የአዳማ ሕዝብ፣ የምስራቅ ሸዋ ህዝብ ቢጠየቅ … – ቀልቤሳ ዘ ቢሾፍቱ

“የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም ለመወሰን የወጣ ረቂቅ አዋጅ” ዙሪያ አቶ ግርማ ካሳ ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት ብለው የጻፏቸው ጽሁፎች ትኩረቴን ስበዉታል። አቶ ግርማ የኦሮሚያ የሸዋ ዞኖች እና አዲስ አበባን ያቀፈ፣ አማርኛና አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ የሆነበት ክልል አስፈላጊነትን ነው መረጃ በማቅረብ ለማሳየት የሞከሩት። ብዙዎች ፖለቲከኞች፣ ፈርተው ዳር ዳር የሚሉበትን ፣ በሕዝብ ልብ ዉስጥ ያለውን አንገብጋቢ ጉዳይ አቶ ግርማ ይዘው በመነሳታቸው ሳላማሰግናቸው አላልፍፍም።

ደብረዘይት/ቢሾፍቱ ተወልጄ ያደኩ፣ አፋን ኦሮሞ ትንሽ ትንሽ የምችል ኢትዮጵያዊ ነኝ። አሁንም የምኖረው እዚያው ቢሾፍቱ ነው። አባቴ የወለጋ ሰው ነበር። እንደሚታወቀው በአጼው ዘመን አየር ሃይልን ይዘው የነበሩ ወለጋዎች ነበሩ ማለት ይችላል። በሚሲዮናዉያን ብዙ የተማሩ እነርሱ ነበሩና። እናቴ ከጎንደር እና ከሐማሴን(ኤርትራን) ናት። የግል ቢዝነሶች አሉኝ። በአምቦ መስመር አንድ ከተማና በምስራቅ ሸዋ ዞን (ቢሾፍትቱና ዝዋይ) ቅርንጫፎች አሉኝ።
በኣምቦ መስመር ሆለታ ገነትን አልፎ የሚኖረው ማህበረሰብ በብዛት አማርኛ ማንበብና መጻፍ ችግር አለበት። ሕወሃት/ኦሕዴድ ለከፋልሀ ግዛ እንዲመቸው፣ ኦሮሞው ከሌላው እንዳይግባባ ለማድረግ፣ ጸረ-አማርኛ ፖሊሲ ነበረው። በዚያ መስመር አካባቢውን ከአማርኛ የማጻዳት እኩይና ከፋፋይ ተልእኮዉን በመጠኑም ቢሆን የተሳካለት ይመስላል። እኩይ ያልኩበት ምክንያት ማህበረሰቡን የጎዳ በመሆኑ ነው።

አንድ ምሳሌ ልጥቅስ። በግል ኩባኒያዬ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው። ከኦሮሚያና ክልል መንግሥት ጋር ለሚኖረን ግንኙነት፣ ቁቤና አማርኛ የምታነብና የምትጽፍና የምታስተረጉም ጸሃፊ አለችን። አንድ ጊዜ አማርኛ የሚናገሩ ሁለት ሰራተኞችን ቀጠርን። በየሳምንቱ ሪፖርት መስጠት ነበረባቸው። አንድ፣ ሁለት ሳምንት አለፈ፤ ሪፖርት የለም። የዲሲፕሊን እርምጃ ለመዉሰድ አስጠራኋቸው። “ለምንድን ነው ሪፖርት በጊዜ የማታቀርቡት ? “ ብዬ ተቆጣሁ። “ጋሼ አማርኛ መጻፍ አንችልም ? በቁቤ ጽፈን ጸሃፊዋ ብትተረጉምልንስ ? “ አሉኝ። አዘንኩኝ። ጭንቀታቸው ተሰማኝ። ቢዝነሳችንን ይገድለዋል። ግን፣ እነርሱ ወደው ሣይሆን ስርዓቱ ያመጣብቸው በመሆኑ፣ “መናገር ከቻሉ አያስቸግራቸውም” ብዬ በስድስት ወራት ውስጥ ማንበብና መጻፍ እንዲማሩ አለበለዚያ ግን መልቀቂያ እንዲያስገቡ ነገርኳቸው። ብዙም ጊዜ አልፈጀባቸውም። አማርኛ ለማንበብና ለመጻፍ በጣም ቀላል በመሆኑ ቶሎ ለመዱ። እኔ አማርኛ ነው የምናገረውና የምጽፈው።አፋን ኦሮሞ ትንሽ ትንሽ ነው የምችለው። ማንበብና መጻፍ በጭራሽ አልችልም። ቁቤው ትንሽ አስቸጋሪ ነው። እንደኛ አይነቶቹ አፋን ኦሮ በቀላሉ እንድንማር ቀለል ያሉ ዘዴዎች ቢፈጥሩልን ጥሩ ነበር። ሰራተኞቼ በቀላሉ አማርኛ መጻፍና ማንብብ እንደተማሩት። እነርሱ አሁን አፋን ኦሮሞም አማርኛም ይናገራሉ፣ ይጽፋሉ ያነባሉ። መታደል ነው።
በስሜንና በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ስላለው ሁኔታ ብዙ አላውቅም። በአዳም ልዩ ዞን እና በምስራቅ ሸዋ ዞን ግን ያለው ሁኔታ በምእራብ ሸዋ ካለው በጣም የተለየ ነው። ሁሉም አማርኛ የሚያነብና የሚጽፍ ነው። በምስራቅ ሸዋ ያለው ማህበረሰብ፣ የአዳማ፣ የቢሾፍቱ፣ የዝዋይ፣የመቂ፣ የዱከም፣ የሞጆ …..ህዝብ አስተሳሰቡ እንደ አዲስ አበባ ህዝብ ነው። የአዳማ ልዩና የምስራቅ ሸዋ ዞን ከአዲስ አበባ ጋር ተዋህደው አንድ ክልል ማድረግ ቢቻል ህዝቡ በእጅጉ የሚደሰትበትና የሚደገፈው ንው የሚሆነው። እንደ ቢሽፍቱ ልጅ እኔም የምደግፈው ነው።

ከገጠር አፋን ኦሮሞ የሚናገሩ ገበሬዎች በብዛት እንደመኖራቸው፣ አቶ ግርማ እንዳሉት፣ አዲስ አበባና አካባቢዋን ባቀፈው አዲሱ ክልል፣ አፋን ኦሮሞም የሥራ ቋንቋ መሆኑ ተገቢ ነው። ከተሜዎች፣ ገጠሬዉም አማርኛም አፋን ኦሮሞም ቢያዉቁና ቢናገሩ የበለጠ ያስተሳስራቸዋል።

ችግሩ ግን ያለው ሕዝቡ ጋር ሳይሆን፣ ገዢዎች ጋር ነው። መጀመሪያዉኑ አገሪቷን በዘር ከፋፍለው ኦሮሚያ የሚባለውን የፈጠሩት ሕወሃት/ኦህዴዶ ናቸው። እነርሱ ሐሳባቸው እስካልቀየሩ ድረስ ወይንም እስካልተለወጡ ድረስ የሚለወጥ ነገር አይኖርም። የሕወሃት ባለስልጣናት ኦሮሞዉን ከሌላ መለየቱ ስትራቴጂካዊ ጥቅማቸውን ያስጠበቅላቸዋል። ሸዋ የሚባል ክልል መፈጠሩ በኦሮሞዉና በሌላው ማህብረሰብ መካከል ያለውን ግድግዳ ያፈራረሰዋል። የኦሮሚያ ክልል እና የኦህዴድ ባለስልጣናት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዙሪያና ከአዳማ የመጡ አይደለም። ለምሳሌ የክልሉ አስተዳዳሪዎች የነበሩትን ብንመልከት፣ ጁነዲን ሳዶና አባ ዱላ ከአርሲ፣ ሙክታር ከድር ከጂማ ናቸው። የቀድሞ አለማየሁ አቶምሳ ከወለጋ ነበር።እነዚህ ባለስልጣናት ሆነ ጨፌ ዉስጥ የተሰበሰቡት የአዲስ አበባና የአካባቢዉን ህዝብ ስነ-ልቦና የሚረዱ አይደለም። ሸዋ(በተለይም ምስራቅ ሸዋ ዞንን) አጡ ማለት ሃይላቸው ተሸረሸረ ማለት ነው። በመሆኑን ለስልጣናቸውና ለጥቅማቸው ሲሉ የሕዝቡን ፍላጎት እያፈኑ መቀጠሉን ይገፉበታል።

ህዝብ ግን ምንግዜም አሸናፊ ነው። ከተደራጀና መብቱን መጠየቅ ከጀመረ፣ እርግጠኛ ነኝ የአቶ ግርማ ካሳ ሐሳብ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ሠደድ እሳት ይቀጣጠላል።ጥቂቶች ስለፈለጉ መሆን የለበትም። የሕዝብ ፍላጎት መጠየቅ አለበት።ሕዝብ የአዳማ ህዝብ፣ የምስራቅ ሸዋ ህዝብ ተጠይቆ በኦሮሚያ ውስጥ እቀጥላለሁ ካለ ያ መከበር አለበት። ግን እመኑኝ በአሥር ጣጤ እፈርማለሁ ሕዝቡ ኦሮሚያን አይፈለግም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.