ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ (ሙሉቀን ተስፋው)

ባሕር ዳር ኮንሠርት ላይ በፈነዳ ቦንብን ምክንያት በማድረግ በርካታ ወጣቶች ታሠሩ፤

ሚያዚያ 21 ቀን 2009 ዓ.ም፤ በባሕር ዳር የመስቀል አደባባይ በነበረ የዘፈን ኮንሠርት ላይ ምሽት 1፡30 አካባቢ በፈነዳ ቦንብ ዝግጅቱ ተቋርጦ የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊሶች ጥይት ይተኩሱ እንደነበር የመረጃ ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡

የዳሽን ቢራ ስሙን ወደ ባላገሩ መቀየሩን ተከተሎ በባሕር ዳር ከተማ የዘፈን ኮንሠርት በማዘጋጀት ለሕዝብ የማስተዋወቅ የመጀመሪያ ሙከራው ሲሆን ኩኩ ሰብሰቤና አረጋኸኝ ወራሽ ነበሩ፡፡ ወንድሞቻችን እየተገደሉና እየታሰሩ ምንም ዓይነት ዘፈንና ጭፈራ አንፈልግም በሚል የባሕር ዳር ከተማ ሕዝብ ወደ ኮንሠርቱ እንዳልሄደ ነው የነገሩን፡፡ የሥርዓቱ ደጋፊዎች የሆኑ ጥቂት ሰዎች በታደሙበት በዚህ ኮንሠርት ኩኩ ሰብስቤ ‹‹ቻልኩበት›› እያለች በመዝፈን ላይ ሳለች ድንገት ከፍተኛ የቦንብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ በዚህም አደባባዩ ውስጥ የነበሩ ቁጥራቸውና የጉዳት መጠኑ በውል ያልታወቁ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡

ኩኩ ዘፈኗን አቋርጣ መጠጊያ ፍለጋ ለመሸሽ ተገዳለች፡፡ መድረኩ ላይ የነበሩ ሰዎች ሁሉ ዘፈኑን አቋርጠው የሸሹ ሲሆን ከፌደራል ፖሊስና ከመከላከያ ከፍተኛ ተኩስ ተከትሏል ብለውናል መረጃዎቻችን፡፡ አስተያየቱ የሠጡን ሰዎች ‹‹እኛ አገር አጥተን የምን ‹ባላገሩ› የሚል አተላ ሹፈት ነው›› ብለውናል፡፡ ይህን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ሰዐታት ብቻ ከመቶ ያላነሱ ወጣቶች በገፍ ታሥረዋል ብለውናል፡፡ በቀበሌ 15፣ 04፤03፣ 05፣ 06 አካባቢዎች የተገኘ ማንኛውም ሰው እየታሠረ እንደሆነ የመረጃ ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአዲስ ዘመን እስከ አምባጊወርጊስና ትክል ድንጋይ ድረስ ከፍተኛ ውጥረት እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.