይ ከናራ ኦሮሞ ታወር በርባቺሳ” ምናምን እያሉ ድንፋታ አይሉት ንግግር ሲያወሩ ሰምቼ አዝኛለሁ፡፡ ዕቅዱ ከአላቸው የሄንን አሁን አንደቁም ነገር ማውራት ለምን አስፈለገ፡፡ ይህ ቁማር የአሮሞ በተለይም አሁን ያለውን ትውልድ ሥነልቦና ስለተረዱት በዚህ መልኩ ለመደለል ካልሆነ በቀር አንድ ሕንጻ በኦሮሞ ሥም መገንባት ለኦሮሞ ሕዝብ ምኑ ሊሆን እንደሚችል አይገባኝም፡፡ ይልቁንም ይህን ያህል ሕዝብን አሳንሶ ማየት ያሳዝናል፡፡ ዛሬ ሕዝብ የሚያስፈልገው ከልብ የሚቆጭ መሪ ነው፡፡ የሄን ላደርግልህ ነው እየለ የሚደነፋለትም አደለም፡፡ እና እላለሁ የአቶ ለማ በጎነት እንታሳቢ ሆኖ አብረዋቸው የሚሠሩትም አስተሳሰብ ወሳኝ ነው፡፡ አቶ ለማ እንዳሉት አዋጭ ሊሆን የሚችለው ሁላችንም ያለን አንዲት አገር ናት ብሎ ማሰብ ነው፡፡ የኦሮምያ ክልል አስተዳዳሪ መሆን አሮሞን ብቻ ብሎ የሚያስብ ከሆነ ያው መቀየር አይኖርም፡፡ የሌላውም እንደዛው፡፡ ሁሉም የሚያስተዳድሩትን ክልል እንደ ክልልነቱ ብቻ አይቶ በዘርና በሀይማኖት ሳይለዩ ማሳተፍ ካልቻሉ መቼም ቢሆን ለውጥ አይመጣም፡፡ ጥፋቱ የዘውግ ክልላዊ መዋቅር መሠራቱ ሳያንስና 25 ዓመት ሙሉ እምን ደረጃ እንዳደረሰን ይባስ ዛሬ ለሕልውናችን ሳይቅር አደጋ እየሆነ እንደመጣ እየታየ አሁንም መማር አለመቻላችን ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ክልሎቹ እርስ በእርስ ቀጥተኛ ግንኙነት በማድረግና በመታባበር በወያኔ ቁጥጥር ሥር የወደቀውን ማዕከላዊ ቡድን ማምከን አለባቸው፡፡ ለዚህ ሕዝባቸውን ዘር ሀይማኖት ሳይሉ ማስተባበር መቻል አለባቸው፡፡ በዚህ መልኩ አገራችንን ወደነበረችበት ለማምጣት እድል ይኖረናል፡፡  ክልሎቹ በዚህ መልኩ የሚሠሩ ከሆነ ሑሉም የሕዝብን አንድነት በመስበክና እንዲተባበራቸው ቢያደርግ እድል አለ፡፡ እንደኔ በአዴን መሆን ማለት የወያኔ ወዳጅ ማለት አደለም፡፡ በአዴን ሁሉ ሆዳም አደለም፡፡ ከማንም በላይ በአዴን ውስጥ ያሉ ብዙ አመራሮች ወያኔን በመፋለም ትልቅ ትግል እያደረጉ እንደሆነ አናውቃለን፡፡ ኦህዴድም ውስጥ በተመሳሳይ ከሕዝብ ጎን ሆነው ከፍተኛ መሠዋዕት እየከፈሉ ያሉ እንዳሉ እናውቃለን፡፡ እስከዛሬ ኦሕዴድ ውስጥ ከፍተኛ አመራሮቹ የወያኔ ተቀጣሪ መሆናቸው ችግር ቢሆንም ብዙ ለሕዝብ መሥዋዕት እስከመሆን የደረሱ አሉ፡፡  ምን አልባት አሁን የመጣው የኦሕዴድ አመራር ከዋናዎቹም ለሕዝብ የወገኑ ከአሉ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ አቶ ለማ አንዱ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ

 

አሜን!

 

ሰርጸ ደስታ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.