የበላይ ዘለቀ ፎቶግራፍ (ዮፍታሔ)

የዘንድሮው የአርበኞች ቀን የስመ ጥሩው አርበኛ በላይ ዘለቀ ስም ጎልቶ እይታሰበ የተከበረበት መሆኑ ተጠቅሷል – ይልቁንም በአማራ ክልል።

ይህንን ተከትሎ ደግሞ ዶክተር ሽብሩ ተድላ “ከጉሬዛ ማርያም እስከ አዲስአበባ የሕይወት ጉዞዬ እና ትዝታዬ” በሚል ርዕስ ያሳተሙትን መጽሐፍበመጥቀስ ከዚህ በታች የሚታየው የበላይ ዘለቀ ፎቶ የርሱ እንዳልሆነ የሚገልጹ ጽሑፎች ወጥተው እያነበብን ነው።

ይህ ፎቶ የበላይ ዘለቀ ያለመሆኑን ለማስረዳት የቀረቡት ማስረጃዎች ደግሞ በላይ ዘለቀ ጽጉሩን አጎፍሮ እንደማያውቅ የሚገልጹ ናቸው። በማስረጃነትበላይ ዘለቀ ያስቀድስ በነበረበት ቤተክርስቲያን ያገለግሉ የነበሩ ዲያቆናት፣ በላይ ዘለቀ የአባቱን ተዝካር ሲያወጣ አንድ ቀን ያዩት ሰውና የአንድ ሌላምደጃዝማች ምስክርነት ተጠቅሰዋል።

ነገር ግን ይህ በዶ/ር ሽብሩ መጽሐፍ የተጠቀሰው መረጃ ሚዛን የሚደፋ መሆኑን ለማረጋገጥ በሌሎች ሰዎች የቀረቡትን ምስክርነቶች ማቅረብምይጠቅማል።

በመጀመሪያ ስብሀት ገ /እግዚአብሔር በየካቲት መጽሔት 3ኛ አመት ቁጥር 7 ሀምሌ 1972 ዓ.ም ያወጣውን ጽሑፍ እንመልከት። ስብሐት ገ/እግዚአብሔር ይህን ጽሑፍ ያወጣው ለበላይ ዘለቀ በጣም ቅርብ የነበሩትንና፣ በአርበኝነት ዘመኑም ያልተለዩትን የሚከተሉትን ሰዎች ምስክርነት ቃልበቃል (የአካባቢው መለያ ከሆነው የአነጋገር ዘይቤ ጋር) በማስፈር ነው።

ሰዎቹም፦
1. ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ – ከበላይ ዘለቀ ጋር የወንድማማች ልጆች የሆኑ፣ ከበላይ ዘለቀ ጋር አርበኝነቱን ከተቀላቀሉ የመጀመሪያ ሃምሳው የበላይዘለቀ ቤተሰቦች አንዱና በላይ ዘለቀን (በእስር ቤት ካልሆነ በቀር) እስከ ዕለተሞቱ ያልተለዩት፣ በዕድሜ በላይ ዘለቀን 4 ዓመት የሚበልጡትመሆናቸውን የገለጹና በቃለ ምልልሱ ጊዜ የ 74 አመት አዛውንት።
2. ፊታውራሪ ተሰማ ላቀው – የበላይ ዘለቀ የአባቱ ትንሽ ወንድምና በቃለምልልሱ ጊዜ 67 አመታቸው የነበረ።
3. ፊታውራሪ ቀለመወርቅ መዝጊያ – የበላይ ዘለቀ ዋና ጸሐፊ የነበሩና በቃለምልልሱ ጊዜ ዕድሜያቸው 62 ዓመት የነበረ።

እነዚህ ሦስቱም አዛውንት ስለ በላይ ዘለቀ አርበኝነት፣ ባሕሪ፣ ስለጠላቶቹ፣ ስለእሥሩ፣ ፍርዱና አገዳደሉ ልቅም አድርገው ሁሉንም ገልጸውታል።

ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ለተነሣሁበት ርዕስ ጠቃሚ የሆነው ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ የበላይ ዘለቀን መልክ የገለጹበት መንገድ ስለሆነ ወደዚያ እንለፍ።ፊታውራሪ ተሻለ የበላይ ዘለቀን ገጽታና አካላዊ መለያዎቹን ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ፦

“አፍንጫው ሰተት ብሎ ወርዶ ቅጠሉ ነፋ ነፋ ይላል። ከንፈሩ ከበድ ይላል። ጠጉሩ ክርክም ጎፈሬ ጺሙ ሙሉ ለስላሳ። ረጅም ጣቱ መልካም ወተትየተነከረ ነው የሚመስለው ጣቱ። እግረ ቀጭን።”

እውነቱ ይህ ከሆነ ዘንዳ በላይ ዘለቀ ጎፈሬ ያልነበረው መሆኑን በመግለጽ ይህንን ፎቶግራፍ የርሱ አይደለም ከማለት በፊት ዶ/ር ሽብሩ ተድላ ሌሎችንመረጃዎች አገላብጠው ነበርን? በማለት መጠየቅ እፈልጋለሁ።

በፊታውራሪ ተሻለ ገለጻ መሠረት የበላይ ዘለቀን “ክርክም ጎፈሬ” እንጂ በዶ/ር ሽብሩ መጽሐፍ ተጠቅሷል የተባለውን “ላሽ ያስቸግረው ስለነበረ ሁልጊዜፀጉሩን ይላጭ” የነበረውን በላይ አንመለከትም። ይህም ብቻ አይደለም በፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ የተገለጹትን የአፍንጫ፣ የከንፈርና፣ የጸጉር አካላዊመለያዎች ላነበበ ሰው ይህ ፎቶግራፍ የበላይ ያለመሆኑን እንዲጠራጠር ከሚያደርገው ይልቅ ፊታውራሪ ተሻለ በቃል የገለጹትን የሚያረጋግጥናፎቶውን እንዲቀበል የሚያደርግ ነው።

የመረጃዎቹ ምንጭ መሆናቸው የተጠቀሱት ሰዎች ለበላይ ዘለቀ የነበራቸው ቅርበትና የእውቀት ደረጃ ደግሞ በዶ/ር ሽብሩ በመረጃ ምንጭነትተጠቅሰዋል ከተባሉት ሰዎች ጋር ተነጻጽረው መታየት ይኖርባቸዋል። ጽሑፎቹ የቀረቡበት ዘመንም ግምት ውስጥ መግባት ይኖርበታል።

ሌላም አለ። ይህም በ 2004 ዓ.ም የበላይ ዘለቀ መቶኛ ዓመት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ምርምር ተቋም አማካኝነት በተከበረበት ጊዜ ከቤተሰቦቹየተገኘ ፎቶ መሆኑ ተገልጾ በማኅበራዊ መገናኛዎች ሲዘዋወር የነበረ የበላይ ዘለቀ ፎቶግራፍ ነው።

በዚህ ፎቶግራፍ በላይ ዘለቀ በአንድ ዛፍ ሥር ሆኖ አርበኞችን በሩቅ ሲያስተኩስ ይታያል። ይህ ፎቶግራፍ ፊታውራሪ ተሻለ በቃል የገለጹትን የበላይዘለቀ ገጽታ (በተለይም ጎፈሬ) የሚመጥን ከመሆኑም በላይ ከሌላው የበላይ ዘለቀ ምስል ጋር የሚመሳሰል መሆኑ አያሻማም። በዚህ ፎቶግራፍ ላይበላይ ዘለቀ በእጁ ወደፊት ሲጠቁም ስለሚታይ የተሻለ ጥራት ያለውን የፎቶውን ኮፒ ማግኘት ቢቻል ፊታውራሪ ተሻለ ስለ በላይ ዘለቀ እጅየጠቀሱትንም ለማረጋገጥ ይቻል ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ።

 

አንድ ልጨምር። ከዚህ በታች በእጅ ተሥሎ የሚታየው ምስል የሚገኘው በበላይ ዘለቀ ትውልድ ቦታ አካባቢ በእነሴ ወረዳ በምትገኘው የቅድስት ድንግል ማርያም ቤ/ክርስቲያን ውስጥ ነው። በሥዕሉ ላይ በላይ ዘለቀ (ከመካከል) ፊታውራሪ ተሻለ ዓለሙ ከጠቀሱት “ክርክም ጎፈሬ” እና “ሙሉ ለስላሳ ጺም” ጋር በግልጽ ይታያል (ጺሙ ከሌሎች በሥዕሉ ላይ ከሚታዩት ሰዎች የተለየ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል)። ከዚህም በተጨማሪ በሥዕሉ ላይ የሚታየው በላይ ዘለቀ በፎቶግራፉ ከሚታየው ጋር ተመሳሳይ ነው። ሥዕሉ የተሣለበት ጊዜም 1934 ዓ.ም እንደሆነ ሰፍሯል። ይህ ወቅት ጣሊያን ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላ በላይ ዘለቀ በደጃዝማችነት ማዕረግ ቢቸና ላይ በተሾመበት አካባቢና ከመሞቱ ደግሞ አራት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው። ይህ ሥዕል የተሣለበት ምክንያትም “የታመኑ አርበኛ ለእመቤታችን የ ብር ቀለም መጋረጃ ስለሰጡን” ስለሚል በላይ ዘለቀ ለቤተክርስቲያኑ ባስገባው መባ መነሻ መሆኑን የሚያመለክት ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት በዚህ መልክ ለመታሲቢያነት የሚሣሉ ሥዕሎች በምን ዓይነት ጥንቃቄ እንደሚዘጋጁ ለሚረዳ ሁሉ የዚህ ሥዕል ዋጋ ግልጽ ይሆንለታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

 

በመጨረሻም የበላይ ዘለቀ መቶኛ ዓመት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ምርምር ተቋም ሲከበር የበላይ ዘለቀ ቤተሰቦች መገኘታቸውና የበላይ ዘለቀንፋውንዴሽን ለማቋቋምም የነበራቸውን ዓላማ ሲገልጹ ስለሚታይ እነዚህ የበላይ ዘለቀ ቤተሰቦች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ሐሳብ ያካፍላሉ ብዬ ተስፋበማድረግ ጽሑፌን እቋጫለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.