መይሳው ማነው? ሰብእናው፣ ዜና መዋእሉ፣ ራዕዩና አሻራው; (መስቀሉ አየለ)

ሰናፍጭ ቁጥር ፩…….

እንደ መግቢያ
የመይሳውን ታሪክ ከውልደቱ እስከ ሞቱ የተጓዘባቸው ዋና ዋናዎቹን አሻራዎች በዚህች አጭር ጽሁፍ ለመዳሰስ ተሞክሯል። ለአገሩ የነበረውን ራዕይ ;አቅምና ምኞቱን ለማስታረቅ የተንከራተተባቸውን ውጣ ውረዶች፣ ስር ከሰደደው የህብረተሰቡ አስተሳሰብ ጋር የገባበትን አጣብቂኝ፤ ለአንድ ምእተ አመት የፈረሰችውን አገር መልሶ ይሰፋት ዘንድ በየቦታው ፈልተው ክነበሩት ብጫቂና ጉምቱ መሳፍንቶች ጋር ቆላ ወርዶ እና ደጋ ወጥቶ ተፋልሞ ቢያሸንፍም እንደገና ሌሎቹ ከስር እየፈሉና በየግዜው እያፈነገጡ እንዴት እንደፈተኑት ለማሳየት ተሞክሯል።እንደ ንጉስ አንድ ቀን በወጉ ቤተመንግስት አርፎ ሳይቀመጥ በአገር አንድነት ላይ እጃቸውን ያነሱትን ሊቀጣ ቆላ ደጋ ሲል፤ ከወታደሩ ጋር በድንኩዋን እንደኖረ ገና በ ፬፰ አመቱ ያለፈ አሳዛኝ ሰው መሆኑን እንዲሁም ቴውድሮስ እንደ መሪ አገሪቱን አንድ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን አጼ ሚኒሊክና ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ላስቀጠሉት የአስተዳደር ዘመን ጥሎላቸው ያለፈው የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሰረት ግንባታ ምን ያህል የሚያኮራ እንደሆነ መረዳት ይቻላል። ጽሁፉ በዚህም ሳይወሰን ቴዎድሮስን ከመቅደላም ባሻገር አሁን ካለው ትውልድ ጋር በማስተሳሰር እንዴት ዘመን የማይሽረው የብሄራዊ ኩራት ምልክት ሆኖ ዛሬ ድረስ መቀጠል እንደቻለ ተሰምሮበታል።

ክፍል አንድ

የዘር ግንዱ ከአንድ የተከበረ ቤተሰብ ከሚመዘዝ ከአቶ ኃይለ ማርያም ወልደ ጊዮርጊስ እና እዚህ ግባ ከማይባል የደሃ ወገን ከሆነች ወሮ አትጠገብ በ1820 በቁዋራ ተወለደ። ባልታወቀ ምክንያት አገር ጥሎ በጠፋው ወላጅ አባቱ የተነሳ እናቱ የወደፊቱን መይሳውን ይዛ በኮሶ ሻጭነት መተዳደር ጀመረች። ይኽ ስራ በዘመኑ ለታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የተተወ የስራ መደብ ሲሆን ብላቴናው እድሜው አስር እንደደረሰም ለቤተክህነት ትምህርት ወደ ወደ ሳንቃ ተክለሃይማኖት ገዳም ተላከ።ቢሆንም ግን በወቅቱ በደጃዝማች ውቤ እና በደጃዝማች ተክለጻድቅ መካከል በተነሳው ጦርነት መሃል ራስ ይማም የተባለ ጦረኛ ባገኘው ክፍተት በዚህ ገዳም ላይ በፈጸመው ዘረፋ የተነሳ የብላቴናው ካሳ ህይወት ለጥቂት ተረፈ። ውሎ ሳያድር ግን ይሕ ብላቴና ወደ ማህበረ ስላሴ አቀና።ካሳ በዚህ ገዳም ውስጥ የቀሰመው ትምህርት በወደፊት ማንነቱ ላይ የራሱን አሻራ እንዳሳረፈበት ከዜና መዋእሉ መረዳት ይቻላል።

በ1835 ከእርሱ የብዙ ግዜ ታላቁ ከሚሆነው የማር ቀመስ ( ደምቢያ) ገዥ ከነበረው የአባቱ ልጅ ደጃዝማች ክንፉ ጋር መኖር እንደጀምረና የወታደራዊ ክህሎቱ በዚሁ ቦታ እንዳዳበረ ይነገራ፤ ለ ፫ አመት ያህል አብሮ ከኖረ ቦሃላ በደጃች ክንፉ ልጅ ላይ “መይሳው ይነግስበታል” የሚል ንግርት ተሰማ ተብሎ ከቤቱ ቢያሰናብተው መይሳው ወደ ጎጃም ተሰደደ።ሆኖም ግን ከአንድ አመት ቦሃላ በ1839 ደጃች ክንፉ መሞቱን ተከትሎ የደጃች ክንፉ ልጅና አጎትየው ዎልደ ተክሌ በራስ አሊ አሉላና እናታቸው መነን ሊበን ከማንኛውም የውርስ መብታቸው ተገፈው ግዛቱን የመነን ልጅ ለሆነው ብሩ ጎሹ የተሰጠ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ማር ቀመስ በራሳቸው በእቴጌ መነን ስር እንዲጠቃለል ሆነ።

ይህንን የመሳፍንቶች መቆራቆስ በቅርብ እርቀት ሆኖ ሲያጠና የቆየው መይሳው ተመለሰና የሽፍትነት ኑሮውን በቁዋራ አከባቢ አንድ ብሎ ጀመረ። በ1845 ገደማ ዝናው እየገነነ ለእቴጌ መነን ስጋት መሆኑን ያስተዋለው ራስ ኣሊ አሉላ ሴት ልጁን ተዋበችን ያገባት ዘንድ ያቀረበለትን ጥያቄ በአኮቴት ተቀበለ።መይሳው ደምቢያን በ1846 ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጠረ። በ1847 ወደ ጎንንደር ሲያቀና በደጃች አሊና በደጃች ውቤ መካከል የከረረ ጦርነት እየተካሄደ ነበር። በዚሁ አመት በሰኔ ወር ላይ እቴጌ መነን ወደ ጎንደር ተመልሳ መይሳው ላይ ጦርነት ገጥማ ተሸነፈችና ከባለቤቱዋ አጼ ዮሃንስ ሶስተኛ ጋር በምርኮ ስር ወደቀች። መይሳው በዙሪያው ካሉ ተቀናቃኝ የአካባቢ መሳፍንቶች ጋር ከሚያደርገው ጦርነት በተጨማሪም በአጋጣሚ በ1848 ላይ በደባርቅና በሱዳን ከግብጾች ጋር ያልተሳካ ጦርነት ሲያኪያሂድ የግብጾች የስኬት ሚስጥር የታጠቁት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ መሆኑን አጢኖታል።

በራስ አሊና በመይሳው መካከል የነበረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ የተበጠሰው በ1852 ሲሆን ራስ ኣሊም የቴዎድሮስን ግዛት ለደጃች ውቤ እንዲሆን በመወሰናቸው የተነሳ በህዳር ሃያ ሰባት 1852 አም ከደጃች ውቤ ጋር ጉራ አምባ ላይ ተዋግቶ ድል ሲነሳ ወደ ዙፋኑ ለመቅረብ ከፊት ለሚገጥሙት ተከታታይና ወሳኝ ፍልሚያዎች የመጀመሪያው ግልጽ ምልክት መሆኑ ነበር። በመቀጠልም ራስ አሊ የቴዎድሮስን ግስጋሴ ለማስቆም በሚያዚያ አስራ ሁለት ቀን 1853 አም በጌምድር ላይ በጥርሱ ጭምር ቢዋጋም ደብረታቦርም ተቃጥላ በመጨረሻም ራስ አሊ ሸሽቶ ወደ የጁ ገባ። ይህ የራስ አሊ ሽንፈት በብዙ ጸሃፊያን ዘንድ የዘመነ መሳፍንትን ማክተም ዋነኛ ምልክት እና የዘመናዊት ኢትዮጵያ ዳግም ልደት ጅማሮ አድርገው ይወስዱታል።በአመቱ መይሳው የጎጃሙን ባሩ ጎሹን ድል አደረገ፤ በየካቲት ዘጠኝ ቀን 1855 አም ከተዋበች ጋር ሃይማኖታዊ ጋብቻውን ፈጸመ። ውሎ ሳያድርም የመጨፍረሻውን ተቀናቃኙን ውቤ ሃለማርያምን በደረስጌ ጦርነት ድል ካደረገ ቦሃላ በ አቡነ ሰላማ አመካኝነት ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ተብሎ በደረጌ ማርያም ዙፋኑን ደፋ::

፪ የንግስና ዘመኑ (1855 -1868)

በዚሁ አመት አጼ ተዎድሮስ እንደገና መናገሻ ከተማውን ደብረታቦር ላይ የመድሃኔዓለምን ቤተክርስቲያን በመትከል የአቡነ ሰላማን መንበር በዚያው በማጽናት ከመቶ በላይ አመታት ተከፋፍላ በማያባራ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ የኖረችውን አገር እንደ ገና እንደ አዲስ ወደ ማጠናከሩ ላይ አተኮረ።

መይሳው በመጋቢት ወር 1855 ፊቱን ወደ ውሎ በማዞር ግዛቱን የጠቀለለ ሲሆን ከመንፈቅ ቆይታ ቦሃላ በብጹእ አቡነ ሰላማ ታጅቦ ወደ ሸዋ ቢገባም ገና ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ሃይለመለኮት ሞት ቀድሞት ኖሮ አያቲቱ ዘነበ ወርቅ፣ እናቲቱ በዛብሽና ወንድሙ ሃይለ ሚካኤል ያለ ምንም ማንገራገር ለአጼው ሲገብሩ አጼውም ለኃለሚካ ኤል በዚያው ባለበት የሸዋውን መስፍንነት መርድ አዝማች ብሎ አጽንቶለታል።ነገር ግን ሸዋ በሌላ በኩል በቴዎድሮስ ላይ መገዳደሩን በመቀጠሉ አጼ ቴዎድሮስ አሁን ሸዋንም ድል በመንሳት በዛብህን ፣ የሟቹን የኃለመለኮትን ሚስት እንዲሁም የዘጠኝ አመት ወንድ ልጁን ሳህለማርያምን (የቦሃላውን አጼ ሚኒሊክ) በምርኮ ወደ መቅደላ ወሰዷቸዋል።

አጼ ቴዎድሮስ በማርች 1856 ከእስር ቤት ሰብሮ ያመለጠውን ተድላ ጉዋሉን ፍለጋ ወደ ጎጃም በተሻገረበት ሰአት እግረ መንገዱን እንግዳወርቅን አገር ገዥ አድርጎ ሾሞታል። ነገር ግን ተሰማ ጎሹን አግኝቶ ከመግጠሙ በፊት ሰራዊቱ ክፉኛ በወረርሽኝ ስለተመታበትና እንዲሁም የዝናቡን ወራት ለማሳለፍ ወደ ጎንደር ተሻገረ። በዚህ መሃል በአጼ ቴዎድሮስና በቤተክርስቲያኗ መካከል ስለ ግብር አሰባሰብ ያለው ልዩነት በሚታይ ደረጃ ግልጽ ሆኖ የወጣበት ወቅት ላይ ደርሰ።ችግሩን በሽምግልና ለማየት በታህሳስ ወር የግብጹ ፓትሪያሪክ አቡነ ሳይሪል አራተኛ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ወደ ኢትዮጵያ ቢመጡም ቴዎድሮስ ግን ለግብጹ ንጉስ ሰይድ ባሳ ሊሰልሉ ነው የመጡት ብሎ በመጠርጠሩ የተነሳ ፓትሪያሪኩን አስሯቸዋል።

ይህን አመት ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ ከሾማቸው ቦሃላ ጥለውት የጠፉትን አምዴ በሽርና ወንድሙን ሊበንን ፍለጋ በመሃል ኢትዮጵያ ያሳለፈ ሲሆን ከ 1858አም ጀምሮ በቀጥዮቹ አመታት የገጠሙት ተግዳሮቶች ባመዛኙ የሚከዱትን ሰዎች ሁሉ እያደነ በመያዝና በመቅጣት ላይ ያተኮረ ነበረ።የላስታው ዋግሹም ታድነው ከተሰቀሉት ውስጥ አንዱ ነበር። የውቤ የእህቱ ልጅ ንጉሴ ወልደ ሚካኤል በወንድሙ ተሰማ እየተረዳና አልፎም ከትግራዩ የደጃዝማች ሳባጋዲስ ልጅ ከሆነው ካህሳይ ጋር በመሆን ቴዎድሮስን ለመገልበጥ ማሴሩን ገፍተውበታል።በዚህ መሃል ድንገት በተፈጠረ ህመም የተዋበች ከዚህ አለም በሞት መለየት የቴዎድሮስ የውድቀት ቁልቁለት ጅማሮ ነበር ማለት ይቻላል።

ከዚህ ቦሃላ የአጼው ትእግስት እያለቀ ቅጣቱም ይበልጥ እየከፋ መጣ። በ1858 የወሎ ኦሮሞችን አይቀጡ ቅጣት ቀጣቸው፤ ከዚያም ፊቱን ወደ ሸዋ በማዞር በኦክቶበር 1859ኦቤቶ ሰይፉ ሳህለ ስላሴን በመደምሰስ በሸዋ ላይ ፍጹም የበላይነቱን አስጠብቀ። ከ1860 ቦሃላፊቱን ወደ ትግራይ የመለሰው ቴዎድሮስ በዚያው አመት የውቤን ልጅ ጥሩወርቅን አገባ። ጥሩውርቅ የአንድዬ ልጁ የአለማየሁ ቴዎድሮስ እናት መሆኗ ነው።

በዚሁ አመት ጋረድ የሚባለው ንግስናው ይገባኛል የሚል ተቀናቃኝ ሸፈተና ጋሸ ብርሃኑ ዘሪሁን እንዳሉት
“ስም ስታወጣ እናት
ጋረድ ብላለች ከጥንት፤
ወገራ ተክሎ ሲያገሳ
ምነው ዝም አለ ያ ካሳ “ የሚል መልእክት ቢልክበት ወገራ ወርዶ ገድሎታል። ጦርነቱ ግን ቴዎድሮስ እንደቀኝ እጁ እንደ መንገዱ ብርሃን የሚያየውን ሰው ህይወት ጠይቆታል። በአገሪቱ ውስጥ ዘመናዊ አስተዳደር እንዲመሰርት የማማከሩን ሚና የሚጫወተውና ኢትዮጵያዊት አግብቶና ሊቀ መኳስ ተሰኝቶ ይኖር የነበረውን ጆን የተባለው እንግሊዛዊ በዚህ ጦርነት ቴዎድሮስን ተከትሎ በመሄዱ ህይወቱን ማጣቱ በቴዎድሮስ ስብእና ላይ ሌላው ጥቁር ጠባሳ ያሳረፈ ክፉ ህመም ነበረ። ይህ ሰው በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን የቴዎድሮስ ቴያትር ላይ

“ሰው አንድም ከፊደል-አንድም ከመከራ ነው የሚማረው
አንድ ቃል ከፊደል ጥበብ – አንድ ቃል ከመከራ መዝገብ
አንድም በሳር “ሀ” ብሎ- አንድም በ አሳር “ዋ” ብሎ “
ሲል የሚሰማው ሰው መሆኑ ነው።

በተደጋጋሚ በሚደርስበት ሸፍጥና የክህደት ፖለቲካ ነፍሱ ክፉኛ የቆሰለችውና የገዛ ሃሞቱ የመረረው መይሳው በዚህ ጦርነት እጁ ውስጥ የገቡትን ወንድማማቾቹን ንጉሴን እና ተሰማን አይገድሉ አገዳደል ነበር የገደላቸው።

፩፰፮፪ ማለት አንጻራዊ በመሆን በሆነ መልኩ ለአጼ ቴዎድሮስ የተረጋጋ የአስተዳደር ዘመን ነበር ማለት አያስደፍርም። ምንም እንኩዋን በየቦታው በነበሩ መሳፍንቶች ላይ ሙሉ ለሙሉ የበላይነቱን አሳይቶ እንደ አንድ መሪ ቢወጣም በዚያው ልክ መልካቸውን የቀየሩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መፈጠራቸው እረፍት አልባ አድርጎታል።

የግብጾች በሱዳን ጠረፍ አካባቢ የሚያደርጉት ተደጋጋሚ ትንኮሳ ሌላው አሳሳቢ ምክንያት ሲሆን በዚያው ዓመት ከደጃች ተድላ ጋር ጎጃም ላይ በተደረገው ጦርነት ሰባት ሺህ ያህል ወታደሮቹ የገደሉበት ደጃች ተድላ ማምለጥ መቻሉ፣የበዛብህ በሸዋ፣ የጢሶ ጎበዜ በወልቃይት ማመጽ እንዲሁም ላስታ በዋግሹም ጎበዜ (ይኽ ሰው ልጁ ቦሃላ አጼ ተክለ ጊዮርጊስ የሚባለው ነው) እጅ መውደቅ፣ የወጣቱ ሚኒሊክ በጁን 30, 1866 ከእስር ቤት ማምለጥና በዛብህን አስወግዶ ስልጣኑን በሸዋ ማጠናከሩ በእርግጥም ይህ ዓመት የቋረኛው ስልጣን እየተዳከመ እንደመጣ በግልጽ ምልክቶቹ መታየት የጀመሩበት ዓመት ነበር ማለት ይቻላል። የበታች ሹማምንቶቹ በእርሱ ላይ ማሴር የጀመሩበት፣ በየቦታው ያሉ የ አካባቢ ሹመኞች እንዴት ስልጣናቸውን አጠናክረው እንደሚያፈነግጡ ያሴራሉ፤ በተከተለው የመሬትና የአስተዳደር ፖሊሲ ያልተደሰተችው ቤተክርስቲያን ጋር ያለው ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ ሆኗል፤ በመጨረሻም ያ ሁሉ ድካሙ ውሃ እንድበላው እያየ ሲመጣ የደብረታቦርን ከተማ አቃጥሎ በ1867 መንበሩን ወደ መቅደላ አዛወረ።

የቴዎድሮስ ፍጻሜ

የቴዎድሮስ ፍጻሜ አይቀሬ ወደ መሆን ያመራው ከ1862 አም ጀምሮ የነበረው አጨቃጫው የእንግሊዛውያን እስረኞች ጉዳይ ሲሆን በኦክቶበር 1867 አም እስረኞቹን ለማስለቀቅ ዙላ የደረሰው የእንግሊዝ ወደ መቅደላ መንጎድ ሲጀምር ከአካባቢ ታጣቂዎች ምንም አይነት ተቃውሞ ሳይገጥመው እንዲጓዝ ከሰሜኑ ሚሊሻ ( ካሳ መረሳ) ከፍተኛ እገዛ እየተደረገለት መቅደላ የደረሰው ወራሪ በኤፕሪል 10 ቀን 1868 አም አሮጌ ፈላ ላይ በተደረገው ውጊያ የቴዎድሮስን ጦር ሲያሸንፍ በውጊያውም ገብርየ የተባላው ዋነኛው የቴዎድሮስ ጀነራል ተሰዋ።በመጨረሻም በኤፕሪል 13 ቀን 1868 የፋሲካ ማግስት በማዕዶት ሰኞ እራሱን መስዋእት በማድረጉ የአጼው ፍጻሜ ሆነ።

እስረኞቹን በእጁ ያደረገው የእንግሊዝ ጦር የሚዘርፈውን ዘረፈና መግቢያ በር ከመክፈት ጀምሮ ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ በየደረጃው የሚቻለውን ያህል ድጋፍ እያደረገና መንገድ እየመራ መቅደላ ድረስ ላደረሰው የትግራዩ ካሳ መርሳ ባንዳ ሆኖ ለፈጽመው አሳፋሪ ተግባር ለውለታው እስካፍንጫው መሳሪያና ቁሳቁስ በማውረስ ውለታውን መልሶና የመይሳውን አንድያ ልጅ ብላቴናውን ልዑል አፍኖ አለማየሁ ወዳ ገሩ ተመለሰ። ካሳ መርሳ ማለት በኋላ አጼ ዮሃንስ አራተኛ ተብሎ የነገሰው መሆኑ ነው።

( ተጨማሪ:– አጼው ያንን ሁሉ መሳፍንት ገንድሶ ማእክለዊ ስልጣኑን ሲያጠንክር ከንጉስ ኢዛና ጀምሮ በየደረጃው የነበረውን የወርቅና የዝሆን ጥርስ እንዲሁም ቅርሳ ቅርስ የመሳሰሉትን ከፍተኛ የሃብት ክምችት ከየመሳፍንቶቹ ለመማረክ ችሎ የነበረ ሲሆን አንድ በቅርብ የማውቀው ሰው የብሪቲሽ ሙዚየምን ሲጎበኝ ያጋጠመውን በወቅቱ ከነበረችው የሜዲቫል ፔሪየድ አስጎብኝ የገጠመውን እይታ እንዲህ ሲል ቃል በቃል ነግሮኛል። እንደ ባለሙያዋ ትንታኔ ” መቅደላ የደረሰው የእንግሊዝ ወራሪ ሃይል ያንን ሁሉ ቅርስና ንብረት በእጁ አስገብቶ በልዋጩ ለትግራዩ ባንዳ አጼ ዮሃንስ አሮጌ ጠመንጃ ለውለታው ሰጥቶ ነበር የወጣው።ይህ ከፍተኛ ሃብት እንግሊዝ ከዚያ በፊት እምብዛም ትኩረት ሰጥታው ያልነበረንን አፍሪካን ቅኝ የመግዛት ፍላጎት እንዲጨምር በር መክፈቱ ብቻ ሳይሆን የቀረውን አፍሪካ ለመውረርም ምንም አይነት ተጨማሪ ወጭ ሳያስፈልገን ከመቅደላ በዘረፍነው ሃብት ብቻ አላማችንን ዳር አድርሰናል። በመሆኑም እኛ የያኔዋን ኢትዮጵያ የምናያት አፍሪካን ቅኝ እንድንገዛ እስፖንሰር ያዳደረገችን አካል አድርገን ነው” ነበር ያለችው ሲል በመገረም ስሜት ነግሮኛል )

ክፍል ሁለት
የመይሳው ራዩና ተግዳሮቶቹ

፩ የመይሳው የውጭ ፖለቲካና ከአውሮፓውያን ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ያደረገው ጥረት…

ምንም እንኩዋን የአውሮፓውን ጉዳይ በግዜው ለነበሩ መሳፍንቶች እንግዳ ባይሆንም ነገር ግን እንደ መሪ ለኢትዮጵያ ራሱን የቻለ የውጭ ፖሊሲ እና እስትራቴጅ እንዲኖራት የቀየሰ የመጀመሪያው መሪ አጼ ቴዎድሮስ ነበረ። እራሱን የቻለ አለማቀፋዊ ፕሮጀክት በመቅረጽ አዲሲቷ የክርስቲያን አገር በወጭ ንገስታት ዘንድ የራሷ የሆነ ቦታ እንዲኖራት አጥብቆ ይፈልግ ነበር።ግብጾችን ከቀይ ባህር ጠራርጎ በማውጣት የራሱ ሆነ አስተማማኝ የባህር በር እንዲረው ማድረግ አንዱ የቴዎድሮስ ወሳኝ የውጭ ፖሊሲ እስ ትራቴጂ እንዲሆን የፈለገበትም አቢይ ምክንያቱ ለዚሁ አውሮፓውያን ጋር እንዲኖረው ለፈለገው የንግድ፣ የፖለቲካና የስራቴጅ ግንኙነት ቁልፍ ነገር መሆኑን ሲሆን የዚያኑ ያህል ደግሞ አውሮፓውያን በጥንቃቄ ካልተያዙም በሂደት በአገሪቱ ህልውና ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን አደጋም ጠንቅቆ ያውቀው ነበረ።

ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን የማዘመን ህልሙን ዳር ለማድረስ እንደ መነሻ የተጠቀመባቸው በግል ያቀረባቸውና ቦሃላም እስከመጨረሻው አብረውት ያልተለዩ ቤል እናፕላውደን ሲሆኑ በቀጣይነትም ሚሽነሪ እየሆኑ ከ 1855 አም ጀምሮ በቀጣይነት ወደ አገሪቱ ውስጥ የገቡት እንደ ክራፕፍ፣ ፍላድ፣ዋልድማየርና ሳልሙለር የተባሉ ሚሽነሪዎችች ተጠቃሾች ናቸው።
በማስከተልም ቴዎድሮስ ተደጋጋሚ ደብዳቤ ከጻፈላቸውና የእደጥበባ ሙያ ያላቸው ሰዎች እንዲልኩለትና ለአውሮፓውያን ቴክኖሎጅ ያለውን ጉጉት ከገለጠላቸው ነገስታት መካከል ጥቂቶቹ ናፖሊዮን ሶስተኛ፣የራሽያው ኒኮላስ አንደኛ እንዲሁም ንግስት ቪክቶሪያ ይገኙበታል።

ቢሆንም ግን በወቅቱ እንግሊዝ ቱርክን በተመለከተ ትከተለው የነበረው የውጭ ፖሊሲ በተለይም በ1860 አካባቢ በመግባባት ላይ የተመሰረተ እንደ ነበረ አጼ ቴዎድሮስ ምንም አይነት ግንዛቤ አልነበረውምና በተለይም ለንግስት ቪክቶሪያ በተደጋጋሚ ይልካቸው የነበሩት ደብዳቤዎች በመተማ አካባቢ በየግዜው ትንኮሳ ከሚፈጥሩበት ግብጽና ሱዳን፣እንዲሁም ቀይ ባር ላይ እስከ-ከተሙት ቱርኮች ሁሉንም ከመጠራረግ ባሻገር ቀይ ባህርን ተሻግሮ የጌታ አገሩን እየሩሳሌምን ከቱርክ እስላሞች ነጻ የማውጣት አላማ እንዳለው የሚገልጡት ምኞቶቹ ይበዙበት ነበር። ሆኖም ግን ለአንዳቸውም ደብዳቤዎች ከንግስቱዋ ምንም አይነት መልስ ማግኘት ባልቻለ ግዜ ቴዎድሮስ በጣም መከፋት መጀመሩ ብቻ ሳይሆን ብቻ ሳይሆን ካሜሮን የተባለው እንግሊዛዊ ከ አገሩ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በደረሰው የውስጥ ትእዛዝ መሰረት በተወሰነ ደረጃ እራሱን ከቴዎድሮስ እንዲያርቅ ብሎም ምንም አይነት አስተያየት እንዳይሰጥ ሲነገረው ግዜ ቴዎድሮስም እንግሊዞች ከቱርክ ጋር ማበራቸውን ከሁኔታው በመረዳቱ ሚሽነሪዎቹን በማሰሩ ሁኔተው ወደ ከፋ ደረጃ ተሸጋገረ።

ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ ተሃድሶ

ከቴዎድሮስ በፊት የነበሩት መሳፍንቶች እንደ የአቅማቸው የአገሪቱን ጦር የማዘመንም ሆነ የእደ ጥበባት ሙያ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆም በቴዎድሮስ ደረጃ ማእከላዊነትን ያስከበረና እንደ አንድ አገር መሪ በሰለጠኑት የውጭ መንግስታት ዘንድ ሳይቀር እውቅናን ያገኘ መሪ አልበረም።

አጼ ቴዎድሮስ ለአዳዲስ የቴክኖሎጅ ፈጠራዎች (ቴክኖሎጂካል ኢኖቬሽን) የነበረው ጉጉት፣ ከጋፋቱ የመድፍ ስራ ውጥን ጀምሮ፣ በመንገድ ስራ፣ መርከብ፣ መኪና የህትመት ማሽን ለመስራት የሄደበት ደረጃ፤ አስተዳደራዊ መዋቅሩን በተመለከተ “ሁሉንም ነገር ጠቅልየ እንደፈለኩ ላድርግ” ሳይል ተጠሪነታቸው በቀጥታ ለእርሱ የሆኑ የአካባቢ አስተዳዳሪችን በመሾምና ከዚያ በፊት ባልታየ ደረጃ አገሪቱ በሁሉም ዘርፍ የመረጃ ምዝገባ አሰራር (Registration) ያስጀመረበት ሁኔታ ነው የነበረው።ከሁሉም በላይ ግን አገሪቱ በታሪኩዋ ለመጀመሪያ ግዜ በቋሚነት ደመዎዝ የሚከፈለውና ሁልገዜም ዝግጁ የሆነ የዘመናዊ ወታደር ግንባታ የተጀመረው በእርሱ ዘመን መሆኑ አንዱ ወሳኝ ምእራፍ ነው::

ጎታች የሆኑ ልማዶችን በማስወገድ እረገድ የመይሳው ጅማሮ ቀላል አልነበረም። የባሪያ ፍንገላን በአዋጅ የሻረ፣ ከአንድ በላይ ጋብቻን እንዲሁም የጥቁር ደምን የበቀል ባህል በህግ ወንጀል ያደረገ፤ የጠቅላይ ፍርድ ዳኝነቱን ለራሱ በማድረግ ነገር ግን ሌሎቹን ወንጀሎች በተቀላጠፈ መልኩ በዚያው በየጥቢያው በኩል በፍትሃ ነገስት እንዲታይ በማድረግ የወንጀልን መጠን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ የቻለ ሰው ነበር መይሳው።

በቤተክርስቲያን የአገልጋዮችን ቁጥር በመቀነስና፣ ቤተክርስቲያኑዋ አላግባብ ይዛዋለች ብሎ ያሰበውን መሬት በመውረስ የገቢ ምንጩን እየገነባው ለነበረው የአገር መከላከያ ሰራውት በጀት ማድረጉ ሁሉ ተጠቃሾች ናቸው።

በምሁራን ዘንድ አከራካሪ ሰብእና አለው የሚባልለት መይሳው ምንም እንኩዋን አንድ ብሎ ወደ ስልጣን የመጣባቸው ውስብስብና እልህ አስጨራሽ ተጋድሎው በዝርዝር እንደሚታወቀው ከፊቱ የቆሙትን መሳፍንት ሁል አንድ ባንድ እየገነደሰ ወደ መጨረሻው የስልጣን ከፍታ የደረሰ፣ በደረስጌ ማርያም በአቡነ ሰላማ እጅ ዙፋኑን ሲደፋ የቀደሙት የኢትዮጵያ ነገስታት ዘራቸውን ከንጉስ ሰሎሞን እየቆጠሩ ሲነግሱበት የነበረውን ስርዓት አልተከተለም። ያም ሆኖ ግን አጼ ቴዎድሮስ ንግስናው ከእግዚአብሔር እንደሆነ ከልቡ ያምን የነበረውን ያህል በሂደት እራሱን ከሶሎሞን ስሮው መንግስት ጋር አስተሳሮዋል። ( RubTew 49; Crummey 1988: 17–23 )

በጥቅሉ መይሳው አገሪቱን ለማዘመንና የህብረተሰቡን አስተሳሰብ ለመለውጥ የሄደበት ወደ ጽንፍ የተጠጋና ሃይል ጭምር የተቀላቀለበት እርምጃው ዋጋ አስከፍሎታል። ይልቁንም በቤተክርስቲያን እና በህብረተሰቡ መካከል የነበረውን በጣም የተሳሰረ ግንኙነት አቅልሎ ማየቱ፣ እርምጃውን ተቁዋማዊ ቅርጽ ከመስጠት ይልቅ በግል ፍላጎቱና ጥረቱ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አካሄድ ማድረጉ፣ እራእዩን ዳር ለማድረስ እንቅፋት ሆኖበታል።

እንደ ማጠቃለያ ሲታይ ምንም እንኩዋን ቋረኛው ብቻውን ነዶ ያለፈበት አገሪቱን የማዘመን ሂደት እድሜ ሰጥቶት በአይኑ ባያየውም ቅሉ መውጣት መውረዱን ባዩ ግዜ፣ ከዙፋን ወርዶ በባዶ እግሩ ከተራው ወዛደር ጋር መንገድ ስራ ሲቆፍር በመዋሉ “ይኽ የንጉስ ላይህ የሌለው” እየተባለ ሲሸሞርበትም ሁሉ ሁኔታውን በግዞት ላይ ሆኖ ለመከታተል እድል ላገኘው ወጣቱ ሚኒሊክም ሆነ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአገሪቱ ላይ ሰርተው ላሳዩት የሶሽዮዮ ኢኮኖሚ እምርታ ፈር ቀዳጅ (ፋና ወጊ) እንደሆነላቸው አያጠያይቅም።

አጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን

መይሳው በጣም ሃይማኖተ፣ በጣም ወግ አጥባቂ በሆነ ኦርቶዶክሳዊ ዶግማ ያደገ ከመሆኑም ባሻገር የጠነከረች ቤተክርስቲያን እና መሰረታዊው የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ለሞናርኪው ጥንካሬም ሆነ ለ አገር እድገትና ህልውና የሚኖረውን አስተዋጾ በደንብ የተገነዘበ ሰው ሲሆን ኢትዮጵያን እንደክርስቲያናዊ መንግስት ብቻ የሚያይ ብቻ ሳይሆን አልፎ ተርፎም የእስልምና አስተምህሮ ለአገሪቱ ጠንቅ ነው ብሎ ከልቡ የሚያምን መሪ ነበር። በቴዎድሮስና በቤተክርስቲያኒቱ መካከል ጸቡ አንድ ብሎ የፈነዳው ዙፋኑን በደፋ ብዙም ሳይቆይ በተከተለው የመሬት ፖሊሲ የተነሳ ሲሆን በዚህም በተደጋጋሚ ከሊቀጳጳሱ አቡነ ሰላማ ጋር ቢጋጭም በጣም ታላላቅ የተባሉት ሊቃውንተ ቤተክክርስቲያን ጣልቃ እየገቡ ሲያስታርቁ ኖረው በመጨረሻውም በ፩፰፮፬ አም በአቡኑ መቅደላ ላይ መታሰር ሂደቱ ተጠናቀቀ፣

ምንም እንኩዋን መይሳው በግሉ በጣም አጥባቂ ሃይማኖተኛና ጸረ እስላም የነበረ ቢሆንም የካህናት የስራ ድርሻ እንዲወሰንና በሌሎችም ተዛማች አስተሳሰቦቹ እንዲሁም ይህንን ለማስፈጸም ይሄድበት የነበረው የሃይል እርምጃና መጸሃፍ ቅዱስ በአማረኛ እንዲሰበክ ያሳየው ፍላጎት ሁሉ ተደማምረው የመገለል ህይወት እንዲደርስበት ብሎም ለውድቀቱ መፋጠን አይነተኛውን ድርሻ ተጫውተዋል።

ቴዎድሮስ የብሄራዊ ጀግንነት ምልክት ሆኖ የመውጣቱ ነገር

ምንም እንኩዋን አንዳድ ምሁራን ስለ መይሳው አወዛጋቢ ሰብእና እንዳለው አድርገው ለማቅረብ ቢሞክሩም እርሱ ግን የዘመናዊት እትዮጵያን ምስረታ መሰረት የጣለ የሃያኛው ክፍለ ዘመን አንጸባራቂ ኮከብ ሆኖ መውጣቱ አይን የማይታሽበት እውነታ ሲሆን መይሳው ማለት የአዲሱ ትውልድ የብሄራዊ ስሜት አይዲዮሎጅ ሆኖ መውጣቱን ለአፍታ መጠርጠር አይቻልም።ቀጣዩ የፊደል ሰራዊት ትውልድ ምልክት ከሆኑት ግርማቸው ተክለሃዋርያት፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ አቤ ጉበኛና ጸጋየ ገብረመድህን በደማሙ ብእራቸው የቴዎድሮስን ዜና ማዋእል ስጋና ደም አልብሰው ለዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ይሕንን ገናና ንጉስ እንደ ገና በአካል እንዲያዩት፣ እንዲያዘክሩት፣ በፍቅሩ እንዲሰክሩለት፣ በስሙ እንዲሞቱለት አድርገው አልፈዋል።መይሳው ዛሬም ድረስ የአትንኩኝ ባይነት፣ እና የአስቸናፊነት ስነልቦና ምልክት ሆኖ መንፈሱ በሰሜን ተራሮች አናት ላይ እንደናኘ ይቀጥላል።

………..ማነህ አንተ የጎንደር ሱሪ ስንት ነው………………???!!!!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.