የግ7ቱ ምሁር አቶ ኤፍሬም ማዴቦና ያልበሰለ ፖለቲካዊ ዕይታቸው! – ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

ኤፍሬም ማዴቦ

ሰሞኑን የግንቦት ሰባቱ ምሁር አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “ኦዚ ደርሶ መልስ!” በሚል ርእስ የጻፉት ጽሑፍ በተለያዩ ድረ ገጾች ተለጥፎ ዓይቸው ነበረ፡፡ ግ7 ከመርሑና ርዕዮተ ዓለሙ ጋር በሚጻረር መልኩ እንደ ኦነግ/ኦዴግ ካሉ ቋንቋንና ዘርን መሠረት ካደረጉ ጎሳ ተኮር የፖለቲካ ፓርቲዎች (የእምነተ አሥተዳደር ቡድኖች) ጋር ጥምረት ማድረግ ከጀመረ ወዲህ ከዚያ በፊት እሰጠው የነበረውን ሞቅ ያለ ድጋፍ ትቸ በየጽሑፌ መልስ ሊሰጡበት የተሳናቸውን የሰላ ትችቶች መሰንዘሬን እረስቸው “አቶ ኤፍሬም ለሰነዘርኳቸው ትችቶች መልስ ለመስጠት ሞክሮ ይሆናልና ጽሑፉን ላንብበው!” ብየ ስላላሰብኩ ጽሑፉን ሳላነበው ቀረሁ፡፡

ከዚያ በኋላ ድረ ገጾችን “እስኪ ምን አዲስ ነገር አለ?” ብየ ስጎበኝ የተለያዩ ሰዎች “መልስ ለአቶ ኤፍሬም ማዴቦ!” ምናምን የሚሉ ጽሑፎችን ሊንኮችን (ይዞችን) ተመለከትኩ፡፡ “እንዴ የሰውየው ጽሑፍ ይሄንን ያህል ትኩረት የሚስብ ነበር ማለት ነው?” ብየ የአቶ ኤፍሬምን ጽሑፉ ፈልጌ አነበብኩት፡፡ ጽሑፉ ያረጋገጠልኝ ሀቅ ቢኖር ከዚህ ቀደም መረጃዎችን በመጥቀስና በመተንተን “ግ7 የያዘውን የሀገር ጉዳይ ወይም ፖለቲካ አብስሎና ጠንቅቆ አያውቅም! አኪያሔዱ የእውር ድምብስ ነው!” ያልኩትን ትችት ትክክለኛነት ነው፡፡ የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር ሰውየው ከአቅም ማነስ ይሁን ከፍላጎት ማጣት አላውቅም በተለያዩ ጊዜያት ላነሣኋቸው ትችቶች በፍጹም መልስ ለመስጠት አለመሞከራቸው ነው፡፡ ዝም ብለው ብቻ እኔ ላቀረብኩት ትችት ድጋፍ የሚሆንን ነገር አውርተው፣ ያልገባቸውን ነገር ቀበጣጥረው፣ ተነጫንጨው ሔዱ፡፡

አቶ ኤፍሬም ያነሧቸውን ትችቶች በቅደም ተከተላቸው እያነሣን ብንተቻቸው ምን ይመስላቹሀል? መልካም አይደለም? በጀኝ! እንቀጥላ እንግዳው፦

“… የቴዎድሮስ ትልቅነትና አዋቂነት ይዞት የተነሣው
ርዕይ ነው እንጂ የተወለደበት ቦታ አይደለም!” ካሉት እንጀምራ! “የቦታ ትልቅ የለውም!” ማለታቸው ነው፡፡ ይኸው አይደል እንግዲህ የበታችነት (inferiority) ሥነልቡና ያለበት ሰው ችግር! ከእውነታ ጋር መላተም፡፡ አቶ ኤፍሬም “የቦታ ወይም የሀገር ትልቅ የለውም ወይም ጎንደር ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገራት ተለይታ ወይም በልጣ ልትታይ የምትችልበት ጉዳይ የለም!” ብለው የሚያምኑ ከሆነ ኢትዮጵያን እወዳታለሁ! እኮራባታለሁ! ብለው የሚያወሩት ነገር ውሸት ነው ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም አቶ ኤፍሬም ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት የበለጠ ወይም የተሻለ ወይም ተወዳዳሪ ወይም የማያሳፍር ታሪክ፣ ማንነት፣ ቅርስ፣ ሥልጣኔና እሴቶች ስላላት ሊኮራባት ልትወደድ የምትገባ ሀገር መሆኗን ሳያምኑ ሊኮሩባት ሊወዷት አይችሉምና ነው፡፡ በዚህ መስፈርት ኢትዮጵያን የወደደና የሚኮራባት ሰው በታሪክ፣ በሥልጣኔ፣ በቅርስና በተለያዩ እሴቶች ጎንደር ተለይታ ወይም በልጣ ካልታየችው ሰውየው ዋሾ፣ የቅናትና የበታችነት ሥነልቦና ቀውስ ተጠቂ፣ አስመሳይ እንጅ እውነተኛና ጤነኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ምክንያቱም ከላይ እንደገለጽኩት አስተሳሰባቸው አመክንዮአዊ አይደለምና፡፡

አንድ ሰው የሚያውቀውን እውነታ መቀበልና ማመን ከተቸገረ ወይም ካልቻለ ጤነኛ ሥነልቡና የለውም፡፡ ጤነኛ ሥነልቡና የሌለው ሰው ደግሞ ለትክክለኛ ሥራና ለእውነት ታማኝ አይደለም፡፡ የጎንደር ታሪክ የ3 ሽህ ዓመታት ታሪክ ነው፡፡ ታቦተ ጽዮን ወይም የሙሴ ጽላት በቀዳማዊ ምኒልክ ወደ ሀገራችን ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ በቀድሞ ስሙ ደብረ ሳሕል በአሁኑ ስሙ ጣና ቂርቆስ በተባለ ጎንደር ውስጥ ባለ ገዳም ቆይታ በ4ኛው መቶ ክ/ዘ በኢዛና እና ሳይዛና ወይም በአብርሃ እና አጽብሐ ዘመነ መንግሥት አቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን ግፊት ወደ አክሱም መወሰዷን ድርሳነ ጽዮን የተባለው የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን መጽሐፍና ስለ ጣና ቂርቆስ ገዳም ታሪክ የሚናገረው እዚያው ገዳሙ ውስጥ ያለ ሌላ ጥንታዊ የብራና መጽሐፍ ይናገራሉ፡፡ ታቦተ ጽዮን ወደሀገራችን በገባችበት ወቅት አክሱም ገና የአክሱም ሥርዎ መንግሥት መቀመጫ አልነበረችም አልተቆረቆረችምም ነበር፡፡ ይሄ ታሪክ ጎንደር ብቻ ሳትሆን ሀገራችንም ከምትጠቅሳቸው ታሪኮቿ ዋነኛው ነው፡፡ የኖሕንና የፋሲል ግንብን ግንኙነት ካነሣን ደግሞ የጎንደር ታሪክ ከ5ሽህ ዘመንም ያልፋል፡፡ አቶ ኤፍሬም ይሄና ሌሎች አኩሪ የጎንደር ታሪኮች፣ ቅርሶች፣ እሴቶች ወዘተረፈ ጀግኖችንና ሊቃውንትን የሚፈጥር የሥነልቡና ሀብት መሆኑን የማያውቁ ከሆነ በቅጡ መማራቸውን ራሱ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ነጥቡ ሲጠቃለል ዐፄ ቴዎድሮስን ትልቅ ጀግናና አዋቂ እንዲሆኑ ያደረጋቸው ይዘውት የተነሡት
ርዕይ ብቻ ሳይሆን ይዘውት የተነሡትን ርዕይ እንዲይዙ ያደረጋቸውን ታሪክ ከያዘችው ጎንደር መውጣታቸውም ጭምር ነው! አቶ ኤፍሬም ከያኔው “ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ ሀገር፤ የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር!” ያለው ከመሬት ተነሥቶ መሰለዎት እንዴ? ሀቅ በመሆኑ እኮነው፡፡ ከያኔው የተረዳውን እውነት መረዳት ባለመቻልዎት ወይም ባለመፈለግዎት በእውነት ሊያፍሩ ይገባል፡፡

እንቀጥል፦ አቶ ኤፍሬም ቀጠሉና ስለ ጎሰኝነት ወይም ስለ ጎሳ ተኮር ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) ሲናገሩ እኔ ከዓመታት በፊት ጀምሬ (በነገራችን ላይ እኔ ካንተ እቀድማለሁ የሚለኝ ካለ መቸና የት ይሄንን ሐሳብ እንዳስተጋባ በመናገር ማረጋገጥ ይጠበቅበታል) ስለ ጎሳ ፖለቲካ አይረቤነትና ፀረ ዲሞክራሲነት (መስፍነ ሕዝብነት) ፣ ፀረ ሰብአዊ መብትነት፣ ፀረ ፍትሕነት፣ ኃላቀር አስተሳሰብነት በማስረጃ አየተነተንኩ ከጻፍኳቸው ጽሑፎች አቶ ኤፍሬም ፈራተባ እያሉ ጥቂቷን ቀንጭበው በማውጣት ከራሳቸው የተሳሳተ ሐሳብ ጋር ቀላቀሉና የሚከተለውን አሉ “”…. ዛሬ እንዲህ ዓይነቶቹ ትላልቅ የኢትዮጵያዊነት
እሴቶች ተረስተው በአንዳንድ የፖለቲካ መድረኮች ላይ
በሀገር መውደድ ስም ብሔርተኝነት እየተሰበከ ነው። ይህ አደገኛ ስብከት አገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ በሚገባ
ካለመረዳት፥ ከግድ የለሽነት፥ ለራስ ጥቅም ከመቆምና
አገር ወዳድነትንና ብሔርተኛነትን ለያይቶ ካለማየት
የሚመጣ በግዜ ካልታከሙት የማይድን በሽታ ነው፡፡ በአገር ወዳድነትና በብሔርተኛነት መካከል የሰማይንና
የምድርን ያክል ትልቅ ልዩነት አለ። አገር ወዳዶች ሰዎችን
ለያይተዉ የሚያዩበት የዘር መነጽር የላቸውም፥ አገር
ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከቱት
እንደወገናቸው ነው። ብሔረተኞች ግን ከነሱ ብሔር ውጭ
የሆነውን ዜጋ ሁሉ እንደራሳቸዉ አድርገው አይመለከቱም።
ለአገር ወዳዶች የሁሉም ነገር መነሻና መድረሻ አገርና
ዜግነት ነው፥ለብሔርተኞች ግን የሁሉም ነገር መነሻና
መድረሻ የነሱ ብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ብሔርተኞች
ከአፋቸው የሚወጣው ቃል ሁሉ “እነሱና እኛ” ሲሆን አገር
ወዳዶች ግን ንግግራቸው የሚጀምረው “እኛ” በሚል
ሁሉን አቀፍ ቃል ነው!”” በማለት ተናገሩ፡፡ ቀጥሎስ ምን አሉ?

“”ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ
መሰማት የጀመረ አንድ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ
ስብከት አለ . . . . እሱም የ“አማራው አማራ ሆኖ
መደራጀት የአማራንም የኢትዮጵያንም ነጻነት ያፋጥናል”
የሚለው ምንም ዓይነት መሠረት የሌለው ስብከት ነው!”” ይላሉ፡፡

ሲጀመር አማራ የተደራጀውና ለመደራጀት የተገደደው ሌሎች በሀገራችን ያሉ የጎሳ ድርጅቶች ለተደራጁበት ውዳቂና ኋላ ቀር ዓላማ አለመሆኑን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በንቃትና በቅርበት እከታተላለሁ የሚሉት አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አላወቁም ወይም ደግሞ ሰውየው ለከንቱ ልፈፋቸው ስለማይመች ሆነ ብለው አውቀው የማያውቁ በመምሰል አማራ የተደራጀው እንደሌሎቹ ጎሳ ተኮር ፓርቲዎች ኢፍትሐዊነት ለነገሠበት ጠባብ የጎሳ አስተሳሰብ እንደሆነ በማስመሰል አላግባብ ለመዝለፍ ጥረት አድርገዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ኃላፊነት የጎደለው፣ አስነዋሪ፣ አሳፋሪና አደገኛ ድርጊትም ነው፡፡

እንደ ፖለቲከኛ (እምነተ አስተዳደራዊ) አቶ ኤፍሬም የአማራ ሕዝብ ድርጅታቸው በተጣመረው ኦዴግ/ኦነግ፣ በወያኔ በሸአቢያና በግብረአበሮቻቸው የዘር ማጥፋት እርምጃ ታውጆበት ይሄው ኢሰብአዊ ጥቃት በየአቅጣጫው ሲፈጸምበት መቆየቱንና በግልጽና በስውር በሚወሰዱ እርምጃዎችም አሁንም ጥቃቱ እየተፈጸመበትና እየጠፋም እንዳለ በሚገባ ያውቃሉ ብየ አስባለሁ፡፡ የሕወሀቱ የቀድሞ መሥራች ታጋይ አቶ ገ/መድኅን አርዓያ ወያኔ በረሀ እያለ ጀምሮ አማራን የማጥፋት ሰይጣናዊ ዓላማ ነድፎ ይሄንን ግቡን ለማሳካት ይጥር እንደነበረ የዓይን ምስክር ሆነው በመረጃ ለሕዝብ ይፋ ያደረጉት ጉዳይ በመሆኑ እንኳን ፖለቲካን ጉዳየ ብለው ከያዙት ከአቶ ኤፍሬም ይቅርና ከማንኛውም ዜጋም ቢሆን ይህ የወያኔ ሰይጣናዊ ድርጊት ከማንም የተሠወረ አይደለም፡፡

ባጭሩ አማራ የተደራጀው ይሄው ከእርስዎም ማየት እንደሚቻለው ሌላው ቀርቶ በአንደበቱ እንኳ አማራ የታወጀበትንና እየተወሰደበት ያለውን የዘር ማጥፋት እርምጃ ለመናገር፣ ደፍሮ ይፋ ለማውጣት የፈቀደና ችግራችንን ለመጋራት፣ ከጎናችን ለመቆም የወደደ ወገን በማጣታችን የራሳችንን ጉዳይ እኛው እራሳችን እንድንይዘው ተገደን ይሄንን ጥቃት ቀልብሰን ህልውናችንን የማስቀጠል አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ስለገባን ለዚሁ እራስን ከጥፋት የማዳን ዓላማ ተደራጀን እንጅ ሌሎቹ ጎሳ ተኮር ፓርቲዎች (ቡድኖች) ለተቋቋሙበት ጠባብ የጥፋት ዓላማ አይደለምና የተደራጀነው ለዚህ ዓላማ እንደተደራጀን አድርገው የሰነዘሩት ዘለፋና ክስ ፈጽሞ አይመለከተንም፡፡

ይሄንን የአማራን ሕዝብ ጉዳይና በከንቱ የፈሰሰውን የንጹሐን ወገኖቻችንን ደም ጉዳየ እንዳላላቹህትና ከምንም እንደማትቆጥሩትማ ከኦዴግ/ኦነግ ወንጀለኛ ድርጅት ጋር ጥምረት በመፍጠር በቁስላችን ላይ እንጨት ስትሰዱብን ከማየት በላይ ምን ማረጋገጫ ያስፈልገናል አቶ ኤፍሬም? ጉዳያችንን ጉዳየ ሊልልን የሚፈልግ ስናጣ፣ እርስዎ እንዳሉት ሰዎችን
ለያይተዉ የሚያዩበት የዘር መነጽር የሌላቸው፥ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ እንደ ወገናቸው የሚመለከቱ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንን በማጣታችን እኛው እራሳችን ሰለባዎቹ ብናነሣውና ራሳችንን ለማዳን ተደራጅተን ብንታገል ስሕተቱ ምኑ ላይ ነው አቶ ኤፍሬም? ቁስላችንን ቁስልዎ ባለማድረግዎና ሊያደርጉም ባለመፈለግዎ፣ ሥጋታችንን ለመረዳት ባለመፈለግዎ ነው መደራጀታችን ስሕተት ሆኖ የታየዎት፡፡

የሚገርመው ነገር የአማራ ሕዝብ ጠላቶች በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ጠላቶች ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ አማራ እራሱን ከፈጽሞ ጥፋት ለመታደግ ህልውናውን ለማስቀጠል በሚያደርገው ህልውናውን የመታደግ የሞት ሽረት ትግል እነኝህ የሀገራችን ጠላቶች የሚደመሰሱና ሀገሪቱ ከጥፋት ኃይሎች ነጻ የምትወጣ መሆኗ ለምንና እንዴት አሳሰበዎት አቶ ኤፍሬም? መለስ ይበሉ አያዋጣዎትም! የልቅስ ሰብአዊነት የሚሰማዎት ከሆነና እውነት የዚህች ሀገር ህልውና የሚያሳስብዎ ከሆነ ይሄንን በአማራ ሕዝብ ላይ እየተወሰደ ያለውን ኢሰብአዊና አረመኔያዊ ጥቃት ለመቃወምና ከኛ ከተጠቂዎች ጎን በመሰለፍ ሀገርንና ወገንን ለመታደግ ሰው መሆንን እንጅ የግድ አማራ መሆንን አይጠይቅምና ከጎናችን ይሰለፉ? ካልቻሉ ግን ቢያንስ አያደናቅፉ፣ ተሳስተው ሰው ለማሳሳትም ጥረት አያድርጉ፡፡ አቶ ኤፍሬም አእምሮና መጠነኛ አክብሮት (A little bit respect) ካለዎትም ያለስማችን ስም ሰጥተው ስም ለማጥፋት ለሞከሩት ስሕተትዎ ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባልና ይሄንኑ ያድርጉ፡፡

ይቀጥሉና አቶ ኤፍሬም “”…የዚህ ስብከት ሰባኪዎች ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከኦነግ ጋር ዉይይት
ሲጀምሩ “በዘር ከተደራጀ ድርጅት ጋር ውይይት እንዴት
ተብሎ!” እያሉ ውይይቱን ይኮንኑ የነበሩና ባጠቃላይ በዘር
መደራጀት ኃጢአት ነው እያሉ የሚራገሙ ግለሰቦች ነበሩ!”” ይላሉ፡፡ አዎ በበኩሌ ያኔ እራገም ነበረ ብቻ ሳይሆን አሁንም ወደፊትም እራገማለሁ! የጎሳ አደረጃጀትን አጥብቄ አወግዛለሁ!፡፡ የግ7 አመራሮች በሳልና ፖለቲካን (እምነተ አሥተዳደርን) የሚያውቁ የሚገባቸው አይደሉም የምለው እኮ ለዚህ ነው፡፡ ይሄ ቀላል ነገር እንደ ሮኬት ሳይንስ (የውንጫፍ መጣቅ) እረቆባቸው መረዳት ተስኗቸው ያለስማችን ስም እየሰጡ እኛን የሚወነጅሉበት ምክንያትም ይሄው ነው ሌላ አይደለም፡፡

በመቀጠልም እኒሁ ሐፍረት የሌላቸው አቶ ኤፍሬም ማዴቦ “”…ማንም ተደራጀ ማን
የዘር ፖለቲካና በዘር መደራጀት የአንድን ሀገር ፖለቲካ
የአልጋ ቁራኛ የሚያደርግ መርዝ ነው!”” ብለውን እርፍ! ይሄንን አይደለም እንዴ ምክንያቱን ጨምሬ እያብራራሁ ዘወትር የምለፍፈው፡፡ የግ7 መሪዎች የሚያደርጉትን አያውቁም አላልኳቹህም? የዘር ፖለቲካ ወይም በዘር መደራጀት መርዝ መሆኑን ካወቁ ታዲያ ለመመረዝ ፈልገው ኖሯል እንዴ ለካ ያውም እጁ በንጹሐን ደም ከተጨማለቀው ከኦነግ/ኦዴግ ጋርና መሰል የጎሳ ፓርቲዎች ጋር የተጣመሩት?

እሽ ቀጥለውስ ምን አሉ አቶ ኤፍሬም? “”…አማራው
በዘር ተደራጅቶ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን በተለየ መንገድ
የኢትዮጵያ ጠባቂ ይሆናል የሚለው አባባል እራስን
አግዝፎ ወይም ሌሎችን አሳንሶ ከማየት የሚመጣ
የአዕምሮ በሽታ ነው። ያንተን ጉዳይ “እኔ አውቅልሃለሁ”
የሚባልበት ዘመን አክትሟል። የአማራው በዘር መደራጀት
የሚጠቅም ከሆነ የሚጠቅመው ይህንን ዓላማ
የሚያራምዱትን ጥቂት የፖለቲካ ልኂቃን ብቻ ነው!”” አሏ አቶ ኤፍሬም፡፡ አቶ ኤፍሬም እስከዛሬ ድረስ የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ምናልባት ሰው እንደመሆናችን በሰው ልጅ ላይ ይንጸባረቁ ዘንድ ከሚጠበቁት ስሜቶች በስተቀር አማራ እንደ ሕዝብ እራሱን አግዝፎ ሌሎችን አሳንሶ የሚያይ ማስተዋል የጎደለው ሕዝብ አለመሆኑን፣ ከፍተኛ የኃላፊነትና የባለአደራነት ስሜት የሚሰማው፣ በከፍተኛ የሞራል (የቅስም) ሕግ የሚገዛ፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሀገሩን የሚወድ ኩሩ ሕዝብ መሆኑን የማያውቁ ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደው ማደግዎን ወይም ጤነኝነትዎን በጣም እጠራጠራለሁ፡፡

“እኔ አውቅልሀለሁ የሚባልበት ዘመን አክትሟል!” ነው ያሉት አቶ ኤፍሬም? ይሄንን አባባል የሀገር ፍቅር ለማያውቀው፣ ኃላፊነት ለማይሰማው፣ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ለሚለው ጠባቡ ጎሰኛ መሠረተ ባንዳ ለወያኔ እና ለአማራ ሕዝብ እኔ አውቅልሀለሁ እያሉት ላሉት ለራስዎ ቢነግሩት ምንኛ ትክክል በሆኑ ነበረ፡፡
ለዚህች ሀገር ገናና ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ፍልስፍና፣ ቅርስ፣ እሴቶች መሠረት ለሆነ ሕዝብ ሲሰነዘር ግን ምን ለማን እንደሚባል አለማወቅን ያሳይ እንደሆን ነው እንጅ የክሱን እውነተኝነት የሚያሳይ አይሆንም፡፡

አቶ ኤፍሬም ይሄንን የነተበ አባባል በነተበ አስተሳሰብ መያዛቸውን እንዲጥሉ አንድ አጭር ትምህርት ልስጣቸው፡፡ አቶ ኤፍሬም “እኔ አውቅልሀለሁ!” የሚለው አስተሳሰብ በራሱ ምንም ክፋት ወይም ችግር የለበትም እሽ? አስተሳሰቡ ችግር የሚሆነው አላዋቂዎች ለአዋቂዎች የተናገሩት ጊዜ ነው እንጅ አዋቂዎች ለአላዋቂዎችማ ካሉት እሰየው የሚያሰኝ ጉዳይ ነው፡፡ ምርጫም ሲደረግ እሱ ያውቅልናል ብሎ ነው ሕዝብ መሪዎቹን የሚመርጠው፡፡ ተመራጩም ሕዝብ ፊት ምረጡኝ ብሎ የሚቀርበው ብቃቱ አለኝ ወይም “ግድ የላቹህም እኔ አውቅላቹሀለሁ!” ብሎ ሲያምን ነው ሕዝብ ፊት ምረጡኝ ብሎ የሚቀርበው፡፡ ድርጅቶች ሥራቸውን የሚሠሩት እኔ አውቅልሀለሁ ብለው ወይም ለደንበኞቻቸው ተመራጭ፣ ተፈላጊ፣ ተወዳጅ፣ ተስማሚ አገልግሎት ይዘው በመቅረብ ነው፡፡ ባጠቃላይ ዓለም የምትተዳደረው በእኔ አውቅልሀለሁ ነውና በጭፍኑ “እኔ አውቅልሀለሁ!” የሚለውን ቃል አይጥሉት እልዎታለሁ፡፡ “የአማራው በዘር መደራጀት
የሚጠቅም ከሆነ የሚጠቅመው ይህንን ዓላማ የሚያራምዱትን ጥቂት የፖለቲካ ልኂቃን ብቻ ነው!” ያሉት አማራ የተደራጀው ለምን እንደሆነ ካለማወቅ የተሰነዘረ በመሆኑ አቶ ኤፍሬም አባባሉን ለጠባብ ጎሰኞች እንዲጠቀሙት እየመከርኩ ልለፈው፡፡

በመጨረሻም አቶ ኤፍሬም “”…ለኢትዮጵያ አንድነት መከበር
የሕይዎት መሥዋዕትነት የከፈሉ አባቶቻችን ታሪክ የተጻፈው
የ“አማራ”፥ “ኦሮሞ”፥ “ሲዳማ”፥ “ወላይታ” ወዘተ
ጀግኖች ታሪክ ተብሎ ሳይሆን የ”ኢትዮጵያ” ጀግኖች ታሪክ
ተብሎ ነው። ይህ ታሪካችንንና እኛነታችንን “ኢትዮጵያዊ”
ብሎ የመጥራቱ ልማድና ባሕል አሁንም ለዘለዓለሙም
ይቀጥላል እንጂ አይቆምም!”” አሉ አቶ ኤፍሬም፡፡ እዚህ ላይ እንስማማለን፡፡ የአንዱ ሚና ሊጎላ የሌላው ሊያንስ የመቻሉ ነገር ነባራዊ ሀቅ፣ ተፈጥሯዊ፣ አመንዮአዊና የሚጠበቅ ቢሆንም ቅሉ ሁሉም በዚህች ሀገር ያለ ጎሳና ብሔረሰብ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለዚህች ሀገር ነጻነት፣ ሥልጣኔ፣ ደኅንነት፣ ህልውና ወዘተረፈ አስተዋጽኦ ላያበረክቱ የሚችሉበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይችልምና ሁሉም የዚህች ሀገር ባለውለታ ናቸው ብሎ ማሰብ ይቻላል ትክክልም ነው፡፡

የእኛም አባቶች ይህ የኃላፊነት ስሜት ይሰማቸው ስለነበረ ነው ማንንም ላለማሸማቀቅና ሁሉም ለሀገሩ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው በማሰብ አማራ ሆነው እያለ በአማራ ስም “አማራ ነን… ፣ የአማራ ሥርዎ መንግሥት!” ብለው በብሔረሰባቸው ስም በተሠየመ መንግሥት ሲገዙ ወይም ሲያስተዳድሩ ያልታዩትና ያልፈለጉት፣ በሌሎች ጥንታውያን ሀገሮች እንደተደረገው ሌላ ሌላ ነገሮች ያልተደረጉት፡፡ ይሄንን ነገር መገንዘብና ዋጋ መስጠት ተችሎ አለማየታችን ቢያሳዝነንም ቅሉ፡፡

አቶ ኤፍሬም አማራ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ያለው የሚሰማው የባለአደራነትና የኃላፊነት ስሜት ይህ ስሜት ደስ ስላለውና “ቢሰማኝ ጥሩ ነው!” ብሎ የያዘው ይመስልዎታል? አይምሰልዎት እሽ እንዲያ አይደለም እውነቱ፡፡ እውነቱ ይህ ስሜት በአማራ ላይ እንዲፈጠር ያደረገው አማራ ለዚህች ሀገር ነጻነት፣ ሉዓላዊነት፣ ህልውና፣ ሥልጣኔ ወዘተረፈ የከፈለው መራራ መሥዋዕትነት፣ የደከመው ድካም፣ የጣረው ጥረት፣ የተሰቃየው ስቃይ፣ የከፈለው ዋጋ ነው በብሔረሰቡ ላይ እንዲህ ዓይነት የሥነልቡና ውርስ እንዲፈተር ያደረገው እንጅ ቢሆን ደስ ስላለው የሆነው ነገር አይደለም እሽ አቶ ኤፍሬም፡፡ ይሄ የባለአደራነትና የተቆርቋሪነት ስሜት ታዲያ “ጎሽ ተባረኩ!” የሚያሰኝ፣ “እኔም እንደነሱ ቀናኢ ተቆርቋሪ ልሁን!” የሚያሰኝ ነው እንጅ እንዴት ሆኖ ነው የሚያስወግዝና “ከእኛ በልጣቹህ ተቆርቋሪ ቀናኢ አትሁኑ!” አሰኝቶ ሊያስወግዝ የሚችለው? ይሄ ጤነኛ ስሜት ይመስልዎታል አቶ ኤፍሬም? የሥነልቡና ሀኪም ቢያይዎት መልካም ነው አቶ ኤፍሬም፡፡

ባጠቃላይ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ አማራን በተመለከተ ያላቸው አመለካከት የተበላሸ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ አቶ ኤፍሬም እውስጥዎ ፀረ አማራ ሕዋስ በቅላ ትታየኛለችና ስር ሰዳ ሳትጠብቅብዎት በጊዜ ነቅለው ቢጥሏት መልካም ነው፡፡ ማን ነው ግን የተከላት ሸአቢያ ነው ወይስ ኦነግ? የሚያሳዝነው ነገር ይህ የእርስዎ አስተሳሰብ የሌሎቹም የግ7 መሪዎች አስተሳሰብ መሆኑ ነው፡፡ ያ ትናንትና የምታውቁትን ያህል እንዲያ እጅግ ስደግፈው፣ ሳበረታታው፣ እንቅፋቶችን ላነሣለት በእነኛ ጽሑፎቸ ስንት ስጥርለት የነበረው የትናንቱ አርበኞች ግንቦት 7 ከኦዴግ/ኦነግ ጋር በመጣመር ከወሰደው የተሳሳተ እርምጃ በኋላ ብቻውን የቀረው ግንቦት ሰባት ግን ነገር ዓለሙ ተበለሻሽቶበት እንዲህ ባለ የፖለቲካ ክስረት ውስጥ ወድቆ በማየቴ በጣም እንዳሳዘነኝ ነው የምነግራቹህ!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
amsalugkidan@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.