የደህንነቱ ሰው በህብር ራዲዮ – በ ታመነ በአምላኩ

አቶ አያሌው መንገሻ በወያኔ በበአለ ፋሲካ ሰሞን ከህብር ራዲዮ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አዳመጥኩት፡፡ አቶ አያሌው የደህንነት ሰው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መምሪያዎች ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ሀያ አመት ያህል የሰሩ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም በመሆኑ በዘመነ ወያኔ የተሰሩ ብዙዎቹን ነገሮች በበቂ መረጃ ሊነግሩን ይችሉ ነበር፡፡ነገር ግን እንደተከታተልኩዋቸው ኀገሩን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተል ማናቸውም ዜጋ ከሚያውቀው የተለየ አዲስ ነገር አልሰጡንም፡፡ ስለሆነም ከዚህ በመነሳት መሞገት ቢቻልም ፋይዳው ሚዛን አይደፋም በማለት ማለፉን መርጬ ነበር፡፡

አቶ አያሌው አብዛኛው ገለጻቸው ማስረጃ አልባ በመሆኑ ከደህንነት ሰው ይልቅ ፖለቲከኛ ያስመስላቸዋል፡፡ ፖለቲካኛ ነገሮችን በጥቅል ይገልጻል፣ የመረጃ ሰው ግን ድርጊትን በግዜ በቦታ እያመሰካረ የአድራጊውን ማንነት በማስረጃ እያሳየ ይናገራል፡፡ ፖለቲከኛ አነጋገር ያሳምራል ብዙም ያወራል፣ የደህንት ሰው ብዙ ማውራት ለስህተት ይዳርጋል ይላል፡፡ ሌላም ሌላም፡፡

አቶ አያሌው ከህብር ራዲዮ ጋር ባደረጉት አንድ ሰአት በፈጀ ቃለ ምልልስ ስም ጠቅሰው ቦታና ግዜ አጣቅሰው የገለጹት የረባ ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎችን ለድርጅት አባልነትም ሆነ ለሰላይነት መመልመል፤የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችንና አባላትን ማጥመድ በማእከላዊ ምርመራ አረመናዊ ድርጊት እንደሚፈጸም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው የደህንነት ባለሙያ ገለጻም ትንተናም የማያሻው ጉዳይ ነው፡

ስለሆነም አቶ አያሌው በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ያውም ለሀያ አመት የሰሩ እንደመሆናቸው እርሳቸው በቀጥታ ወይንም በርሳቸው ትእዛዝ ሌሎች የፈጸሙትን ሊነግሩን ባይፈቅዱ በደህንነቱ መስሪያ ቤት የተፈጸሙ ድርጊቶችን ቀን ቦታና አድራጊዎችን በመግለጽ ቢነግሩን ይመረጣል፡ፕ/ር ዓሥራት በከርቸሌ ተመርዘው ነው የሞቱት፡፡ በአዲስ አበባ የኒቨርስቲ የአራተኛ አመት የህግ ተማሪ የነበረው ተሸመ ቢምረው ከጎጃም ከመጡ አርሶ አደሮች ጋር ታስሮ ከተለቀ በኋላ ታፍኖ ተወስዶ የደረሰበት አልታወቅም፤አቶ አሰፋ ማሩ በጠራራ ጸሀይ በአደባባይ ነው የተገደሉት፤ የሰኔ 1/97 ግድያ፤የህዳር 98 እልቂት ብለን የደህንነት ክፍሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው ድርጊቶች መጥቀስ እንችላለን፡፡ አንድ ትልቅ የደህንት ሹም እነዚህንና መሰል ጉዳዮችን ስቴየትና ማብራሪያ ሳያበዛ በመረጃ እያስደገፈ በማስረጃ እያረጋገጠ ቢናገረ ነው ለመማማሪያም ለመተራረሚያም ለመጠያየቂያም የሚበጀው፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል ሆኖብን እንጂ ለዚህ ጽሁፍ መነሻ ምክንያቴ ግን ይህ ከላይ የገለጽኩት አይደለም፤ የመረጃው ሰው ማስረጃ ሳያቀርቡ ግለሰብና ፓርቲ ሲወነጅሉ መስማቴ እንጂ፡፡ በተግባር የምናውቀውና የሂደቱ አካል የነበርንበት ጉዳይ ተጭምሮ ተቀንሶ ወይንም ሙሉ በሙሉ ተለውጦ በተለይ ደግሞ በመረጃ ሰው ሲገገርም ሆነ ሲጻፍ በዝምታ ማለፍ ከአድራጊው የበለጠ ጥፋተኛ ያደርጋል፡፡ ነገርግን የነበሩበትን ነገር ሙሉ ለሙሉ አውቃለሁ ማለት አይቻልምና በመረጃ ተደግፎ በማስረጃ ተረጋግጦ ቢቀርብ እንዴት ከውስጥ ሆኜ ይህን ሳላውቅ ብሎ ራስን ለመጠይቅ መለስ ብሎም ያሳለፉትን ሂደት ለመፈተሸ ያግዛል፣ ለመማሪያነትም ይጠቅማል፡፡ እንኳን የመረጃ ሰው የፕሮፓጋንዳ ሰራተኛ እንኳን አያሌ ሰዎች በሚያዳምጡት ራዲዮ ቀርቦ ሲናገር መረጃ እየጠቀሰ በማስረጃ እያረጋገጠ ቢሆን ነው ተአማኒነት ሊያገኝ የሚችለው፡፡

ይህን ካላሟላው የአቶ አያሌው ንግግር ጥቂት አብነቶችን በመጥቀስ ትክክል አለመሆናቸውን በማስረጃ ላሳይ፤ ጥያቄም ልጠይቃቸው፡፡ ስለ እውነት ለመነጋገር የግለሰቦች ወይንም የድርጅቶች ጠበቃ መሆን ሳያስፈልግ ነው፡፡ በመሆኑም አቶ አያሌው ስለ ልደቱ ስለተናገሩት ማስረጃ ስጠይቅ ልደቱን ንጹህ በማድረግ ወይንም ለእርሱ ለመከራከር እየዳዳኝ አይደለም፡ራሱን ለገደለ ሰው ምንኑ ይከራከሩለታል፡፡ ዓላማየ ትልቁ የደህንነት ሰው ስለሚነግሩን ነገር መረጃና ማስረጃ ማቅረብ የሙያቸው ግዴታ መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡ እንደውም የመስኩ ባለሙያዎች የደህንነት ሰው ንግግር አምስቱን ወርቃማ ጥቄዎች የሚመለስ መሆን አለበት ይላሉ፡፡

1-ኢዴፓን ያቋቋመው ወያኔ ነው፣ አቶ አያሌው ይህን ሲናገሩ እንዴት፣ በምን ሁኔታና፣ በእነማን እየታገዘ ወያኔ ኢዴፓን እንዳቋቋመው አልገለጹም፣ የደህንነት ሰው እንጂ የአሉባልታ ሰፈር ሰው ባለመሆናቸው መግለጽ የሙያቸው ግዴታ ነበር፡፡ ኢዴፓ በ1988 ዓ.ም ከመአህድ በተባረሩ ወጣቶች በ1992 ዓም የተመሰረተ በ1993 ዓም አንደኛ ጉባኤውን አካሂዶ አንቱ የተባሉ ኢትዮጵያውያንን ለማቀፍ የቻለ እስከ ምርጫ 97 በቁጥር አንድ ከሚጠቀሱ ፓርቲዎች አንዱ የነበረ ነው፡፡ በስድስት አመት ከሰራቸው ተግባራት አንድም በወያኔነት የሚያስፈርጅ ቀርቶ የሚያስጠረጥረው ነገር የለም፣ካስፈለገ አንዚህን በዝርዝር ማቅርብ ይቻላል፣መለስ ብሎ ጽሁፎችን በማገላበጥም መረዳት ይቻላል፡፡

አንድ ዌንም ሁለት ግለሰቦችን ወያኔ ማለትና ድርጅትን ወያኔ ማለት በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፣ ጭራሽ ወያኔ የመሰረተው ማለት ደገሞ ከሁለቱም የባሰና የከፋ ነው፡፡ ማስረጃ ሳይቀርብ ያውም በደህንነት ባለስልጣን ሲነገር ደግሞ…፤

2-ዶ/ር ኃይሉን በወያኔነት መፈረጅ፤ ከአንድ የመረጃ ሰው ያውም በወያኔ መዋቅር ውስጥ ሀያ አመታት በሀላፊነት ከሰራ ሰው ይህን ስሰማ በእጅጉ አዘንኩ፡፡አቶ አያሌው ከመረጃ ሰውነት ወደ ፕረፓጋዲስትነት የተቀየሩ ሆነውም ታዩኝ፡፡ ለመሆኑ አቶ አያሌው ለዚህ አባባልዎ ማስረጃ ይቅር መረጃ ማቅረብ ይችሉ ይሆን! አዘንኩብዎት፡፡

ስለ ዶ/ር ኃይሉ ከሚታወቀው ትንሽ እንባቢን ላስታውስ፤በደርግ የመጨረሻው ሰአት በብሔራዊ ሸንጎ ሰብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት መንግስቱን “እርስዎም ክኒኗን ይዋጧት” ያሉ ሰው ናቸው፡፡ በዚህ ንግግራቸው አቸፍቻፊው ሁሉ ዘመዶቹ አምቦ መድረሳቸውን አይቶ ተማምኖ ነው እንዲህ የተናገረው ሲላቸው፣ ፕሬዝዳንቱም ሊያስሯቸው አስበው በበጎ መካሪ ሰዎች እንደተዋቸው ብዙዎች ተናግረዋል ጽፈዋል፣ (የኮ/ል ፍስኃ ደስታን መጽኃፍ በማስረጃነት መጥቀስ ይቻላል፡፡) እንዲሁም ራሳቸው ፕሬዝዳንት መንግሥቱ፣ “ሀይሉ ደፈረኝ” ብለው ለጋዜጠኛ ገነት ነግረዋት ጽፋዋለች፡፡

በምርጫ 97 ማግስት ዶ/ር ኃይሉ በቅንጅት በታሰሩበት ግዜ ከትንሽ እስከ ትልቅ ወያኔዎች ከሀዲ እያሉ እንዴት ያደርጉዋቸው እንደነበረ አብረዋቸው በእስር የቆዩ ሰዎች ይመሰክራሉ፡፡ ነገርግን ይህ ሳይበግራቸው፣ የእድሜ መግፋት ሳያግዳቸው አንድነት እስከ ፈረሰበት ግዜ ድረስ በተቃውሞው ጎራ ነበሩ፡፡ ታዲያ እኚህ ሰው ዛሬ የወያኔ የደህንነት ባለሥልጣን ሆኖ ለሀያ አመት በሰራ ሰው አንደበት ያውም በራዲዮ ወያኔ ሲባሉ መስማት አያሳዝንም! በዘረኝነት በሽታ ያልተለከፈን፣ በጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ የማያምንን ዜጋ ሁሉ የሚያበሳጭ ይመስለኛል፡፡ እርሳቸው ወያኔን ሲታገሉ እርሱ የወያኔ ባለሥልጣን ሆኖ ሲገድልና ሲያስር የነበረ ሰው እንዲህ ለመናገር መድፈሩ ለአድማጩ ያለውን ንቀት ነው የሚያሳየው፡፡

3-ሳንጠይቃቸው ራሳቸው እየመጡ መረጃ የሚሠጡን የተቀዋሚ ድርጅት መሪዎች ነበሩ፡፡ይህ አይሆንም ማለት አይቻልም፣ማስረጃ አልቀረበበትምና ነውም ብሎ መቀበል አይቻልም፡፡ ግን አቶ አያሌው ይህን ያሉት ከእውነታቸው ከሆነ የሰዎቹን ስም መግለጽ ለምን ገደዳቸው? መቼም እነዚህ ሰዎች ተቀዋሚ እየተባሉ እንዲኖሮ የሚፈልጉ አይመስለኝም፣ማስረጃ ከሌላቸው ደግሞ አንዲህ አይነት ጉዳይ ወሬ ለማሳመር አይነገርም፣ነበርኩበት ለሚሉት የኃላፊነት ደረጃ አይመጥንም፡፡

4-ከምርጫ 97 በኋላ ምን እንዳርግላችሁ ተብለው አንዳንዶቹ የኢዴፓ አመራሮች ወደ አውሮፓ ለመሄድ ችለዋል፡፡ አቶ አያሌው ይህን ሲናገሩ ልበ ሙሉ ሆነው ነው፡፡ ልበ ሙሉ ያደረጋቸው አሜሪካ መሄዳቸው ሳይሆን ያላቸው መረጃና ማስረጃ ቢሆን አንዴት መልካም ነበር፡፡ እዚህ ላይ ነገር አላበዛም አቶ አያሌው አስቲ አንድ ሰው ይጥቀሱ?

5-ልደቱ የወያኔ የወጣት ፎረም አባል ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ነው፡፡ የትኛው ፎረም? በመቼ አመተ ምህረት?ከእነማን ጋር?

6-የትኛው እስረኛ ነው ቀበሌ ጽ/ቤት ታስሮ ስልክ ቀርቦለት የሚነጋገረው፤ ይህን ያሉት ልደቱን ነው፤ ልደቱ የታሰረባቸው ግዚያትና ቦታዎች በወቅቱ የተዘገቡ እሱም ሲፈታ በቃለ ምልልስ የገለጻቸው በመሆኑ ይታወቃሉ፡፡ ምን አልባት አቶ አያሌው የነገሩን ሚዲያውም ያልገለጸው እሱም ያልተናገረው ርሳቸው በሚያቸው የደረሱበት ከሆነ መቼ ? የትኛው ቀበሌ? በምን ምክንያት ? አንደነበረ እባከዎት በመረጃና ማስረጃ ይንገሩን፡፡

አድማጮች፣ ተመልካቾች አንባቢዎችም ዝም ብለን የሚሰጠንን የምንቀበል አንሁን፡፡ትክክለኛው እውነት ነጥሮ የሚወጣው ውሸቱና እውነቱ ሲፋጭ ነውና፡፡የወያኔን የደህንንት ሰዎች በጠኑም ቢሆን አውቃቸዋለሁ ጉልበት እንጂ እውቀት፣እብሪት እንጂ ክህሎት አላይባቸውም፣የመረጃ ስራ የአእምሮ ስራ አንደመሆኑ በአስተሳሰብ በልጦ መገኘት ቢሆንም በወያኔ ደህንነቶች ዘንድ ያለው ግን ለስልጣን ባበቃቸው ጠመንጃቸው ሁሉንም ነገር ማድረግ የመቻል ደካማነት ነው፡፡አቶ አያሌው ለመረጃና ማስረጃ ዋጋ አለመስጠታቸውና እንደ አፈተታቸው መናገራቸው ሀያ አመት የሳለፉት በዚህ መዋቅርና አሰራር ውስጥ በመሆኑ ተጽእኖው አርፎባቸው ይሆን! የመረጃ ሰው አስቦ የሚናገር ብቻ ሳይሆን እየተናገረም የሚያስብ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.