የጥቃት ኢላማ ለሆኑት ወገኖቼ፣ ፈተና ውስጥ ላለችው ሀገሬ መጮሄን አላቆምም (አይናዲስ ተሰማ)

ከጥቂት ቀናት በፊት የአርበኞች ግንቦት 7 ቃል አቀባይ የነበረውን የአርበኛ ዘመነ ካሴን መጥፋት በተመለከተ መረጃ እንዲሰጡን ግንቦቶችን በጽሁፍ ጠይቄ ነበር። ጽሁፉ በሳተናው ላይ ወጥቶ ስለነበር ብዙ ሰው ሳያነበው እንዳልቀረ እገምታለሁ። ዘሀበሻም በፌስቡክ ገጹ ሸር አድርጎት ስለነበረ በዚያ ላይ የተሰጡኝን አስተያየቶች ለማየት ዕድሉን አግኝቻለሁ። ተራ ስድቡ እንዳለ ሆኖ አንዳንዶች ግን በትግል ላይ ያለ ሰው ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል ማወቅ አለመቻሌ እንዳስገረማቸው በስላቅ አስተያየታቸውን አስፍረዋል። አስተያየት ሰጭወቼ ያልተገነዘቡልኝ በትግል ላይ ላለ ሰው መቁሰል፣ መማረክ፣ መሞት እንግዳ ነገር አለመሆኑን አለመዘንጋቴን ነው። እኔ እያልሁ ያለሁት ለምን የሆነው ነገር በትክክል አይገለጽልንም ነው። ተገድሎ ከሆነ በትግል ላይ እያለ ተሰዋ፣ ተማርኮም እንደሆነ መማረክ በሱ ስላልተጀመረ በውጊያ ላይ ተማረከ ቢባል የሚያሳፍር አይሆንም። መሸፋፈኑ ለምን! ዕውነቱ ይነገረን ለማለት ነበር የፈለኩት። አሁንም ቢሆን ትልቅ አላማ ይዞ ውድ ዋጋ ለመክፈል የተሰለፈው ወንድማችን እንደቀልድ ከቆሻሻ ገንዳ ተጥሎ ማንም እንዲረሳው ሊደረግ ስለማይገባ “ስለዘመነ ዕውነቱን ንገሩን!” ከማለት አልቦዝንም። ስለተስፋሁን አለምነው መጠየቄን አላቆምም። አማሮች ብቻ እየተለቀሙ ሲያልቁ ድምጼን አጥፍቼ ዝም ልል አልችልም። መከራ እየተቀበለ ስላለው ሕዝቤ፣ ፈተና ውስጥ ስላለችው ሀገሬ ጉሮሮየ እስኪሰነጠቅ እጮሀለሁ። ወገኖቼን “ንቁ!” እያልሁ እጣራለሁ። ውስጥ ለውስጥ እየታሸ እየተብላላ ያለው ብሶት አንድ ቀን ማንም ሊያጥፈው የማይችል ኃያል ክንድ እንደሚፈጥር እርግጠኛ ስለሆንሁ ያ ጊዜ እንዳይዘገይ ማለት ያለብኝን ሁሉ እላለሁ፤ ማድረግ ያለብኝን ሁሉ አደርጋለሁ።

ወገኖቼ!

በአሁኑ ጊዜ ሀገራችን በብዙ መጥፎ ነገሮች ተወጥራ የተያዘችበት ጊዜ ነው። ችግሮቹ ውጫዊ ወይም ውስጣዊ ሊሆኑ ይችላሉ። ትልቁ ችግር ግን የውስጥ ችግራችን ነው። ለውስጥ ችግራችን መፍትሄ መጥፋት ተጠያቂ የሚሆኑት በዋናነት የፖለቲካ ፓርቲወች ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲወች ሀገራችንን ወይም እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማያውቁ ናቸው ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት መላው ኢትዮጵያውያን በወያኔ መዳፍ ሥር ውለው እንደቆሎ መታሸታቸው ቀጥሏል።

የወያኔ መንግሥት በዐዕምሮ በሽተኞች የተሞላ በመሆኑ የሕዝብና የአገር፣ ጥቅምና አንድነት የሚያሳስበው አይደለም። ተቃዋሚውም ቢሆን ዘላቂ ሰላም እና የደህንነት ዋስትና ሊያስገኝ የሚያስችለውን መንገድ መምረጥ ያልቻለ የጥፋት ተባባሪ ሆኖ በሕዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው መከራ መቋጫ እንዳያገኝ እንቅፋት በመሆን ለወያኔ በስልጣን መቀጠል ትልቅ ድጋፍ የሚያደርግ በሽተኛ አካል ነው። በተለይ አብዛኞቹ የጎሣ ድርጅቶች ዛሬ ላይ ግፍ እየፈጸመ ያለውን ወያኔን መታገሉን ትተው ምንም ስልጣን የሌለውን አማራ ለማጥፋት በማሴር ጊዜያቸውን እና ጉልበታቸውን ላላስፈላጊ ነገር የሚያባክኑ ለአንጀት ካንሰር የጉንፋን ክኒን መዋጥ የመረጡ የለየላቸው ዕብዶች ናቸው። ይህ ሁኔታ በዚህ መልኩ እስከቀጠለ ድረስ ማንም ያሰበውን ሳያሳካ፣ ጥፋቶችን አርመን በሀገራችን ኮርተን በዕኩልነት እና በሰላም ለመኖር የሚያስችለንን ዕድል አምክነን በጭቆና ስር ለመኖር እንገደዳለን።

አማሮች መጥፎ ሁኔታወችን ወደመልካም አጋጣሚ ለመለወጥ፣ ከችግሮች መሀል ጥሩ ነገር ጨምቆ ለማውጣት ትኩረት ሰጥተን መስራት ይኖርብናል። በወያኔ ጎራ ያለውም ሆነ አብዛኛው በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፈው ኃይል አማራን በጠላትነት የሚያይ በመሆኑ የአማራው ዕጣ በአረቦች እንደተከበበው የእስራኤል ሕዝብ ሆኗል። እስራኤል እንደሀገር ለመቀጠል እና የሕዝቧን ሰላም ለማረጋገጥ ሌት ተቀን ጥንቃቄ የተሞላበት ተግባር ታከናውናለች። እኛ አማሮችም ራሳችንን ከጥፋት ለማዳን ልክ እንደእስራኤል ሕዝብ አንድነታችንን ጠብቀን የተጠና ትግል ማድረግ ይኖርብናል። በጊዜ ሂደት በተለያየ ስልት ቀስ በቀስ ሊያጠፉን እየሰሩ ያሉትን ጠላቶቻችንን መቅደም ይኖርብናል። ቢያንስ እነሱ ከሚያስቡት እጥፍ ማሰብ፣ እነሱ ከሚራመዱት እጥፍ መራመድ ካልቻልን አማራ ተረት ሆኖ ይቀራል።

ስለዚህ እያንዳንዱ ቤተሰብ አማራው የተደቀነበትን መከራ ለልጆቹ ማስጠናት፣ የአማራ ሕዝብ ታጋይ ድርጅቶች በአንድ በመሰባሰብ ረቀቅ ያለ የትግል ስልት ማቀድ ይኖርባቸዋል። በተለያዩ መንገዶች ወጣቱን በትናንሽ ቡድኖች በማደራጀት የማንቃት ሥራ መስራት፣ የመረጃ መረብ መዘርጋት፣ ለውትድርና የሚመለመሉትን ወጣቶች በአላማ ማስታጠቅ፡ በድራማ፣ በሙዚቃ፣ በስነጽሁፍ የተደገፈ የፕሮፓጋንዳ እና የቅስቀሳ ሥራ መስራት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። በአማራው ላይ የተፈጸሙ ግፎች ለታሪክ ተመዝግበው እንዲቀመጡ ሕዝባችንም የተፈጸመበትን እና እየተፈጸመበት ያለውን መከራ እንዲያውቀው ለማድረግ በወያኔም ሆነ በሌሎች ድርጅቶች በተለይ አማራን በሚመለከት የተነገሩ፣ የተጻፉ፣ በቪዲዮ የተቀረጹ ነገሮች ሁሉ በጥንቃቄ መሰባሰብ ይኖርባቸዋል። ሚስጥር መጠበቅ ቁልፍ ተግባር በመሆኑ ሕዝባችንን በከፍተኛ ዲሲፕሊን መግራት፣ እያንዳንዱ አማራ የጉዳዩ ባለቤት መሆኑን እንዲረዳ በጥልቀት የማስረጽ ሥራ መስራት ይኖርብናል።

አንድ መገንዘብ ያለብን ነገር አለ! የአማራ ድርጅት የሚባለው ብአዴን አማራ ባልሆኑ እንዲያውም አማራን በሚጠሉ ሰዎች የሚመራ ድርጅት መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለብንም። ጠላታችን ብዙ ነው። ሀገር በቀል የጎሳ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን በቅኝ ሊገዙ ሲሉ ውርደት የተከናነቡት፣ ከኢትዮጵያ ጥቅም ፈልገው የተነፈጋቸው፣ የሩቅና የቅርብ ሀገሮች ሁሉ የአማራን ውድቀት ማየት የሚናፍቁ ናቸው። በምግብ ለሥራ ያሰባሰባቸውን ድርጅቶች ይዞ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት መስርቻለሁ እያለ የሚያሾፈው ወያኔ በበኩሉ በ1968ቱ ማኒፌስቶው ያረጋገጠው የትግራይ ሕዝብ ጠላት አማራው እንደሆነና መጥፋት እንዳለበት ነው። በዚህ መሰረት አማራውን የማጥፋት ሥራ ያለገደብ ሲሰራ ቆይቷል፤ አሁንም ቀጥሏል። ተማምነው፣ ተማምለው መርሀ ግብር ነድፈው የተነሱበት ጉዳይ ስለሆነ ዕቅዳቸውን ካላሳኩ በስተቀር አርፈው አይተኙም። የውጪ ትኩረት ላለመሳብ ሲሉ በአማራው ላይ እየደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ ጋብ ያደረጉ ይመስሉና መልሰው በሌላ ስልት የማጥፋቱን ሥራ ይቀጥላሉ። እንዲህ እንዲህ እያሉ ቀስ በቀስ እኛን አጥፍተው መሬታችንን ወርሰው እፎይታን ያገኛሉ።

እነሱ አማራውን ለማጥፋት በጽናት ሲሰሩ እኛ ራሳችንን ለመከላከል ጽናት ሊጎድለን ከቶም አይችልም። ሕዝብ ጨርሶ አይጠፋም የሚለውን ነገር ከአፍ አፍ እየተቀባበሉ ቢያወሩት ትርጉም የሚሰጥ አይደለም። ጋፋት አልጠፋም? ካጠፉት የማይጠፋ ነገር የለም፤ ማንነትን ማጣትም መጥፋት ስለሆነ። ስለዚህ በማንም ሳይሆን በራሳችን ትግል ከወያኔና መሰሎቹ የጥቃት ከበባ ለመውጣት አንድ ሆነን በረቀቀ ስልት፣ በከፍተኛ ዲሲፕሊን፣ በጽናት ሌት ከቀን መስራት ይኖርብናል።

ለእኛው ያለነው እኛው ነን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.