አባ ኮስትር ማነው? (መስቀሉ አየለ)

ደጃዝማች በላይ ዘለቀ (1902 ወሎ – 1938 አዲስ ከተማ)

ሰናፍጭ ቁ ፪
(መስቀሉ አየለ)

በላይ ዘለቀ ዘመን ተሻጋሪ ስመ ጥር አርበኛ ሲሆን በምድረ ጎጃም ላይ ለአምስት አመታት ያህል የፋሽት ከጣሊያንጋር በተደረገው ትንቅንቅ እንደ ተራ የጓድ መሪ ተጋድሎውን ጀምሮ በአጭር ግዜ ውስጥ እንደ መብረቅ አስፈሪነጎድጓድ መሆን የቻለ ነገር ግን በድል ማግስት የጠፋ አንጸባራቂ ኮከብ ነው።

በላይ ዘለቀ ትውልዳቸው ብቸና ከሚሆን፣የልጅ እያሱ የግል አጃቢ(ቦዲ ጋርድ ) ከነበሩ ባሻ ዘለቀ ላቀውና ከወሎየዋ ወላጅ እናቱ ወሮ ጣይቲ አሻኔ 1902 በውሎ አማራ ሳይንት ተወለደ።

ልጅ እያሱ ላይ መፈንቅለ መንግስቱ እንደተፈጸመ ብዙም ሳይቆይ ባሻ ዘለቀ ወደ አማራ ሳይንት ተመልሰው ሁለቱን ልጆቻቸውን በላይንና ወንድሙን እጅጉን ይዘው ወደ ጎጃም አቀኑ። ብቸናም እንደደርሱ የአካባቢው ገዥ በታጣቂዎች ቤታቸውን አስከብቦ ባሻ ዘለቀን እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠይቃቸውም ባሻው ግን ፈቃደኛ ባለመሆን እስከ መጨረሻው ተዋግተው ቆሰሉና ተያዙ፤ በመጨረሻም በሁለት ወንድ ልጆቻቸው ፊት ተሰቀሉና ፍጻሜያቸው ሆነ።ይኽ ትራጀዲ የወደፊቱን አባ ኮስትር በላይ እንደገና አቡክቶ ጋገረው ማለት ይቻላል።ከዚህም ቀን ጀምሮ ጥቃትን በበቀል ማወራረድ የበላይ ሁለተኛ ተፈጥሮው ሆኖ በውስጡ ህይወት መዝራቱን ቀጠለ።

ቁጭት ከጥፍሩ ጀምሮ የሚነዝረው ትኩሱ ትንታግ በላይ ጥቂት ዘመዶቹን አስከትሎ ወደ አባይ በረሃ ለመውረድ ግዜ አልወሰደበትም።ይልቁንም በጥቂት ሰዎች የተጀመረው ይኽ የበላይና የባልደረቦቹ ዱር ቤቴ ያሉበት የሽፍትነት ኑሮ የተከታዮቻቸው ቁጥር እየጨመረና የበላይም ስም እየገነነ ሄደ። ይኽ የሆነው እንግዲህ ቅድመ ጣሊያን ወረራ መሆኑ ነው።

ይኽ በዚህ እንዳለ የጣሊያን ኢትዮጵያን መውረር ዱር ቤቴ ብሎ አባይ በረሃ ለከተመው አባ ኮስትር በላይ ወደ ላይኛው ሰገነት የሚያወጣው የክብር መሰላል ሆነለት። ጀግና በክፉ ቀን ይወለዳልና በላይ ዘለቀም ፋሽስቱን ለመዋጋት ከውሳኔ ላይ ይደርሳል። ይኽ በሆነ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከማርቆስ ወደ ብቸና የሚጓዝ የጣሊያን ኮምቦይ አገኘና በሙሉ ገድሎ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ወሰደ።ተከታዮቹንም ይበልጥ በመሳሪያና በላቀ ብሄራዊ ወኔ አስታጥቆ የጥቃት ወረዳውን በማስፋት በወሎ፣ በድፍን ጎጃምና በሸዋ ምድር በድል ምንጣፍ ላይ የሚራመድ የማይቆረጠም የብረት አለሎ ሆነ።በህዝቡ ልብ ውስጥ የኩራት ምልክት ፤ ሁሉ በስሙ የሚገጥሙለት ፤ በየምሽቱ የሚወደስ ፤ የተከታዮቹም ብዛት ለቁጥር የሚያታክት ሆነ። በአጭሩ በላይ ማለት በራሱ ግዜ በደቀመዛሙርቱ ላይ እራሱን ለማንገስ የሞራል የበላይነቱን ወሰደ፤ እንደ የድካማቸውም ፍሬ፣ እንደ ብርታታቸው መጠን ቀኝ አዝማች፣ ፊታውራሪ፣ ደጃዝማች እንዲሁም ራስ እያለ በማእረግ ለተጋድሎዋቸው እውቅና ሰጠ።በወቅቱ የደጃዝማችነት ማእረግ የተሰጠው የገዛ ወንድሙ አንድ ጥያቄ ጠይቆት እንደነበር ይነገራል፤ ዕሁሉንም የማእረግ አይነት አድለህ ጨረስክና ላንተ የቀረኽ ምን ይሆን፧ዕ ቢለው አባ ኮስትር የወንድ ቁና ግን ዕአንድ ግዜ እናቴ በላይ ብላኛለችና ምን ያደርግልኛልዕ ማለቱ ይነገራል።

የነጻነት ቀን ስትመለስና የወደቀችው ባንዲራ ስትነሳ ንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲመለሱ የበላይ ጦር በሚያስፈራ ግርማ በንጉሱ ፊት ያለ ማቁዋረጥለ ሰዓታት እንደ አባይ ወንዝ ፈሰሰ።በአርበኞቹ ብዛትና ወኔ የተደመሙት ንጉሱ “ምን ላደርግልህ ትወዳለህ?!” ሲሉ ጠየቁት፤ “እኔ ምንም አልፈልግም፤ ነገር ግን ለነዚህ አርበኞች የሰጠኋቸውን ማእረግ ያጽኑልኝ” ነበር ያላቸው።በመጨረሻም ንጉሱ ለበላይ ዘለቀ የደጃዝማች ማእረግ ሰጥተው የብቸና አስተዳዳሪ አድርገው በወላጅ አባቱ የትውልድ መንደር ላይ ሾሙት።

ነገሩ የሚጀምረው ከዚህ ቦሃላ ነው። ብቸና በሹመት ሳለ የቀድሞ የበረሃ አርበኞችን በየቦታው እንዲሾሙለት ይፈልጋል። ነገር ግን የጎጃም ጠቅላይ ግዛት አስተዳዳሪዎች በዚህ ድርጊቱ ላይ ደስተኛ አልነበሩም። በሌላ በኩል እነርሱ በተጋድሎው ዘመን ባንዳ የነበሩትን ሁሉ በመሾም ተጠምደዋል፤ ይኽ ሸፍጥ ደግሞ ለበላይ ሌላው ተጨማሪ ህመም ሆኖበታል፤ አለመግባባቱ ከግዜ ወደ ግዜ እየከፋ ሲመጣ የጠቅላይ ግዛቱ ሹመኞች ወደ ንጉሱ ማሳበቁን ተያያዙት፤ “የግርማዊነትዎን ትዕዛዝ ሳይቀር የማይቀበልና እራሱን ከህግ በላይ አድርጎ የሚያይ በመሆኑ መስራት አልቻልንም” ሲሉ አጥብቀው ቢወተውቱ ንጉሱ በላይን አስሮ የሚያመጣ ጦር ከአዲስ አበባ ወደብቸና አዘመቱ። ይኽን እርምጃ ከክህደት የወሰደውና በቀልና እያመነዥከ ያደገው በላይ እንዲሁ ተይዞ በባንዶች ፊት መዋረድን ምርጫው ሊያደርግ የሚችልበት ሰብዕና የለውምና ወደ ሶማ ተራራ ሸፈተ።

ከአዲስ አበባ ድረስ ተነድቶ የመጣው የንጉሱ ጦር ከአንድ በላይ ጋር ቢገጥምም እጣ ፋንታው እንደ ክረምት አግቢ መርገፍ ሆነ። በላይ የወንዶች ቁና እንደገና በተፈጠረበት፣በኖረበት የሽፍትነት ማህጸን ውስጥ ዳግም መጋሙን ቀጠለ። የላኵትን መናጆ ሁሉ እስኪሰለቸው ገደለላቸው። ።ከዚህ በኋላ እርሱን ለመያዝ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ትርጉም አልባ መሆኑን የተረዱት ንጉሱ ምህረት ያደረጉለት መሆኑን በመግለጽ እጁን በሰላም ሰጥቶ እንዲመለስ አማላጅ ልዑካን ላኩበት።

የንጉስ ቃል እንደ እግዚአብሔር ቃል ነው። እንዲህ በመናኛ ነገር ይታጠፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ወቅቱ “የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” የሚለው ስነ ቃል የህብረተሰቡ የሞራል የውሃ ልክ ሆኖ በሆነበት በዚያ ዘመን አባኮስትር በላይ የንጉሱን ማተባቸውን ተስፋ አድርጎ እጁን ለይቅርታና ለሰላም ቢዘረጋ አይገርምም። ያለመታደል ሆኖ ግን ይህ “የደግ ግዜ ባላገር የክፉ ግዜ ወታደር፤እጁ መንሽና ጠመንጃን እኩል የሚያውቅ ” ተብሎ የተነገረለት አርበኛ ለሴራ ፖለቲካ እንግዳ ነበረና ለሰላም የተዘረጉት እጆቹ እጣ ፋንታቸው በእግረ ሙቅ መጠፍነግ ሆነና በአፋጣኝ በተዋቀረ አስቸኳይ የፍርድ ችሎት እንደ እራፊ በሚንቃቸው ባንዶች ፊት ለፍርድ ቀረበ። ጉዳዩን ያስቻለውም ችሎት ክሱን መርመርኩ ብሎ የሞት ብይን ሰጠበት።ነገር ግን ንጉሱ የአርበኝነት ዘመን ተጋድሎውን ግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔውን ወደ ዕድሜ ይፍታህ ቀየሩለትና ቀሪ ዘመኑን በእስር ሊገፋ ወደ ታላቁ ቤተመንግስት ተወሰደ።

የጣሊያን ባንዳ ሆኖ በአገርና በወገን ላይ ግልጽና ከባድ ክህደት የፈጸመ ነው ተብሎ በዚሁ ቤተመንግስት ልጅ ማሞ ሃይለሚካኤል የሚባል አንድ ነውረኛ ሰው ባጋጣሚ ከበላይ ጋር ይታሰራል። እለት እለት በላይን በሚፈጥርበት ጫና አማረረው።”አንተ አገሬ ብለህ ምን ተጠቀምክ?፤ እኔስ ባንዳ ተብዬ ካንተ በላይ ምን ተጎዳሁ?፤ የኔስ ባንዳነት አንተ ላይ የሞት ፍርድ ከፈረዱት ዳኞች ባንዳነት በምን ይብልጣል?፤ አይንህን አልገልጥ ብለህ አገር፣ ድንበረ፣ ንጉስ ባንዲራ ስትል መጨረሻህ እንደኔ ዘብጥያ ሆነ ” እያለ እለት-እለት የሚወጋው መርፌ ክፉኛ ቢጠዘጠዘው በዚህ ሰውየ ንጝግር የተማረረው በላይ እስር ቤቱን ሰብሮ ለማምለጥ ያልተሳካ ሙከራ አደረገ።

በመጨረሻም በማጎንበስ ሳይሆን እንደ አንበሳ ደረቱን በመንፋት፤ ከፍ ባለ የስነልቦና የበላይነት፤ እንደ ንስር አይን በሚወጉ አይኖቹ ዙሪያ ገባውን እየቃኘ በፉከራና በቀረርቶ ወደ ተዘጋጀለት ገመድ አመራ፤ “አንች አገር ወንድ ልጅ አይብቀልብሽ!!!” ብሎ የወንድ ቁናው በላይ ዘለቀ ከወንድሙ እጅጉና ከሌሎች አርበኞች ጋር በጥር 4 ቀን 1938 ዓም አዲስ ከተማ ላይ ተሰቀለ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.