ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በዚህች ትንሽ አጋጣሚ ዕንወቅ – ነፃነት ዘለቀ

እንደአካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማያውቅ ወይም ለማወቅ የማይጓጓ ዜጋ መኖር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ማለት ከእያንዳንዱ ዜጋ ልብ ውስጥ መጥፋት የሌለበት የሁሉም አለኝታና ከአባትና እናት የማይተናነስ ቦታ ያለው ነውና፡፡ አንድ ዕድለኛ ቤተሰብ ውስጥ እናትና አባት ይኖራሉ፡፡ አንዱ ቢጎድል ከሁለት አንዱ ይኖሩና ክፍተቱን በተቻለ መጠን ለመሙላት ይሞክራሉ፡፡ ሁለቱም ከጎደሉ ግን በተለይ ልጆች ትንንሽ ከሆኑ ብዙ ችግር ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪም የወላጆች መኖር ብቻውን ምንም ማለት የማይሆንበት አጋጣሚ መኖሩንም መዘንጋት አይገባም፡፡ በዋል ፈሰስ የሆኑ አባትና እናት ያጋጥሙና መንጋው የሚበተንበት ወይም ዘምቦለል የሚሆንበት ሁኔታ ቢፈጠር ችግሩ የቤተሰባቸውን አውራ(ዎች) በሞትና በመሰል መጥፎ አጋጣሚዎች ከተነጠቁ ወገኖች ባልተናነሰ የሚገዝፍ መሆኑ አይካድም፡፡ ቤተሰብና ሀገር ደግሞ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ቤተሰባዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣ አባውራ ሀገር ቀርቶ የቅሬ(ዕድር) ሊቀ መንበርም መሆን አይችልም፡፡ ሌባ ከላይ ከታዬ ከታችም ሌባ ነበርና ቤተሰቡም እንዲሁ ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ …

የኛ ችግርም እንደዚሁ ነው – በላይኛው አንቀጽ መጨረሻ አካባቢ እንደተገለጸው ዓይነት፡፡ ሲጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር የለንም፡፡ ሲቀጥል አለ የሚባለው ጠቅላይ ሞንስተርም ለአቅመ አሻንጉሊትነትም ያልደረሰ በጌኛ ፈረስነት ሕወሓትን ለማገልገል የተጎለተ መሆኑ ወያኔ በቆራጣ ጅራቱ ሊሸፍነው የማይችለው አገር የሚያውቀው ፌዝ ነው፡፡ ወያኔ ትግሬ በእንደራሴ አገር መግዛትን ከጥንትም ያውቅበታልና ይህን ጉልቻ አስቀምጦ እየተጫወተብን ነው፡፡ (በል ብሎኝ ቲቪ ሳይ ይህን “ጠ.ሚኒስትር” እመለከትና በሣቅ ፍርስ እላለሁ፡፡ “እርሱስ ያምንበት ይሆን?” ብዬም መልስ የማላገኝለትን ጥያቄ ራሴኑ እጠይቃለሁ፡፡ ሆ! ምን ዓይነት ለዛቢስ ቲያትራዊ ቀልድ ነው እባካችሁን ወያኔዎች በዓለም ሕዝብ ፊት እየተወኑ ያሉት፡፡ የሚገርመው ይህን ቲያትራቸውን እያዬ የሚዝናና “ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ” መኖሩ፡፡)

አነሳሴ ጉልቻውን ለምን እንደተጎለተ መግለጽ አይደለም፡፡ የሰማሁትን የዚህን ሰው ነውር ለመናገር እንጂ፡፡ ያገራችን ድንጋይ ራስ ባለሥልጣናት የማይሠሩት ወንጀልና ሙስና የለም፡፡ ባይሞስኑ ኖሮ ለምሣሌ ቀደም ባለ አንድ ወቅት ይሄው የክርስቶስ ልጅ ነኝ ባዩ የሁለት ጌቶች ባሪያ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ በአንድ ጊዜ ግብይት አሥር ሺህ ዶላር የሚያወጣ ሸቀጥ በአንድ ሱፐርማርኬት እንደገዛ ባልተገለጸ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ደሞዝ ይህ ግዢ የሚታሰብ አይደለምና፡፡ እኛ እርቃናችንን እንሄዳለን እነሱ በወርቅ በተሞላ በርሜል ውስጥ ይዋኛሉ፡፡ ዕንቆቅልሽ፡፡ ግድያውንና ስቃዩን በተውልን ኧረ! የወርቁስ ነገር እዬዬም ሲዳላ ነው፡፡

ይህን ምሥጢር ከሰማሁ ብዙ ጊዜየ ነው፡፡ ግን የነገረኝ ሰው ጠቅልሎ ውጪ እስኪወጣ ምሥጢሩን መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ የሰማሁት ነገር ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው፡፡

የማውቀው ሀብታም አዋሳ ውስጥ አንድ ቢዝነስ ሊጀምር ለሚመለከተው ኃላፊ ቢሮ ያመለክታል፡፡ ጊዜው ራቅ ይላል፡፡ የዚያ ቢሮ ኃላፊ ደግሞ የአሁኑ ውዝፍ ጠቅላይ ሚኒስትር የያኔው የተጠቀሰው ቢሮ ባለሥልጣን ደሳለኝ ማነው ኃይለማርያም ደሳለኝ ነበር፡፡ ያ ስሙንና ሥራውን አሁንና እዚህ የማልገልጸው ወዳጄ በዚህ ጉልቻ ሰውዬ የተጠየቀው ጉቦ ግን የጉልቻውን ሰውዬ ቁጥርን ያለማወቅ ደደብነት በግልጽ የሚናገር ነበር፡፡ “ለዚህ ጉዳይ (ለፈገግታ ያህል ‹ዳ›ን እንደርሱው ብታነቡልኝ ደስ ይለኛል) 500 ሺህ ብር ካልሰጠህ አይፈጸምልህም፡፡ ለኔ ብቻ ሣይሆን ለብዙ ሰው ስለሚከፋፈል – በኔ አማርኛ – ‹ከዚህ በታች አያዋጣንም፡፡›…” ብሎ ነበር ቅስሙን ሰብሮ ከቢሮው ያስወጣው – የኛ ፕሮቴስታንት ‹የኢየሱስ ልጅ›፡፡ ሃይማኖት እንዲህ መቀለጃና ማጭበርበሪያ ይሁን? ለነገሩ ዛሬ ጊዜ ሃይማኖት እንጂ ሃይማኖተኛ የት አለ? ምሎ የነገረኝ በመሆኑ ስለእውነትነቱ ሃሳብ አይግባችሁ፡፡ ከዚህም በላይ አለና የሙስና ነገር በኛ ሀገር የእጅ ሰላምታን ያህል በጣም ቀላልና የማይታፈርበትም ነው፡፡ የሚያሳፍረውና የሚያሸማቅቀውስ አለመሞሰን ነው፡፡ ሙስና እግር አውጥቶ እንደልቡ የሚሄድበትና የሚንቀባረርበት ብቸኛዋ የዓለም ሀገር ኢትዮጵያ ለመሆኗ ጥርጥር አይግባችሁ፡፡

የኛ ጠቅላይ ሚኒስትር – ለላግጣም ቢሆን – ይሄን መሰሉ ነው፡፡ እንደኔ አፈራችሁ?

በመሠረቱ ሕወሓት ጋር ለመሥራት ቆሻሻ ስብዕና አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የማይደራደሩበት ቅድመ ሁኔታም ነው፡፡ ንጹሕ ሆነህ ቆሻሻ ጋር ዝምድና አይኖርህምና ወያኔ ጋር ለመሥራት ወይም ከነሱ ጋር አንዳች ኅብረት ለመፍጠር በግድ ሞሳኝና በምግባርህ የበሸቀጥህ መሆን አለብህ፡፡ የወረደ ስብዕና ከሌለህና አእምሮህን በአግባቡ ልጠቀም የምትል ከሆነ ከዚህ ወራዳ ድርጅት በልጅ ልጆቼ አገላለጽ በአፋጣኝ ‹መፋታት‹ አለብህ፡፡ ጨለማና ብርሃን የጋራ ነገር የላቸውም፡፡ በዘመነ ክርፋትና ጥምባት አልባብ አልባብ እየሸተትህ ልሂድ ብትል አትችልም፡፡ አብረህ ጠምብተህ መጓዝ ብቸኛ አማራጭህ ነው፡፡ ልንገልጸው ቃላት የሚያጥሩን የሙስና አዘቅት ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን፡፡

ኃይሌ ለውሸትም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሬ ሆኖ ሳየው የሀገሬን ማርጀትና መበስበስ እረዳለሁ፡፡ እንዲህ ያለ ሙሰኛና ጉቦኛ ብቃትን ተጎናጽፎና ምሉዕነትን ተላብሶ ከ100 ሚሊዮኑ ሕዝብ “በመመረጥ” ጠቅላይ ሚኒስትሬ ሲሆን መታዘብ ምን ያህል በኩራት እንደሚያስፈነድቅ እናንተም ይታያችሁ፡፡ የአለመታደላችን ዙሪያጥምጥምነትና ጥልቀት እጅግ ያስደነግጣል፡፡

ሙሰኝነት – እርግጥ ነው- የዚህች ምድር አንዱ መገለጫ መሆኑን አላጣሁትም፡፡ ግን ግን ዓይነት ዓይነት አለው፡፡ የጣሊያንም፣ የጃፓንም… መሪዎችና ባለሥልጣናትም እንደሚሞስኑ ይነገራል፡፡ የነሱ ሙስና ግን መልክ አለው፡፡ ከታላላቅ ተቋማትና ከካምፓኒዎች ሊያውም በእጅ አዙርና የሀገርን ጥቅም በማይነካ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንጂ ከግለሰብ ዜጋ ተደራድረው ክብራቸውንና የኃላፊነታቸውን ወንበር አዋርደው አይደለም – አሁንም እርግጥ ነው ያም ትልቅ ስህተትና ዋጋም የሚከፍሉበት ነው፡፡ የኛዎቹ ግን እስከዚህን የወረደ ደረጃ ድረስ  ቅሌታሞች ናቸው – የግለሰብን አጥንት የሚግጡ ጅቦች፡፡

የአንድ ባለሥልጣን የሥልጣን መወጣጫ እርካብ መጠናትና እንዲህ ያሉ ልክስክሶች ተነቅረው የሚተፉበት አሠራር ካልተፈጠረ ሀገራችን እንደደማችና ሕዝቧም እንደተዋረደ እንደተጎሳቆለም ይኖራሉ፡፡ ስለሀገራችን የሙስና ጡዘትና ዐይን አውጣነት ብመለስበት ደስ ይለኛል (እንዴ፣ ምንም ነገር ካለሙስና አይፈጸምም እኮ! ባለኝ ግንዛቤ ተፈጥሯዊ ሞት ብቻ ናት ካለ ሙስና የምትገኝ)፡፡ ብቻ ለአሁኑ ሰላም፡፡

መሰነባበቻ፡-

  • በቅርብ አንድ ብዕር መንጠፉ ተሰማ – የአቶ አሰፋ ጫቦን ነፍስ ይማር፡፡ ከርሱም በፊት ሁለት ስመጥር ዜጎችን በማይቀረው ሞት አጥተናል – ጄ. ጃጋማና ፕሮፌ. ዮሐንስ፡፡ ሞት እንኳን ነፍስ ዐውቆ እንዲህ ከየብሔረሰቡ ሲወስድ ማደጊያቸው ላይ ቁልቋልና ቅንጭብት የበቀለባቸው ወያኔዎች ግን በዚያቺው ትግራይንና ትግሬን በማስቀደሙና ሌሎችን በማውደሙ ጠባብ የአስተሳሰብ ጉድባ ውስጥ እንደተሰነቀሩ አሉ፡፡ ሲያሳዝኑ!
  • ቴዲ አፍሮ ላይ ብትር መብዛቱ ተሰማ – ጥሩ ሀገራዊ ሥራ እንኳንስ የዐድዋውን ቴዎድሮስ ፀጋየንና መሰል የወያኔ ቡችሎችን ይቅርና ሆድ አደሮችንም ያበሳጫልና ቴዲ አፍሮ ታድለሃል፤በርታ፡፡ ከነጋበት ጅብ ፈጣሪ እንዲታደግህ ላንተም እጸልያለሁ፡፡
  • ከ4000 ጥይቶች የተረፉ ታላቅ ሰው በሕይወት መኖራቸው ተሰማ – እሰይ! እንኳንም ከ4000 የደርግ ጥይት ተረፉልን፡፡ ተዓምር ዱሮም አልነበረም አይባልም፡፡ ግን ማን ቆጥሮት ይሆን? ደርግ የጥይት ሀብታም ነበር ማለት ነው!
  • ወያኔ አማራውን ለማጥፋት ልዩ የጤና ፖሊሲ ዘርግቶ እንደነበር ተሰማ – ወያኔ ምን አጠፋ? የታወጀበትን የዕልቂት ዐዋጅ ተባብሮ ከማክሸፍ ይልቅ እርስ በርሱ እየተከፋፈለ የሚናቆር ሕዝብ ከተገኘ ያ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለመጥፋት ፈቃደኛ የሆነ ሕዝብ የልቡ እንዲደርስ አቅም በቻለ መጠን መተባበር ክፋት የለውምና ለዓላማቸው ስኬት አንድም ቀን ተሳስተው የማያውቁት ወያኔዎች አላጠፉም፡፡
  • የወያኔዎች ምሥጢር በቀድሞ ባልደረቦቹ እየተዘከዘከ መሆኑ ተሰማ – ይዘክዘካ! ማን ምን ያመጣል? የወያኔ ምሥጢር ዱሮውንስ ከማን ተደብቆ ያውቃል? ችግሩ እኮ የምሥጢራቸው አለመታወቅ ሣይሆን ቀን ከሌት ተግተው እንደመሥራቸው ጠላቶቻቸውን ለመበታተንና ኅብረት ለማሳጣት የሚያደርጉት ጥረት ፍሬያማ ሆኖ መቀጠሉ ነው፡፡
  • ይብቃኝ – ስንቱን “ተሰማ” ጠቅሼ እዘልቀዋለሁ?

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.