የወልቃይት ጠገዴ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግል ነው (አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር)

 የጎንደር ሕብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ምሽት

አክሎግ ቢራራ (ዶ/ር

ክፍል አንድ

መጀመሪያ ይህን የጎንደር ህብረት ለኢትዮጵያ አንድነት ብርእሕህስብሰባ ያዘጋጃችሁትን ወገኖቸን ከልብ አመሰግናለሁ። ለዚህ ስብሰባ መሰረት፤ በህይውታቸው መስዋእት የከፈለቱን ሁሉ በሕሊና ጸሎት ለማስታወስ እንድንነሳ እጠይቃለሁ። አመሰግናለሁ!!  

በዚህ ምሽት እንድናገር የተጠይቅሁት ጎንደሬውንና ሌላውን የአማራ ሕዝብ ስለሰፈሰበው፤ ግዙፉ ችግሮችን ስላስከተለው የወልቃይት ትግል ተብሎ ስለሚጠራው ነው። በእኔ እምነት፤ ይህ ጉዳይና ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው።

መጀመሪያ የአገራችንን ሁኔታ በአጭሩ አቀርባለሁ።

ይህን የአቅም ግንባታ ስራ ስናካሂድ፤ ህወሓቶችና  በጥቅም የተገዙ ግለሰቦች እንድንከፋፈል ጥረት እንደሚያደርጉ እናስታውስ። ህወሓቶች እኛን ለማጥቃት የቻሉት በራሳቸው አቅምና ጥንካሬ አይደለም።

በሶስት መሰረታዊ ክስተቶች ነው።

አንድ፤ እኛን በመከፋፈልና ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም

ሁለት፤ ታሪክን ያለ መረጃ በመፍጠርና

ሶስት፤ የውጭ መንግሥታት አገልጋይ በመሆን።

አባካችሁ፤ ለእነዚህ ከፋፋዮች ቦታ አንስጣቸው!!!

ጀግናዉ የጎንደር ሕዝብ ገና ከመነሻዉ ደፍሮና ቆራጥነት አሳይቶ፤ የአገሩን ሰንደቅ ዓላም ይዞ፤ በማያሻማ ደረጃ ህወሓትንና አጋሮቹን ተቃዉሞ ወደ አደባባይ ሲወጣ “በኦሮሚያ የሚፈሰዉ የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም የእኛም ደም ነዉ!! በቀለ  ገርባ  መሪያችን  ነዉ!!” የሚል ድምጽ አሰምቷል። በተመሳሳይ፤ የኦሮሞ ወጣቶች ይዘዋቸዉ ከተሰለፉት መፈክሮች መካከል በህወሓት ፍላጎት፤ እቅድና የውስጥ ስምምነትና “ፈቃድ፤ እየተቆረሰ ለጎረቤት አገር ሱዳን የተሰጠዉ የጎንደር ወገኖቻችን መሬት የእኛም መሬት ነዉ”፤ “የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ የእኛም ጥያቄ ነዉ”፤ “የጎንደር ወገኖቻችን የፍትህ የነፃነት፣ የማንነትና የድንበር ጥያቄዎች የእኛም ጥያቄዎች ናቸዉ” የሚሉ መልዕክቶችን ያዘሉና የጎንደሬውንና የኦሮሞውን ወንድማማችነትና እህትማማችነት ያጠናከሩ እሴቶች ይገኙበታል። የጎንደሬውና የኦሮሞው ወጣት ትውልድ ባለፉት 26 ዓመታት ህወሓቶች የጫኑበትን የከፈፍለህ ግዛው ስልትና ሰበካ ሰብረውት ወጥተዋል። “በኦሮምያ የሚፈሰው የኦሮሞ ወንድሞቻችን ደም ደማችን ነው” ትክክል ብሂል ነው። “በህወሃቶች ፈቃድ እየተቆረሰ ለሱዳን መንግሥት” እንደ ስጦታ የሚሰጠው መሬት “የእኛም ጥያቄ ነው” የሚለው የኦሮሞ ወጣቶች መልእክት” የኢትዮጵያዊነት መንፈስን የያዘ ነው። ትክክል ነው።

እስኪ እኛ ጎንደሬውንች እኛ አማራዎች “የማንኛውም አማራ ደም ደማችን ነው” ለማለት እንድፈር!! እኛ የራሳችን መንነት ተቀብለን፤ የራሳችን መብት ካላስከበርን ማንም አያስከብርልንም። ስርዓቱ ለጎንደሬ ህይወት ደንታ የለውም። ለኦሮሞ ህይወት ደንታ የለውም።

ባለፈው ዓመት በተከሰተው ሕዝባዊ አመጽ በጎንደርና በባህር ዳር፤ ከሃምሌ እስከ መስከረም 2009 ባለው ጊዜ ውስጥ የሞቱት ወኖቻችን ቁጥር በትክክል ባይታወቅም፤ በአንድ ቀን ብቻ ከመቶ በላይ መስዋእት ሆነዋል። የአስቸኳዩ አዋጅ ከታወጀ ወዲህ የሞተውን፤ የቆሰለውን፤ የታፈነውን፤ የታሰረውን፤ እንዲሰወር የተደረገውን፤ የተሰደደውን የአማራ ሕዝብ ቁጥር ለማወቅ አይቻልም። በብዙ ሽህዎች ይገመታል። ህወሓት ይህን የንጹሃን እልቂት ዋጋ አይሰጠውም። እኛም ቸል ስላልነው የውጭ አገር መንግሥታትና የሰብአዊ መብት ተቋማት ለአማራው ሕዝብ እልቂት ድምጽ ለማሰማት አልፈለጉም። በእኛ ጀርባ እንደ ገና ድርድር ቢደረግብን አይገርመኝም!!

ለምን እንታገላለን? ብለን ከጠየቅን ጉዳዩ የህልውና ጥያቄ ስለሆነ ነው። ዛሬ እንደ ጎንደሬው ለመብቱ፤ ለነጻነቱና ለሃገሩ ቆርጦ የተነሳ ሕዝብ አለ ለማለት አልችልም። መነሻችን የጎንደሬው ሕዝባዊ አመጽ ነው። መድረሻችን ግን ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ማዳን ነው። ጎንደሬውና ሌላው ኢትዮጵያዊ  ሕዝብ ያለ ኢትዮጵያ አገር የለውም። የወልቃይት ጉዳይ ሲባል ማሰብ ያለብን ይኼን የኢትዮጵያዊነት መለያችን ጭምር ነው!! “እኔም ወልቃይቴ ነኝ” ማለት ኩራት እንጅ ሃፍረት ሊሆን አይችልም። የወልቃይቴው እልቅት የመላው አማራ እልቂት ነው። ወልቃይቴዎች “እኛ አማራዎች እንጅ ትግሬዎች አይደለንም” ሲሉ ሕገ መንግሥት ቢኖርና ቢከበር ኖሮ በወልቃይቴው ላይ እልቂት አይደረግም ነበር።

ህወሓቶችን ውሸታሞች ናችሁ ለማለት እንድፈር

በአሁኑ በህወሓቶች የበላይነት በሚገዛው ስርዓት እውነቱንና ውሸቱን ለመለየት አይቻልም። እኛ፤ በተለይ ምሁራንና ልሂቃን እውነቱን ከውሸቱ መለየት አለብን። አራት ምሳሌዎችን እጠቅሳለሁ።

አንድ፤ ለመብታቸው ሲታገሉ የሞቱት ወገኖቻችን በትግራይ ተወላጆች ላይ አንድም ጥይት አልተኮሱም። አንድም የትግራይ ተወላጅ ከቀያችን ይውጣ ብለው ጩኸት አላሰሙም። ጎንደሬው ከትግሬዎች ጋር አልኖርም አላለም!! ማንኛውም ጎንደሬ እንደሚያስታውሰው በጎንደር ከተማ አብዛኛውን ዘመናዊ እኮኖሚ ይዘውት የነበሩት ትግርኛ ተናጋሪዎችና የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ጎንደሬው የሚናገረው ኢትዮጵያ የሁላችንም አገር ናት ነው እንጅ ከትግሬዎች ጋር አብረን አንኖርም አይደለም!! በዋልድባ ገዳም የሚኖሩት፤ እንደ አባ ገብረየሱስ እና ሌሎች 38 አባቶች ከመስቀልና ከምርኩዝ ውጭ ምን መሳሪያ ይዘው ነው ህወሓት ያሰራቸው? እነዚህ አባቶች ለትግራይ ሕዝብ ምን አደጋ ፈጠሩ? ምክንያቱ የዋልድባውን መሬት ለመንጠቅና ወደ ትግራይ ለማጠቅለል ነው።

ህወሓቶች ትግላቸውን ሲያካሂዱ ወደፊት የሚነጥቋቸውን መሬቶች፤ ዋልድባን ጨምሮ በጥናትና በምርምር ገምግምግው እንደ ነበር መረጃዎች አሉ። ለምሳሌ፤ መንፈሳዊ የሚመስሉ ሰላዮችን ወደ ዋልድባ በማስገባት “ማን ምን” እንደሆነ ለማወቅ ችለዋል። በገዳሙ የሚገኙ መዛግብትን ወስደዋል። መሬቱ ለምን ጥቅም ሊውል እንደሚችል አጥንተዋል። ዛሬ የዋልድባን ገዳም መሬት ለማጠቃለል በሚያስችል ሁኔታ ዘመናዊ የእርሻ እቅድ ተልመዋል። ነዋሪ የሆኑ ጎንደሬዎችን ከቀያቸው እንዲባረሩ በማድረግ ላይ ናቸው። የዋልድባ መንፈሳዊ አባቶችን ያሰሩበት ዋና ምክንያት መሬቱን ስለሚፈልጉት ነው።

ሁለት፤ ህወሓቶች በጎንደር/ቤጌምድር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ለጦርነት የተሰበሰበውን የትግራይ ተወላጅ ሁኔታዎች በጠየቁት መሰረት ወደ ሱዳን እንዲሰደድ አመቻችተው ነበር። ከሱዳን ጋር የተፈጠረው ወዳጅነት በዚህ ምክንያት መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም። ከላይ የኦሮሞ ወጣቶች እንዳሉት ህወሓት የሱዳንን ውለታ የከፈሉት የጎንደሬውን መሬት ቆርሰው ለወዳጃቸው ለሱዳን መንግሥት በመስጠት ነው። በተጨማሪ፤ ህወሓቶች ስልጣን ከያዙ በኋላ የተሰደዱትንና ሌሎችን የትግራይ ተወላጆች በወልቃይት፤ በሰቲት ሁመራና በሌሎች ሊነጥቋቸው በወሰኑት መሬቶች አስፍረዋል።  ሰፈራው የተለመደ ስለሆነ ምን ችግር አለበት?

ሰፈራ የተለመደ መሆኑ አያከራክርም። ሆኖም፤ በአብዛኛው ሰፋሪዎች ሲሰፍቱ ራሳቸውን ከነዋሪው ሕዝብ ጋር አቀላቅለው፤ ጉርብትና ፈጥረው፤ ቀስ በቀስ ከሌላው ሕዝብ ጋር ተጋብተውና ተዋልደው ይኖራሉ። ህወሓቶች ያደረጉት ከዚህ የተለየ ነው። የትግራይ ተወላጆችን በትግሬነታቸው የራሳቸው ማንነት ተጠብቆ ልዩ እንክብካቤና እውቅና እንዲኖራቸው ተደርጓል። የትግራይ ተወላጆች የቁጥር ብዛት እንዲኖራቸው ጎንደሬውን ከቀዩ አስወግደውታል፤ እልቂት አካሂደውበታል። ይህ ጣሊያኖች በኢትዮጵያ፤ እንግሊዞች በዝምባብዌና በደቡብ አፍሪካ ወዘተ፤ አሜሪካኖች በአሜሪካ ካደረጉት አይለይም። ውጤቱ ሰፋሪዎቹ የመሬት ባለቤት እንዲሆኑ አመቻችቷል። ህወሓት የፈጠረው የቋንቋና የብሄር ፌደራሊዝም ይህን የመሬት የበላይነት እንደምታ ስኬታማ ለማድረግ ችሏል። የወልቃይት ሕዝብ “እኛ አማራዎች እንጅ ትግሬዎች አይደለንም” ብሏል። የወልቃይቴው የማንነት ጥያቄ አግባብ ያለው፤ ህወሓቶች በማያከብሩት ሕገ መንግሥት የተመዘገበ ነው። ወልቃይቴው ማንነቴ ይከበር ሲል የአማራውን የማንነት ጥያቄም በማንጸባረቅ ነው። የአማራው ብሄር በተከታታይ ማንነቴ ይከበር፤ በማንነቴ “እልቂት አይካሄድብኝ” ሲል ቆይቷል። ሰሚ ግን አላገኘም። ህወሓቶች የወሰኑት “በአማራው መቃብር ላይ” ታላቋን ትግራይን ለመመስረት ነው።

ስለሆነም፤ የወልቃቴው አማራ ሆነ የሌላው የአማራ ሕዝብ ተቃርኖው ከጠባብ ብሄርተኛውና ከጎጠኛው ከህወሓት ጋር ነው። ከሰፊው የትግራይ ሕዝብ ጋር አይደለም። ኢትዮጵያን በበላይነት ከሚቆጣጠረው “ከትግራይ መንግሥት ጋር” እንጅ ኢህአዴግ ተብሎ በጅምላ ከሚጠራውም ስርዓት ጋርም አይደለም። በኢህአዴግ ውስጥ ታፍነው የሚገኙ የህወሕት አባላትና ህወሓት መሰል ግለሰቦችና ቡድኖች ያልሆኑ ሁሉ ራሳቸውን ከህወሓት መንጋጋ ነጻ ማውጣት ይኖርባቸዋል። የትግራይ ሕዝብ የረዢም ጊዜ ጥቅም ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በመሬት ነጠቃ አይደለም። አብሮ በመኖር ብቻ ነው።

ህወሓቶች በየቦታው የሚፈጽሙት ወንጀል ለኢህአደጎችም አደጋዎችን እየፈጠረላቸው ነው። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግሥት የሚባል ነገር የለም። ያለው የህወሓት መንግሥት ቢባል አግባብ ይኖረዋል።

ህወሓቶች ቅማንቶችን እናነተ “ትግሬዎች እንጅ አማራዎች አይደላችሁም” የሚል ውሳኔ ወስኖባቸዋል። የዚህ ቡድን አምባገነናዊነት ለማንነት ጥያቂዎች አግባብ ያለው መፍትሄ ሊፈጥር አይችልም። የፌደራል ስርዓቱ ለዲሞክራሲ ሳይሆን ለመሬት ነጠቃ ዋና መሳሪያ ሆኗል።

ሶስት፤ ህወሓቶች ወጣት ትግሬዎችን ሲያስተምሩ ራስ ዳሸን የትግራይ አካል ነው ብለው ነበር። በአዲስ ዘመን የሚኖሩ ጎንደሬ ወጣቶች ትግርኛ እንዲማሩ ተደርጎ ነበር። ይህ ጎንደርን ለማጠቃለል የታቀደ ሴራ ነበር። አስቡት!! ወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ፤ ለሱዳን የተሰጠው መሬት፤ ዋልድባ፤ ቀስ በቀስ ራስ ዳሸን፤ አዲስ ዘመን ሲወሰዱ፤ ለጎንደሬው ምን ቀረው? ይህን ነው የጎንደሬው አማራ ሕዝብ ጉረሮ ታንቋል የምለው።

አራት፤ ህወሓት የሚቆጣጠረው ኢህአዴግ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ችላለች ይላል። ግን ምግብ ትለምናለች። ለም መሬቷን ለውጭና ለምርጥ የትግራይ ተወላጅ ኢንቬስተሮች አስተላልፋ፤ ነዋሪዎቹን አስወግዳ ህንዶች፤ አረቦች፤ ምርጥ የትግራይ ተወላጆች፤ ከኢትዮጵያ ባንኮች ብድር ያለ መያዣ ተበድረው ያልከሰሩትና አገር ለቀው ያልወጡት ሩዝና ሌላ አምርተው ለውጭ ገበያ እንዲሸጡ አመቻችታለች። ይህ ሊሆን የቻለበት ዋና ምክንያት ዘመናዊው ኢኮኖሚው በሙሉ በህወሓቶች ስለተማረከ ነው።

በስዊዲሾች የተዘጋጀውን “የሞቱ አህዮች ጅብ አይፈሩም፤ Dead Donkeys Fear No Hynas” የተባለውን የመሬት ነጠቃ ፊልም እንድታዩትና ራሳችሁ እንድትፈርዱ እጠይቃለሁ። ይህ ፊልም፣ ኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መንግሥት እንደሌላት ያሳያል። እኔ The Great Land Giveaway በሚል ያሳተምኩትን መጽሃፍ ሙሉ በሙሉ ያንጸባርቃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የመሬቱ ባለቤት አይደለም። ባለቤቱ ህወሓትና የጥቅም ተባባሪዎቹ ናቸው።

ሕግ የሌለባት የህወሓቶች ኢትዮጵያ

የህወሓት ሕገ መንግሥት መጠቂያችን ሆኗል!! የዋልድባ አባቶች መታሰር ከጀርባው መልእክት አለው። ይኼም መልእክት፤ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሕግ አውጭው፤ ሕግ አስተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው እኔ ነኝ የሚል የህወሓት መልእክት ነው። ይህ የሕግ የበላይነት አለመኖር ጉዳቱ ሰፊ ነው። የህወሓትና የአጋሮቹ የማጥቂያና የመሬት የበላይነት መሳሪያ ሆኖ ለ26 ዓመታት አገልግሏል!! ሕግ በማይከበርበት አገር የሚለመደው ውንብድና ነው። የወልቃይት-ጠገዴ፤ የጠለትምት፤ የሰቲት ሁመራ፤ የዋልድባ ነጠቃ ውንብድና ነው!!

በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ማንኛውም ዜጋ ለመብቱ ሲታገል የሚታሰርበት፤ አካለ ስንኩል የሚሆንበት፤ በገዳምም ውስጥ ቢኖር በሌላ ቦታ መሬቱና ቤቱ የሚነጠቅበት፤ እህቱ፤ ሚስቱ፤ እናቱና አክስቱ የሚደፈሩበት፤ ክብሩ የሚነካበት ዋና ምክንያት ኢትዮጵያ ሕግ የሌለባት የጥቂት ወንበዴዎች አገር በመሆኗ ነው። አሜሪካ ለኢትዮጵያ $30 ቢሊየን ለገሰች፤ $30 ቢሊየኑ ተሰረቀ (Forbes). ማን እንደሰረቀው፤ ማን ኃብት እንዳካበተበት ለመገመት ትችላላችሁ። ላረጋግጥላችሁ የምችለው የሰረቀው ጎንደሬው፤ አኟኩ፤ ኦሮሞው፤ ጉራጌው አይደለም። ይህን ያክል ግዙፍ ኃብት የሚሰርቅ ቡድን ዋልድባን፤ ወልቃይትን ወዘተ ቢደፍር አያስደንቅም። የሕግ የበላይነት ቢኖር ዋልድባ አይደፈርም፤ ወልቃይት-ጠገዴ፤ ጠለምት፤ ሰቲት ሁመራ አይነጠቅም።

የሰብአዊ መብቶችን እረገጣ ብንመራመር የኢትዮጵያ ሕዝብ “እግሩና እጁ በህወሓቶችና በአጋሮቻቸው ታስሯል።” ነጣቂ ለመሆን ሕገ-መንግሥቴን “አትንኩብኝ” ማለትን ይጠይቃል። ሕግን የማያከብር ቡድን “ሕገ መንግሥት አለ” የሚለው በመሳሪያ ኃይል ስለሚመካ ብቻ ነው። የአንድ መንግሥት ትርጉሙ ሁሉን በቅንነት፤ ሚዛናዊ በሆነ መስፈርት ማገልገሉ ነው!! ባንኮቹን በሙሉ እየተቆጣጠረ ብዙ ቢሊየን ብር ጠፋና ተሰረቀ ይላል። ሌቦቹ እነማን ናቸው ተብሎ ቢጠየቅ መልስ የለውም። “ከፍተኛ ሌቦች” እየሰረቁ ዝቅተኛ ሌቦችን ያስራሉ። ብዙ ቢሊየን ዶላር ከአገር እያሸሹ አገሪቱ ለማኝ እንድትሆን ያደርጋሉ!!

ባለፈው ዓመት የኦሮሞውና የአማራው ሕዝብ በገፍ አምጾ ለህወሓት/ኢህአዴግ የላከው መልእክት “ከአሁን በኋላ የአንተ ሕገ መንግሥት፤ ስርዓት እጀንና እግሬን ሊያስር አይችልም፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ በባርነት ልኑር ብሎ ቃል አልገባልህም!! ለነጻነቴ፤ ለፍትህ፤ ለሃገሬና ለመብቴ መከበር መስዋእት እሆናለሁ ብየ ተነስቻለሁ” የሚል ነው። ሕዝብ ከባርነት ነጻነትን ሲመርጥ አብረን መቆም ግዴታችን ነው።

ህወሓቶች የሕዝቡን እሮሮ አይሰሙትም። የቅርብ ምሳሌ ላቅርብ። ከአንድ ዓመት ጥናትና ምርምር በኋላ ህወሓት የሚመራው “የሰብአዊ መብት” ተቋም መስዋእት የሆኑትን ወገኖቻችን “ጉዳይ መርምሮ” የደመደመው ከአሳፋሪነት ደረጃ አልፎ ይዘገንናል። ሰላማዊ ሰልፉን የመሩትን ወገኖቻችን  ወንጀለኛ አድርጓቸዋል። ለፍትህ የሞቱት ወንጀለኞች፤ ገዳዮቹ ንጹሆች የሆኑባት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት ለማለት እደፍራለሁ። በምርጫ ዘጠና ሰባትም የሆነው ተመሳሳይ ነው። ህወሓቶች ያቀረቡት ዘገባ ሟቾቹንና ከጀርባ አሉ ተብለው የተከሰሱትንና በእስር ቤት የሚገኙትን መሪዎች ወቅሶ፤ ለሞቱት “ተመጣጣኝ እርምጃ” መውሰድ ማንንም የመንግሥት ባለሥልጣን በሃላፊነት አያስጠይቅም ወደሚል ድምዳሜ ላይ መርቶታል። ይህ ስለወልቃይት ጉዳይ ቁም ነገር አለው።

ከህወሓት/ኢህአዴግ “መንግሥት” ተብየ ቡድን ፍትህ አንጠብቅ። በተለይ የመሬት ነጠቃን በሚመለከት። ይህ ቡድን የብሄር ጥላቻን መርዝ ሰርጭቶ በአንድ በኩል በትግራይ ሕዝብ፤ በሌላው በኩል በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል በመሳሪያ አቅም የተደገፈ የመሬት ነጠቃ፤ የሰብአዊ መብቶች አፈናና ረገጣ፤ የብሄር እልቂት አሁንም በባሰ ሁኔታ አያካሄደ ነው። በምንም መስፈርት ብንመረምረው ይህ ቡድን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን አይወድም። ስልጣን ለመልቀቅ ቀርቶ ለመጋራት አይፈቅድም።

ህወሓት ለትግራይ ተወላጆች ይጮሃል!! ህወሓት የአማራው ሕዝብ ከሚኖርበት በገፍ ሲፈናቀል፤ ቀደም ሲል በጅምላ ሲጨፈጨፍ አንድም ጊዜ ድምጽ አላሰማም። ምክንያቱም፤ ከጀርባ ሆኖ እልቂቱን ያካሄው ራሱ ህወሓት ስለሆነ ነው። ይህን እልቂት በሚመለከት ሙሉቀን ተስፋውና ተክሌ የሻው ያቀረቧቸውን መረጃዎች ማየቱ ይጠቅማል። በወልቃቴው ላይ እልቂት ተካሂዷል (Crimess against humanity). ወልቃይቴው እማራ ነኝ ብሏል። የተካሄደው እልቂት በአማራው ሕዝብ ላይ ነው።

እኔ የወልቃይትን ጉዳይ በተናጠል አላየውም። በአማራው ላይ የተደረገው የጥላቻ ውሳኔ ውጤት ነው። በተጨማሪ፤ የወልቃይትን ጉዳይ ሳስበው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚካሄደውንም ስቃይ፤ ሰቆቃና እልቂት ማገናዘብ እፈልጋለሁ። የተለየ የሚያደርገውም ህወሓት በአማራው ብሄር ላይ ያካሄደውና አሁንም የሚያካሂደው የተቀነባበር የእልቂት ዘመቻ ነው። እልቂት ሰዎችን መግደል ብቻ አይደለም። የተፈጥሮ ኃብታቸውንም ነጥቆ እንዲደየኸዩ፤ እንዲሰደዱ፤ ቀስ በቀስ ቁጥራቸው እንዲቀንስ ማድረግንም ይጨምራል።

የወልቃይት ጉዳይ ቀስቃሽ ነው

ለማስታወስ የምፈልገው፤ የወልቃይት-ጠገዴ ሰብሳቢና ሕዝባዊ ትግል ሌሎችንም የመሬት ነጠቃዎች እንደሚያጠቃልል መሆኑን ነው። የጠለምትን፤ የሰቲት ሁመራን፤ የዋልድባን፤ የራያን፤ የመተክልን፤ ለሱዳን ብፍላጎት የተሰጡትን መሬቾች ሁኔታም ወዘተርፈ ይመለከታል።

የወልቃይት-ጠገዴ ጉዳይ የመላው ጎንደሪዎች፤ የመላው የአማራ ሕዝብ ጉዳይ ነው። የመላው ጎንደሬና የመላው አማራ ሕዝብ ጉዳይ ደግሞ የመላው ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው። የኦሮሞ ወጣቶች የተናገሩትን አንርሳው። ፊት ለፊት የሚዋጋውና መስዋእት የሚሆነው ጎንደሬ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ በዚህ ጥያቄ መስዋእት የሆነው ጎንደሬው ብቻ አይደለም። ለምሳሌ፤ 270 የሚሆኑ የጎጃም አማራዎች በዚህ ጉዳይ ብቻ መስዋእት ሆነዋል። ነገ ጥዋት እንደ ገና የኦሮሞው ወጣት ህወሓቶችን “ጎንደሬዎችን አትጨፍጭፉ” ቢል ህወሓቶች አይምሩትም።

በህወሓቶች የተነጠቁ መሬቶች ጉዳይና ሕዝባዊ ትግል ትላንት የተጀመረ አይደለም። ትግሉ የተጀመረው ገና ህወሓት ተመስርቶ ስልትና ዘዴዎችን ይፋ ካደረገ በኋላ ነው። ቢያንስ ከ1972 ወይንም ከአርባ አመታት በላይ ሲካሄድ የቆየ የሞት-የሽረት ጉዳይ መሆኑ ነው። ህወሓት ይኼን ለብዙ መቶ ዓመታት የታሰበበት ሴራ ሲጠነሥስ ሕዝቡን እየጨፈጨፈ አካባቢው መሪ፤ ተቆርቋሪና ባለቤት የለውም ከሚል ከተሳሳተ ድምዳሜ ተነስቶ ነው። ወጣቱን ትውልድ ከገደልኩ ባለቤት አይኖርም በሚል በተሳሳተ አእምሮ የተጸነሰ መርህ ዙሮ ዙሮ ወደ-ተሳሳተና አጥፊ የፖሊሲ መርህ ይወስዳል። ለትግራይ ተወላጆችም አይበጅም።

የአማራው ሕዝብ ለምን ኢላማ ሆነ?

በአማራው ላይ በተከታታይ የተካሄደውን ጭካኔ ለማጤን ከተፈለገ ትኩረታችን ከሰብሳቢው ከወልቃይት-ጠገዴ የማንነት፤ የመሬት ባለቤትነትና የኢትዮጵያዊ ዜግነት ጥያቄዎች ላይ መሆን ይኖርበታል።

“የወልቃይት ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው።”  የጎንደሬው ብቻ አይደለም። የአማራውም ብቻ አይደለም። ጎንደሬው “የኦሮሞ ደም ደማችን ነው” የሚል መፈክር ይዞ ሲወጣ ኢትዮጵያ የጋራ አገራችን ናት፤ ህወሓት እንደ ባሪያ እንዲገዛን፤ መሬታችን እንዲነጥቀን አንፍቀድለትም ማለቱ ነው። ጎንደሬውና ሌላው የአማራ ሕዝብ ቅድመ አያቶቹ ከመሰረቷት ከእናት አገሩ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፍላጎትና ምኞት የለውም። ስልጣንም የመያዝ ፍልጎት የለውም። ፍላጎቱ ማንነቱን፤ መብቱን፤ ነጻነቱን ማስከበር ብቻ ነው።

ቤቱን ልጠይቅ!! ይህንን ስለ ኦሮሞ ወንድሞቻችን የቀረበ መፈክር ሁላችንም እንጋራለን አይደል!!! የኦሮሞ ወንድሞቻችንስ መልእክት!! ኦሮሞውና አማራው የአገር ምሰሶዎች ናቸው። እነዚህ ሕዝቦች የሌሉባትን  ኢትዮጵያን ለማሰብ አልችልም።

ችግሩን በግልጽ ላቅርበው። የወልቃይት-ጠገዴ ወዘተ ጥያቄ የህልውና ጥያቄ ነው።  የመኖር አለመነኖር ጥያቄ ነው። ልክ ህወሓቶች ለትግራይ ሕዝብ ህልውና የመሬት ነጠቃን ሕጋዊ ለማድረግ እንደሞከሩት ሁሉ፤ መሬቱ የተነጠቀባቸው ዜጎች ይኼን መሬት የማስመለስ ግዴታ አለባቸው። ልክ ህወሓቶች የመሬቱን ባለቤትነት የትግራይ ሕዝብ የጋራ ግብ እንዳደረጉት ሁሉ፤ የአማራውም ሕዝብ ነጠቃውን የጋራ ጥቃት አድርጎ የጋራ ትግል ማካሄድ ይኖርበታል። እኛ ከተባበርን ማንም ኃይል አያሸንፈንም!!

የህወሓቶች የተሳሳተ መርህ የመጀመሪያ ውጤት የአካባቢውን የወልቃይት-ጠገዴን፤ የጠለምትን፤ የሰቲት ሁመራንና የሌሎችን የአማራ ብሄር አባላት ህልውና ማጥፋት፤ የቀረውን ማሰርና እንዲሰደዱ ማስገደድ መሆኑ በመረጃ ይደገፋል። የማይካደው ገጽታ አንድ ነው፦ በአማራው ሕዝብ ላይ እልቂት ተካሂዷል፤ በተለይ በወልቃቴው ላይ።

የለም መሬት ፍላጎቱ ከፍተኛ ስለሆነ፤ ህወሓት ታላቋን ትግራይ የሚመሰርተው በጎንደሬውና በሌላው መቃብር ላይ ነው። አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች በዚህ የትግራይ ታላቅነት ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። ወልቃይትን ጨምሮ የነጠቅነው መሬት ሁሉ የእኛ ነው የሚል እምነት አላቸው። በእኔ ጥናት ግን ይህ “ታሪካዊ መብት” ተብየ በምንም መስፈርት አይደገፍም። ነጠቃው፤ የህወሓት የፖለቲካ ውሳኔ ነው።

ከመሬት ነጠቃው ጀርባ ያለውን ሴራ በአጭሩ ላቅርበው

የችግሩ እምብርት የህወሓት ጸረ-አማራና ጸረ-ኢትዮጵያ አቋም ነው። ይህ አያከራክርም።

የብሄር ጥላቻ መርዝና ካንሰር ነው። ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። የሰላምና የእድገት ጸር ነው። በ1978 ህወሓቶች የመመሪያ ሰነድ አዘጋጅተው “የአማራው ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው” ብለው በዚህ ብሄር እሴቶችና ህልውና ላይ ጦርነት አወጁበት። ጦርነቱ ቀጥሏል! ይህን የኢትዮጵያ ምሰሶ የሆነ ሕዝብ ራሳቸው በጥላቻ ፈርጀው ሌላው ብሄረሰብና ኃይማኖት እንዲጠላውና እንዲመታ ሁኔታዎችን አመቻቹ። አማራው ከቀዩ እንዲባረር የተደረገበት መሰረታዊ ምክንያት ጉረሮውን ለማነቅና እንዲጠፋ ለማመቻቸት ነው። ዛሬ የአማራው ሕዝብ በውሳኔና በአመራር አይሳተፍም። ከእነዚህ ተወግዷል።

በአማራው ብሄር ላይ የተካሄደው እልቂት (Ethnic cleansing and genocide) አንዳለ ሆኖ፤ እኔ የምከራከርባቸው የራሴ ስድስት መስፈርቶች አሉ። እነዚህም፤

  1. ታሪክ አንጻር ሲመረመር የተነጠቁት መሬቶች የትግራይ አካል ሆነው አያውቁም።

ለምሳሌ በኣጼ ዘርዓ ያዕቆብ (14ኛው ክፍለ ዘመን)ወልቃይት ጠገዴና ሌሎች የተነጠቁ መሬቶች በትግራይ ስር አልነበሩም። የጀርመኖች፤ የእንግሊዞች፤ የፖርቹጊሶች፤ የጣሊያኖችና ሌሎች ካርታዎች የሚያሳዩት የተነጠቁት መሬቶች የቤጌምድር/ጎንደር አካል እንደነበሩ ነው። አጼ ዮሃንስ ለእንግሊዝ ንግሥት ቪክቶሪያ በጻፉት ደብዳቤ ወልቃይት የቤጌምድር/ጎንደር እንጅ የትግራይ አካል አለመሆኑን ያሳያል። በትግራይና በቤጌምድር/ጎንደር መካከል የጦፈ ንግድ እንደሚካሄድ ያመለክታል። ጥናቶችና ምርምሮች የሚያሳዩት መረጃ የትግራይና የቤጌምድር/ጎንደር ድንበር ተከዜ መሆኑን ነው። የአጼ ኃይለ ሥላሴና የደርግ መንግሥታት ያስከበሩት የአስተዳደር ካርታ ይኼኑ ድንበር ነው።

  1. ከመሬት ይዞታ አንጻር (Defined Territory) ሲታይ፤ የተነጠቁት መሬቶች በሕግ የሚታወቁበት መጠሪያ አላቸው፤ ጎንደር፤ ወሎ፤ ጎጃም፤ አፋር ይባላሉ። በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ ጎንደሬ፤ ወሎየ፤ ጎጃሜ፤ አፋር ይባላል። ይህን ስል ሌሎች ብሄሮች የሉም ማለቴ አይደለም። ጎንደር የተለያዩ ብሄሮችንና ኃይማኖቶችን የምታስተግድ ክፍለ ሃገር ናት።
  2. ከአስተዳደር አንጻር ሲታይ የሚያሳየው፤ እነዚህ ክፍላተ ሃገራት በትግራይ ተወላጆች የበላይ ባለሥልጣናት አልተገዙም። ለትግራይ አስተዳደር ግብር ከፍለው አያውቁም። የሱዳንን ጠረፍ ያስከበረው ጎንደሬው ነው።
  3. ከሕዝብ ስርጭት አንጻር ሲመረመር፤ የህወሓት ተስፋፊነት የነዋሪውን የብሄር ስርጭት በኃይል ከመቀየሩ በፊት (Before TPLF’s enforced demographic changes in the annexed lands and its 1994 census) ያለው ሁኔታ የሚያሳየው፤ በተነጠቁት አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝብ፤ ከ98 በመቶ በላይ አማራ፤ ሌላው ቅማንት፤ አገው ወዘተርፈ መሆኑን ነው። በእንዚህና በአፋር ክልል የሚኖረው ጎንደሬ፤ ወሎየና ጎጃሜ፤ አፋር እንጅ፤ የትግራይ ብሄር አባል አለመሆኑን ነው።
  4. ከባህል፤ ከስነ ልቦና፤ ከስነ ጥበብ ከሕዝብ ግንኙነት፤ ከጋብቻ፤ ከመከደጋገፍና ከተመሳሳይ እሴቶች አንጻር ሲታይ በጎንደር የሚኖረው ሕዝብ በጎንደሬነቱ እንጅ በትግሬነቱ አያምንም፤ ወልቃይቴው “ጎንደሬ፤ አማራ ነኝ፤ ማንነቴ ይከበር” እያለ በግድ “ትግሬነትን ተቀበል” የሚለው ጭፍን መርህ ህገ-ወጥ ነው።
  5. ከጅኦግራፊ አቀማመጥና ከኢኮኖሚ ትሥስር አንጻር ሲታይ ጎንደሬው በግልጽ የሚታወቅ ድንበር ነበረው፤ ወሎየው፤ ጎጃሜውና አፋሩም ተመሳሳይ ድንበር ነበረው። የኢኮኖሚውና የማህበረሰብ ግንኙነቱም የሚያንጸባርቀው ይህን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ ድንበርና በመሬት ላይ የሚታይ የኑሮ ግንኙነቶች ሁኔታ ነው። ህወሓትና አጋሮቻቸው የፖለቲካ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ተከታታይ የኢትዮጵያ መንግሥታት ይኼን የውስጥ አስተዳደር ድንበር አክብረውት ነበር።

መከራከሪያ ነጥቦቸን ለመደምደም፤ ከታሪክ፤ ከመሬት ይዞታ፤ ከአስተዳደርና ከግብር ክፍያ፤ ከጅኦግራፊ፤ ከሕዝብ ስርጭት፤ ከስነ ልቦና ባህል ወዘተርፈ አንጻሮች ሲታይ ህወሓት የመሳሪያ ኃይልን ተጠቅሞ የፈጠረው አዲስ የመሬት ነጠቃ፤ ተስፋፊነት፤ የሕዝብ ሰፈራና አዲስ ካርታ ህገ-ወጥ ነው። እኛ መቀበል የለብንም።

ክፍል ሁለት ይከተላል

 

 

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.