ጠ/ሚኒስትሩ በኢህአዴግ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች መካከል መጠራጠር እንደነበር በይፋ አመኑ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማሪያም ደሣለኝ ሚያዝያ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በጽሕፈት ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።  በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። በተለይ በዚህ ዓመት በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገዢው ግንባር ፓርቲዎች አመራሮች መካከል መጠነ ሰፊ የመጠራጠር ፖለቲካ መራመዱን በግልጽ አምነው፣ ይፋ አድርገዋል። ስለፓርቲያቸው ጤንነትም ተጠይቀዋል። በብአዴን እና በሕወሓት መካከል ያለው የፖለቲካ አየር ምን ይመስላል ተብሎም ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።  እንዲሁም በጋምቤላ ባለሃብቶች ላይ የተደረገው ጥናት ተአማኒነት ቀርቦላቸው ምላሽ ሰጥተዋል። በናይል ውሃ አጠቃቀም የዑጋንዳ አቋም እንዴት ይመለከቱታል ለሚለውም ጥያቄ ምላሻቸውን አቅርበዋል። የዓረብ ሀገሮች የሕዳሴውን ግድብ ማኩረፊያ እያደረጉት ነው፣ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ተብለው ተጠይቀዋል።  ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡትን ምላሽ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኘው ፋኑኤል ክንፉ በዚህ መልክ አቅርቦታል። መልካም ንባብ። 

 

ሰንደቅ፡- ገዢው ፓርቲ በጥልቅ ተሃድሶው፣ የነበሩ ስጋቶች ተቀልብሰዋል የሚል መግለጫ አውጥቷል። በርግጥ ስጋቶቹ ተቀልብሰዋል? ዳግም የነበሩ ስጋቶች እንደማይመለሱ ገዢው ፓርቲ ምን ማረጋገጫ ይሰጠናል? ብአዴን በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መጽሔቱ፣ አመራሮቼ እና አባሎቼ በቀውሱ ወቅት ህወሓትን ተጠራጥረውት ነበር። እንዲሁም የድርጅቱ መጽሔት አዲስ ራዕይ የፖለቲካ አመራሩ ብዥታ ውስጥና በመጠራጠር ውስጥ እንደነበሩ ያትታል። በምን ፍጥነት ነው፤ እነዚህ በአመራሩ ላይ የነበሩ አደገኛ ጥርጣሬዎች ተወግደው በማይቀለበስ ደረጃ ላይ ናቸው የሚለው ድምዳሜ ላይ የተደረሰው? በርግጥ ገዢው ፓርቲ በአሁን ሰዓት ጤነኛ ነው? በተለይ በብአዴን እና በህወሓት መካከል ያለው ፖለቲካዊ ግንኙነት እንዴት ነው የሚገለጸው?
ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፡- ከጥልቅ ተሃድሶ ጋር የነበሩ ስጋቶች መቀልበሳቸው እርግጥ ነው። መቀልበሳቸውን የምናረጋግጠው በሕዝባችን ላይ ካለን አመለካከት ነው እንጂ፤ ረብሻ ከሚፈጥሩ ጥቂት ኃይሎች ጋር አይደለም። ስለዚህ ማንኛውም ሂደት አስተማማኝ ነው ሊባል የሚችለው በሕዝቡ ውስጥ ካለው ሁኔታ በመረዳት ነው። እኛ በሕዝቡ አቅም እናምናለን። በሕዝቡ ሃያልነት እናምናለን። በሕዝቡ ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህ ነገር እንዳይደገም ሊያደርግ የሚችል ሁኔታ መፈጠሩን ስለምናምን ነው። ሕዝባዊ መንግስት እንደመሆናችን መጠን፣ መነሻችንም መድረሻችንም ሕዝብ ነው። የግምገማችን መነሻም እሱ ነው እንጂ፤ ከላይ የተለያዩ ጽሁፎችን የሚያሰራጩ አካላትን መነሻ አድርገን አንገመግምም። ስለዚህ ይሄ በማይቀለበስ ደረጃ ሄዷል፣ መቀጠል አለብን የሚል ነው።
በርግጥ በዚህም ግምገማችን ላይ ያስቀመጥነው፣ የማይቀለበስ ደረጃ ላይ ይደርስ ከሆነ ያገኘነውንን እድል ወይም ተስፋ አጠናክረን መቀጠል አለብን ብለን አስቀምጠናል። እኛ ካበላሸነው ሊበላሽ ይችላል። እንዳይበላሽ የሚያደርግ ግን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቂያችን ርግጥም ጥልቀት ያለው እንዲሆን ማድረግ የሚገባን ይሆናል ማለት ነው። በሕዝባችን እንተማመናለን፣ ስለዚህም ነው በግምገማችን ወቅት በምክር ቤቱ ስብሰባችን መጨረሻ ያስቀመጥነውም ይህንኑ ነው። ሁኔታው ግን የሚወሰነው ባስቀመጥነው የጥልቅ ተሃድሶ አቅጣጫ አጠናክረን ስንቀጥል ነው በሚል በግምገማም አስቀምጠናል። መተግበር ሲቻል ነው።
በብአዴን የፖለቲካ ጽሁፎች ውስጥ አመራሮች እርስ በእርስ እንጠራጠር ነበር የሚለው፤ ይህ ገሃድ ነው። በብሔራዊ ድርጅቶች መካከል የነበረው የአመራሮች ግንኙነት በሚፈለገው ጓዳዊ ጥንካሬ ላይ አልነበረም። የተለያዩ ጥርጣሬዎች ያሉበት መሆኑን ገምግመን ሂስ ግለሂስም አድርገን እያንዳንዱ ሰው ራሱን ሂስ አድርጓል። ስለዚህ ይህ ራሳችን በደንብ ያየንበት ጉዳይ ነው። እናም መጻፉም ትክክል ነው፤ ግምገማውም ትክክል ነው። አሁንም መጠራጠሩ ቀጥሏል የሚል ሰው ካለ፤ ምንአልባት በመረጃ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ጥሩ ነው። በቀጣይነትም እንገመግማለን። በእኛ እምነት ግን፣ ኢሕአዴግ ም/ቤት ውስጥ ባደረግነው ግምገማ በድርጅቶቹም በአመራሮቹም መካከል ያለው ግንኙነት በእጅጉ ተሻሽሏል። አሁን አንዳችን ለአንዳችን በወንድማዊና በጓዳዊ መንፈስ ለመተቻቸት፣ የተሳሳተም ካለ ተሳስተሃል ለማለት አቅጣጫ እንዲይዝ፣ ጠንካራ የሰራ ካለ ጥሩ ሰርተሃል ብሎ ለማመስገን በሚያስችል ጥሩ ግንኙነት ተፈጥሯል። አንዳችን ለአንዳችን መስዋዕት ለመሆን የሚያስችል ግንኙነት ፈጥረናል የሚል እምነት አለን።
ይህ ዛሬ የተፈጠረ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። በትጥቅ ትግሉም ወቅት አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት መጠራጠሮች ይፈጠራሉ። ተፈጥረውም ነበር። ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ነገሮች አይከሰቱም ሳይሆን፣ ሲከሰቱ የምንፈታበት ግልፅ አሰራር አለ። የአሁኑ አስተማማኝ ነው የምንለው፤ ከዚህ በፊት በፈታነው መንገድ አሁንም ግልፅ ውይይት በማድረግ እና በመተማመን የሚፈታው። መተማመን ተፈጥሯል። እነዚህ በጥርጣሬ ላይ የተመሰረቱ፤ አንዳንዴም በእውነት ላይ ያልተመሰረቱ፤ መለስተኛ እውነት ያላቸውም በሆኑ ጊዜ በጥልቀት በመገምገም እና በመተማመን ነገሮችን ያሉት ክፍተቶችን በመዝጋት አብሮ መስራት ይቻላል በሚል ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችን ተጠናክሮ የወጣበት ሁኔታ አለ። የነበሩ ብዥታዎች በአብዛኛው የጠሩበት ሁኔታ ነው ያለው።
ድርጅታችሁ ጤናማ ነው? ተብሎ ለቀረበ ጥያቄ፤ ድርጅታችን እጅግ ጤናማ ነው። ድርጅቱ በባሕሉም እንደዚሁ የቀጠለ ድርጅት ነው። ማንኛውም ነገሮች ባጋጠሙን ጊዜ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ እያቀረብን እየገመገምን ሁኔታውን እየተረዳን በመተማመን ላይ የተመሰረተ ጉዞ የምናካሂድ ድርጅት ነን። በባሕላችን መሰረት ይህንን በማድረጋችን ለጥርጣሬ ሊጋለጥ የሚገባው ጉዳይ አይደለም። በአብዴን እና በሕወሓት መካከል ብቻ አይደለም ጥርጣሬ የተፈጠረው። ይህ ጥርጣሬ፣ በኦሕዴድ እና በሕወሓት መካከል፤ በኦሕዴድ እና በብአዴን፣ በኦሕዴድ እና በደሕዴድን መካከል ነበር። ደረጃቸው ግን ይለያያል። በአመራሮቹ መካከል መጠራጠር ነበር። የነበረውን መጠራጠር በሚገባ የፈታንበት ሁኔታ አለ ተብሎ ሊወሰድ ይገባል።
ንደቅ፡- በጋምቤላ ክልል የተደረገው የግብርና ኢንቨስትመንት ጥናት በእርስዎ አቅጣጫ ሰጪነት መደረጉ ይታወቃል። በክልሉ ልማት ላይ የተሳተፉት ባለሃብቶች በመካከላቸው አጥፊ ባለሃብቶች እንዳሉ ያምናሉ። ከተሰጠው አጠቃላይ 4.2 ቢሊዮን ብድር መካከል 3.1 ቢሊዮን ብር ለውጭ ባለሃብቶች የቀረበ ነው። ቀሪው 1.9 ቢሊዮን ብር ለ194 የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች የቀረበ ነው። ከዚህ ውስጥም 800 ሚሊዮን ብር ለሁለት ባለሃብቶች የተሰጠ ብድር ነው። ቀሪው 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ለ192 የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች የተሰጠ ነው። የተሰጠውን ብድር ለሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ቁጥር ብናካፍለው በአማካኝ የሚሰጠው ክፋይ በራሱ ትርጉም አለው። የዚህን ጥናት ትክክለኛነት ምን ያህል እውነት ነው ብለው ያምናሉ? ባለሃብቶቹም እርስዎን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርጉም እንዳልተሳካላቸው ይገልፃሉ።
ዝግጅት ክፍላችን የተደረገውን የጥናት ሰነድ ተመልክታል። እንዲሁም በካፒታል ሆቴል በልማት ባንክ እና በባለሃብቶቹ የምክክር መድረክ ላይ ተሳታፊ ነበር። በዚህ የምክክር መድረክ ላይ፤ ባለሃብቶቹ እንዲያለሙ ከተሰጣቸው 54ሺ ሔክታር መሬት ውስጥ ከ51ሺ ሔክታር በላይ ማልማታቸውን ለባንኩ ፕሬዝደንት ሲያስረዱ፤ የልማት ባንኩ ፕሬዝደንት በበኩላቸው የተባለው መሬት መልማት፣ አለመልማቱን ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚል ምላሽ አልሰጡም። በዚህ ነጥብ ላይ ግልጽ ምላሽ ቢሰጥበት?
ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፡- እንደተባለውም ሁሉም ባለሃብት ሌባ አይደለም። ሌባ አለ፤ ሌብነት ብቻ ሳይሆን ሥራ ያልሰራ አለ። ጥናቱ የተሰራው ሌብነት ላይ ብቻ አይደለም። መሬት ወስዶ፣ ብድርም ሳይወስድ ሳይሰርቅም መሬት ያላለማ አለ። በርካታ ሔክታር መሬት ወስደው ለአመታት ያላለሙ አሉ። እነዚህ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል ተብሎ የተቀመጠ ነው።
ከዚህ ባሻገር ምርጥ በሆነ ደረጃ ልማት ያለሙ ባለሃብቶች አሉ። አርባ ሁለት ተቋማት መንግስት ካስቀመጠው ግብ በጣም ርቀው ሄደው አልምተዋል። ትልልቅ ተቋሞችም ያላለሙ አሉ። እንደካራቱሪ አይነቶች አላለሙም። ስለዚህም እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው። ትልቅም ይሁን ትንሽ ያላለማ አካል ላይ እርምጃ ይወሰዳል። ሁለተኛው፣ ልማት ውስጥ ገብተው ከእጅ አይሻል ዶማ የሆኑ አሉ። ጥናቱን አይተናል ካላችሁ፣ ዘመናዊ አርሶ አደር እንኳን በሔክታር ሰማንያ ኩንታል ያገኛል። በጋምቤላ አራት ኩንታል ነው እያለሙ ያሉት። ስለዚህ ይህ ልማት ሊባል አይችልም። እንደዚህ ዓይነት ልማት አለማን የሚሉትም፤ (አንተ) ቅድም ስታነሳ ይህንን ያህል ሔክታር ለምቷል ብልሃል። ሔክታር መልማቱ አይደለም፣ የለማው ሔክታር ምን ያህል ፍሬ አውጥቷል ነው። ፍሬ ካላወጣ የለማው ሔክታር ብዛቱ አይደለም፣ ልማት የሚባለው። ስለዚህ እነዚህ በሙሉ ናቸው በጥናቱ የተካተቱት። እነዚህ በሙሉ ገምግመን ትክክለኛ እርምጃ ወስደናል የሚል እምነት አለኝ።
በጥናቱ ውስጥ የተወሰኑ ስህተቶች ይኖራሉ ብዬ የምገምታቸው አሉ። በተለይ መሬት በቅርቡ ወሰድው፣ ጊዜ በአግባቡ ያላገኙ አካላት አሉ። በርግጥ እነሱም ቢሆኑ፣ ማልማት ነበረባቸው። ከሌሎቹ ጋር ሲወዳደሩ ቅርብ ጊዜ መሬት የወሰዱ ነገር ግን ወደ ልማት ለመግባት ትንሽ ጊዜ የሚጠይቃቸው አካላት፣ ከአካባቢ ወጣ ከማለቱ አንፃር ከመሰረተ ልማት ችግር ጋር ተገናዝቦ ጊዜ ሊሰጣቸው የሚገባ አካላት አሉ ብዬ አስባለሁ። ከዛ ውጪ ግን ጥናቱ ትክክለኛ ነው። ውሳኔውም ትክክለኛ ነው።
ሁሉም በሀገር ውስጥ ያለ ባለሃብት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር የለባቸውም። መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ አይደለም። በየደረጃው የመንግስት አካላት አሉ። በእኔ ጽ/ቤት ውስጥ በሚኒስትር የሚመራ የሕዝብ ቅሬታና አቤቱታ የሚያዳምጥ ጽ/ቤት አለ። ሚኒስትሩ አነጋግሯቸዋል። ስለዚህም እኔ ማነጋገር አስፈላጊ አይደለም። ጽ/ቤቱ ውስጥ ሚኒስትሩ ካነጋገረ፣ የእኔ አቋም ወስዶ ነው ያነጋገረው ማለት ነው። የእኔ ተጠሪ ሚኒስትር ስለሆነ። ሁሉም ችግር የገጠመው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያነጋግር ከተባለ፣ ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም ደሣለኝ አቤቱታ ተቀባይ እንጂ ሥራ ሊሰራ አይችልም። ይህ ግልጽ ሊሆን ይገባል። እናም፣ ስህተት አይደለም፤ መንግስት ተቋም ነው። ተቋም በየደረጃው ያወያያል። እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ለሚኒስትሩም መድረስ አልነበረባቸውም። ከታች ማለቅ አለባቸው። አለበለዚያ፣ ሁሉም ነገር ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የሚመጡ ከሆነ፣ ሌሎች ተቋማት ሥራ አይሰሩም ማለት ነው።
ሰንደቅ፡- በዑጋንዳ ጉብኝት ማድረግዎ ይታወሳል። በዚህ ጉብኝት በጋራ ከዑጋንዳው መሪ ሙሴቬኒ ጋር በሰጣችሁት መግለጫ፣ የናይል ውሃን አጠቃቀም በተመለከተ ከግብፅ ጋር ተጨማሪ ውይይት መደረግ እንዳለበት በዑጋንዳ በኩል ተገልጿል። እኛ በዑጋንዳ መሬት ላይ ተገኝተን የናይል ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ የቀረበውን የCFA ሰነድ ፈርመን በፓርላማም አጸድቀናል። ዑጋንዳ ግን እስካሁን አላጸደቀችም። ዑጋንዳ ያላጸደቀችው፤ ኢትዮጵያ እና ዑጋንዳ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ውስጥ በሚያራምዱት የተለያየ የጥቅም ማስጠበቅ የመስመር ልዩነት መነሻ የመጣ ክፍተት ነው ብለው ትንታኔ የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ።
ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግስት አስር ዓመታትን የለፋበትን ፍትሃዊ የናይል ውሃ አጠቃቀም የማስተባበር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተፅዕኖ ከምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ከግብፅ እና ከኤርትራ ወጣ ገባ የሚሉ ግፊያዎችም እየመጡ ነው። ይህንን እንዴት ያዩታል?
ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፡- ሲ.ኤፍ.ኤውን ሶስት ሀገሮች በፓርላማ ወስደን አጸድቀናል። ኬኒያ ወደ ፓርላማ ልካለች። ደቡብ ሱዳንም በካቢኔ አይተውት ወደ ፓርላማ ልከዋል። ከብሩንዲ ጋር ሰሞኑን ባደረግነው ግንኙነት ወደ ፓርላማ እንደሚልኩት ገልጸዋል። ስለዚህ ዑጋንዳ ብታጸድቅም፣ ባታጸድቅም ስድስት ሀገሮች እስካጸደቁ ድረስ ወደ ሥራ ይገባል። ዑጋንዳዎች ይህንን አጥተውት አይደለም።
የተፈለገው ነገር ምንድን ነው፣ ከዚህ በፊት ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ ግብፅ በቀውስ ውስጥ በነበረችበት ጊዜ አንድ የገቡት ቃል ነበር። ታስታውሱ እንደሆነ፤ የግብፅ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት እኛ ጋር መጥተው ነበር። ዑጋንዳ ውስጥ፣ የግብፅ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ በመጣ ጊዜ ፕሬዚደንት ሙሴቬኒ አንድ ቃል በሚዲያ ላይ ገብተዋል። ይኸውም፣ አዲስ የግብጽ መንግስት ተመስርቶ ከተመሰረተው መንግስት ጋር ከተወያየን በኋላ ነው፣ ሲ.ኤፍ.ኤውን ወደ ማፅደቅ የምንገባው ብለው ቃል ገብተዋል። ስለዚህ እያደረጉ ያሉት የገቡትን ቃል ላለመጣስ ከአዲሱ የግብፅ መንግስት ጋራ አንድ የውይይት መድረክ ተካሂዶ በዚያ የውይይት መድረክ ከእኛ ጋር አምነው የሚሰለፉ ከሆነ፣ እናያለን። የማይሰለፉ ከሆነ፣ ዑጋንዳ በቀጥታ ወደ ማፅደቅ ትሄዳለች የሚል ቃል ለመጠበቅ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደሆነ ገልጸውልናል።
ስለዚህ ይህንንም በአውዱ ማየት ጥሩ ነው የሚሆነው። ከዚህ አኳያ ዑጋንዳ ያለው አቋም ምን እንደሆነ ይታወቃል። ከውሃ አጠቃቀም አንፃር ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍልና አጠቃቀም እንዲኖር የዑጋንዳ መንግስትና ሕዝብ የማያወላዳ አቋም ነው ያላቸው። የተለወጠ አቋም የለም ብለው በግልፅ ነግረውናል። ነገር ግን የገቡትን ቃል መተግበር ስላለባቸው ለመጨረሻ ጊዜ ግብፆች በዚህ አቋም መጥተው የሚሰለፍ ከሆነ እንይ፣ የማይሰለፉ ከሆነ በቀጥታ ወደ ማጽደቁ ተግባር እንገባለን ብለዋል። ስለዚህ ውስጥ አዋቂ የዲፕሎማሲ ሁኔታ በማይኖርበት ጊዜ ለተለያዩ ትንተናዎች የመጋለጥ እድሉ ይኖራል። ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ የለኝም። ሁሉም አካል ከተለያየ መነሻዎች በመነሳት ግምገማዋችን ያደርጋል። ሀቁ ግን አሁን የተናገርኩት በመሆኑ በሂደት ዑጋንዳም ቢሆኑ ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ይገባሉ የሚል እምንት ነው ያለን። እምነታችንን በሒደት የምናየው ይሆናል።
ከደቡብ ሱዳን ጋር ካለን ግንኙነት ጋር የሚገናኝ አይደለም። ደቡብ ሱዳን በበኩሉ በካቢኔ አጽድቆ ወደ ፓርላማ ልኳል፤ ሁላችሁም እንደምታውቁት። በዚህ ደረጃ ብንረዳው መልካም ነው።
ሰንደቅ፡- ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ከግብፅ ላይ ሁለት ደሴቶችን ለመውሰድ 17.1 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ለፕሬዝደንት አልሲሲ መንግስት ፈቅዶ ነበር። በንጉሶቹ እና በአልሲሲ መንግስት መካከል የተደረሰውን ስምምነት፣ የግብፅ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አድርጎታል። በዚህ የፍርድ ውሳኔ የተበሳጩት የሳዑዲ ዓረቢያ ነገስታቶች ቅሬታቸውን ለመግለጽ የሕዳሴውን ግድብ መጥተው ነው የጎበኙት።
እንዲሁም በገልፍ ካውንስል ስብሰባ ላይ የኳታሩ ኢሚር ንግግር ሲያደርጉ፣ የግብጽ ፕሬዝደንት አልሲሲ ልዑካቸውን ይዘው ስብሰባውን ረግጠው ወጥተዋል። በዚህ በአልሲሲ ተግባር የተበሳጩት የኳታሩ ኢሚር ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያ ጎብኝተዋል። ጉብኝቶቹን አስመልክተን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ስናቀርብ፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን ውጤት ነው ብለው ያስረዳሉ።
በእኛ በኩል (በሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል)፣ ከግብፅ መንግስት ጋር በአንድም በሌላ መልኩ የሚሻኮቱ የዓረብ ሀገሮች የህዳሴውን ግድብ ማኩረፊያ አድርገውታል። ከምንከተለው ስትራቴጂክ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንፃር፣ ከዚህ መሰል የዓረብ ሀገሮች ኩርፊያ ጠብ የሚልልን ነገር አለ ወይ?
ጠ/ሚ ኃ/ማሪያም፡- የኳታሩ ኢሚር ሀገራችንን ለመጎብኘት ከተወሰነ ሁለት ወር ነው። የገልፍ ሀገሮች ስብሰባ የተካሄደው በቅርቡ። በምን መልኩ ሊገናኝ እንደሚችል አይገባኝም? አንዳንድ ነገሮች በበቂ መረጃዎች ላይ ሳይመሰረቱ የሰሚ ሰሚ፣ ይሆናል በሚል የሚደረጉ ትንተናዎች የተሳሳተ መድምደሚያ ላይ ይወስዱናል። የኳታሩ ኢሚር ጉብኝትን በተመለከተ ደብዳቤ ይዞ የመጣው የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ነው። ደብዳቤውን የሰጠኝ ለእኔ ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የነገሩን ቀን ሁላችሁም ታውቃላችሁ።
ስለዚህ እንደዚህ አይነት የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ መድረስ የለብንም። ሀገሮቹ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችላል። እኛ በእነሱ በኩል ሆነን ልንገመግምላቸው አንችልም። የሆኖ ሆኖ ከግብፅ ጋር ስለተጣሉ ወደ ሀገራችን መጥተዋል የተባለው የተሳሳተ ነው። ለሀገራችንም የምንሰጠው ክብር በዚያው ልክ የወደቀ ይሆናል። እነዚህ የገልፉ ሀገሮች ሀገራችንን በተደጋጋሚ የሚጎበኙበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያ አሁን በምታደርገው የኢኮኖሚና የአካባቢ ተፅዕኖ እንቅስቃሴ ላይ የአፍሪካ የመግቢያ ቦታችን ናት ብለው ገምግመው ነው የሚመጡት።
ለአጭር ጊዜ ፍላጎት ከግብፅ ጋር ባላቸው ጠብ አይደለም የሚመጡት። ስለዚህም ግንዛቤ መያዝ የሚገባው ሀገራችን በአሁን ሰዓት ተፈላጊ ሆናለች። ተፈላጊ በመሆኗ ወደሀገራችን የሚመጡትን በሙሉ በቁንፅል የምንገመግም ከሆነ፣ ትክክለኛ ድምዳሜ ላይ አያደርሰንም። ሀገራችን በአፍሪካ ቀንድ ላይ ሰላም በማረጋጋት ከፍተኛ ሚና የምትጫወት ሆናለች። አሁን ላይ ደግሞ ለሁለት አመት በጸጥታው ምክር ቤት ተመርጠን የገባን በመሆናችን፣ ሁሉም ይፈልገናል። ስለዚህ ከዚህ ተነስቶ የጎተተው ጉብኝት እንጂ ከግብፅ ጋራ ካላቸው ግንኙነት ምክንያት የመጣ ተደርጎ አይወሰድም።
አንድ ነገር ብነግራችሁ፣ እነዚህ አካላት በሀገራችሁ ልማት ማካሄድ እንፈልጋለን ነገር ግን ከዓባይ ውሃ ጋር የተገናኘ እንዲሆን አንፈልግም ነው፤ ያሉት። ይህንን ያሉ ወገኖች፤ በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ነው ወደ ሀገራችን የመጡት የሚለው ምክንያት የተሳሳተ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ድሮም ጀምሮ፣ ፍትሃዊ የሆነ የናይል ሃብት አጠቃቀም ላይ የተዛባ አመለካካት የላቸውም። የዛሬ ሁለት ዓመት በሳዑዲ ጉብኝት ባደረኩበት ወቅትም መንግሳታቸው የገለጸው ይህንኑ ነው። ከዚህ አቋማቸው በመነሳት ነው ይህንን ተግባር ያከናወኑት። በዚህ መንፈስ መረዳት ጠቃሚ ይሆናል።
በነገራችን ላይ እነዚህ መንግስታት ከሱዳንም ጋር የበለጠ የጠበቀ ወዳጅነት ነው ያላቸው። በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሱዳን ከሳዑዲ፣ ከኤሜሬት እና ከሌሎች የገልፍ ሀገሮች ጋር ያላት ግንኙነት በጣም ጥልቅ ነው። ስለዚህም ሱዳኖች በዚህ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አቋም በሚገባ ያውቃሉ። ግንኙነቱ በአጠቃላይ ግምገማ ላይ የተመሰረተ እንጂ፤ በቁንጽል በአንድ ግድብ መጎብኘት አለመጎብኘት ወይም በአንድ ስብሳባ መኮራረፍ የተደረገ ነው የሚል እምነት የለኝም። ስለዚህም በጥልቀት ማየት ጥሩ ነው የሚሆነው። ይሄ የራሱ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፣ ሊኖረው ይችላል። ከዚህ ባሻገር ግን ጉዳዩ በጥልቀት ማየቱ ጥሩ ነው።

ምንጭ፦- ሰንደቅ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.