ትንታ የቀጨው እጮኛ (ትንታ የቀጨው እጮኛ )

በላይነህ አባተ(abatebelai@yahoo.com)

ዶክተር ገዘኻኝ አሜሪካ እሚጠይቀውን መመዘኛ አሟልቶ ሳንፍራንሲስኮ በህክምና የተሰማራ ሐኪም ነው፡፡ ዶክተር ገዘኻኝ ትምህርቱና ሙያው ቢሳካለትም ትዳር መመስረት እንደ ዶክተር መረራ የሊማሊሞን ዳገት መውጣት ሆኖበታል፡፡ ትዳር አለመመስረቱ ያሳሰባቸው ዘመዶቹም በደወለ ቁጥር “ገዙዬ ሙሽራዬን የምንዘፍንልህ መቼ ነው” እያሉ ይጠይቁታል፡፡ በተለይም እናቱ ወይዘሮ ጥሩነሽ “የኔ ልጅ! ጉልበቴ እየደከመ፣ ዓይኔም እየደነገዘ መሆኑን ታውቃለህ! አቅም አጥቼ ታልጋ ሳልውል፣ ብርሃኔንም ሳይነሳኝ አበባህን ልየው” እያሉ ሲያስጨንቁት “የምትሆነኝ ስላጣሁ፤ እህል ውኋ ስላላገጣጠመን” እያለ ይመልሳል፡፡ “የእነ ብላታ ዘርጋውን፣ የነቀኛች ሺበሽን፣ የእነ ፍታራሪ ጫኔን የልጅ ልጆች ብናጭልህ ፊትህን አዞርክብን፡፡ በኛ ምርጫ ታልኼድክ የምትሆንህን ራስህ ፈልግ፡፡ ያገር ልጅ ጥላ ስለማጥል የጦቢያ ልጅ ብትሆን ደሞ ደስ ይለናል! ሳይመሽ አዱኛህን እንይ፤ አንተም ዓይንህን ባይንህ እይ! እኛ በጊዜ በመውለዳችን አደለም እየጦራችሁን ያላችሁት? እባክህ ልጄ እባክህ!” እያሉ ይለምኑታል፡፡

ጓደኞቹም እንደ ዘመዶቹ ዶክተር ገዘኻኝ ሚስት እንዲያገባ ይገፋፉታል፤ ባለማግባቱም ይተርቡታል፡፡ አንድ ጓደኛው “እነ ቄስ ታደሰ ባለትዳሮችን ሳይቀር ከባላቸው እየነጠቁ ሲወስዱ አንተ ሴተላጤዋን እንኳ መጥለፍ አቃተህ፡፡ ሁለት ጥምቀት ጭምት ያላደረገው ፓስተር ተከስተ የሰው ሚስት አማሎ የባህርዳር አገልግል የሚያካክሉ ጡቾችን ተንተርሶ  ሲያድር አንተ የጥጥ ፍሬ እሚያካክሉ ጡቶችም ሳትንተራስ አምሳን ተሻገርክ” እያለ ይቀልድበታል፡፡ ሌላው ጓደኛው ደግሞ “ወይ መንነህ ገዳም አልገባህ  እንዴት እንደ መነኩሴ ቆመህ ትቀራለህ?” እያለ ሲተርበው “በዚህ ዘመን የመነነና ቆሞ የቀረ መነኩሴ ጥቂት ስለሆነ እኔም ቆሜ አልቀርም!” እያለ ይመልስለታል፡፡ የተቀሩት ጓደኞቹም ዶላር ከፍራሽህ ውስጥ እየከከርክ እንዴት ቆንጆ የላይም የግርጌም ትራስ አድርጎ እንደሚተኛው አላሙዲንና ለንቦጩን ለሞዴል አጉርሶ እንደሚያድረው ዳንጎቴ መሆን ያቅትሃል?” እያሉ ይሳለቁበታል፡፡

ቅዳሜ ቀን አስማማው የተባለው ተሳላቂ ጓደኛው መጠጥ ቤት ቢራቸውን ሲገለብጡ “አዲሳባ ሂድና ሞዴሏን አግብተህ ና!” ሲለው” ካዲሳባ እንኳን ሞዴሏን ተራዋን ሴትም ማምጣት ሞላን መሆን ነው” አለው፡፡

“ሞላ ምን ሆነ?” አለ አስማማው ሞላ የሆነውን ለመስማት ሁለት ተጨማሪ ጆሮዎች አብቅሎ፡፡

“ሞላ ካዲሳባ ሚስት በማምጣት በዋሽንግተ ዲሲ የሚታወቅ ሰው ነው”፡፡

“በሚስት ይነግዳል?”

“ሚስት አምጪ ድርጅት አቋቁሞ የበጎ አድራጎት ሥራ ይሰራል፡፡”

“ኢት ዳዝኖት ሜክ ሴንስ! ምን ለማለት ፈልገህ ነው” አለ በንግግር መሐል እንግሊዘኛ መቀላቀል የመማርና የመሰልጠን ምልክት መሆኑን የሚያምነው አስማማው፡፡

“ጓደኞቹ ሞላ ሚስት ካዲሳባ እንዲያመጣ ይመክሩታል፤ ዘመዶቹም ፅገሬዳ የመሳሰሉትን ቆነጃጅት እየመረጡ ይጠብቁታል፡፡ ሞላ ቆነጃጅቶችን ለማስደሰት እየሸቀለ ዶላር በዌስተርን ዩኒየን ይልካል፡፡ ቆነጃጅቱም ዶላራቸውን ከዌስተርን ዩኒዬን ይቀበሉና የብረት መዝጊያ የመሳሰሉትን ጎረምሳዎች ይዘው ላንጋኖ፣ ሶደሬ፣ አዋሳ፤ ባህርዳርና ሌሎችም ሥፍራዎች ይዝናኑበታል፡፡ ይህን ጉድ እማያዬው ሞላም ቪዛቸውን ጨርሶና ያውሮፕላን ትኬታቸውን ገዝቶ ያመጣቸዋል፡፡ የመጡት ሚስቶች ግን ሶስት ወራቸውን ሳይደፉኑ ሌላ ወንድ እንደ ጩልሌ ይጠልፋቸዋል፡፡ እስካሁን ባለው የሞላ ሚስት አምጪ ድርጅት ስታስቲክስ ሞላ አምስት ሚስቶች አምጥቶ አምስቱም ትተውት ሄደዋል፡፡”

“ለስድስተኛዋ ተራ መያዝህን መቼ አወኩ!” አለውና ተሳሳቁ፡፡

ዶክተር ገዘኻኝ እድሜው እየገፋ መሄዱ፣የቤተሰቦቹ ውትወታና የጓደኞቹም ተረብ ሚስት እንዲፈልግ አስገድዶታል፡፡ ሚስት ለመፈለግም ሴቶች ከሚገኙበት ማህበራዊ ግንኙነቶች አዘውትሮ ይሄዳል፡፡ ሐዘንተኛ መስሎ ከማያውቀው ሰው ለቅሶ ይደርስና ነጠላቸውን እየዘቀዘቁ የሚገቡትን ወይዛዝርት ከእግር ጥፍራቸው እስከ ራስ ፀጉራቸው ባይኑ ካሜራ ይልፋቸዋል፡፡ እንደ ተሳላሚ ቤተክርሲትያንም ይሄድና ከጀርባ ተገትሮ አጎንብሰው የሚጸልዩትን ሴቶች መቀመጫ፣ ዳሌና ባት ሲመለከት አርፍዶ ይመለሳል፡፡ ከሰርግ ቤት ይሄድና በጌጥ ነደው በእሳት የተያያዙ ሻማዎች የመሰሉትን ሸቀጥ ሰራሽ ቆነጃጅት ሲያደንቅ ይውላል፡፡ በየዘፈንና የዳንስ ቤቶች እንደ ዝምብ ወተት ጥቡልቅ ይላል፡፡ በየሄደበት ብዙ ሴቶች ሊያገቡት ቢፈልጉም ሊያገቡት እሚፈልጉት ወደውት ሳይሆን ዶክተር ስለሆነና ገንዘብ ስላለው እየመሰለው “ሞኛችሁን ፈልጉ” እያለ ይሸሻቸዋል፡፡

ዶክተር ገዘኻኝ ልቅሶ ቤቱ፣ ቤተከርስትያኑ፣ ዘፈንና ዳንስ ቤቱ ሚስት አላፈራለት ስላሉ የባልና የሚስት ፈላጊዎች መገበያያ ወደ ሆነው የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን አመታዊ የስፖርት ፌስቲቫል መሄድ ጀመረ፡፡ ከዚህ ፌስቲቫል እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም. ዋሽንግተን ዲሲ በሄደበት ወቅት አስማማው በሰው አፈላልጎ ዘወትር አሸናፊ የምትባል ወይዘሪት አስተዋወቀው፡፡ ዶክተር ገዛኻኝ የሚያጩትን ሴቶች ሁሉ አንስቶ አየጣለ አሁን “የሚስት ያለህ” ብሎ እንደሚጮኸው ወይዘሪት ዘወትርም ያጫትን ወንድ ሁሉ ዶማ ራስ፣ አለቅላቂ፣ ቦቅቧቃ፣ ቀጣፊ፣ አጭበርባሪ፣ ሸውራራ፣ ሸፋፋ ወዘተርፈ እያለች እንደ በሰበሰ የገበያ ሽንኩርት አንስታ ስትጥል ኖራ እድሜዋ አርባን ሲሻገር “የባል ያለህ!” ማለት የጀመረች ባል ፈላጊ ሴት ናት፡፡ ወይዘሪት ዘወትር ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በሕግ የተመረቀች፤ አሜሪካ ከመጣች በኋላ ደግሞ በአንትሮፖሎጂ ፒ. ኤች. ዲ. ዋን ሰርታ ዩንቨርሲቲ የምታስተምር ረዳት ፕሮፌሰር ናት፡፡

“ዶክተር ዘወትር የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰር” ብሎ አፈላልጎ ያገኛት ጓደኛው አስማማው ሲያስተዋውቀው ዶክተር ገዘኻኝ “በልቡ ቆንጆ ሴት ፕሮፌሰር ስትሆን ቀርቶ ዩንቨርሲቲ ደጃፍ ስትረግጥ ማየት ብርቅ ነበር፤ ምናልባት እስካሁን ሴልፎን ታሪክ እንዳደረገው ስልክ እንጨት ገትሮ ያቆዬኝ እህል ውኃዬን ከዚች ቆንጆ ጋር እንዲሆን ፈልጎ ነው” ሲል አሰበና “ገዘኻኝ እባላለሁ” ብሎ ራሱን አስተዋወቀ፡፡ “ስምን ከነአባት ማወቅ ደስ ይለኛል” ስትለው “ደስ ይበልሽ የኔ እመቤት ገዘኻኝ ብሩ” እባላለሁ አላት፡፡ “ገዘኻኝ ብሩ! ቆንጆ ስም! ብር እማይገዛው ማን አለ!” ብላ ቀለደችና “ዘወትር አሸናፊ እባላለሁ!” ስትል “ለመሸነፍ ዝግጁ ነኝ!” አላትና ተሳሳቁ፡፡ አስማማው ከጆሮው ጠጋ አለና “የሞላ ሚስት አምጪ ድርጅት በበጀት እጥረት ስለተዘጋ፤ ይቺኑ አጥብቀህ ያዝ” አለና ተሰናብቷቸው ሄደ፡፡ ዶክተር ገዘኻኝ “እዚያ ጋ እስታር ባክስ አይቻለሁ “ሻይ ቡና እንበል?” ሲል የወይዘሪት ዘወትርን ፈቃድ ጠየቀ፡፡ “ኳስ ተጨዋቾቹንስ ማን ይመልከታቸው?” አለች ወይዘሪት ዘወትር የኳስ ፍቅር እንዳላትና ጨዋታ ለማየት እንደሄደች ሁሉ፡፡ “ተጨዋቾቹን የፌደሬሽኑ የቦርድ አባላትና የዋሽንግተን ዲስ ሰማይ ይመለከታቸዋል!” ብሎ ሲቀልድ “ከንፈሮቿን ተጠንቅቃ እንደ ሐር መጋረጃ ሰብስባ የጧት ጮራ የመሰለ ፈገግተዋን” ለገሰችው፡፡ ዶክተር ገዛኻኝ  ጮራ ፈገግታዋ ዓይኑን ሰንጥቆት ሲገባ ከሞቀ ውሀ እንደተጨመረ ጨው ከመቅጽበት ፍርክስክስ አለ፡፡ ወይዘሪት ዘወትርም በልቧ “ተጫዋች ይመስላል፤ ከዳር ያድርስልን!” አለችና እሽ ብላው ስታር ባክስ ሄዱ፡፡

ወይዘሪት ዘወትርና ዶክተር ገዘኻኝ የይርጋ ጨፌ ቡናቸውን ይዘው እንደተቀመጡ ዶክተር መንገሻ ኪሮስ የሚባለው ጓደኛው “ጃዝ! እንዴት ነህ!” አለና ዶክተር ገዘኻኝ ላይ ወደቀበት፡፡ ሰላምታ ተለዋውጠው ዶክተር መንገሻ እንደተለያቸው “ከሜዲካል ስኩል ጀምሮ ጓደኛዬ!” ነው አላት፡፡ “ሜዲካል ዶክተር እንደሆንክ ተነግሮኛል፡፡ የት ተማርክ?” ስትል ጠየቀችው፡፡” ዶክተር ገዘኻኝ በዱክትርናው ተኩራርቶና ትከሻውን ነፍቶ፣ ቡናውን በቄንጥ ፉት አደረገና የቀኝ ተረከዙን ከግራ ጭኑ አሳርፎ ጣቶቹን በምሁር ወግ እያፍተለተለ “የሜዲካል ዲግሪዬን ያገኘሁት ጅማ ጤና ሳይንስ እንስቲቱዩት ነው፡፡ ሰቃይ ተማሪ ስለነበርኩ እዚያው ጅማ ባስተማሪነት ተቀጠርኩ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ አዲስ አባባ ዩንቨርስቲ ሚዲካል ፋኩልቲ ኢንተርናል ሜዲሲን ስማር ደጉ መንግስት ለኤድስ ኮንፈረንስ ልኮኝ እንደወጣሁ ቀረሁ” አለ፡፡ “መኖሪያ ፈቃድህን እንዴት አገኝህ?” ብላ ስትጠይቀው “ፖለቲካል አሳይለም ጠይቄ ነዋ!” ሲል መለሰ፡፡ “ደግ መንግስት የላከው ፖለቲካል አሳይለም ይጠይቃል?” ብላ ያልጠበቀውን ጥያቄ ስትጠይቀው ላብ በላብ ሆነና ለመንበላጠጥ ከጭኑ ያሳረፈውን ቁርጭምጪሚቱን አውርዶ ከመሬት አሳረፈው፡፡ እንደምንም ብሎ በሐፍረት የተበተነውን ቀልቡን ሰብስቦ “አሜሪካ ለመቅረት እማይደረግ አለ! እንደተለመደው መንግስት ቶርቸር አርጎኝ፣ የዚህ ተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሆኘ፤ ግፍ የሚፈጸምበት ዘር ሆኘ እንላለን! አላት፡፡ መጨነቁን አይታ “ይቅርታ አቋረጥኩህ የጀመርከውን ጨርስ” ስትለው ከጭንቀቱ ተላቀቀና “ከመጣሁ አራት ፈተናዎችን በከፍተኛ ውጤት አልፌ ዩንቨርሲቲ ገብቼ በመጀመሪያ ኢንተርናል ሜዲስን ከዚያም በካርዲዎሎጅ እስፔሻላይዝ አድርጌ  አሜሪካ አንቱ ከሚባሉት ካርዲዎሎጂስቶች አንዱ ለመሆን በቅቻለሁ” አለ፡፡ “ጠንካራ ሰው ነህ” ስትለው በጉረኛነት እንዳልፈረጀችው አወቀና ከመሬት አሳርፎት የነበረውን የቀኝ ቁርጭምጪሚቱን አንስቶ እንደገና ከግራ ጪኑ ሲያሳርፍ ሆዱ ተከነቲራው አፈትልኮ ቅጠሉ የረገፈ ዱባ መስሎ አየችው፡፡ “ድንቄም ካርዲዎሎጅስት! የምግብ ጥንቃቄና የስፖርት እንቅስቃሴ እሚያደርግ አይመስልም” አለች በልቧ፡፡

ዶክተር ገዘኻኝ ስለ ትምህርቱና ሥራው ተናግሮ ሲጨርስ ለአርባ አምስት ሰከንዶች ጸጥታ ሰፈነ፡፡ “እኔን እንደ ዛር አስለፍልፈሽ ስላቺ መናገርሽ መቼም አይቀርም” አለና የሰፈነውን ፀጥታ እንደ ጉም ገፈፈው፡፡

“የኔን ታሪክ መስማት ያስከፍላል” ብላ እየተሽኮረመመች ፈገግታዋን እንደበቆሎ እሸት ስትፈለቅቀው ልቡን የሸፈናት ደረቱ እንደ ቡሄ ዳቦ ክፍል አለና “የጠየቅሽውን እከፍላለሁ!” አለ፡፡

“የሰው ልብም ቢሆን”

“የሰው ልብማ ለልብ ሐኪም ቀላል ነው! ነፍስም ቢሆን እከፍላለሁ”

“የሞተ ሰው ልብ አምጥተህ ልታስታቅፈኝ?”

“የራሴን ልብ እሰጣለሁ!”

“ስቀልድብህ ነው! እኔ እንኳን እሚያስከፍል ስሙልኝ ብዬ ለምኘም የሚደመጥ ታሪክ የለኝ፡፡ መቼስ ንገሪኝ ታልክ ከአዲስ አበባ ዩንበርሲቲ በሕግ ተመረኩ፡፡ ከዚያም እዚህ አገር ከመጣሁ በኋላ ኮሎምቢያ ዩንቨርሲቲ አንትሮፖሎጂ አጠናሁና ቦስተን ዩንቨርስቲ በማስተማር ላይ እገኛለሁ”

“አንትሮፖሎጅ የሚባል የሙያ መስክ እንዳለ አውቃለሁ፤ ምን ላይ እንደሚያተኩር ግን እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ አንትሮፖሎጅ ምንድነው?”

“በግሪክ አንትሮፕ ማለት ሰው ማለት ነው፡፡ ሎጅ እንደምታውቀው ጥናት ነው፡፡ እንግዲህ በጥሬ ቃሉ የሰው ወይም የማህበረሰብ ጥናት መሆኑ ነው፡፡ አንትሮፖሎጅ ብዙ ዘርፎች አሉት፤ የህብረተሰብ፣ የአእምሮና ሥነልቡና፣ የባህል፣ የአዝጋሚ ለውጥ፤ የቅሬተ አካልና የሎችንም ጥናቶች ያጠቃልላል አለችው፡፡”

“ውቂያኖስ አቋርጠኝ መጥተሽ ካላጣሽው እንዴት ይህንን ታጠኛለሽ? እልቅ በሕጉ ገፍተሽ ገንዘብ አትሰበስቢም ነበር!”

“ከገንዘብ ፍላጎቴን አስቀደምኳ!”

“ምንድነው ፍላጎትሽ?”

“ፍላጎቴማ የሰውን ባህሪ ማጥናት ነው?”

“የሰው ባህሪ ብዙ አይነት ነው፤ የትኛውን የሰው ባህሪ ማጥናት ፈለግሽ?”

“ለምሳሌ አንዳንዱ ሰው ለሌሎች ሰዎች ወይም ለማህበረሰቡ ብልጽግና፣ ነጻነት፣ ፍትህ ሲል ከመታሰር፣ ከመገረፍ አልፎ እስከ መሞት ሲደርስ ሌላው  በተቃራኒው ለጥቅሙና ለስልጣኑ ሲል ዜጎችን ከማሳርና ከማሰቃየት አልፎ ሕዝብን በመደዳ  ይፈጃል? በእነዚህ  ሁለት ተቃራኒቆች መካከል ያለው ሕዝብ እንዲሁ የተወሰነው ለሆዱ ሲል ገዳዩን ሲደግፍ ሌላው ደግሞ ለፍትህ ሲል ተገዳዩን ይደግፋል? ቺምፓዚ ሳይቀር ለሌሎች ችምፓዚዎች በሚያስብበት ዓለም ከሁሉም ያልሆነው አብዛኛው ሕዝብ ዝምብሎ እንደ አሳማ ሲበላና ሲጸዳዳ ኖሮ ይሞታል! አንትሮፖሎጅን የመረጥኩት ለእኒህና እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ነው?”

“እና መልስ አገኘሽ ”

“እየሞከርኩ ነው?”

“እንደነዚህ ዓይነት የፍልስፍና ጥያቄዎች ውስጥ ምን ዘፈቀሽ”

“ዘፈቀሽ አልክ!” ብላ ፈገግ አለችና “የዘፈቀኝማ ከሕግ ትምህርት እንደ ወጣሁ በሰላዮች እጃቸውን የተቆረጡ፣ ሽባ የሆኑ፣ የተኮላሹ፣ የታወሩ፣ የደነቆሩ ወዘተርፈ ዜጎች ጠበቃና ፕሮፌሰር መስፍን ላቋቋሙት የሰብ…” ብላ ሳትጨርስ ትን ብሎት የደም ሥሩ እንደ ልብስ ማድረቂያ ገመድ ተወጣጠረና ላብ ከብብቱና ካንገቱ ፈሰሰው፡፡ “ውሀ ጠጣ፣ውሀ  ላምጣልህ!” ስትለው አገጩን እንደ ጋሊሊዮ ፔንዱለም እያወዛወዘ የአዎንታ ምልክት አሳያት፡፡ ውሀ እስከምታመጣ ትንታው ቢቆምም በላቡ ምክንያት ጠምቶት ስለነበር ውሀውን ትንፋሽ ሳያሰማ ሰረበቀው፡፡

ዶክተር ገዘኻኝ ውሀውን ሰርብቆ ሲጨርስ “አስደነገጥከኝ እኮ! ስትል “ጉንፋን ይዞኝ ስለነበር ትኩስ ነገር ስጠጣ ያዝ ያደርገኛል” የሚል መላ ሰጠ፡፡ “ባለም የታወቀ የልብ ሐኪም ገደለች እየተባልኩ በቲቪና በፌስ ቡክ ከመታዬት አዋጣኝ” ብላ ስትቀልድ ቀልዱ ብዙም ስላማረው “ይቅርታ ንግግርሽን አቋረጥኩብሽ” ብሎ የውይይቱን አቅጣጫ ወደነበረበት ሊመልሰው ሞከረ፡፡ እርሷ ግን ከትንታው ተጣብቃ ቀረችና “ያሜሪካን ምርጥ የልብ ሐኪም ተምገል ንግግሬ ቢቋረጥ ይሻላል!” አለች፡፡ “ባንቺ ንግግር ከሞትኩ እንኳን ነፍሴ ሥጋዬም መንግሰተ ሰማያት ስለሚገባ ንግግርሽን እንዳታቋርጭ” ሲላት ሰውነቷ እንደ ብረት ግሎ መልሶ ቀዝቀዝ ሲል “ምን ላይ ነበር ያቆምኩት? አዎ ከሕግ ፋኩልቲ እንደተመረኩ በአገዛዙ ግፍ ለተፈፀባቸው ዜጎችና ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በጠበቃነት ስሰራ ታሰርኩ፡፡ ከእስር ቤት ስወጣ የሙያ ፈቃዴን ተነጠኩ፡፡ እንዳጋጣሚ ሁማን ራትይትስ ዋችና ፍሪደም ሐውስ ለስብሰባ ጋብዘውኝ እንደመጣሁ ቀረሁ” አለችው፡፡

በታሪኳ ሲጨነቅ የቆየው ዶክተር ገዘኻኝ ወይዘሪት ዘወትርን ሳያስከፋ በነበራት ሥራ ላይ ያለውን አስተያየቱን እንዴት እንደሚገልጽ ሲያቅማማ ላርባ ሰከንዶች ቆዬና “አሁንም ከነዚህ ሰብአዊ…ምናምን፤ ሁማን ራይትስ ጂኒ ጃንካ ከሚባሉት ጋር ግንኙነት አለሽ?” ብሎ ጠየቃት፡፡ “ሰብአዊ መብትን ምናምንቴ ሁማን ራይትስስ ጂኒጃንካ ብለኸው አረፍክ” ብላ ግንባሯን እንደ እሾህ ከሰከሰችው “ይቅርታ አድርጊልኝና ለፖለቲካ፣ ለብአዊ ቅብጥሶ ቅብጥሶ አለርጂ ነኝ” አላት፡፡ “ለካስ ቅድም ከሞት አፋፍ የደረስከው አለርጅህን እንደ ሲጃራ ከፊትህ አቡንኘብህ ነው!” ስትለው “እማያገባኝን መንግስት ከበደንና ጫላን ገደለ፤ ዘበርጋናና ደሌቦን አሰረ እያልኩ ስጨነቅና ስጠበብ መኖር አልፈልግም፤ ተደስቼ መኖር ነው እምፈልገው” አለ፡፡ ወይዘሪት ዘወትርም “ይህ ሰው መጽሐፍ እየሽመደደ ዶክተር ሆኗል እንጅ ከአሳማዎችና ከቺምፓዚዎች ያነሰ ፍጡር ነው” እያለች በልቧ ስታሰላስል ዝምታ እንደ ጥቅጥቅ መጋርጃ ለያያቸው፡፡

የለያያቸውን የዝምታ መጋረጃ ለመጠቅለል ፈለገችና “ቡና እምታፈላው ኢትዮጵያዊ ደስ አትልም” አለች ከግርግዳ የተለጠፈችውን ቡና የምታፈላ ቆንጆ ኢትዮጵያዊ በጣቷ እየጠቆመች፡፡ “ቺንፓዚ በሚያጠኑ አንትሮፖሎጅስቶች መነጸር ስትታይ ቆንጆ ልትሆን ትችላለች” አለ፡፡ “በልብ ሐኪሞች ስተቴስኮፕ ስትደመጥስ” ብላ ስትመልስ  “በልብ ሐኪሞች ስቴስኮፕ ስትደመጥ ባለም ላይ ቆንጆ አንድ ሴት ብቻ ናት” ብሎ ሳይጨርስ  ወይዘሪት ዘወትር ሐር የመሰለውን ፀጉራን በሁለት እጇ ጠቅልላ አነሳችና መልሳ ወደ ኋላዋ እንደ አንሶላ ስታነጥፈው እንደ ዝቋላ ተራራ ኮራ ካለው ዳሌዋ ከበቀለው ተውረግራጊ ሽንጧ አረፈ፡፡ የዶክተር ገዛኻኝ አይኖችም ፀጉሯን ተከትለው የጀርባዋን ቁልቁለት ወርደው ተውረግራጊ ሽንጧ ከበቀለበትና እንደ ዝቋላ ተራራ ተጀንኖ ከተቀመጠው ዳሌዋ እረፍት አደረጉ፡፡ “ይህን ውበት ይዛ እስኳሁን ያላገባችበት ምስጢር አልገባኝም” እያለ በሰመመን ሲያሰላስል፡፡ “ነገ ቦስተን ስለምመለስ በጊዜ መዘጋጀት አለብኝ” ስትል አባነነቸው ፡፡ “አንድ ሁለት ቀን ቆይና እንጨዋወት እንጅ” አለ፡፡ “ከነገወዲያ ኮንፈረንስ ስላለኝ መሄድ አለብኝ” አለችውና ስልክና ኢ ሜል ተለዋውጠው ተለያዩ፡፡

ከስታር ባክስ እንደተመለሱ ከአዲስ አባባ የሕግ ፋኩልቲ አብራት የተመረቀችውና በኳስ ጨዋታው ወቅት አብራት ያረፈችው የወይዘሪት ዘወትር ጓደኛ “ሀው ወዝ ዩር ዴት አለቻት?” “ዴት አልሽው እንዲሁ መተዋወቅ ነው” አለች ወይዘሪት ዘወትር፡፡

“ከመተዋወቅ አይደል ሁሉ ነገር እሚጀምረው፡፡ ስታር ባክስ ስትሄዱ እንዳየሁት አፍንጫው ጉምድ ቢልም ወንዳ ወንድ ይመስላል” አለች ጓደኛዋ ወይዘሪት ዘወትርን በስርቆት እየተመለከተች፡፡

“እግሩ ሽፍፍ ያለ፤ ጸጉሩ ጎመን የተደፋበት አይብ የመሰለ፤ ሆዱም እንደ ቢራ ገልባጪ አበሻ የተዘረገፈ ነው” አለች፡፡ ከንፈሯን አሸራማ!

“የምትይው ሁሉ ይስተካከላል! ሆዱ በምግብና በስፖርት ይጠፋል፤ ፀጉሩም ጎመን የተደፋበት የመሰለው አቀባቡን ስላላወቀበት ሊሆን ስለሚችል ቀቢ ቀጥረን እናሰለጥነዋለን፡፡ ገንዘብ ስለማያጣ እግሩም በፕላስቲክ ሰርጀሪ ይስተካከላል” አለቻት ጓደኛዋ

“ስቀልድብሽ ነው እባክሽ! ውጫዊ መልክ ግድ አይሰጠኝም!” አለች፡፡

“ታዲያ ውስጣዊ መልኩ ነው ችግርሽ? ውስጡ ምን ሆነ?”

“ገና በደንብ ባለውቀውም ትንታ እንዳለበት ተረድቻለሁ”

“ትን እማይለው አለ? አንቺንም ብዙ ቀን ትን ብሎሽ ያውቃል! ህ…ካብሮ አደግህ ጋር አትሰደድ አለ”

“ማህሌትዬ! የሱ ትንታ የተለዬ ነው! ስላላየሽው ነው”

“እንደ ዛር ኸው..ኸውኸው..እያሰኘ ያስጎራዋል ወይስ እንደ ጅብ አውው…እያሰኘ ያስጮኸዋል?” በምንድነው የሱ ትንታ እሚለየው?

“በመንስኤው?”

“መንስኤውን ደሞ እንዴት አወቅሽ? ከሐኪም ጋር ስለዋልሽ ሐኪም የሆንሽ መሰለኝ? መንስኤውን ታወቅሽ ምንድነው?”

“አለርጂ አለበት?”

“ሶስት ቢሊዮን ያለም ሕዝብ አለርጂ አለበት! ምን ይጠበስ!”

“የሱ አለርጂ የተለየ ነው”

“ይቺ ናት ማህሌት ለማ! ለምን የሱ አለርጂ ልዩ ሆነ? የመድሃኒት፣ የሽቶ፣ የጠጀሳር፣ የፖለን …አይደለም?”

“የሱ አለርጂ ለሰሚው ግራ ነው!”

“ለሰሚው ገራ? አለርጅው እሚነሳው ከሴት ጋር ሲሆን ነው? የማይወገድ ነገር ነው?”

“አዎ መወገድ እማይችል አለርጂ?

“ምን ነገር እንደ መጫኛ ማስረዘም ነው? የምን አለርጅ?”

“የሰብአዊነት አለርጅ?”

“ዋት? አንቺ ልጅ ባንድ ቀን ፍቅር አበድሽ እንዴ?”

“ሙች ማህሌትዬ ! አሸናፊ ይሙት እልሻለሁ! የሥራየን ታሪክ ጠይቆኝ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንደሰራሁ ልነገረው ሰብአ…እንዳልኩ የትንታ ጣረሞት ወደ ገደል ይዞት ጭልጥ ሲል እግዚአብሔርና የኩባያ ውሀ ናቸው ከሞት አፋፍ የመለሱት”

“ሰብአዊ መብት የሚለው ቃል የትንታው መንስኤ መሆኑን በምን አረጋገጥሽ! ምራቅም ትንታ ያመጣል!”

“ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው ትል ነበር አያቴ! እርሱ ራሱ ለሰብአዊ መብት አለርጂ ነኝ ብሎ አስጠንቅቆኝ”

“ሰብአዊ መብት እርሱ ነፍስ ውስጥ የለችም? ወይ እርሱ ሰው አይደለም?”

“የሚገርመው እርሱ አደል”

“የምትይውን ማመን ያቅተኛል! ነገር ግን የሰብአዊነት አለርጅም መወገድ ይችላል፡፡ ለማስወገድም እያዋዛሽ በመጀመሪያውው ቀን “ሰ”ን በሁለተኛው ቀን “‘ብ’ን በሶስተኛው ቀን “አ”ን በአራተናው ቀን “ዊ”ን እንደ መሰረተ ትምህት ተማሪ ፊደል ስታስቆጥሪ ስንብተሽ በ”አምስተኛው ቀን “ባንድነት” ስትይው ሳያስበው “ሰብአዊ” ብሎ ያርፈዋል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ እያዋዛሽ አለማምደሽውም ትን ሊለው ስለሚችል  እግዚአብሔርንና የኩባያ ወሀን ከጎንሽ አታርቂ ስትላት” ሁለቱም ፈርፈር ብለው ሳቁ፡፡

ዶክተር ገዘኻኝ ወደ ከኳስ ሜዳው እንደተመለሰ

“በዚያው ቦስተን የሄድክ መስሎኝ ነበር!” አለው አስማማው፡፡

“ያፍህን ቢያደርግልኝ ደስ ይለኝ ነበር”

“እንደባቄላ ንፍሮ ባንዴ ሙክክ አድረገችህ እንዴ!”

“እንኳን በአምሳ በአስራ ስምንት ዓመቴም ባንዴ እጄን አልሰጠሁ” አለ ራሱን ሲያኩራራ ከንፈሩ ከአገጩ እስቲንዘላዘል እንዳልወደዳት ሁሉ

“ስለ ባህሪዋና ታሪኳ እማውቀው የለኝም፡፡ በውጪ ስትታይ ግን ቆንጆ ናት፤ በዚያ ላይ የተማረች ናት፡፡” ሲል አስማማው አስተያዬት ሰጠ

“ለኔ አስበህ ይህንን ሁሉ በማድረግህ አመስግናለሁ”

“ምንም አይደለም! ጓደኛ ለመቼ ነው! በርታ እንግዲህ! ፈረስ ያደርሳል እንጅ አይዋጋም”” አለውና ወደ ሆቴላቸው ሄዱ፡፡

ዶክተር ገዛኻኝ ገና ልማታዊ ገበሬዎች፣ ልማታዊ ተማሪዎች፣ ልማታዊ ጠበቆች፣ ልማታዊ ሐኪሞች፣ ልማታዊ አስተማሪዎች፣ ልማታዊ ነጋዴዎች፣ ልማታዊ ሚስቶች፣ ልማታዊ ባሎች፣ ልማታዊ ዲያስፖሮች፣ ልማታዊ አቡኖች፣ ልማታዊ ጳጳሶች፣ ልማታዊ መነኩሴዎች፣ ልማታዊ ቄሶች፣ ልማታዊ ገብሬሎች፣ ልማታዊ ማርያሞች፣ ልማታዊ በሬዎች፤ ልማታዊ አይጦችና ልማታዊ ጉንዳኖች ሳይፈጠሩ በልማታዊ ሐኪምነት ተሰማርቶ ከብሯል፡፡ ዶክተር ገዘኻኝ ገና ተሐድሶ እንደ ዝንብ ከነቆሻሻው ቤተክርስቲያን ሳይገባ ህዳሴም እንደ ተቅማጥ ተስረግርጎ ዓባይ ውስጥ ሳይገባ፤ ሰይጣንም ህዳሴና ልማት እያለ መስበክ ሳይጀምር፤ ህዳሴአዊ ወይም ልማታዊ መባል ሰይጣናዊ እንደመባል ከመቆጠሩ በፊት ልማታዊ ሐኪም ነበር፡፡

ልማታዊው ሐኪም ዶክተር ገዘኻኝ ከልማት ካድሬ ጓደኛው ዶክተር መንገሻ ኪሮስ ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ የመድኃኒት ፋብሪካ ከፍቷል፡፡ ከባለስልጣኖች ጋር በትላልቅ ከተማዎች መድሀኒት ቤቶችና ሆቴሎች ከፍቷል፡፡ ለዶክተር ገዘኻኝ ይህ እድል እንደ መስኮት የተከፈተለት ባለስልጣናት ያዘዙትን ሁሉ ስለሚፈጽም ነው፡፡ ዶክተር ገዘኻኝ ለፖለቲከኛ እስረኞች ሐኪም አድርገው ልከው የእስረኞችን በሽታ ዘርዝሮ እንዲያቀርብ የቃል ትእዛዝ ሲሰጡት የሒፖክራትስን ቃለ መሐላ ቦጫጭቆ ዘርዝሮ ያቀርባል፡፡ በዶክተር ገዘኻኝ ሪፖርት መሰረት ሊሞቱ አንድ አሙስ የቀራቸው ወህኒ ቤት ሞቱ እንዳይባሉ እንደ ፕሮፌሰር አስራት ይፈታሉ፡፡ ዶክተር ገዘኻን ፕሮፌሰር መስፍንን በታሰሩበት ወቅት ቶሎ የሚገል በሽታ የለባቸውም የሚል ሪፖርት በማቅረቡ ባለስልጣኖች ተበሳጭተው “ይኸ በጥባጭ ሽማግሌ ሲጃራውን ሲያጨስ ኖር እንዴት ቶሎ አይሞትም ብለህ ትጽፋለህ?” ተብሎ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶትም ነበር፡፡

ዶ/ር ገዘኻኝ የእስረኞችን በሽታ ዓይነትና ጥንካሬ ለባለስልጣኖች ከማስተላለፉም በተጨማሪ በጥይትና በግርፋት የሞቱትን ዜጎች በድንገተኛ በሽታ ወይም በአደጋ ሞቱ እያለ ከሞት ሰርቲፊኬታው በመጻፍ ተሳትፏል፤ መረጃ ለመሰብሰብ እስረኞችን ማደንዘዣ መድኃኒት የሚወጉትን ሰላዮችም አማክሯል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዶክተር ገዘኻኝ ትሁት፣ እታይ እታይ የማይልና ከሰው ተግባቢ ሰው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ዶክተር ገዘኻኝ በእንደነዚህ ዓይነት የገዥዎች አረመኔአዊ ድርጊት ይሳተፋል ተብሎ እሚጠረጠር አልነበረም፡፡ በዚህ ተሳትፎው ንብረት ማግበስበሱንም አብሯቸውን ወንጀል ከሚሰራው ባለስልጣኖች በቀር እንኳን ሌላው ቤተሰቦቹም አያውቁም፡፡ በቤተሰቦቹ ጎረቢቶችም እሚያውቀው ዶክተር ገዘኻኝ አሜሪካን አገር ካሉት የልብ ሐኪሞች ሁሉ የላቀ በመሆኑ ገንዘብ ሻንጣው እንደቻለ የሚያፍስ መሆኑን ነው፡፡ ዶክተር ገዘኻኝ ምንም እንኳ ሚስጢሩን ብዙ ሕዝብ እንዳላወቀበት ቢረዳም ንጹሕ እንቅልፍ ተኝቶ ያደረበት ጊዜ የለም፡፡ ከአረመኔ ገዥዎች ተባብሮ የሰራው ግፍ እንደ እሳት ያቃጥለዋል፡፡ የእነ ፕሮፌሰር መስፍን ስምና ሰብአዊ መብት የሚሉት ቃሎች ሲነሱ የተመለከተው የሕዝብ ሰቆቃ ይታሰበውና ጉረሮው ጥርቅም ይላል፡፡

በዚህ ጉረሮ በሚያንቅ በሽታ በመሰቃየት ላይ ሳለ ነበር ዶክተር ገዘኻኝ ወይዘሪት ዘወትርን የተዋወቃት፡፡ ወይዘሪት ዘወትርን ገና ሲያያት ቢወዳትም የሰብአዊ መብት ጠበቃነቷና ከእነ ፕሮፌሰር መስፍን ጋር ያላት ግንኙነት የራስ ምታት ሆኖበታል፡፡ “ይህችን የመሰለች ልጅ ተዝናንታ፣ ጨፍራና ተደስታ በመኖር ፋንታ ሰብአዊ መብት፣ ፍትህ፣ ነጻነት እያሉ መቃጠል ውስጥ ምን ከተታት? ምናለ ፍቅሯ ዘፈን ቤት ከመሄድ፤ ልብስና ጌጣጌጥ መግዛት ቢሆን? የሰውን ወንጀል ምርመራ ውስጥ ምን ከተታት? እንኳንም እኔ የፈረምኩበት የሕክምና ወረቀት ሁሉ ተቃጥሏል፡፡ የኔን ታሪክ ማን ይነግራታል? ቢነግሯትም ግጥም አድርጌ እክዳለሁ፤ ደሞስ በምን ታረጋግጠዋለች? ከተጋባንና ልጅ ተወለድን ብታውቅ ደግሞ ለልጆቿ ስትል ዋጥ ታረገዋለች፤ እንዲያውም ለኔ ጠበቃ ልትሆን ትችላለች” ሲል አስቦ ፈገግ አለና ወዲያው ደሞ “የለም! የለም! ይህቺ ሴት ቆቅ ናት! ከመጋባታችን በፊት ፈልፍላ ልታገኝብኝ ስለምትችል ትቅር፣ ጥንቅር ትበል! ደሞ እገሌ ታስሮ፣ ይኸ ሕዝብ ተጨፍጭፎ ባለች ቁጥር ማን ትን ሲለውና ጉረሮውን ሲታነቅ ይኖራል! ጎመን በጤና ! ትቅር!” አለና ከሶፋው ጋደም አለ፡፡

የእንቅልፍ ሰመመን እንደጀመረውም ወይዘሪት ዘወትርን ከልቡ እሚያወጣለት እንከን ለመፈለግ ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ጠጉሯ በሐሳብ ቃኛት፡፡ “ያ! ያ! አፍንጫዋ የኬንያን ዝሆን ኩምቢ ያህላል፡፡ የዝሆን ኩምቢ እየወጋኝ እንዴት እተኛለሁ?” አለና ራሱን ጠየቀ፡፡ ቀጥሎ ደሞ “ኩምቢ አፍንጫዋ ስትጠጣ ብርጭቆ ውስጥ ቀድሞ ገብቶ አፏን ውሀ እንዳይጠጣ ሲከለክለው አየው፡፡ ከዚያም ጉንፋን ይዟት ከኩንቢ አፍንጫዋ ንፍጥ እየተዝረበረበ ከምትጠጣው የብርቱካን ጭማቂ ሲገባና የተረፋትን እንዲቀምሰው ስትሰጠው ታየውና “ኢው..! ሰውን ሲወዱ ከነንፍጡ እሚለው እኔ ላይ አይሰራም” ብሎ ባነነ፡፡ ተመልሶ ተኛና ሲነጋ ተነስቶ ወደ ስራው ሄደ፡፡

ምሽት ከሥራ ተመልሶ ለወይዘሪት ዘወትር ልደውል ወይስ ልትው እያለ እንደመሰንበቻው ፈራ ተባ ሲል ዶክተር መንገሻ ኪሮስ ደወለ፡፡

“ሃይ ጃዝ” አለ ዶክተር መንገሻ

“እንዴት ነህ መንግሽ” አለ ዶክተር ገዛኻኝ

“ሚስትህ እንዴት ናት”

“የምን ሚስት አመጣህ ደሞ!”

“ዘወትር አሸናፊ!”

“መቼ ተጋባን፤ ደሞ ያባቷን ስም እንዴት አወክ?”

“እሷ አታውቀኝም እንጅ እኔ አውቃታለሁ!”

“የት ነው እምታውቃት”

“ስትበጠብጥ!”

“ስትበጠብጥ? ማንነው የምትበጠብጠው?”

“ኢትዮጵያን”

“ምን ብላ”

“ውሸቷን መንግስት  ሰው ገሏል፤ አስሯል …እያለች ለገንዘብ ሰብሳቢ ድርጅቶች ሪፖርት ያደረገች” የኢትዮጵያ ገጽታ ታጠፋለች”

“ለየትዮቹ ገንዘብ ሰብሳቢ ድርጅቶች?”

“ሁማን ራይትስ ዋች …. አምነስቲ… ጂኒ ጃንካ ለሚባሉት ነዋ”

“እሷ ሪፖርት ማድረጓን እንዴት አወክ?”

“ያልሆነ ነገር ነግሬህ አውቃለሁ? ደሞ መጠራጠር ጀመርክ ቡኣ!” አለ በቁጣ

ዶክተር ገዛኻኝም በልቡ “ይኸ እንደ ይድረስ-ይድረስ ሽሮ ግንፍል- ግንፍል የመድሐኒት ፋብሪካውንና የሆስፒታል ‘ሸሬን’ ለመንጠቅ ” ሲል ሰጋና ጊዜ እስቲያልፍ ያባትህ ባሪያ ይግዛህ በሚል ብሒል “እሱስ እውነትህን ነው ስሟን ከናባቷ መንገርህ ብታውቃት አይደል?” አለና ቁጣውን አበረደው፡፡

ዶክተር መንገሻም አለቃነቱን አረጋግጦ ቁጣው ከምድጃ እንደወጣ ጀበና እንፋሎት ወረድ ሲልለት “ጃዝ በጥባጭ መሆኗንማ በደንብ ስለማውቅ አትጠራጠር!” አለ

“ችግር ነው! እንከን የሌለባት ሴት ጠፋች!” አለ ዶክተር ገዝኻኝ፡፡

“ሙንም ቹግር የለውም፡፡ እንዲያውም ካንተ ጋር ስያት ደስ ነው ያለኝ፡፡”

“በጥባጭ ከሆነች ለምንድነው ደስ እሚልህ?”

“ሙክንያቱም አንድ ወፍ ሁለት ድንጋይ ትገላላህ” አለ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ትገላለህ ለማለት ፈልጎ፡፡

“ጥይቱ ምንድን ነው? ወፎችስ?”

“ጡይቱ አንተ፤ አንደኛው ወፍ ሚስት መሆኗ ሁለተኛው ወፍ ደሞ ቦጥባጭነቷን መቆሙ”

“ገባኝ! ገባኝ! አስብበታለሁ” ሲል ዶክተር ገዛኻኝ”

“ሞቶ በሞቶ ማድረግ ትችላለህ! ገንዘብ ስታይ ሴት እንኳን አንተን ሸበላውን ቆማጣውንም ታቅፋለች”

“የሚቻለው ሁሉ ይደረጋል!”

“ይህን ግብር ስትፎጽም የሁለት ቶኩል ሚሎን ፖርጀክት ተሰርቶ ስጦታ ይሰጥሃል፡፡ “ፕሮጀክቱ ሰርፕራይዝ ስለሆነ አሁን አልነግርህም” አለና ዶክተር መንገሻ ወይዘሪት ዘወትርን የመጥልፉን ሥራ ከዶክተር ገዝኻኝ  ሰጥቶ ስልኩን ዘጋው፡፡

ምንም እንኳ ዶክተር ገዘኻኝ ብዙ ንብረት ያካበተ ቢሆንም ስስት ያለበት በቃኝን ስለማያውቅ “ቆንጆ ሚስትና ሁለት ተኩል ሚሊዮን ሚሊዮን ብር  ህ!…” ብሎ በደስታ አልጋው ላይ ተንከባለለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ለገንዘብ ሲል ሲሰራው የኖረው ሐጥያት ሁሉ ታወሰውና አእምሮው ከፀሐይ እንደተሰጣ ሌጦ ተጨማደደ፡፡ የተጨማደደውን አእምሮውን ለማፍታታት ስታር ባክስ በነበሩበት ጊዜ በእጅ ስልኩ  ያነሳው የወይዘሪት ዘወትርን ፎቶ እየተመለከተ የተነጋገሩትን ሁሉ ማውጣት ማውረድ ጀመረ፡፡ “መንገሻ እንደቀባጠረው በገንዘብስ እምትታለል አትመስልም፡፡ ግን ከመናገር ደጃዝማችነት ይቀራል ይባላል፤ ሞክሬ ቢቀርስ ምናለ፡፡ ለነገሩ ይኸ መንገሻ የተባለ ሰላቢ ሲክለፈለፍ መጥቶ ከእርሷ ጋር ስላዬኝ አንድ ነገር ካላደረኩ ቢዝነሴን ጠቅላላ ይወስድብኛል!” እያለ ሲያወጣ ሲያወርድ አደረና በነጋታው ለወይዘሪት ዘወትር ደወለ፡፡

“ገዘኻኝ ነኝ፤ ደህና ሰነበትሽ?”

“አንተ! ባገር አለህ?”  ሳይደውል የሰነበተው ስላልፈለገ ነው በሚል ተጨንቃ የሰነበተችው ወይዘሪት ዘወትር ደስ አላትና

“ልቦች ሁሉ በሽተኛ ስለሆኑ፤ ልቦችን ስጠግን ነዋ”

“በሽተኛ የሆነውን ልብ ስትጠግን በሽተኛ ያልሆነው ተጎዳ እኮ” ብላ ሳቀች

“የተጎዳውንም እጠግናለሁ” አለ

“በሪሞት ኮንትሮል አይጠገን” ስትል

“ለኢመርጀንሲ ስጠራ የትም እሄዳለሁ”

“ተጠርቶማ ማንም ይመጣል! “እሚፈለገው አስቦ እሚመጣ ነው እንጅ”

“አስቤ አደል የደወልኩት፤ ትኬት ቆርጫለህሁ ልመጣ ነው”

“መቼ?’

“በሁለት ሳምንት ውስጥ”

ከሁለት ሳምንት በኃላ ዶክተር ገዝኻኝ አርብ ቀን ወደ ቦስተን በረረ፡፡ ከአውሮፕላን ማረፊያ ወይዘሪት ዘወትር ስትቀበለው “ናይስ ቱ ሲ ዩ ዚ” አለ ዘወትር የሚለውን ዚ በሚል የእንግሊዝኛ ቁልምጫ አሳጥሮ፡፡ “የምን ዚ…ዛ ዜ ዝ ዞ ነው! እረ ዘውዬ ወይም ዘውዋ በለኝ እንዳገሬ” አለች ጉንጩን እየሳመች፡፡ “ወግ አጥባቂ! ሸገር አድገሽ  ቦስተን እየኖርሽም እንዳያትሽ እንድጠራሽ ትፈልጊአለሽ” አለና ሳቀ፡፡

“እንዴት ነበር ጉዞው ረጅም ነው አደል አልችው”፡፡ “የሚጓጉለት ሲኖር አምስት ደቂቃም ረጅም ነው እንኳን የስድስት ሰዓት በረራ!” ሲል ያንን የሚወደውን ፈገግታዋን ከንፈሯን እንደ መጠቅለያ ሰብስባ እንደ ስጦታ አበረከተችለትና ደስ አለው፡፡ “ስለመሸ ምግብ ቤቶች ሳይዘጉ ራት ብንብላ አይሻልም?” ስትል “ከቤት አላዘጋጀሽም?” ብሎ ቀለደ፡፡ “ዶክተር አባወራማ ገና አልሆኑም እኮ! እንደ ልብ ምት አይጣደፉ! ረጋ ይበሉ እንጅ!” አለች፡፡ “እረ እንደ ባህር የረጋሁ ነበርኩ ወደ ቦስተን ቦይ እስቲቀደድልኝ” አላትና ተሳሳቁ፡፡

ራታቸውን ሲያገባድዱ “ልክ የዛሬ ስድስት  ወር ፕሮፎሰር መስፍን መጥተው እዚቹ ቦታ ላይ እራት ጋብዣቸው ነበር” ብላ ሳትጨርስ ጉረሮውን በሁለት እጁ ይዞ ለመተንፈስ መታገል ጀመረ፡፡ ድምጿን ከፍ አድርጋ  “ሄልፕ” ብላ ስትጮህ ፡፡ አንድ በትንታ መጀመሪያ እርዳታ የሰለጠነ ግድንግድ ፈረንጅ መጣና ከዶክተር ገዝኻኝ ጀርባ ቆሞ የስምንት ወር እርጉዝ የመስለውን ሆዱን ተጭኖ ያነቀውን ስጋ እንደ ካርታ ጥይት አስፈንጥሮ አስወጣው፡፡”

“ዶክተር ደህና ነህ! ደህና ነህ! እንካ ውሀ!” ብላ ሰጠችው፡፡ ትንታው ሲለቀውና መነጋገር ሲጀምር ” የዛሬውስ ደሞ ድምፅም የሌለው ትንታ ነው! ይቅርታ ጥፋቱ የኔ ነው፡፡ ማረኝ የኔ ጌታ” አለችው፡፡ “አይ ምንም አይደል ርቦኝ ስለነበር እየተቻኮልኩ ስበላ ነው” ብሎ ሲመለስ “አንትሮፖሎጅውን ትቼ ትንቶሎጅ ማጥናት ሳይኖርብኝ አይቀርም” ስትለው “ጨዋታ ጨምረሻል ልበል!” ሲል “ድሮ የት ታውቀኛለህ በስልክ ብቻ ስታነጋግረኝ የሰነበትከው! አትገርምም ሁለት ወር ሙሉ አስችሎህ ሳንፍራንሲስኮ ስትቀመጥ!” አለችው፡፡ “ደሞ ጥፋተኛው እኔ ልሆን ነው? በተዋወቅን በአንድ ሳምት ውስጥ ልምጣ ስልሽ አይመቸኝም አላልሽኝም” አለ፡፡ “እንዲያው ላስወሸክትህ ፍልጌ ነው” እያለችውና እየተሰሳቁ ሆቴሉ አድርሳው በነጋተው ሊገናኙ ተቀጣጥረው ተለያዩ፡፡

በማግስቱ ቅዳሜ እለት ቁርስ በሉና በባቡር እያሽከረከረች ቦስተንን ታስጎበኘው ጀመር፡፡ “ቦስተን አርባ አራቱ ታቦት እንደሚገኙበት ጎንደር አርባ አራት ዩንቨርሲቲዎች የሚገኙበት የጥንት ከተማ ነው!” አለችው፡፡ “አርባ አራት ቀርቶ አስራ አራቱንስ የጎንደር ቤተከርስቲያኖች እሚጠራ አለ እንዲያው አንዱ አርባ አራቱ ታቦት ሲል ሌላውም በዘልማድ አርባ አራት እያለ ተከትሎት ነው እንጅ፡፡ “እዚህ ላይ ያዝከኝ አርባ አራቱን ታቦት አሁን ልጠራልህ አልችልም፡፡ መቼም እኛ የራሳችንን ሳናውቅ የሌላውን ማወቅ ስለሚቀናን የቦስተንን ዩንቨርስቲዎች ግን ልጠራ እሞክራለህ” ብላ “ሃርቫርድ፣ ኤም አ ቲ፣ ቴፍት፣ ቦስተን ዩንቨርሲቲ፣ ዩንቨርሲቲ ኦፍ ማሳቹሲትስ፣ ቦስተን ኮሌጅ፣ ኖርዝ ኢስተርን ዩንቨርሲቲ …እያለ ይቀጥላል፡፡” ብላ አቆመች፡፡ በእነዚህ ዩንቨርሲቶዎች ያሉ ምሁራን ታዲያ እንደ አንተ ከካርዲዎሎጅ ብቻ ሙጪጭ ያሉ ሳይሆኑ ሐኪም ሆኖ የሕግና የኢንጅነሪግ ዲግሪ ያለው፣ ኢንጅነርም ሆኖ የቲዎሎችጅና የፊሎዞፊ ዲግሪ ያለው ወዘተረፈ ናቸው፡፡ አያቴ ይሉት እንደንበረው እነዚህ የትምህርት ተቋማት ሙሉ በኩሉሔ የሆኑ ልሂቃን የሚያስተምሩበት ነው፡፡ በሌላ አንጋገር የፊዚክስ መምህር ስለባሌ ማውራት የለበትም እየተባለ ትእዛዝ የሚሰጥበት ቦታ ሳይሆን ከራሱ አልፎ የህብረተሰብን ኑሮ ለማሻሻል የማይጥር ምሁር የሚናቅበት ሥፍራ ነው፡፡” እያለች ዋና ዋናዎቹን ዩንቨርሲቶች አስጎበኘችው፡፡ እና ይኸ ሁሉ ዩንቨርስቲ ደሞ ያንን ትንታህን የሚያመጣብህን ሐረግ መናገር የሚያዘወትሩ ምሁራን ያሉበት ቦታ ነው፡፡ እና ከተጋባን መቼም ቦስተን መኖር አንችልም፡፡ ሳር ቅጠሉ ያንን ቃል ስለሚናገር በትንታ ትሞትብኝአለሃ” አለች፡፡ “ዘወትር አሸናፊ ዩንቨርሲቲስቲን አቋቁመን ሸገር እንኖራለን!” አላት፡፡ ለህብረተሰብ መብት የማይሟገት ዩንቨርስቲ በኔ ስም አይቋቋምም” እያለች ስትመልስ ከሆቴሉ ደረሱና ደህና እደር ብላ ስትሰናበተው አብራው ከክፍሉ እንድትገባ ጠየቃት፡፡ “ብልሹ ከበዛበት ሳን ፍራንሲስኮ የመጣ ሰው እንደ ጨጓራ ዳዊት በደንብ መጠናትና መታጠብ አለበት” ብላ ቀለደችና ተሰናብታው ወደ ቤቷ ሄደች፡፡

በነጋታው እንደዚሁ ያላያቸውን የቦስተን አካባቢዎች ስታሳየው ዋለችና የራት ሰዓት ስለደረሰ “ያበሻ ምግብ ይሻልሃል ወይስ የፈረንጅ” ስትለው የፈረንጅ አለ፡፡ “ጥሩ ምርጫ ነው፤ እንኳን አበሻ ምግብ ቤት ገብተህ አበሻ የገባበት የፈረንጅ ምግብ ቤትም ትንታህን አልቻልኩት” ስትለው በሳቅ ፈነዳ፡፡ ካምብሪጅ ይዛው ሄዳ እራት ሲበሉ ካካርዲዎሎች ውጪ ሌላ ምን ትወዳለህ ስትል ጠየቀችው “አንቺን!” “ከካርዲዎሎጅና ከእኔ ውጪስ” ስትለው “ምንም” አለ፡፡ “የምትወደው የስፖርት ዓይነት?” “ስፖርት ብወድ ይሄ ነገር ወደ ውጪ ይወጣ ነበር?” አለ ሆዱን እንደ ድርስ እርጉዝ እየነካካ፡፡ “ማንበብ እምትወደው የመጽሐፍ ዓይነት?” ብላ ስትጠይቀው “የካርዲዎሎጅ መጻሕፍት” አለ፡፡

“ካርዲዎሎጅማ እንጀራህ ስለሆነ ነው፡፡ እንዲያው ሌላ  መጻሕፍት ለጠቅላላ እውቀት ወይም ለአእምሮ እርካታ ማለቴ ነው እንጅ”

“ጥቅም በማያስገኝ ነገር ለምን ጊዜን አሳልፋለሁ?”

“ያምሮ እርካታ ጥቅም አይደለም”

“ያምሮ እርካታ ስንት ብር ያወጣል?”

“እና ጊዜህን የምታውለው ብር፣ ወይም ቁሳዊ ንብረት ለሚስያገኝ ነገር ብቻ ነው?”

“ፕሪቲ ማች!” አለ

“እና እኔንም ልትጠይቅ የመጣሃው ለራስህ ጥቅም ነው?”

“ለጋራ ጥቅማችን”

“የጋራ ጥቅማችን ስንት ብር ያዋጣል?”

“ሁለት ሚሊዮን ብር”  ብሎ ሲመልስ ወይዘሪት ዘወተር ሰብአዊ መብታቸውን ለተገፈፉት ጠበቃ ሆና ስትሰራ ለገንዘብ ሲሉ በሐሰት የሚመስክሩ፣ ለገንዘብ ሲሉ በሐሰት በሰዎች እድሜ ይፍታህ የሚፈርዱት፣ ለገንዘብ ሲሉ በሰዎች ጉረሮና ፊንጢጣ ስንጥር እንጨት የሚሰዱ፣ ለገንዘብ ሲሉ በወንዶች ብልት የላስቲክ ውሀ የሚያንጠለጥሉ ከንቱዎች በህሊናዋ መጡባትና ትን ብሏት “እ…እ..ኦቲስ…እ…እ ኦቲስ” ብላ ስታነጥስ “ውሀ! ውሀ ልስጥሽ!” አለ ዶክተር ገዛኻኝ የብርጭቆ ውሃ እያሳዬ፡፡ በእጇ ያያዘችውን አንገቷን እየነቀነቀች የእሽታ ምልክት አሳዬችና እጇን ወደ ብርጭቆው ዘረጋች፡፡ ዶክተር ገዘኻኝ “ሄምሊክ ማኑቨር” የሚባለውን የእንቅታ ማስወገጃ ዘዴ የሚሰራ መስሎ ከጀርባዋ ሄዶ ጡቷን እንደ ስፖንጅ ጨመቅ፤ ጨመቅ ማድረግ ጀመረ፡፡

“ምን እያደረክ ነው”

“ትንታ እያስወጣሁ!”

“ትንታ ወተት አይደል በዚያ በኩል እሚወጣ!” ስትለው ተሳሳቁ፡፡

ከሳቁ ሲመለስም “አትፍረድ ይፈረድብሃል! ተይ አትፍረጅ ብዬሽ ነበር” አለና በመቀጠልም “ሁለታችንንም በአንድነት ትን ቢለን ማን ውሀ ሊያቀብል ነው?” አለ፡፡

“ሁለታችንንም አንዴ ትን ሊለን አይችልማ!” አለችው

“ለምን”

“አልርጃችን የተለያዬ ስለሆነ”

“ያንቺ አለርጅ ምንድነው?”

“ጥቅም!”

“አንቺ የሸገር ልጅ አይደለሽም! እንዴት ጥቅም አለርጂ ሊሆንብሽ ይችላል?”

“እንዳንተ ዓይነቱ ጉምት ካልሆነ በቀር የሸገር ልጅ ሁሉ የጥቅም ሰው ነው ያለ ማነው? ትናንት ራት ስንበላ ስማቸው በትንታ አንቆ ሊገልህ የነበሩት ሰውዬም እኮ የሸገር ልጅ ናቸው፡፡”

“እነዚህን ወግ አጥባቂ የሰማንያ የዘጥና ዓመት ሽማግሎችን አላልኩም፡፡ ስላሁኑ ትውልድ ነው እማወራው”

“ለጥቅም አልገዛም ብለው ውህኒ እሚማቅቁት ያሁኑ ትውልድ የሸገር ልጆች ያንተን ያህል ብልጠት አጥተው ነው? እኔስ ሚኒስቴር እናርግሽ ሲሉኝ ያህዮች ሚኒስቴር አልሆንም ብያቸው የመጣሁን እንዳንተ ጮሌ መሆን አቅቶኝ ነው?”

“ተሞኝተሻል! ሚኒስቴር ብትሆኝ ይሻልሽ ነበር”

“ሚኒስቴር ብሆንማ አታገኘኝም ነበር!”

“ሚኒስቴር ብትሆኝማ አንቺን ለማግኘት ይህንን ያህል ጊዜ አይፈጅብኝም ነበር”

“እንዴት ሚኒስቴር ተብዮችን የምትመለምለው አንተ ነህ?”

“መልማዮችን በደንብ አውቃቸዋለሁ፤ ቢዝነስም አብረን እንሰራለን!”

“ምነው ለፖለቲካ አለርጅ ነኝ አላልከኝም ነበር?”

“ከጥቅም ጋር ሲመጣ ጥቅሙ ለፖለቲካ አለርጅ እንደ አንቲ ዶት ያገለግላል”

“ጥቅም አለርጅ ለሆነበትስ አንቲ ዶቱ ምንድነው”

“የጥቅም ሰው አግብቶ ዲሴንሲታይዝድ መሆን”

“ዲሴንሲታይዝ ምን ማለት ነው”

“ቀስ በቀስ መለማመድ ማለት ነው”

“ታዲያ አንተን ከራስ ጥቅም አሳዳጅነት ወደ ሕዝብና አገር አሳቢነት እንድትቀየር ለምን ዲሴንሲታይዝ አላደርግህም?”

“እንግዲህ አብረን እንኑርና በዲሴንሲታይዝ ያሸነፈ ያሸንፍ” አለ፡፡

“ዘወትር አሸናፊ እንደሆንኩ ታውቃለህ”

“ገዛኻኝ ብሩ መሆኔን አትዘንጊ”

“ሥምን መላክ ያዋጣል” አለችውና ወደ ሆቴሉ ከሚሄደው ባቡር መሳፈሪያ ሄዱ፡፡ “ነገ ነው እምመለሰው ክፍሌ ውስጥ ትንሽ አንጫወትም” ሲል ” እጩ እንጅ ገና ባል አይደለህ! ለሁሉም ጊዜ አለው ብሏል ጠቢቡ ሰለሞን! በጊዜው ይደርሳል!” አለችና ጉንጩን ሳመችው፡፡ “በቃ ይኸው ነው?” ሲል “ከዚህ እዚያ  ጋ ለመድረስ መንገዱ ከዓባይ በርሃ ጎዳና የባሰ ጠመዝማዛ ነው፤ ረጅም ጊዜም ይፈጃል፤ እንደ ኢቮሉሽን ሩቅ መንገድ ነው! አሳማ ቺምፓንዚ ሆኖ ችምፓንዚ ደሞ ሰው እስኪሆን ማለት ነው፡፡” አለች በሌባ ጣቷ ከጉንጩ እስከ ከንፈሩ መስመር አሰመረችና፡፡ በመጨረሻም “እንደበፊቱ እንዳትረሳኝ ከልጅነት እስከ እውቀት የተነሳኋቸውን ፎቶግራፎቼን እዚህ ውስጥ ታገኛቸዋለህ” ብላ ሁለት ሲዲዎች ከቦርሳዋ አውጥታ ሰጠቸው፡፡ እነዚህን ፎቶግራፎች ስትመለከት ትንታ ሊመጣብህ ስለሚችል የኩባያ ውሀና እግዜአብሔር ከአጠገብህ አይለዩ አለችና” ሳቀች፡፡

ዶክተር ገዘኻኝ ሳንፍራንሲስኮ ከሚሄደው አውሮፕላን ውስጥ የወይዘሪት ዘወትርን ፎቶግራፎችን ሊያይ ቢጓጓም የያዘው “ላፕቶፕ” ሲዲ የሚያስተናግድ ስላልነበረ ማየት አልቻለም፡፡ አውሮፕላኑ ውስጥ ቦስተን ደርሶ ወይዘሪት ዘወትርን ለማየት የሳሳውን ያህል ሳንፍራንሲስኮ ደርሶ ከልጅነት እስከ እውቀት ያጠረቃቀመቻቸውን ፎቶግራፎቿን ለማየት ጓጓ፡፡ ከአውሮፕላን ወርዶ ከቤቱ እንደ ደረሰ  ሻንጣው ከወለል ወርውሮ ቢራውን ያዘና ‘ዴስክ ቶፕ’ ኮምፒተሩን ከፍቶ ፎቶግራፎችን ማየት ጀመረ፡፡ የመጀመሪያውን ፎቶ ጫን ሲያደርግ ወይዘሪት ዘወትር ከሕግ ት/ቤት ስትመረቅ  የተነሳችውን  ፎቶ አየና”ያኔ ካሁኑም የበለጠ ለሐጪ የምታስጥል ጉብል ኖራለች” አለና እንደ ሀይለስላሴ ዝናብ-ተንባይ አህያ አገጩን ወደ ሰማይ ቀስሮ ቢራውን አንደቀደቀው፡፡ ከዚያም የሚቀጥለውን ምስል ሲጫን ወይዘሪት ዘወትር ከቢሮዋ ኮስተር ብላ መዝገብ ስታገላብጥ አየና “ለሥራዋ ያላት ትኩረት ያስፈራል!” አለ፡፡ ከሥራዋ ከተነሳችው ፎቶ ብዙም ሳይቆይ ቢራውን እንደ እንጀራ በአፉ እያንገዋለለ የሚቀጥለውን ምስል ሲጫነው በታጣቂቆች ጭንቅላቱ እንደሸክላ የተከፈለ ለግላጋ ወጣት አየ፡፡ “እብድ መሆን አለባት! እንዴት ይህንን ከራሷ ፎቶች ትቀላቅላላች!” ብሎ ሳይጨርስ ትን አለውና ደጋግሞ አሳለው፡፡ ከትንታው ሲመለስ “በስህተት ያስገባችው ፎቶ መሆን አለበት!’ ብሎ ከመቅጽበት የሚቀጥለውን ሲጫነው ራሱ ዶክተር ገዛኻኝ “የሞቱ ምክንያት የማይታወቅ” ሲል የፈረመበትን በአጋዚዎች የተረሸነ  የአስራ አራት ዓመት ልጅ አንጀቱ ተዘርግፎና እንደ ክርስቶስ ጎኑን ተወጋግቶ ደም ሲንዥቀዠቀው አየና በላብ ተነከረ፡፡ በዚህ ጊዜ ቢራ ሳይሆን ውስኪውን ጭልጥ አደረገና የጠጣበትን ብርጭቆ ወረወረው፡፡  በድንጋጤና በአልኮል የተደናበረው አእምሮው ሲፈጥመው ወደኖረው ዘግናኝ ወንጀል ቢኮበልልም ጣቶቹ ምስሎቹን መነካካቱን ቀጠሉ፡፡  በሐሰት “ወድቀው፣ በመኪና ተገጭተው፣ ከሰው ተጣልተው፣ ሰክረው፣ ራሳቸውን አንቀው ወዘተርፈ ሞቱ” እያለ በቅጥፈት በሙታን ሰርቲፊኬቶቻቸው የፈረመባቸው ገዥዎች ባሰማሯቸው ነፍሰ-ገዳዮች ጭንቅላታቸውን የተበረቀሱ፣ አንገታቸውን የተቀነጠሱ፣ ደረታቸውን የተበሱ፣ አንጀታቸውን የተጎለጎሉ፣ ብልታቸውን የተቆረጡ፣ ታፋቸውን የተገነጠሉ፣ ጥፍራቸውን የተነቀሉ፣ ቆዳቸውን የተተለተሉ ወጣቶች፣ ጎልማሶች፣ አሮጊቶች፣ ልጆችና እናቶች ምስሎች በተከታታይ መጡ፡፡ “ምነው!…ምነው.. ምን በደልኳትና እንዲህ አደረገችኝ! ” አለና “ሚ…አውውው!’ ሲል እንደ ድመት አይሉት እንደ ጅብ ጮኽ፡፡ “ምን” ያለበት ዝላይ አይችልም እንደሚባለው ጅብ እንኳን የሚያከብረውንና የሚፈራውን የሰው ልጅ እርሱ በጥቅም የቀየረበት ወንጀሉ የታወቀበትና ወዲያውኑም  ከሕግ ፊት የሚቀርብ መሰለውና ከወዲያ ወዲህ ተቅበዘበዘ፡፡ የሚያቅበዘብዘውን ጭንቀት ለመወጣት ከፊቱ ያገኛውን እቃ መወርወር፣ ቴሌቪዥኑንና መስኮቱቹን መሰባበር ጀመረ፡፡ ጭንቀቱና መቅበዝበዙ ግን በደምና በግፍ የጨቀየ ታሪኩን ባስታወሰ ቁጥር እየበረታ ሄደ፡፡ በዚህም ምክንያት በመድሐኒት ብዛት የተቆጣጠረው የደም ግፊቱ አሻቀበ፤ የልብ ትርታውም ያለመጠን ጨመረና የደረት ሕመም ተሰማው፡፡ “የልብ ጉዳት ነው! ልቤ ነው! ልቤ ነው! መሞቴ ነው! መሞቴ ነው!” አለና በደመ ነፍስ 911 ለአምቡላንስ ደውሎ ድንገተኛ የልብ ሕመም እንደገጠመው ተናግሮ ሳይጨርስ ከወለሉ ተዘረጋ፡፡ ከወል ተዘርግቶ ሲያጣጥር ከነፍሰ-ገዳይ ገዥዎች እየተሻረከ የገነባው ሆስፒታል፣ የከፈተው ፋርማሲ፣ ያቋቋመው ሆቴልና የሚያጣድፈው ያየር ባየር ንግድ በህሊናው መጣበት፡፡ “ወይኔ ብኩኑ! ለዚሁ ነው! ለዚቹ እድሜ ነው! ሁሉንም ትቼ መሄዴ ነው! መሞቴ ነው! ምስጥ ሊበላኝ ነው! አለቀ! በቃ! አከተመ” እያለ የባጥ የቆጡን ሲያወርድ አምቡላንሱ ደረሰ፡፡

“አይ አም ….ካር…ካርዶ…ሎጅ.. .ሄ…ል..ፕ ሚ..” አለ በሰነነ ድምጽ የልብ ሐኪም መሆኑን ሲያውቁ የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጡት በማመን፡፡ “ዊ ዊል ቴክ ዩ ቱ ኤምርጄሲ ሩም፤ ኖት ቱ ካርዲዎሎጅስት!” አለ ከአንቡላንሱ ሰዎች አንዱ ዶክተር ገዛኻኝ በሰነ ድምፅ “ካርዲዮሎጅስት ነኝ እርዱኝ!” ያለውን ካርዲዮሎጅስት ቢሮ ውሰዱኝ  ያለ መስሎት፡፡ የዶክተር ገዛኻኝን የበሽታ ታሪክ በፍጥነት የሚዘግቡት ሁለት የአንቡላስ ሰዎች “መድሀኒት ትወስዳለህ?” ብለው በእንግሊዝ አፍ ሲጠይቁት በደከመ ድምጽ የሚወስዳቸውን የስኳር፣ የደም ግፊትና የኮሌስትሮል መድሐኒቶች ነገራቸው፡፡ በቃሬዛ ተሸክመው ከአንቡላስ እንዳስገቡት ልቡ ቀጥ አለች፡፡ በሰለጠኑበት ጥበብ ደረቱን ለሶስት ደቂቃዎች ተጭነውና እስተንፋስ ሰጥተው ልቡን መለሷት፡፡ ወዲያውም አንቡላንሱን አስነስተው ያለማቋረጥ “ጲጵ…ጲጲጲ..ጲጲጲጲጵጲ……ኡ ኡ ኡ…..ጲጲጲጲጵጲ….! “.እያሰኙና ሰማያዊና ቀይ መብራት በማፈራረቅ እያሳዩ ሳንፍራንሲስኮ አጠቃላይ ሆስፒታል ከድንገተኛ መታከሚያ ክፍል ሲያደርሱት እንደገና ልቡ በቃኝ አለች፡፡ አሁንም የድንገተኛ መታከሚያ ክፍል ሰራተኞች ደረቱን በእጃቸው መዳፍ መርገጡንና ኦክስጅን መስጠቱን ቀጠሉ፡፡  ከአምስት ደቂቃቆች በኋላ ልቡ እንደገና በትክክል መምታት ጀመረች፡፡ ብዙም ሳትቆይ ልቡ ደከማትና የልብ ትርታ መቆጣጠሪያ ሰሌዳው የመጋዝ ጥርስ የመሰለ ሥዕል ማሳየት ጀመረ፡፡ መድሐኒት በደም ሥሩ ሲሰጡት ሰሌዳው ለቅጽበት ጤናማ የልብ አመታት መልክ አሳዬ፡፡ ወዲያው ደግሞ ኮቢ መያዝ የጀመረ ሕጻን የሞነጫጨረው የመሰለ ሥዕል  በሰሌዳው ታዬ፡፡ “ስታርት ሲ ፒ አር” አለ የዶክተር ገዛኻኝ ህይወት ለመታደግ የተሰለፈውን ቡድን የሚመራው ዶክተር፡፡  ከቡድኑ ሰዎች አንዱ “ዋን  ቱ ስሪ ፎር ፋይቭ …..” እያለ ሰላሳ ጊዜ ደረቱን ሲጫን ሌላው ኦክስጅን ማግኘቱን ያረጋግጣል፡፡ አንዷ መድሀኒት በደም ስሩ ስትሰጥ ሌላዋ የሚደረገውን ነገር በነቂስ ትመዘግባለች፡፡ በዚህ መልክ የጤና ባለሙያዎቹ ዶክተር ገዝኻኝን ሊታደጉ ለሃያ ደቂቃዎች ቢታገሉም እንደ ገንዘብ አማለው ልቡን ሊመልሷት አልቻሉም፡፡ ከሃያ ደቂቃዎች የነፍስ-ውጪ ነፍስ-ግቢ ጥረት በኋላ ጂኦሜትሪ “በሁለት ነጥቦች መካከል የሚገኘው አጭሩ ርዝመት ቀጥ ያለ መስመር ነው!” የሚለው ዓይነት ቀጥተኛ መስመር ከልብ ምት መቆጣጠሪያ ሰሌዳው ታዬ፡፡

ይህ ከልብ ትርታ መቆጣጠሪያ ሰሌዳው የታዬው ቀጥተኛ መስመር የዶክተር ገዛኻኝ ነፍስ ከሥጋው የተለችበት ምልክት ሆነ፡፡ ከስጋው የተለየችዋ ነፍስ ወደ ተጠራችበት ዓለም ነጎደች፡፡ ከነፍሱ የተለየው ሥጋው ግን ከዚሁ መከራና ግፍ ከማይከብዳት ምድር ቀረ፡፡ ጠቅላላ ሰውነቱ ገረረ፣ የሞት ሰርቲፊኬት የፈረመባቸው ጣቶቹ ተኮማተሩ፡፡ ቱጃር ያደረጉት ምላሱና ላንቃውም ተሳሰሩ፡፡ አፉና አፍንጫው ከድሃ ገላ እየገሸለጠ በዘነቸረው ሥጋና ከጎስቋሎች ደም ሥር እየማገ በሰረበቀው ደም ፈርስ ተሞሉ፡፡ አጥንቱና ሥጋው ከመቃብር ለምስጥ ግብዣ ቀረቡ፡፡ ሥሙና ታሪኩ ግን ከትውልድ ትውልድ ሊተላፉ በምድር ተጻፉ፡፡

 

ሚያዝያ ሁለት ሺ ዘጠኝ ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.