እናንተ ፖለቲከኞች ምን እያላችሁ ነው? ጥያቄ ነው !!!። ከተማ ዋቅጅራ

ለስልጣን ብሎ ህዝብን ማስፈጀትና ማፋጀት ከወንጀልም ሁሉ የከፋ ወንጀል ነው። ከፓለቲካ  ለሚገኝ ትርፍና ጥቅማ ጥቅም የህዝብን አንድነት መናድና ማፍረስ ከበደል ሁሉ የከፋ በደል ነው። ስልጣንን ለማስጠበቅና በቀቢጸ ተስፋና ነገ ስልጣንን እንይዛለን በማለት የዘር ሃረግንና ቋንቋን ተገን በማድረግ በዙሪያ ያለውን ማህበረሰብ እንደጠላት ፈርጆ  መጓዝ ከአጥፍቶ ጠፊ ቡድን ተለይቶ አማይታይ አደገኛ አካሄድ ነውና ከወዲሁ  ቢታሰብበት መልካም ነው ። አባቶች ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ እኔም እንዲህ እላለው። በተገኘው አጋጣሚና በተገኘው መድረክ ላይ ለርካሽ ፓለቲካዊ ትርፍ የምትሯሯጡ ነገ በህዝብና በአገር ላይ ለሚደርሰው አደጋ ከተጠያቂነት እንደማታመልጡ ልትገነዘቡት ይገባል።

በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ህዝብ ለሌላው  ህዝብ ጠላት ሆኖ የተነሳበት አጋጣሚ የለም። እንዲህ ቢሆን  ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ እና አንድ ሃይማኖት ብቻ ይኖር ነበረ። በአለማችን ላይ  ያሉት የታሪክ እውነታዎች ይሄንን ይነግሩናል። ከኢትዮጵያ በኋላ ክርስትናን የተቀበሉ ምዕራብያኑ በአገራቸው አንድ ቋንቋ እና የክርስትና እምነት ብቻ እንዲኖር አድርገዋል። ከኢትዮጵያ በኋላ እስልምናን የተቀበሉ አገራቶች የራሳቸውን ቋንቋና እምነት በመትከል ሌላውን እንዲጠፋ አድርገዋል። ለምን ቢሉ  እኔ የማምነውን አምላክ ካላመንክ እኔ የምናገረውን ቋንቋ ካልተናገርክ መጥፋት አለብህ ብለው በመነሳታቸው በምዕራብያውያኑም ሆነ በአረቡ አለም ከፍተኛ እልቂት እንደተከሰተ የታሪክ ድርሳናት ይነግሩናል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ከሁሉ በፉት ክርስትናን ብትቀበልም የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሳውዲ በስደት ሲመጡ ከለላ ሰጥታ አኖረች  እንጂ የኛን እምነት ካልተቀበላችሁ ጥፉ አላለችም ያለው የታሪክ እውነት የሚነግረን ይሄንን እውነት ነው። ኢትዮጵያ የምዕራብያኑን አልያም የአረቡን አለም አካሄድ ሄዳ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ነገር በአንድ ተጨፍልቆ አንድ ወጥ ነገር እናይ ነበረ።

ታድያ የዛሬዎቹ ፓለቲከኞች ከየት የታሪክ መነሻነት ተነስተው ነው አንዱ ህዝብ በዳይ ሌላኛው ተበዳይ እያደረጉ የሚያቀርቡት በዳይ ህዝብ የት ቦታ እንዳለ ተበዳይ ህዝብ የት ቦታ እንደተበደለ ፓለቲከኞቹ ግልጽ መረጃ ተኮር መልስ ለህዝብ ልትሰጡ ያስፈልጋል። አንድ ህዝብ ሌላኛውን ህዝብ ጠላት ድረግ የተነሳበትን ታሪክ ለኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክ አጥኚዎች ፊት በመቅረብ የማስረዳት በህግ የምትገደዱበት ግዜ ወደፊት እንደሚጠብቃችሁ ለማስገንዘብ እወዳለው።

እንዴት አንድ ህዝብን እመራለው  የሚል ፓለቲከኛ በውሸትና በሰይጣናዊ መንገድ በመሄድ ያልነበረን እና ተደርጎ የማይታወቅን ታሪክ በህዝብ ላይ እንደተደረገ አስመስሎ በማቅረብ ህዝብን የሚያጠፋ መርዝ በመቀመም ወደ ትግል ሜዳ ይገባል። በምንስ ህሊና ነው ህዝብን አጫርሶ አገርን በትኖ የተሻለ የፓለቲካ አመለካከት አለኝ በማለት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ብትንትኗ ትውጣ ብለው በአገር ላይ ግልጽ ወንጀልና በህዝብ ላይ ግልጽ እልቂት በማወጅ ፓለቲካ ትግል ሊሆን የሚችለው? እውነት እውነት እላችኋለው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄዎችን አንግቦ በግልጽ ይጠይቃችኋል። እናንተ ድብቅ ተልኮ ያላችሁ ፓለቲከኞች የተናገራችሁት በድምጽ እንዲሁም በቪዲዮ ያለ ማስረጃ ስለሆነ ለህዝብ በግልጽም በህግም ተገዳቹ  የምትናገሩበት ግዜ እሩቅ አይደለም።

ነጻ የትግራይ መንግስት እመሰርታለን ብሎ አንገቱ  ላይ የመጥፊያውን ሸምቀቆ አድርጎ የሚውተረተረው ወያኔ በወልቃይት፣ በጠገዴ፣ በሁመራ ግዛቴ ነው በማለት ምን ያህል ህዝብ እንደተጨረሰ እና አሁንም እየጨረሰ እንዳለ የሚታወቅ ነው ። ይሄ ሁሉ ግፍ በህዝብ ላይ ቢፈጸምም የሚፈልጉትን ግብ ግን ሊመቱ አልቻሉም ምክንያቱም ህዝብን ታግሎ እና ጨፍጭፎ ማሸነፍ አይቻልምና ነው። ወያኔ እየተከተለ ያለው አካሄድ እኔ ልብላህና ልኑር አንተ ተበላና አኑረኝ ነገር ነው። ይሄ በሽታ ዛሬ አድማሱን አሳድጎ ወያኔ ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ከፋፍሎ ለመግዛት ያወጡት ካርታ ላይ ሌሎችን እንደእንግዳ ወይንም መጤ በመቁጠር አገርኛ እና አገር አልባ በማለት ፓለቲከኛ ነን የሚሉቱ ለስልጣን ጥማታቸው ህዝባችን ላይ ከ80 ሚሊዮን በላይ ጠላት አስነስተውብናል። ይሄንን ነገር በቀላሉ መመልከት ሞኝነት ነው።

ዛሬ ነገሮች እጅግ ተለውጠዋል። ምክንያቱም ፓለቲከኛ ነን የሚሉቱ ህዝብን እንደ ጠላት ፈርጀው በመንቀሳቀሳቸው ያ ጠላት የተባለው ህዝብ በመደራጀታቸው አደገኛ የሚባሉ የየራሳቸው ካርታዎችን በማስቀመጥ ላይ ይገኛሉ ከነዚህ አደገኛ እና ህዝብን ሊያጫርስና አገር አልባ ሊያደርጉ ከሚችሉት ውስጥ 5ቱን እንመልከት፤
1ኛ. የዚህ ሁሉ ጠንሳሽና አነሳሽ የወያኔ ካርታ ትግራይ ትግርኛ የሚለው ካርታ።

2ኛ. ኦነግ እስከ ወሎ ድረስ የሚደርስ የሰራው ኦሮሚያ የሚለው ካርታ።

3ኛ. አማራ ጥቂት ቦረና ጥቂት ባሌ ጥቂት ኦጋዴን ሲቀረው በወያኔ ዘመን የኦሮሚያ የሚባለውን ግዛት እና አሶሳን ጨምሮ በማካለል ቤተ አማራ የሚለው ካርታ።

4ኛ. ታላቋ ሱማሌን እንመሰርታለን በማለት ግማሽ ሸዋን ግማሽ አፋርን ቦረናን ባሌን አርሲን ሐረርጌን በመጨመር የሰሩት የታላቋ ሱማሌ የሚለው ካርታ።

5ኛ. ሲዳማ ግማሽ ቦረናን አርሲን አዋሳን በማካተት የሰሩት የሲዳማ ካርታ። አደገኛ የሚባሉ ናቸው ።

ጥያቄ ዘርን ብቻ ተኮር አድርጋችሁ ለፖለቲካ ጥቅማችሁ ብቻ በማስቀደም የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነታ ትታችሁ  ለምትውተረተሩ ለተነሱት ጥያቄዎች ታሪካዊ እና እውነታን በተመረኮዘ የይገባኛል ጥያቄዎችን መፍታት የምትችሉት በምን አይነት መንገድ ይሆንን?። እናንተ በሰራችሁት ስህተት በሰላም በአገሩ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ላይ ለሚመጣበት አደጋ እና ህዝብና ህዝብን አጋጭታችሁ እንደ ፍልስጤም አገር አልባ ሊሆን እንደማይችል  የምታቀርቡት ማረጋገጫ አልያም የምትሰጡት  ዋስትናችሁ ምን ይሆን?። ለነዚህና መሰል አደጋዎች ዘርን ከዘር ሃይማኖትን ከሃይማኖት በማጣላት በዘርና አሃይማኖት ሽፋን በመደበቅ ለምትፈጥሩት አደጋ ከተጠያቂነት እንደማታመልጡ ከወዲሁ ልታውቁት ይገባል።

የገዢዎች አንባ ገነን እንጂ የህዝብ አንባ ገነን የለም። የህዝብ አንባ ገነን ከየት የመጣ አስተሳሰብ እንደሆነ ከነማስረጃው እንፈልጋለን። ወያኔ ስንል የትግራይ ህዝብን ማለታችን አይደለም ደቂቀ ወያኔም ስንል ደቂቃኑን እንጂ ሌላ ማህበረሰብን አይደለም። ደቂቀ ወያኔዎች ስህተቱን ቢያጦዙትም ቅሉ ግንባር ቀደም  ድርሻውን የሚወስደው ወያኔ ነውና ለተፈጠረው እልቂት እና ለሚፈጠረው አደጋ ሙሉ ድርሻውን ይወስዳሉ። የኢትዮጵያ ህዝብ የሚታገለው አንባገነናዊ አገዛዝን በማጥፋት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት የሚከበርባትን አገር ለመመስረት ነው እንጂ ዘውዱን ገልብጦ ጎፈርን ለማንገስ አይደለም።

ከተማ ዋቅጅራ
07.05.2017
Emial፡ waqjirak@yahoo.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.