እናት! – መልካም የእናቶች ቀን (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

ንቃት ሥልጣኔ፣ የሰው ልጅን ስለረዳ፤
ጥቂት አቅሎት ይሆናል፣ የእናትነትን ዕዳ፡፡

እሱም አልፎ አልፎ እንጅ፣ በዓለም ሲታይ ግን በጥቅሉ፤
እናት ብቻዋን ናት፣ ልጅ ለሚያስከፍለው ሁሉ፡፡

በእንስሳቱ ዓለምማ፣ አሁንም እስከ መቸው፤
ተጀምሮ እስኪፈጸም፣ የእናት ብቻ ነው ዕዳው፡፡

እናት ለምትከፍለው፣ ለዚያ ሁሉ ዋጋ፤
የተሰጣት ምላሽ፣ የመወደድ ጸጋ፤

በቂ አይደለምና፣ ሌላም ነገር ካለ፤
ከመወደድ በላይ፣ የበዛ ላቅ ያለ፤

ከመመለክ በታች፣ የአንዱ አምላክ ነውና፤
ሁሉ ይገባታል፣ ለእናት ሁለንተና፡፡

ከእርሷ በላይ ልጇን፣ ለምታይ ስስታም!
አፍቅራ ለማትጠግብ፣ ለማትሰለች ድካም!

ለልጅ ባላት ፍቅር፣ ለማትጨርስ ሰጥታ!
ራሷን ለምትሠዋ፣ ሳታመነታ አፍታ፤

ይሰጣት! ይቸራት!፣ ይታደላት! በሉ፤
ባለዕዳዎች ናቹህ፣ ሁሉንም ክፈሉ!
ነፍሳቹህንም ቢሆን፣ ሳታወላውሉ!
ያኔ ነውና መጥፊያው፣ የዕዳ ቁልሉ፡፡

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ጥቅምት 2007ዓ.ም.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.