ኦዚ ደርሶ መልስ (ኤፍሬም – ማዴቦ) – መልሱን እነሆ! (አንዱዓለም ተፈራ)

ፐርዝ ወይም ኦክላንድ ቢበሩ፤ ሜልቦርን ወይም አስመራ ቢሰፍሩ፤
የኤፍሬም ማዴቦ ጉዳይ ነው። የዐማራውን ትግል ግን ለቀቅ ያድርጉት!!!

አንዱዓለም ተፈራ

አርብ፣ ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፱ ዓመተ ምህረት

ኤፍሬም ማዴቦ

“ኦዚ ደርሶ መልስ” በሚል ርዕስ፤ ኤፍሬም ማዴቦ የከተቡትን አነበብኩ። ኤፍሬም ማዴቦ፤ ይህን ጽሑፋቸውን፤ “(እዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ያለዉ ሀሳብ በሙሉ የኔ የግሌ፣ የኔና የኔ ብቻ ነዉ)” በማለት ይጀምራሉ። ለመሆኑ፤ ያሰፈሩት ጉዳይ፤ በምን ሂሳብ ነው የኤፍሬም ማዴቦ የግላቸውና የራሳቸው ብቻ የሚሆነው? ምን አስፈራቸው? የተላኩት የኤፍሬም ማዴቦን ቤት ለመሥራት ሳይሆን፤ የድርጅታቸውን የግንቦት ሰባትን ተልዕኮ ተሸክመው ነው! ለምን ፈሩ? ከዚያ የተቀበሏቸውም ሆነ ንግግር ያደረጉላቸው፤ የድርጅታቸው አባላትና ደጋፊዎቻቸው ነው። ታዲያ “የግሌ ነው!” ን ምን አመጣው!

ልቀጥልና፤ በዚሁ ወቅት፤ የድርጅታቸው መሪ፤ በዘር ከተደራጀ፤ ለዚያውም ኢትዮጵያዊነቱን ከጥያቄ ውስጥ ካስገባ አንድ ድርጅት ጋር፤ የትግል አንድነት በማድረግ ፊርማ አስቀምጠዋል። ያ እንዳይመሳቅልባቸው ፈርተው ይሆን! አይ የፖለቲካ ነገር! ይሄን ለሳቸው ልተወው። እንዳልተወው ግን፤ ይህ የመሪያቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን ከጥያቄ ውስጥ ካስገቡ ድርጅቶች ጋር መፈራረምና መግለጫ ማውጣቱ፤ የመጀመሪያቸው ወይንም የመጨረሻቸው እንዳልሆነ ሀገር ያውቀዋል! “አለ ነገር!” ያስብላል። ለመሆኑ ይሄን የመሰለ፤ ለሌሎች ብሔሮች መደራጀት ተገቢ ሲሆን፤ ለዐማራው ግን፤ ሀገር አፍራሽ የሆነበት ምን ምክንያት አለ? ግንቦት ሰባትን ይሄን ያህል ያስፈራው ምንድን ነው? ይሄን ዝቅ ብዬ አቀርበዋለሁ።

ኤፍሬም ማዴቦ ዐማራው ያለበትን የኑሮ ሁኔታ፤ እንደባለቤቱ እንዳማራው ሊያውቁና፤ የዐማራውን የልብ ትርታ ሊገነዘቡ እንደማይችሉ፤ ከወዲሁ አውቃለሁ። ነገር ግን፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ፤ በተወሰነ ደረጃ፤ ዐማራው አሁን በተፈጠረው የፖለቲካ ሀቅ፤ ስነልቡናው ወዴት እንዳለ በትንሹም ቢሆን ይረዱታል፤ የሚል ግምት ነበረኝ። በርግጥ የባለቁስሉን ያህል፤ ሕመሙን ሌላ ግለሰብ ዘርዝሮ ሊያውቀው እንደማይችል፤ አንባቢ ይረዱልኛል። እስኪ ምን አልባት አእምሯቸውን መክፈት ችለው መከታተል ከሆነላቸው፤ ስለሌላ ሳይሆን ስለራሴ ላውጋቸው። እግረ መንገዳችሁን እናንተም እስኪ እባካችሁ እህ! በሉና፤ አብራችሁን አዝግሙ።

ከሃምሳ ዓመት በላይ በኢትዮጵያዊነት ታግያለሁ። የትግሬዎቹ ገዥ ቡድን ጦሩን ከቶ ወልቃይት ሲገባ፤ በቦታው፤ በወቅቱ በነበርኩበት ድርጅት በኩል ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገን፤ በእውነት የወቅቱን የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር “ጀግንነት!!!” መሬት ለመሬት በሚያስኬድ ሁኔታ እስኪንበረከክ ድረስ፤ አንፏቀን ሰደነዋል። ያን በሌላ ጊዜ። የዚያን ጊዜ የትግሬዎቹ ገዥ ቡድን አመራርና የዛሬ ቢሊኒየር ቱጃሮች፤ እንጭጭ ለጋ የትግራይ ወጣቶችን ማገዶ አድርገው፤ መሰላል አድርገው ተወጣጥተውባቸው፤ ለዛሬው ጉድ ተረፈዋል። በዚያ በሸረላ ጦርነት፤ የቀኝ እጅ ትከሻዬ ላይ ተመትቼ፤ አሁንም ድረስ ሰባራ አጥንት ይዤ እጓዛለሁ። ይህ የሆነው ከሰላሳ ሰባት ዓመት በፊት ነው። ከዚያ በፊት አደርግ እንደነበረው ሁሉ፤ ከዚያ በኋላም በኢትዮጵያዊነት ትግሉን ቀጠልኩ።

ኤፍሬም ማዴቦ በዘር ከተደራጁ ክፍሎች ጋር ለመተባበር ወዲያ ወዲህ ሲሯሯጡ፤ እኔ ትክክል አይደለም ብዬ፤ በ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” ራዕይ ቀጠልኩ። የፖለቲካ ሂደት አንዱ ገጹ፤ ዛሬ ወሳኝ የነበረው ኩነት ተቀይሮ፤ ነገ ክብደቱ ቀናሽ መሆኑ ነው። ነገ ሌላ ሀቅ ተተክቶ፤ ወሳኝነቱን ከዛሬው ወሳኝ ጉዳይ ይቀማል። በኢትዮጵያ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት አለመኖርና፤ የትግሬዎች መንግሥት መንገሥ፤ ያን ንግሥና ይሄው የትግሬዎች ገዥ ቡድን ይዞ፤ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሀቅ መለወጡና ለሃያ ስድስት ዓመታት መሾፈሩ፤ ትናንት የነበረውን የፖለቲካ ስሌት ቀየረው። አልቀየር ብሎ እምቢ ያለ ቢኖር፤ ራስ ደጀን ነው። ራስ ደጀን፤ “አሁንም ጎንደር እንጂ፤ ትግራይ አይደለሁም ያለሁት!” ብሎ ካለበት ንቅንቅ አላለም። በፖለቲካ ትግል፤ የዛሬው ወዳጅ የነገ ጠላት፤ የዛሬው ጠላት ደግሞ የነገ ወዳጅ ሊሆን መቻሉን መቀበል አለብን። ያ የሚሆነው፤ ሁኔታዎች ስለሚለዋወጡ ነው። በኢትዮጵያ ያለውም ሁኔታ ተለዋውጧል።

ከላይ እንዳሰፈርኩት፤ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ መንግሥት የለም። ያለው የትግሬዎች መንግሥት ነው። የዐማራው ትግል፤ ከትግሬዎች መንግሥት ጋር እንጂ፤ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አይደለም። ይህ የትግሬዎች መንግሥት ደግሞ፤ ከመነሻው ጀምሮ የፖለቲካ ፍልስናው መሠረት፤ በዐማራው መቃብር ላይ፤ የትግራይን ሩፑብሊክ መመሠረት ነው። በፍልስፍና ደረጃ ብቻ ሳይሆን፤ ባለፉት ሃያ ስድስት ዓመታት ይሄንኑ ነበር ሲተገብር የቆየው። “ለትግሬው መኖር የዐማራው መጥፋት!” “ለትግሬው መበልጸግ የዐማራው መምከን! ግድ ነው!” ብሎ ያመነ የትግሬዎች መንግሥት መከሰት ያስከተለው የፖለቲካ ሀቅ ውጤት! እኔና መሰሎቼ ኢትዮጵያ ወይም ሞት ስንል፤ የትግሬዎቹ መንግሥት፤ ዐማራውን ከምድረ ኢትዮጵያ ለማጥፋት፤ ያለ የሌለውን ጉልበት፣ ንብረትና፣ እውቀት አረባረበበት። በዚህ ወቅት ዐማራው፤ ከሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ብቻ ሳይሆን፤ ከራሱ ከዐማራው አካባቢም ተፈናቀለ። ተባረረ። ታሰረ። ተገደለ። የመጨረሻው የሞትና ሽረት ደረጃ ሲደርስ፤ እኔም፤ “ኧረ! ይሄማ እንዴት ይሆናል? ዐማራው ከምደረ ገጽ ሲጠፋማ ዝም ብዬ አላይም!” አልኩ።

እናም ዐማራው ከምድረ ገጽ እንዳይጠፋ፤ ተፈጥሯዊ ግዴታ አለብኝ። በርግጥ ኤፍሬም ማዴቦ፤ የኔን ያህል የዐማራው ጉዳይ ቆርቁሯቸው ይነሳሉ የሚል ቅዠት የለኝም። ለሳቸው የዐማራው የህልውና ጉዳይ፤ ከፖለቲካ ስሌታቸው ውስጥ፤ አንዱ ክፍል ነው። በምን መንገድ ብይዘው፤ ለትግሌ ስኬት ይጠቅመኛል? ከሚል ነው የሚነሱት። ለኔ ደግሞ፤ “ከሁሉ በፊት ዐማራው መዳን አለበት!” “ከምንም ነገር በፊት የዐማራው ሕልውና!” የሚለው ነው። እንግዲህ በሳቸውና በኔ መካከል ያለው ልዩነት ይሄ ነው። እኔ፤ ለዐማራው የሚደረገውን ትግል፤ ለኢትዮጵያዊነት የሚደረገው ትግል አንድ ክፍል አድርጌ ዓየዋለሁ። እሳቸው ይሄ አይዋጥላቸውም።

ዐማራው፤ “ሀገሬ ኢትዮጵያ ናት!” እንዳለ ነው። አሁንም ዐማራው በኢትዮጵያ በሙሉ በኢትዮጵያዊነቱ ሰፍሮ፤ በዚህ ተግባሩ ደግሞ፤ ከማንም በላይ እየተሰቃዬ ነው። አሁንም ጎንደር ተሰለፈ ባህርዳር፤ ወልድያ ተሰለፈ ደብረ ብርሃን፤ “የኦሮሞው ደም የኔ ደም ነው!” እንዳለ ነው። ዐማራው፤ “ሰንደቅ ዓላማዬ አረንጓዴ ብጫ ቀይ ቀለሙ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ነው!” እንዳለ ነው። ዐማራው፤ “ዳር ደንበሬ የኢትዮጵያ ዳር ደንበር ነው!” እንዳለ ነው። ዐማራው፤ “በዐማራነቴ መበደል የለብኝም!” ነው ያለው። ይሄን ለማድረግ፤ የማንንም ፈቃድ ሆነ ምርቃን አይጠብቅም። ምነው ኤፍሬም ማዴቦ፤ ይህ እንቅልፍ ነሳዎት! የርሶን ቡራኬ እስክናገኝ መጠበቅ ነበረብን!

እሳቸው እንዲህ አሉን፤

“ . . . አማራዉ በዘር ተደራጅቶ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን በተለየ መንገድ የኢትዮጵያ ጠባቂ ይሆናል የሚለዉ አባባል እራስን አግዝፎ ወይም ሌሎችን አሳንሶ ከማየት የሚመጣ የአዕምሮ በሽታ ነዉ።”

በማለት፤ ከየት እንዳመጡት ያልገባኝን አባባል አስፍረዋል። አንድን የተነገረ ሀቅ ገጥሞ መሟገት አንድ ነገር ነው። ያልተባለን መሞገት ግን፤ ለኔ ቢያንስ ጤነኝነት አይደለም። ዐማራው በተለይ ተደራጅቼ፤ የኢትዮጵያ ጠባቂ ልሁን አላለም። ብሏል ካሉ፤ የት ቦታ? እና ማን? የሚለውን መግለጥ ይጠበቅባቸዋል። በደፈናው የፈለጉትን እንዳሻቸውና እንደመጣላቸው ሲናገሩ የሰማኋቸው እብዶችን ብቻ ነው። ዐማራው ራሴን ከዘር ማጽዳት ላድን አለ እንጂ፤ ኢትዮጵያን ለብቻዬ ላድን አላለም። ይልቁንም፤ “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ማለታችሁን ትታችሁ፤ ዐማራውን ለምን አታድኑም!” የሚል መልዕክት ነው፤ በአሁኑ በትግሬዎች ገዥ ቡድን ግፍና በደል የተጠበሰው ወጣት፤ እንደኔ ያለውን ኢትዮጵያዊ ነኝ ያለውን ዐማራ የጠየቀው። የዐማራው ትግል፤ “በማንነት ላይ የሚደረግ በደል፤ መቆም አለበት!” የሚል ነው። ይሄ መቼም በኔ ግምት፤ ኤፍሬም ማዴቦን አብሮ ያዘለና፤ እሳቸውም፤ “እኔም አለሁበት!” ሊሉበት የሚገባ ትክክለኛ ትግል ነው። ነገር ግን፤ የፖለቲካ ጉዳይ ሆነና፤ ያልተባለውን ተባለ፤ ያለውን የለም ብሎ መቅዘፉ፤ የባለ ድብቅ አጀንዳ ነገር ስለሆነ፤ ጠበል አይረዳም።

“ራስን አግዝፎ ወይንም ሌሎችን አሳንሶ ከማየት የሚመጣ የአዕምሮ በሺታ ነው።” ድርብርብ መልዕክቶችን የያዘ ጉዳይ ነው። የመጀመሪያውና ግልጹ፤ እንደ የትግሬዎች ገዥ ቡድን፤ ዐማራው ትምክህተኛ ነው የሚል ነው። ዐማራው በትግሬዎቹ ገዥ ቡድን የተከሰሰበትን ወንጀል አሁንም በሌላ ሸማ ጠቅልሎ መቅረብ ነው። ግድየለም፤ አሁንም እኮ ዐማራው ያለው፤ ሌሎች ለኔ ሊታገሉልኝ ስለማይችሉኅ ተደራጅቼ መታግገሌ ግዴታዬ ነው! እናም አደርገዋለሁ ነው። ኤፍሬም ማዴቦ በግልጽ አይሰለፉ እንጂ፤ ዐማራውን ውንጀላቸው እኮ ከትግሬዎቹ ገዥ ቡድን አልለዋቸውም! አይገርማችሁም! በዚህ አባባላቸው፤ ትምክህተኛ፣ ሌሎችን ናቂ፣ የአዕምሮ በሺተኛ፣ . . .  ምን ያላሉን ነገር አለ! እውነት በሺተኛው ማን ይሆን? የወደቀ ግንድ ምሳር ይበዛበታል፤ ሆነና !!!

በርግጥ አመቺ ሆኖ ካገኙት፤ ለኤፍሬም ማዴቦና ለድርጅታቸው፤ ከሌላ በዘሩ ተደራጅቶ ከተሰለፈ ድርጅት ጋር መተባበሩ፤ ዓይናቸውን አያሹበትም። ምክንያቱም፤ ቁም ነገር ብለው የሚወስዱት፤ የጉዳዩ አንድነት ሳይሆን፤ ለሳቸው የፖለቲካ ሂደት ይረዳል? ወይንስ አይረዳም? የሚለው የፖለቲካ ቅመራ ነውና! ዐማራውን በተመለከተ፤ ኤፍሬም ማዴቦ ችግር አላቸው። ያሰፈሩትን ልጥቀስ፤

“ . . . አጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መሳፍንትን ዘግተዉ ዘመነ አንድነትን ጀመሩ እንጂ እንደዛሬዎቹ የሳቸዉ ልጆች ነን ባዮች ቋንቋና ዘርን አልሰበኩም። አንድ ኢትዮጵያዊ ቴዎድሮስ ልጅነኝ ለማለት ቋራ፥ ጎንደር ወይም አማራ ክልል መወለድ የለበትም። ኢትዮጵያዊ የትም ይወለድ የት አንድነትን እስከሰበከ ድረስ የቴዎድሮስ ልጅ ነዉ። የቴዎድሮስ ትልቅነትና አዋቂነት ይዞት የተነሳዉ ራዕይ ነዉ እንጂ የተወለደበት ቦታ አይደለም።”

አሉ።

በሳቸው ቅመራ ከሆነ፤ ድርጅታቸው ከሌሎች የዘር ድርጅቶች ጋር ሲነጋገርና ሲያብር፤ እኒያ የድርጅት አባሎች፤ የቴዎድሮስ ልጆች አይደሉም። ባይሆኑም ግን፤ ስለሚጠቅሙ፤ ከነሱ ጋር መዋሀዱ ተገቢ ነው። ይሄ ኤፍሬምኛ ይባላል። ዐማራውን በተመለከተ ግን፤ እሳቸው፤ ማለት ኤፍሬም ማዴቦ፤ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው በተለሙለት መንገድ ካልተጓዘ፤ ትክክል አይደለም! በሺታ ነው! አይ የዴሞክራሲ ነገር! ብቻ ላመሰግናቸው የሚገባ አባባል ጣል አድርገዋል። አዎ! የቴዎድሮስ ልጅነት፤ ለዐማራው ብቻ አለመሆኑን በሚገባ አቅርበውታል። አሁንም አፄ ቴዎድሮስ የኛ ብቻ ናቸው ያለ ዐማራ አላውቅም። ይልቁንስ ከዘመናቸው በፊት የተወለዱ፤ የመላው ጭቁን ሕዝብ ንጉሥ ናቸው፤ ባዮቹ ብዙ ነን።

ኤፍሬም ማዴቦ አልፈው ተርፈው፤

“እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደዚህ አይነት ጠንካራ መርህ እንዲኖረን የግድ አማራ ሆነን፥ ትግሬ ሆነን ወይም ኦሮሞ ሆነን ወዘተ መፈጠር የለብንም። ኢትዮጵያ የምትባል አገር ዉስጥ ሰዉ ሆነን መፈጠር ብቻ ነዉ ያለብን። ዛሬ እንዲህ አይነቶቹ ትላልቅ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ተረስተዉ በአንዳንድ የፖለቲካ መድረኮች ላይ በአገር መዉደድ ስም ብሄረተኝነት እየተሰበከ ነዉ። ይህ አደገኛ ስብከት አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ በሚገባ ካለመረዳት፥ ከግድ የለሽነት፥ ለራስ ጥቅም ከመቆምና አገር ወዳድነትንና ብሄረተኛነትን ለያይቶ ካለማየት የሚመጣ በግዜ ካልታከሙት የማይድን በሽታ ነዉ።”

በማለት፤ በሺታ አስታቅፈውን አረፉ።  ከመነኮሱ ላይቀር እንደ ኤፍሬም ማዴቦ ነው! ለምንድን ነው ለሌሎች የሠጡትን የመቀራረብና የአንድነት መፍትሔ ፍለጋ ለዐማራው መሥጠት ያልፈለጉት። ዐማራው ያ መብት የለውም ካለው ከትግሬዎቹ ገዥ ቡድን የቀዱት ይሆን! ምን አልባት ብዬ ነው!

በዚህ በኤፍሬም ማዴቦ ጽሑፍ፤ ምን ያህል ራሳቸውን እና ድርጅታቸውን በሚገለባበጥ የፖለቲካ ቅመራ እንደነዱት ማየቱ ቀላል ነው። ነገር ግን፤ እሳቸው ማየት የተሳናቸውን ወይንም ሆን ብለው ያደበዘዙትን ጉዳይ፤ ሌሎች ማየት አይችሉም ብለው መናቃቸው ያስገርማል።

ጥሩ ሰባኪ ናቸው። ችግሩ ግን የሚሰብኩትን ማድረግ አይፈልጉም። “አገር ወዳዶች ሰዎችን ለያይተዉ የሚያዩበት የዘር መነጽር የላቸዉም፥ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከቱት እንደወገናቸዉ ነዉ።” ብለው ሰብከው፤ ዐማራው ይሄን ያህል ተገልጾ በማያልቅ ጉዳት ላይ ተቀምጦ፤ ምንም አንዲት ጣታቸውን ሳይነሱ፤ አሁን ራሴን ላደራጅ ሲል፤ ጉራ ከረዩ አሉ! ምነው ዐማራው ወገኔ ነው ካሉ፤ የዘር ማጽዳት ሲፈጸምበት የት ነበሩ?

አንዳንድ ጊዜ፤ በሌላ በኩል ያለውን ወገኔን ጥሩ ጎን የግድ ፈልጌ ማየት እንዳለብኝ አውቃለሁ። እናም፡

“ዛሬ እያንዳንዳችን የፈለገዉን ያክል ጠንካራ የብሄር ድርጅት ቢኖረንም ህወሓትን በተናጠል ገጥመን ማሸነፍ አንችልም፥ ምክንያቱም በብሄር የተደራጁ ሀይሎች ሁሉ እንደ ጠላት አድርገዉ የሚመለከቱት ህወሓትን ብቻ ሳይሆን ከራሳቸዉ ዉጭ ያለውን ብሄር ሁሉ ነዉ። ስለዚህ እርስ በርስ እየተዋጋን ህወሓትን እናሸንፋለን ማለት ዘበት ነዉ።”

ችግሩ ደግሞ፤ በትክክል አንድን ነገር ብቻ ግልጽ አድርጎ ማቅረብን ፖለቲከኞች አይፈልጉም። ተጨማሪ አጀንዳቸውን ሸጎጥ ማድረጉን ተክነውበታልና! “እንደ ጠላት አድርገዉ የሚመለከቱት . . .  ከራሳቸዉ ዉጭ ያለውን ብሄር ሁሉ ነዉ።” በማለት፤ በራሳቸው ጭንቅላት ብቻ የሚሽከረከረውን ጣሉበት። ይሄን የት እንዳነበቡት አላውቅም። ሁሉም የብሔር ድርጅቶች እንዲህ ከሆኑ፤ ታዲያ ድርጅታቸው አብሮ ለመሥራት የሚያሳድደው እነማንን ነው?

አክለውም “እርስ በርስ እየተዋጋን ህወሓትን እናሸናለን ማለት ዘበት ነው።” ብለዋል። ለርስ በርስ ውጊያ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ነገሩን! ይገርማል። ርስ በርስ መዋጋትንና ማቸነፍን እዚህ ላይ ምን አመጣው? ይሄን ሁሉ ልተውና፤ የትግሬዎቹን ገዥ ቡድን በተናጠል ገጥመን ማቸነፍ አንችልም፤ ያሉትን በጎ አባባል ልውሰድላቸው። ትክክል ነው! ታዲያ አንድ ጤነኛ ሰው፤ ከዚህ ተነስቶ፤ ከተናጠል ወደ አንድነት ትግሉ ለመሄድ ምን ላድርግ? ብሎ ነው የሚያስበው። ለምን ይሄ ኤፍሬም ማዴቦን ተሳናቸው! ለሁሉም ድርጅቶች ጠላትና ወዳጅ ቀማሪ እሳቸው ሆኑ!!! ምን የሚሳናቸው አለ!

ኤፍሬም ማዴቦ፤

“ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ መሰማት የጀመረ አንድ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ ስብከት አለ . . . . እሱም  አማራዉ አማራ ሆኖ መደራጀት የአማራንም የኢትዮጵያንም ነፃነት ያፋጥናልየሚለዉ ምንም አይነት መሠረት የሌለዉ ስብከት ነዉ።”

አሉን።

እንዴ! ዐማራው የኢትዮጵያ አንድ አካል መሆኑን ምነው የሚነግራቸው ጠፋ! ምነው የዐማራው መዳን፤ የኢትዮጵያ አንድ አካል መዳን ነው፤ ብለው ማሰብ አቃታቸው። የኦሮሞው መዳን የኢትዮጵያ መዳን ነው። የኢትዮጵያዊ ሱማሌው መዳን የኢትዮጵያ መዳን ነው። ይሄን እንዴት ሳቱት! ወይንስ ሆን ብለው ነው? ወይንስ ለዐማራው ሲሆን ሎጅክ ባፍ ጢንባሩ ይደፋል! ዐማራው ዐማራ ሆኖ መደራጀት ለምን እንቅልፍ ነሳቸው!

እስኪ በቀላል መንገድ የዐማራውን ትግል እንደገና ልግለጥ። ዐማራው የሚታገለው፤ በዐማራነቱ የሚደርስበትን በደል ትክክል አይደለም፤ ብሎ ነው። በዚህ በዐማራነቱ ደግሞ፤ ከማንም የበለጠ በደል ደርሶበታል። ይህ በደሉ ደግሞ፤ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ፣ በቤንሻንጉል፣ በትግራይ፣ በጋምቤላ፣ በዐማራ ቦታዎች ሁሉ ነው። በበላይነት የትግሬዎች ገዥ ቡድን ሲቀመጥ፤ በበታችነት ደግሞ፤ ይሄው ገዥ ቡድን የፈለፈላቸው የስም ድርጅቶችና ለሆዳቸው ያደሩ ዐማራዎች፣ ኦሮሞዎች፣ ትግሬዎች፣ ሶማሌዎች፣ ቤንሻንጉሎች፣ ደቡቦች አባሪነታቸውን አስመስክረውበታል። ከመንግሥቱ መዋቅር ወጥቷል። የዘር ማጥፋት በደል እየተፈጸመበት ነው። ይሄን የመሰለ በደል በሌሎች ላይ አለተተገበረም። እንግዲህ ይህ፤ በጠቅላላ ኢትዮጵያዊያን ላይ የትግሬዎች ገዥ ቡድን ካደረሰው በደል ተጨማሪ፤ በተለይ በዐማራው ላይ የተደረበውን ለመጥቀስ ነው። ታዲያ ዐማራው መደራጀትና ራሱን ከዘር ማጥፋት መከላከል የለበትም ወይ?

ኤፍሬም ማዴቦ፤ በተለይ እኔን፤ ቀጥለውም ተመሳሳይ አመለካከት ያለንን በማንሳት፤

“የዚህ ስብከት መሰረተ ቢስነት የሚጀምረዉ ከሰባኪዎቹ ማንነት ነዉ። የዚህ ስብከት ሰባኪዎች ከጥቂት አመታት በፊት አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኦነግ ጋር ዉይይት ሲጀምሩበዘር ከተደራጀ ድርጅት ጋር ዉይይት እንዴት ተብሎእያሉ ዉይይቱን ይኮንኑ የነበሩና ባጠቃላይ በዘር መደራጀት ኃጢያት ነዉ እያሉ የሚራገሙ ግለሰቦች ነበሩ። እነዚህ ግለሰቦች ከላይ ከሰማይ ተቀብተዉ የተላኩ የዘመናችን ነቢያት ካልሆኑ በቀር የኦሮሞን በዘር መደራጀት ኃጢያት የነሱን በዘር መደራጀት ፅድቅ የሚያደርገዉ ምንም ምክንያት ሊኖር አይችልም። ማንም ተደራጀ ማን የዘር ፓለቲካና በዘር መደራጀት የአንድን አገር ፖለቲካ የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ መርዝ ነዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ አንድ ብሄር በተናጠል የሚወስዳቸዉ እርምጃዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ነፃነት ሊያራዝመዉ ወይም ሊያሳጥረዉ ይችላል፥ ከዚህ በተረፈ ግን ማንም ብሄር በራሱ ወይም ብቻዉን የኢትዮጵያ ነፃነት ዋስትና መሆን አይችልም። የኢትዮጵያ ነፃነት ዋስትና የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ።”

በማለት፤ እሳቸውን ጻድቅ፤ ሌሎቻችን ግን ርጉም በማድረግ ስለዋል። ድንቅ ልበልና፤ ውስጡ ልግባ።

በመጀመሪያ ኤፍሬም ማዴቦ ያልገባቸው ነገር አለ። ሊገባቸው ያልፈለጉት ቢባል ይቀላል።

ለኤፍሬም ማዴቦ፤

“ያንተን ጉዳይ  ‘እኔ አዉቅልሃለሁየሚባልበት ዘመን አክትሟል።”

አሉን። ታዲያ እሳቸው መለኮታዊ ሥልጣናቸው ነው፤ ዐማራውን፤ “እኔ በምልህ መንገድ ብቻ ነው መታገል ያለብህ!”  እንዲሉ የፈቀደላቸው?

“እዉነቱን እንናገር ከተባለ የአማራዉ በዘር መደራጀት በአንድ በኩል ህወሓት ከተቃዋሚዉ ጎራ የሚፈልገዉ ትልቁ ስጦታ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአማራዉ በዘር መደራጀት ኢትዮጵያ ከተጋረጡባት አደጋዎች ሁሉ ትልቁ ነዉ።”

“ለመሆኑ በአማራዉ በዘር መደራጀት ኢትዮጵያ ተጎድታ አማራ የሚጠቀምበት ሁኔታ አለ? መልሱን አማራዉ በዘር መደራጀት አለበት ብለዉ ለተነሱ ጥቂቶች እተዋለሁ።”

ይሉናል። ኤፍሬም ማዴቦ፤ ምን ለማለት ፈልገው ነው። ለምን በቀጥታ፤ “ኢትዮጵያና ዐማራ የማይገናኙ፤ ፍጹም የተለያዩና የማይዛመዱ ሁለት ተቃራኒ አካላት ናቸው!” ብለው በግልጽ አይወጡም። ዐማራው ሲጠቀም ኢትዮጵያ ለምን ትጎዳለች? ይህ ምን ማለት ነው? ዐማራውና ኢትዮጵያ ለምን በአንድነት የሚጠቀሙበት ሁኔታ እንዳለ መረዳት አልፈለጉም! ለምን ዐማራውን የኢትዮጵያ አካል አድርጎ መቀበሉ ቸገራቸው? ከዚህ የከፋ ዘረኝነት ከየት ይመጣል? ማንስ ኢትዮጵያ ተጎድታ ዐማራ ይጠቀም አለ? እስከማውቀው ድረስ፤ ኢትዮጵያን አፈራርሰን ኦሮሞን እንገነባለን ያሉት እሳቸው አብረዋቸው ለመስራት የፈለጉት ሰዎች ናቸው። በቪዲዮ ተመልክቼዋለሁ። ታዲያ ዐማሮች ይሄን አሉ የሚሉበትን ማስረጃ ያቅርቡ! አለያ ዋሾው ማን እንደሆን እንረዳ!

“እነዚህ ግለሰቦች ከላይ ከሰማይ ተቀብተዉ የተላኩ የዘመናችን ነቢያት” የሚለው አረፍተ ነገር፤ በድብቅ ዐማራውን የትግሬዎቹ ገዥ ቡድን ባጠቃው መሳሪያ ጎኑን መውጋት ነው። ይሄን ማየት ማንም አይሳነውም። በግልጽ እኮ ብለውታል። ምነው በድብቅ ደግሞ መጨመር አስፈለገዎ! ይሄን ከዚህ በላይ አልሄድበትም።

ዐማራው አሁንም፤ ኢትዮጵያን የሚያድናት የኢትዮጵያዊያን መሰባሰብና በአንድነት መታገል መሆኑን ያምናል። እንዲያውም ሁሉ እንዲተባበርና ባንድነት እንዲታገል ዐማራው ይፈልጋል። ዐማራው ግን፤ በዚያ ለመሳተፍ፤ መጀመሪያ መኖር አለበት። ራሱን በሕልውና ማኖር ደግሞ የዐማራው የተፈጥሮ ግዴታ ነው። ይሄን ለምን ኤፍሬም ማዴቦ መረዳት አቃታቸው! ወይንስ አይፈልጉም። ወይንስ እያወቁ የለም ብሎ መካዱ የፖለቲካ ጉዟቸውን ያቀናላቸዋል! አዛዥ ናዛዡ እሳቸው ናቸው። ምናለ ታዲያ፤ እሳቸው ለራሳቸው እንደሆኑ፤ የኛን ለኛ ቢተውልን! ዐማራው ለካስ በኤሬም ማዴቦ ስሌት፤ ከቁጥር አይገባም!

አዎ! በግልጽ እንነጋገር ከተባለ፤ ድርጅታቸው ከኤርትራ ተነስቶ፤ በኢትዮጵያን ወዳዱ ኢሳያስ አፈወርቂ ታግዞ፤ ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው በዐማራው መሬት ነው። አሃ! ዐማራው ከተደራጀ፤ ይሄ መንገዳቸው፤ ከተጓዙ ማለት ነው፤ ችግር ሊገጥመው ነው። እናም ዐማራው መደራጀት የለበትም። ከተደራጀ ደግሞ፤ በኤፍሬም ማዴቦ ፍላጎትና ፈቃድ ብቻ መሆን አለበት። ታዲያ ይሄን በግልጽ ለምን አያስቀምጡትም! አይ ፖለቲከኛ! ፖለቲከኛ ሲጠማዘዝ ይኖራል! ግቡን እስኪመታ!!!

 “ከዘረኛዉ የህወሓት አገዛዝ ነፃ ለመዉጣት ብቸኛዉ መንገድ እንደ ህወሓት በዘር መደራጀት ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሆኖ በጋራ መታገል ብቻ ነዉ።”

ኤፍሬም ማዴቦ!

ዐማራው ብቻ ነው በዘር የተደራጀው? ለምን ዐምራው ሲደራጅ ይሄን ለመናገር ጣደፉ? አይፍሩ ኤፍሬም ማዴቦ። ዐማራው ከኢትዮጵያ ነፃ ሊወጣ እየታገለ አይደለም። ዐማራው አሁንም ለአስረኛ ጊዜ ልድገመውና፤ የሚታገለው፤ ሕልውናውን ለመጠበቅ ነው። የመንግሥት ሥልጣን ለመጨበጥ መርኀ-ግብር ነድፈው፤ መንግሥታዊ ፖሊሲ አውጥተው የተነሱ ሌሎች ነፃ አውጪ ድርጅቶች ናቸው። ራሱን በመከላከል ያለው ዐማራ አይደለም። በሁለት ቢላዋ መብላቱን ያቁሙ። በዚሁ በዘር መደራጀትን አስመልክቶ፤ በአንድ በኩል ዐማራውን እያወገዙ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ጋር እየተሞዳሞዱ፤ የድርጅትዎን የሥልጣን ሩጫ፤ በዐምራው ወጣት ጉሮሮ ለመሰንቀር የሚጥሩት ዋጋ የለውም። አሁንም ዐማራው ራሱን እየጠበቀ፤ በራሱ ተደራጅቶ፤ ከሌሎች ወገኑ ጋር ይሄን የትግሬዎች ገዥ ቡድን ይጥላል። ከዚያ የሚቀጥለውን የሀገራችንን ሁኔታ፤ በትግሉ ሂደት፤ ታጋዮቹ የሚወስኑት ይሆናል። ዐማራው ግን፤ አሁንም ሆነ ኋላ፤ ይሄን የመሰለ የዘር ማጽዳት በደሉ በማያዳግም ሁኔታ የማይከሰትበትን ሀቅ የመፍጠር ተፈጥሯዊ ግዴታ ስላለበት፤ ያለርስዎ ፈቃድ ይቀጥላል።

አያምታቱት። ነጋዴዎችን፣ ባህል ጠባቂዎችን፣ ምን የተረፈዎ አለ! ብቻ ሁሉንም ከርስዎ በስተቀር ወንጅለው፤

“ . . . ዛሬ ተወልደን ያደግንባት አገራችን ኢትዮጵያ የማናዉቃት አገር ሆናለች። ባህላችን ከመረሳቱ የተነሳ ባህል ያለን ሰዎች አንመስልም። ማህበራዊ እሴቶቻችን ከመዉደማቸዉ የተነሳ ነጋዴዎቻችን በርበሬና ቀይ አፈር ቀላቅለዉ መሸጥ ጀምረዋል። የመሪዎቻችን አዋቂነትና ትልቅነት የሚለካዉ በሚናገሩት የዉሸት አይነትና መጠን ሆኗል። የሀይማኖት መሪዎቻችን ተበዳዮች በዳዮችን ይቅርታ እንዲጠይቁ ማግባባት ዋና ስራቸዉ ሆኗል። ሽማግሌዎቻችን ህሊናቸዉን ሽጠዉ የነብሰ ገዳዮች ተላላኪ ሆነዋል። አንድነታችን ከመላላቱ የተነሳ ጎረቤቶቻችን ንቀዉናል።”

በማለት ከሰማይ የተላኩ አዳኝ ነብይ ሆነውልናል። በሚያመችዎ መንገድ ከግራ ቀኝ እየረገጡ፤ ሰማይ ሊደረመስ ነውና፤ ለኔ ድርጅት ድረሱልኝ ማለትዎ፤ የፖለቲካ ስልትዎ ግቡን ለምምታት ምን ያህል ርቀት እንደሚጓዝ አሳዩን።

በርግጥ የሚመከሩ ቢሆን ኖሮ፤

“የለም፤ የሚታገለውን ክፍል ወደ አንድ ለማምጣት፤ የግድ የአንዱ ድርጅት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉንም ማዳመጥና፤ ከምን እንደተነሱ አጢኖ፤ የጋራ የሆነውን በመፈለግ፤ መቀራረብ እንዲኖር መጣር ነው። እናም እኔ ካልፈለግሁት በሺታ ነው የሚሉትን ትተው፤ ሌሎችን፤ እኛ እንዲህ ነን የሚሉትን ተቀብሎ፤ በራሳቸው ገለጻ ያቀረቡትን ማንነት ለመረዳት መጠጋት ተገቢ ነው።”

ባልኩዎት ነበር። ነገር ግን ያን ብል እርስዎን አያውቁም ብሎ መስደብ ይሆንብኛል። በያዙት መንገድ ቸር ይግጠምዎ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.