የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፤ በአዲስ አበባ አስተዳደር ውስጥ ጥቅሙን መጠየቁን አረጋገጠ::

አሚርአቦክር

በኢፌዲሪ ሕገመንግሥት መሠረት ኦሮሚያ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ያለውን ጥቅም በተመለከተ የኦህዴድ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዝርዝር ሠነዱን ለሚመለከተው አካል ማቅረቡን ክልሉ ማረጋገጫ ሰጠ። ሆኖም በማኅበራዊ ድረገጾች ስለተሰራጨው ሠነድ ጉዳይ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስተባብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሰንደቅ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ምላሽ፣ “የኦሕዴድ ሥራ አስፈፃሚ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት፣ በሕገመንግስቱ በተቀመጠው አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 መሠረት የልዩ ጥቅም አተገባበርን በተመለከተ መካተት አለባቸው ያሏቸውን፤ ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ዘርዝረው ለሚመለከተው አካል አስተላልፈዋል። እስከዚህ ድረስ የሚታወቅ ነገር አለ” ብለዋል።

“የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጥናትሰነድ ነው እየተባለ በመገናኛ ብዙሃን እና በማሕበራዊ ድረ ገፆች ተለቋል። ይህንን የጥናት ሰነድ ወይም በአንዳንዶች ረቂቅ ሰነድ ተብሎ ስለተዘገበው ጉዳይ በክልሉ የሚታወቅ ነገር አለ? ወይም በክልሉ ነው የተዘጋጀው? ወይም በዚሁ ጉዳይ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?” ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ አቶ አዲሱ በሰጡት ምላሽ፣ “ወደኋላ ሄጄ የተዘጋጀው የጥናት ሰነድ ነው …ረቂቅ ሰነድ ነው ..እንትን ነው ስለሚባለው የማውቀው ነገር የለም። ረቂቅ ሰነድ የተባለውም እንዴት በዚህ መልኩ ለአደባባይ እንደሚበቃ የምናውቀው ነገር የለም። እንዲሁም ኦሕዴድ ነው ያዘጋጀው… እገሌ ነው ያዘጋጀው ስለሚባሉት ነገሮች ቢሆኑም፣ ረቂቅ ሰነድ የማዘጋጀት ሥልጣን የእኛ የሥራ ድርሻዎች ባለመሆኑ አስተያየት ለመስጠት እንቸገራለን። ሕግ የሚያወጣው ሕግ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አካል በመሆኑ፣ በእኛ በኩል የተለየ አስተያየት የምንሰጠው ነገር የለም።” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።
ይህ የተሰራጨው ረቂቅ ሰነድ ወደ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ተላልፏል የሚሉ ወገኖች አሉ። በዚህ ነጥብ ላይ ምን ይላሉ? ላልናቸውም፣ “መተላለፉን አላውቅም። የሕግ ረቂቅ የማውጣት ስልጣኑም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመሆኑም፣ በእኛ በኩል በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሰጠው አስተያየት የለም።” ሲሉ አቶ አዲሱ አረጋ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.