በስያትል ከተማ የተካሄደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባዔ በመልካም ውጤት ተጠናቀቀ

በዘውገ ፋንታ

መግቢያ

በስያትል ከሚገኙት አንዱ ነባር ድርጅት፣ ‘የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ፎረም’ የተባለው ለስድስት ወራት ያህል የተዘጋጀበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባዔ ለሁለት ቀኖች ሲካሄድ ቆይቶ ዛሬ በምሽቱ በ12 ሰዓት ላይ በአስደሳች ውጤት ተጠናቋል። ይህ ጸሐፊ በቦታው ተገኝቶ ስለነበር፣ የቀረቡትን የተለያዩ ሀሳቦች፣ ውይይቶችና የጥያቄ መልሶች፣ ምንም እንኳን ሁሉንም ተንትኖ ለማቅረብ ባይቻልም እየቆነጣጠበ ከፊሎቹን ለማቅረብ ይሞክራል። ከአስራ ስምንት ሰዓት በላይ የተወሳውን  ለማቅረብ እጅግ ይከብዳል። ስለዚህ አንባቢ ይኽን እንዲረዳ ጸሐፊው ይጠይቃል።

በመጀመሪያ፣ ጸሐፊው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ፎረም ያደረገውን ጥረትና የጉባዔውን መሳኪያ ድርጊቶች መለስ ብሎ ወደፊት መጭውን በመመልከት ግምቱን ያቀርባል። ቀጥሎ የውይይቶቹን ቁምነገር ስለተናጋሪው ቅደም ተከተል በሌለው መልክ ያወሳል። ከዚይ በኋላ፣ አወያይ የሆኑትንና ያወያዩትን ጉዳዮች ከቀረበው ሰፊ ትችት እየገነጠለና እየነጣጠለ ያቀርባል። በመጨረሻ በጉባዔው ፍጻሜ ላይ የፈለቁ ጉዳዮች ስለነበሩ፣ ምንድን እንደሆኑ ጸሐፊው ለመግለጽ ይሞክራል። በመጨረሻ፣ የወደፊቱን አላማ አስመልክቶ የታቀዱትን ድርጊቶች ገልጾ ጽሑፍን ይደመድማል።

ውይይቶቹ

በሁለት ቀኖች በ16-18 ሰዓቶች ውስጥ ከ24 የማያንሱ ተናጋሪዎችን ማቅረብ በጥሩ ዕቅድ መሰረት የተዘጋጀ ቢመስልም፣ ለውጤቱ ችግር አስከትሏል ወይስ አላስከተለም የሚለውን ጥያቄ ላዘጋጁ ኮሚቲ ይተወዋል። በልምድ አንጻር ግን፣ ጥቃቅን ጉድለቶች ታይተዋል። የፕሮግራም ግጭቶች እንዳይኖሩ አስቀድሞ ሰፊ ጥናት ማድረግ የተጋባዡን ቁጥር እጅግ ይለውጠዋል።

ጉባዔው ተጀምሮ፣ ከመጀመሪያዎቹ ተናጋሪዎች ታላቁ መምሕር ፕ/ር መስፍን ወ/ ማርያም የኢትዮጵያ ፍልስፍናዎችን ያዘሉ ታሪኮችን በጽሑፋቸው አቀርበዋል። የጥንቱን፣ ያሁኑን እንዲሁም የ2020 ትንቢት ስለ ተናገሩ፣ ሕዝብ በጉግት እንዲጠብቅ አድርገውታል። የኢትዮጵያኖች የመለገም ባህሪ ዘውድ አፍራሽ ጭምር ስለሆነ፣ የደርግን ምንግሥት ምሳሌ በማድረግ ገልጸዋል። የወያኔውን መንግሥት ጽዋው በዚሁ መልክ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። ወያኔ በማያውቀው ‘ሙሉአለም’ ፍልስፍና ሕንጻን በመስራት ሀገርን አዳብራለሁ በሚል ግምት እየባከነ እንደሆነ ገለጹ። ‘ግሎባላይዜሽን’የሚባለው የእንግሊዝኛ ቃል፣ በአማረኛ ‘ሙሉአለም’ እንዲባል አዲስ ቃል በመዝገበቃል/በቃለመዝገብ እንዲገባ አድርገዋል። ጽሑፋቸው እንዳለ በኢትንተርኔት/ ድረገጾች እንደሚሰራጭ ይገመታል።

አቶ ሌንጮ ባቲ ስለ ኢትዮጵያ መንግሥታዊ አለዋወጥ ስልት ሰፋ ያለ ሀሳብ አቅርበዋል። በሳቸው ልቦናና ጥረት፣ ድርጅታቸው በሂደቱና ፍልስፍናው መሰረታዊ ለውጥ እንዲያደርግ የተከፈለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት ሲገልጹ ከተገንጣይነት ሚና ኢትዪጵያን በዲሞክራሲ መገንባቱ የተፈለገውን ግብ እንደሚያመጣ በመረዳት፣ ቅዱስ አላማን በመጸንሰስ አንዱ የኢትዮጵያ የለውጥ ኃይል መሆናቸውን ገልጸዋል። አድማጩ ከመቀመጫው በተደጋጋሚ በመነሳት ለሰማው ታሪካዊ ድርጊት የተሰማውን ደስታ በከባድ ጭብጨባ ገልጿል። ከሳቸው ቀጥለው የተናገሩት መጋቢ ኃዲስ ልዑለ ቃል አካሉ አለሙ ስለ አቶ ሌንጮ ሲናገሩ፣ በቴሌቪዥንና ሬድዮ ሲናገሩ ስሰማ፣ የሚፈሩ ሰው አድርጌ እገምታቸው ነበር። እኒህን የኢትዪጵያ ግርማሞገስ የተሞላባቸውን መልካም ሰው በአካል ሳያቸውና ንግግራቸውን ሳዳምጥ አዕምሮየ ተለውጦ ልገልጸው የማልችለው ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል።  አዳማጩም እንዲሁ የተሰማውን ስሜት ለመግለጽ ከመቀመጫው ብድግ ብሎ የደመቀ ጭብጨባ አድርጓል። አቶ ሌንጮ ስለ አዲሲቱ ኢትዮጵያ ያላቸውን የዲሞክራቲክ ለውጥ ጎዳና እና በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት የሚገነባውን ርዐይ በሚገባ አስቀምጠዋል። ይኼም በዕኩልነት ላይ የሚመሰረት ብቻ መሆኑን ተንትነው በመግለጽ ነው። ኢትዮጵያ ለወገኖቿና ዜጎቿ ዕኩል ዕድል፣ ዕኩል መብትና ዕኩል አገልግሎት የምትሰጥ እንድትሆን የአሁኑ እና የወደፊቱ ትግላቸው እንደሆነ ገልጸዋል። ሀስባቸውን እና ሕልማቸውን በመደገፍ አድማጩ በሞቀ ጭብጨባ ተቀብሏል።

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ፣ ወያኔ አቅጣጫው ሲቀይር፣ ቀድሞ የነበረውን አላማ ሲለውጥ፣ ስለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳት ያደረባቸውን ስጋት ለድርጅቱ በመግለጽ ተቀባይነት ስላጡ ክድርጂቱ የተለዩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ እሳቸው ከፈሩት ጥፋት ላይ መድረሱን ገልጸዋል። ዶ/ር አረጋዊ ወያኔ ማለት ትግራዮች፣ ትግራዮች ማለት ወያኔዎች ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል። ወያኔ ኢትዮጵያን ከሚያሳፍር ደረጃ ማድረሱ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ጥፋትና ዕልቂት ደረጃ እያሸጋገሯት እንደሆነ ተንትነው በማስረዳት፣ ይኼን አስጊ ሁኔታ የሚገታው የኢትዮጵያ ሕዝብን ማደራጀት አስፈላጊ እንደሆነ አጥብቀው አሳስበዋል። ወያኔዎች መሄጃ ስለሌላቸው እስከመጨረሻ ደም የሚፋሰሱበት እንጂ ለለውጥ ሀሳብ ብቁ ስላልሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድነት ያለ ዕልቂት ኃይላቸውን ባዶ የሚያደርግበትን መፍትሔ መንገድ ማፍለቅ እንዳለበት በሰጡት ሀሳብ አብራርተዋል።

ቀጥለው እንዲናገሩ የተጋበዙት መጋቢ ጥበበ(እንደ አወያይ)፣ መጋቢ ኃዲስ ልዑለ ቃል አካሉ አለሙ፣ አቶ መንሱር ኑሩ፣ ኢቫንጀሊስት ያረድ ጥላሁን ነበሩ። መጋቢ ጥበበ፣ እነዚህ የኃይማኖት አባቶች እንደ ኃይማኖት መሪ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ በሚዘረጋበት ታላቁ አዳራሽ ምሶሶዎቹ እንደሆኑ ገልጸዋል። ከነሱ ውጭ ምንም ለውጥና ዘላቂነት ያለው ርምጃ እንደማይመጣና እንደማይሰራ አስረድተዋል። የተባለውን ሁሉ ለመተንተን ባይቻልም፣ አባታችን መጋቢ ኃዲስ ልዑለ ቃል፣የኢትዪጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን  ለድሆች እና ለጭቁኖች የቆመች መሆኗን ከታሪክ አንጻር በሰፊው አስረድተዋል። ቤተክርስትያን መሪን (ንጉሥም ይሁን ፕረዚዳንት)ኃይሉ ሲከፋ እንዲታገስ በመምከር፣ ካልተቀበለም በማውገዝ የተደረጉትን ታሪኮች በሰፊው ገልጸዋል። ወንጀለኛ ሸሽቶ ቤተክርስትያንን መጠለያ ሲያደርግ፣ ሲቻል ምሕረት ካልሆነም በጎ ፍትህ እንዲሰጠው ስታደርግ መኖሯ ግልጽ ነው (ጸሐፊው)። በጦርነትም ጊዜ ታቦት ከወታደር ጋር አብሮ እንዲዘምት የተደረገበትን ዘመን ሁሉ ገልጸው የተሰውቱንም ጳጳሳት ጠቅሰዋል። ለወደፊትም ከስደተኛው ሕዝብ ጎን ምን ጊዜም የሚቆሙ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዚያም በላይ በአስተባባሪነት ለመሳተፍ ያላቸውን ፈቃደኝነት ገልጸዋል። አድማጩ የመጋቢ ኃዲስ ልዑለ ቃል አካሉን ምክሮች በታላቅ ደስታ በጭብጨባ ተቀብሏል። አቶ መንሱር ኑሩ ኢትዪጵያ ለእስልምና ኃይማኖት ዕድገትና ታላቅነት ያበረከተችውን በሰፊው ተመራምሮ በይፋ የማይታወቁትን ዕንቁ ታሪኮች አሰምቷል። ይኽ ማለት በኢትዮጵያ የእስልምና ኃይማኖት ለፍትሕ፣ ለነጻነትና ሰላም የቆመ መሆኑን መሰረቱን ለመግለጽ ነው ብሏል። ነብዩ ሞሀመድ የተወለደበት ቦታ ሲከበር ከዚያ ክብር ቀጥሎ፣ እምነቱ ወደ አለም የተሰራጨበትንና የተስፋፋበት ሀገር ኢትዮጵያ ስለሆነች ምድሩም ሕዝቡም በእስልምና የተባረከ መሆኑን እንዳይታወቅ የዘመኑ ፖለቲካ ውዝግቦች ታሪኩን ስለሸፈኑት፣ የአቶ መንሱር ዘገባ ልዩ ቦታ ይገባዋል(ጸሓፊው)። ምሑሩ ፓስተር ያሬድ ጥላሁን በኢትዮጵያ ፍልስፍና ዕድገት ላይ ወደር የሌለው ደግሞ ደጋግሞ መነገርና መስተማር ያለበትን ጥበብ አቅርቧል። በዕውነቱ እያንዳንዱ አረፍተነገር መሪ ቃል የያዘ ስለሆነ ለይቶ ማቅረቡ አስቸጋሪ ሆኗል። ምሑር ያሬድ ያቀረበው ታሪካ አዲሲቷን ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን የሚገነቡ ምርጥ ሃሳቦች፣ መሪዎችን እና ድርጅቶችን እንዲሁም ለመላው ሕዝብ ብሩህ ገጽ የሚያሳዩ ስለሆኑ በሰፊው መሰራጨት እና መታወቅ ያለበት ባህላዊና ታሪካዊ ጥናት ነው(ጸሐፊው)።

ቀጥሎ ዶ/ር በያን ኣሶባ፣ ፕ/ር ተድላ ወ/ ዮሐንስ እና ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ በየተራ በመቅረብ በንግግራቸው ጥልቀትና ብልህነት ሕዝቡን በመመሰጥ ከመቀመጫው እንዳይንቀሳቀስ አድርገውታል። ፎ/ር በያን በፖለቲካ ያሳለፉትን አሁንም እየተዋጡት ያለውን ሁኔታ ጠቅሰው ሲናገሩ ሕዝቡ አክብሮቱን ቆሞ በጋለ ጭብጨባ ገልጿል። እየተናደ ያለውን ታላቅ ሕዝብና ሀገር እንደ ሶማሊያ እና ሌሎች የወደሙ ሀገሮች ኢትዮጵያም ይህ ጽዋ እንዳይገጥማት አስተዳደሩንና ያለውን ስርዓት ማስወገድ እንዲቻል ሕዝብ መሰባሰብ እንዳለበት ገልጸዋል። እንደተባለው ግንዱ ያለ ቅርንጫፍ እና ቅጠል፣ ቅርንጫፍና ቅጠል ያለ ግንድ ዛፍ እንደማይባል ሁሉ፣ የኦሮሞው ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ግንድ፣ ቅርንጫፍ እና ቅጠል ሆኖ እንዲኖር በበኩላቸው ካለፈው የበለጠ አስተዋጽዖ እያደረጉ ያሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ዕውነተኛ ዲሞክራታዊ ፌደሬሲሽን ለሕዝባዊ፣ ኢኮኖማዊና ፖለቲካዊ (አስተዳደር) ዕድገት የሚበጀውን ለመቀየስ ሰፊ ትኩረትና ጥናት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እኒህ የኢትዮጵያ ታላቅ ልጅ አዲሲቱን ኢትዮጵያ ከመላው ሕዝቦቿ ጋር ተባብረው ለመገንባት ወደኋላ እንደማይሉ አስገንዝበዋል።

ፕ/ር ተድላ ኢትዮጵያ የታደለች ከሚያሰኟት ዕንቁ ልጆቿ አንዱ ናቸው። የመሪዎችን የተፈጥሮ ጸጋ ወይም የተፈጥሮ እንከን በምሳሌ እያረጉ አስተምረዋል። ግራ የሚያጋባውን የወያኔን ሰው ባሕሪ የተፈጥሮ ጉድለቱን ሌላው ሰው በልዩ መልክ እንዲረዳው ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው ብለዋል። ይኼም ለመጠንቀቅ እንጂ ለመቅረብና ለመወዳጀት እንዳልሆነ ይመስላል። ዓለም አሁን ያለበት ከባድ ችግር፣ ኢትዪጵያ ልትጨመር አፋፍ ላይ ይታወቃል። አሁን ያለችበት አዘቅት፣ በተፈጥሮ እጅግ ተጣመው በተፈጠሩት ምክንያት እንደሆነ በሚገባ ገልጸውታል። እኒህ ምሑር በየጉባዔው በመገኘት ይህንን ዕንቁ ፍልስፍና ለኢትዮጵያ ወገኖች ቢያስተምሩ ጠቃሚነቱ ወደር የሌለው ይሆናል። በጎውን ሕዝብ የሚያበለጽገውን መንገድ ሲያሳዩ፣ እንከኑን ደግሞ አንጓሎ የማስወገዱን መንገድ ጥበብን የሚጠይቅ መሆኑን አሳይተዋል። የሰውን የተለያየ ተፈጥሮ መገንዘቡ ለመሪም ለተካታዩም ሕዝብ እጅግ ጠቃሚ ነው።

የሚቀጥለው ተናጋሪ ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ ነው። ጸሐፊው ሰለ ዶ/ር ኮንቴ ንግግር ለመጻፍ ሲጀምር ብዙ ሀሳቦች በአዕምሮው ተንዣበዋል። “አይ! እኒህ ወለየዎች/አፋሮች ሊንጋጉ ነው!የግመል ሽንት ወደኋላ!ቀጥለውም እንዝፈን እስክስታ!ፍቅር! ፍቅር! ወሎ መጀን! እንጫወት!’አይ በቃችሁ! ምነው ሸዋ!’” ይህን ያሰበ አልተሳሳተም።

ፕ/ር መስፍን ሕዝብ (ወሎ?)ለግሟል፣ የለገመ መንግሥት ያጠፋል ያሉት እንዳለ ሆኖ፣ የኢትዮጵያ አፍና ሆድ ትግራይ ቢሆንም (ራሱ ታች ወርዷል፤ እግሩን ኤርትራ አድርገን እናሰብ)የኢትዪጵያ ዕምብርት ወሎ ነው። ቅኔአቸው እንደ አቶ ሌንጮ የላቀ መሆኑን ዶ/ር ኮንቴ በሰጡት መልስ አድማጭ ተረድቷል። ወይ ቅኔ! መጥቃ ሄደች ዕድሜ ለኮንቴ!አቶ ሌንጮ ከብሩህ ገጻቸው ላይ እንደታየው ከልብ ካሳቀ፣ ሌላውን አንደፋድፋለች ማለት ይቻላል። ይብላኝ በአዳራሹ ላልነበረውና ለቀረበትና በቅቡአ ወደ ኃላ ለቀረው! የኢትዮጵያ ልጆችን በያሉበት በላይ በታች እግዜር ይባርክ!

ዶ/ር ኮንቴ በፍልስፍናው ጥልቀት እና ሰፊ ምርምር፣ አርቆ አሳቢነቱ፣ በቅኔው እና በመሪነቱ ነገ ዘረያዕቆብን ተካ ቢባል የዛሬው ትንቢት ሆነ ማለት ነው። የሉሲ የልጅ ልጅ ነኝ ባዩ ዶ/ር ኮንቴ መጀመሪያ የራሱን ታሪክ ሲናገር በፎቶግራፍ ጭምር ነበር። ዳሎል የተባለውን ልዩ ምድር ከ10,000 ዓመቶች በፊት የፈነዳው እሳተ ገሞራ ያጠፋውን የአፋር ምድረገጽ ትርፍራፊ፣ ሌሎቹንም የኢትዮጵያ ልዩ ሀብቶች የተቀበሩባቸውን ምድረገጾች በልጅነታቸው የግመል ዕረኛ ሳሉ የሮጡበት አስደናቂ ምድር ፎቶግራፎች ለናፈቀው ወገን አሳይተዋል። የአፋር ሕዝብ የደረሰበትን ግፍ እንደ አቧራ አራግፎ ወደፊት የሚያስፈልገውን ለማድረግ አንድም ደቂቃ ማባከን እንደሌለበት ዶ/ር ኮንቲ ግልጽ አድርጎ በመግለጽ የወደፊቱን የሕብረት ግስጋሴ ስራ መሰረተ ሀሳቡንና ዕቅዱን አስረድቷል። የአፍር ሕዝብ ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ ምሰሶ እንደሚሆንና እንደሚገባው በታሪክ አንጻርና የሃያ አንደኛው ዘመን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ማዕከል እንደሚሆን አጉልቶ አሳይቷል። በዚህ ሀገራዊ አንድነት ስልት ጉዳይ ላይ ያላውን ኃላፊነትና ሀገራዊ-ወገናዊ ግዳዥ እንዳለበት ገልጿል።

ከዚህ ቀጥሎ፣ የጋዜጠኞችን ሚናና በግብራቸው ላይ የሚያጋጥማቸው ችግር (በኢትዮጵያና በዲያስፖራው)ተንትነው ለመግለጽ የብዙ ሽልማት ተቀባይ ባለቤት የሆነው አቶ አበበ ገላው፣ በዚህ ሙያ ቁንጮየዋ ወ/ሮ ንግሥት ሰይፉ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም የሰው ልጅ መብትን ባጓደለ መንግሥትና መሪዎች ላይ ማስረጃ ለሆነችው የብዙ ክብር ሽልማት ተቀባይዋና በለቤት ክብርት ወ/ሮ ርዕዮት አለሙ፣ በዚሁ ሙያቸው ሌት ከቀን ከወያኔ ሸረሪቶች ጋር በዲሞክራስያ ብዕራቸው የሚፎካከሩና ለወገናቸው በሰላም ኃይል ተሰልፈው ጧት ማታ የሚሟገቱት የጥብቅና ምሑሩ አቶ እሸቱ ሆማ ኬኖና የዶክቴሬት ፍልስፍና ተማሪው የታወቀው የወ/ሮ ርዕዮት አለሙ ድርጅት ዞን 9 ሚድያ አጋር ቆርቋሬ አቶ እንዳልካቸው ጫላ፣ እነዚህ ወጣት ሊቆች እጅግ የሰፋና የጠለቀ መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ አበበ ገላው የእሳት ዋና ዲሬክተር ሆኖ መስራት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በማስተላለፊያው ሞገድ  በየቀኑ በሚደርሰው የቴክኒካል ችግር፣ በሚተላለፈው ዜና የሚመጣው ውዥግብ ድርጂቱ በጽናት መቆየቱን እያደነቀ፣ ከዚያም በሰራተኞቹ ላይ የሚደርሰውን ከባድ ፍትትን በምሳሌ እየጠቀሰ አስረድቷል። ከዚይም ለተሰነዘሩት ክሶች በቂና አስደሳች የሆኑ ማስረጃዎችን በማቅረብ ችግሩን ቁልጭ አድርጎ ገልጿል። አበበ ገላው የኢትዪጵያኖችን ከፍተኛ ችግር በዓለም ደረጃ ያቀረበ ሰው ስለሆነ፣ ከሱ የሚጠበቀው እጅግ እያደገ መሄዱ ለማንም ሰው ግልጽ ነው። እሱም አብረን እንስራ፣ የናንተን የተለያየ ድጋፍ ምንጊዜም የምንሻ ብቻ ሳንሆን፣ ድጋፉን ማገኘቱ ግዳታ ነው ሲል ገልጿል። ወ/ሮ ርዕዮት አለሙ ያሳለፈችው ተነግሮ የማያልቅ ግፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ወገኖቿ የደረሰውን አሁንም እየደረሰ ያለውን እጅግ አሰቃቆ ግፍ ተሸክማ የምትኖር መሆኗን ገልጻለች። በህይዎት እስካለች ድረስ፣ ፍትህ በኢትዮጵያ እስኪነግስ ድረስ ያለማቋረጥ እንደምትታገል ቃል ገብታለች። ጠበቃው አቶ እሸቱ ሆማ ኬኖ በ’ፊስቡክ’ከ40 ሺህ ሰራዊት በላይ ተከታይ ያለው ሲሆን፣ ወገኖችን አሰባስቦ ባለታሪኳ እናት ሀገራቸውን ክብሯን፣ ስሟን፣ የወገኖቿን አንድነት ሀሳብ እያሰራጩ ይገኛሉ። የዲሞክራሲ አስተዳደር ተሟጋች በመሆን፣ ክፉው መንግሥት ተፈንቅሎ የሕዝብ መንግሥት እንዲተካው የሰላም ለውጥ እንዲሆን እያነቃቃ ይገኛል። አቶ እንዳልካቸው ጫላ በበኩሉ እጅግ የሚወደደውን የዞን 9 መዲያን የሚያስተናግድ ሲሆን እሱም እንዲሁ የሰብአዊ መብት የሚነሱትን ህገወጥ ድርጊቶች እየተከታተል ያወጣል። እነዚህ ወጣቶች ብዙ ሺህ ደጋፊ ቢኖራቸውም፣ የወያኔ ትንኞች የሚፈጥሩትን ውዥግብ መቋቋም ከባድ ስራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመጨረሻዎቹ ተናጋሪዎች አንዱ፣ እድሜ ልክ ለኢትዪጵያ ዲሞክራሲ የታገሉት፣ አሁንም ከትግሉ ያልተለዩት የሀርፐር ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምሕር ፕ/ር ጌታቸው በጋሻው፤ ሁለተኛ፣  በኢትዮጵያ አንዎክ ዜጎቿ ላይ ወያኔ የፈጸመውን የዘር ማጥፋት ድርጊት በዓለም ደረጃ እንዲታወቅና እንዲመዘገብ ያደረጉ፣ አሁንም ለተበደሉት ፍትህ ለማገኘትና እንዲያገኝ የሚጥሩና የሚሟገቱ፣ በተጨማሪ ላዲሲቱ ኢትዮጵያ ምስረታ እንቅስቃሴ ግብረኃይል በዲሬክተርነት ደረጃ የሚያገለግሉት የኢትዮጵያ አለኝታ አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ ሶስተኛ፣ ለኢትዮጵያ በተለያዩ የውትድርና እና በሲቪክ የሥልጣን መደቦች ለረጂም ጊዜ ያገለገሉ፣ በተባበሩት መንግሥታት በተለያዩ ከፍተኛ ደረጃ በምርምርና በተመልካችነት ያገለገሉ፣ አሁን ድግሞ በቆረቆሩት የ“ስትራተጂክ ኤንድ ሰኩሪቲ” ጥናቶች ድርጅት ውስጥ በዋና ዲሬክተርነት የሚያገለግሉት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ናቸው።

አቶ ኦባንግ ዲሞክራሲ በህዝቦች ላይ እንዲሰፍን መሰረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ በየአንዳንዱ ግለሰብ ሲኖር እና ሲታይ ነው ይላሉ። ዲሞክራሲ ከፍተኛ የሰው ባሕሪን ለውጥ የሚጠይቅ እንደሆነ አስረድተው፣ መጀመሪያ ዜጋዎች ብቁና ብቁ የሆነ ባህሪ መያዝ አለባቸው ይላሉ። ዲሞክራሲ በማይተዋወቁ ሰወች መካከል አብሮ የመስራት ቀርቶ መግባባትም እንኳን ያዳግታል። ካልተግባቡ ደግሞ፣ ፈጽሞ አንድ አላማና ግብ ለመፈየም የማይቻል እንደሆነ በምሳሌ እያረጉ አስረድተዋል። አሳፋሪውን ባህላችንን፣ አደናቃፊ ሀሳቦችን ጥለን መሄድ ስላለብን ብዙ መተዋወቅ ማድረግ እንደሚገባን ገልጸዋል። በምሳሌ ያቀረቡት እያንዳንዱን ሰው ራሱን እንዲፈትሽ የሚያደርጉ ምሳሌዎችን አቅርበዋል። አዳማጮች በመቆምና ባልበረደ ጭብጨባ አዎንታቸውን ገልጸዋል። ኦባንግ የኢትዮጵያና ለዲሞክራሲዋ ሂደት አንዱ ዋናው ኃይልና ተስፋ ናቸው። በዚሁ ተምሳሊነት በአሜሪካ ኮንግረስና በሌሎችም ሀገሮች ተጋብዘው ስለ ሀገራቸው አስጊ ሁኔታና ጭቆና ከፍተኛ ገለጻ አቅርበዋል።

ዶ/ር ጌታቸው አስቀድመው ሀሳባቸው ሰፊ ምርምርን እና ጥያቄን የሚያስከትል መሆኑን ገልጸዋል። በፍልስፍናው አንጻር፣ የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ (በጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃምና ሸዋ የሰፈረው ሕዝብ)ወያኔ በሁለቱ መካከል በፈጠረውና ባስፋፋው ግጭት ዳግማዊ ዕልቂት እንዳይመጣ፣ በአንድነት የጋራ ጠላትን ወያኔን እንዲቋቋሙ መግባባትና አብሮ የመስራትን ዕቅድ ሲያደርጉ የሚያስከትለው ሰፍ ጥቅምና ጉዳትም በሰፊ ምርምር ያጠኑትን አስረድተዋል። ጽንሰ-ሀሳቡ የዲያስፖራ እንዳይባል፣ “የጎንደሩ ሕዝብ ‘ደምህ ደሚ ነው!’ በማለት ለኦሮሞው ሕዝብ መልዕክቱን ሲያስተጋባ፣ በአጤፌታው የኦሮሞው ሕዝብ ትክክል ለኔም‘ደምህ ደሚ ነው!’ሲል መመለሱ፣ የመግባባቱን መሰረት ፈጥሯል ብለዋል። ይህ ታሪካዊ እንቅስቃሴ፣ ወያኔን በከፍተኛ ደረጃ እንዳስጨነቀው ፕ/ር ጌታቸው ገልጸዋል። ከባርነት አውጥተን ነጻነት ብናድላቸው፣ ባርነትን መልሰው መረጡ በማለት ወያኔውች በተለመደ ባህሪያቸው የተናገሩት የኦሮሞና አማራ ሕዝብን በበለጥ የሚያስተባብር አድርጎታል ብለዋል። በዚህ ጸሐፊ አስተሳሰብ፣ የሁለቱ ጎሳዎች በጠቅላላው የሌሎቹንም ጎረቤት ሀገሮች የፖለቲካ ገጽ ይለወጣል። ኤርትራ የፌደሬሽኑ መስራች ለመሆን ትሽቀዳደማለች። ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያ ሁለት እጆቿን፣ ኬንያ በኢኮኖሚክ ለመተሳሰር እጃቸውን ይዘረጋሉ። ይህ የወያኔ ስልት ሳይሆን፣ በውድቀቱ ማግስት የሚመጣ ጉዳይ ነው። ኢሳኢያስ “ባርነት ወይስ ነጻነት?ምረጡ!” ብሎ ነበር። አሁን ኤርትርያኖች “ምርጫው ይደገም። አለበለዚያ ‘ባርነት’ አጥግቦን ነበር፣ ባርነትን እንመርጣለን።” ይላሉ ተብሏል። ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው እንዳሉት፣ የሁለቱ ዘርፍ ህዝቦች (ኦሮሞና አማራ)አንድነት ወያኔን እጅግ አድርጎ እንዳስፈራውና ለምን እንዳስፈራው በምርምር ያገኙትን ገልጸዋል። ወያኔ በዚህ ግልብጥብጦሽ በደም በተለወሰ እጆቹ ላይ ሰላማዊ ዘለቄታ ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ አመልክተዋል። ዳሩ ግን፣ የኢትዮጵያ ሁኔታ ከማትነሳበት ደረጃ ወያኔዎች እያደረሷት መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዲሞክራሲውና ለዕድገቱ ሌላ አማርጭ እንደሌለው ያስረዳሉ። አንድነቱ የሚካሄድበትን ስትራተጂክ መንገድ ለወገናቸው ለክቡር ሻለቃ ዳዊት እተዋለሁ ስላሉ፣ በዚህ ልምድ እሶት የማይታሙት ክቡር ሻለቃ ዳዊት ከፍልስፍናው አስተሳሰብ ወደ ምድረ-ገቡ ስርዓት በማምራት ዕቅዱን በትንተና ገለጹ።

አማራ ነህ ባይባልም፣ አማራ ነኝ የሚለውን መከራከር ከማይቻልበ ዘመን ገብተናል። ነፍጠኛ ነህ የተባለው አሁን ‘አዎ! ትክክል ነፍጠኛ ነኝ የሚለውን መገፍተር ከማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። የኢትዮጵያን አንድነት ማገሮች ናቸው። ምሶሶዎቹና ማገሮች፣ ሻለቃ ዳዊት ኢትዮጵያን የመገንቢያ ወታደሮች ሆነው አገኝቷቸዋል። ወያኔ በኔ ላይ ኢትዮጵያ የምትለውን ቤት አትሰራም በሬሳየ የሚል አቋም እንዳለው ፕ/ር ጌታቸውና ፕ/ር ተድላ ገልጸውታል። ይህ ጸሐፊ ባለው(ፕላንኒግ/ ኢንጂነሪንግ)አስተሳሰብ መሰረት ቤት ከቤት በላይ ለምስራት እንደሚችል ምሳሌ ለሻለቃ ዳዊት ስራ አመቻች ዕቅድ ሊያቀርብ ይሻል።

በአንድ ኮረብታ ላይ አንድ ቤተሰብ ከአንድ ቤት በላይ ቤት ሊሰራ ያቅዳል። የኗሪው ቤት ባለቤት፣ ከበላየ ሌላ ቤት ከተሰራ ጎርፍ ሊያጠቃኝ ነው። ስለዚህ እንዳይሰራ አደርጋለሁ በማለት ከማዘጋጃ ቤት የስራ ማገጃ አቤቱታ ያስገባል። ማዘጋጃ ቤቱ፣ ከላይ የሚመጣው ጎርፉ የታችኛውን ቤት እንዳያጥለቀልቅ ፈቃድ እንድታገኝ ማገጃ ዕቅድ አምጡ ብሎ ይመልሳቸዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን ግቢና አጥር የማይነካ፣ የወያኔ ልጆች መጫወቻ ሚዳ በውሀ እንዳይጥለቀለቅ፣ ጥሩ ዕቅድ አምጣ ብሎ ሻለቃ ዳዊትን አዘዘ ማለት ነው። እንደማለት አርጋችሁ ውሰዱት። ሕዝብ ለነበረው አግዞ ለዚያኛው ዕድል አይነሳም። በተዘዋዋሪው መልክ እንዲሁ። የቀረበው ዕቅድ አላለቀም። አልቆ መቅረብ የነበረበት ጊዜ አይደለም። ሻለቃ በጉባዔው የነበሩትንና ሌሎቹን አካቶ፣ ቧንቧውን ቀብሮ አንድም በመሬት ላይ ጠብታ ውሃ (ደም) እንደማይፈስ መልካም ዕቅዱን ለሕዝብ ማቅረብ አለበት። ወታደር ስለነበር ይች ለሱ ቀላል ነች። ዕድሜውን የሚጨርስባት አትሆንም። ቶሎ አጥንቶ ማቅረብ አለበት። እግዜር ይርዳው!

ትንሽ መሰናክል

ተናጋሪ እንግዶች ከስድስት እስከ 20 ሰዓቶች በአየር ተጉዘው እንደመጡ ተነግሯል። ለሃያ ደቂቃ ንግግር መሆኑ ትልቅ ስህተት እንደነበር አዘጋጆቹ አጥብቀው እንዲያስቡበት ማሳሰብ ያስፈልጋል። እንኳን ዶ/ር ብርሃኑ አልመጡ!ተናጋሪዎች ሶስት ወይም አምስት ተጨማሪ ደቂቃዎች መውሰዳቸው የሚያጠያይቅ አልነበረም። ግን አንድ ሰው (ከአዘጋጆቹ መካከል አይመስልም) ዳንዔል (?)የተባለ ከመድረክ ወጥቶ፣“ሽማግሌዎች ከኛ ከወጣቶቹ ተማሩ!”ማለቱ ተሰማ። ፕ/ር መስፍን ተነስተው፣ ወጣቶች እኮ ናቸው  ይችን ሀገር አዘቅት ውስጥ የከተቷት። ለስልጣን ሺሚያ እርስ በርስ ተጫረሱ፣ ተገዳደሉ። አሁን የቀሩት አርጀተው (ዘወር ብለው በመቃኘት)እዚህም አይጠፉም አሉ። “ውሰዳት!ተረከብ” አሉት መሰል፣ ለዚያ መለስ፣ የጠፋችና የተበላሸት ሀገር ምኗን እንረከባለን?የሚል መልስ ሰጥቷል። ፕ/ር ጊታቸው ሊናገሩ ሲቀርቡ፣ ለዚሁ ሰው፣ ከተነገረው ትምህርት ቀስመህ ቢሆን ኖሮ አንድም ሰከንድ በከንቱ አለማባከናችንን ትረዳ ነበር። ሽማግሌዎቹ የተናገሯቸው ቃሎች ጥበብ የተሞላባቸው ሕዝብን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ናቸው በማለት ሊያስተምሩት ሞከረዋል። በዚህ ጸሀፊ ግምት ከነበሩት አዳማጮች 80% የሚሆኑት ከአርባ ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑት ይመስላል። ከእንግዶቹ አንዱ በዚህ ወርቅ ጉባዔ ለምን ብዙ ሰው ሳይሳተፍ ቀረ ሲሉ ጠይቀዋል። የመጡትን ከማማረር ይልቅ ዳንዔል ከውጭ ያሉትን ጓደኞቹን ሰብስቦ ማምጣት ይሻለው ነበር፣ ወይም እሱም ከዚያው በቆየ!

የአቅጣጫ ግጭት

በደመቀ ጭብጨባ የፕ/ር ጌታቸውና የሻለቃ ዳዊት ንግግር አልቆ ነበር። ግን፣ የቀረበውን የፍልስፍና መርህ እና የስራ ዕቅድ ትልቅ ጥያቄና መሰናክል ከሁለት አቅጣጫ ተሰማ። አንድኛው ከፕ/ር መስፍን ወለደማርያም የቀረበው አስተያየት ነበር። ጉባዔው እስክ ጧት ድረስ በደህና ተካሂዶ ነበር። አሁን በሁለቱ የቀረበው ሌላውን ሁሉ ዝጭ አድርጎታላ በማለት ገለጹ። ዶ/ር አረጋዊም እንዲሁ የቀረበው ሀሳብ በሁለቱም በኩል ስለት ያለው ቢላዎ ነው ብለዋል። ስለዚህ የቀረበው ሀሳብ እጅግ አደገኛ እንደሆነ የሁለቱም ሊቃውንት አቋም ገልጾታል።

የልዩነቱ መሰረት

ኦሮሞውና አማራው ከተዋቀሩ የወያኔን ኃይል ወደ ዝቅተኛ አቋም ስለሚያዘነብለው ወያኔ ለህይወቱ ሲል ወደ ጦር ሜዳ እንዲጓዝ ያደርገዋል፣ ያም ፍጅትን ያስከትላል የሚል ፍራቻ ይመስላል። ሁለተኛው ፍራቻ ሁለቱ ጎሳዎች በዕርግጥ አንድነት ከፈጠሩ በንዑሷ ትግራይ ላይ ወይም በትግራይ ተወላጅ ላይ የቂም በቀል ተጽዕኖ ይደርሳል የሚል ፍራቻ ጎልቶ ይታያል። የፕ/ር መስፍንና የዶ/ር አረጋዊ መንፈስ ይህን ያዘለ ይመስላል። ምንም አማራውና ኦሮሞው የስነምድር ኩታ-ገጠምነት ባይኖራቸውም፣ በስማቸው የውጩ ድርጅቶች የሚያካሂደውን እንጂ፣ አንድነቱ በህገር ውስጥ ቢፈጸም (ለመፈጸም ስትራተጂካሊ አይቻልም እንጂ) ማንም ሰው የሚቋወመው አይመስልም። ወ/ሮ ርዕዮት አለሙ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳለችው፣ የአማራው ሕዝብ ለመደራጀት ካልፈለገ  በዲያስፖራው እንዲደራጅ ለምን ይገደዳል ብላለች። ሁኔታው እንደዚያ መሆኑ ማስረጃ የለም። እንደዚያ ከሆነ ሕዝብ “አታደራጁን፣ የኛ ፈቃድ አይደለም”ብሎ ለመግለጽ ስለሚችል በዚያ ይቆም ነበር። በሁለቱም በኩል ዕውነተኛ ፍራቻ አለ። ዕውነተኛ ችግር ስላለ ዕውነተኛ መፍትሔን ፍራቻ ማገድ የለበትም። የወያኔ መወገድ የኢትዮጵያ ሰላምና ዲሞክራሲ ማስፈን ነው። የማይቀር ጉዳይ ነው። የሕዝቦች አንድነት ዕልቂት ያስከትላል የሚለው ፍራቻ መፍትሔ አለው። ፍራቻው ግን ሌላውን ማገድ ፈጽሞ አይችልም።

ወያኔ በተመሳሳይ ፍራቻ ለ 26 ዓመቶች ስለኖረ፣ ይበቃዋል ይላሉ። በተጨማሪ የውጭ ሀገር መንግሥታት “መቸ ተዘጋጃችሁ? ለኛ ድጋፍ ብቁ ሆናችሁ አልቀረባችሁም። ተዘጋጁና ጠይቁን” ብለዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ዕጣ በውጩ ምረቃ መኖሩ ሲያዛን፣ ግን ወያኔም ያለው በዚሁ ስነስርዓት መሆኑን ግልጽ ነው። በነሱ አወንታ ሥልጣን መቀባበሉ የሚያሳዝን ሲሆን፣ የዓለምን እውቅ ሁኔታ ያሳያል። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ለተበደለው አማራው ድርጅት ይኑረው አይኑረው ወሰኙና ሚና ተጨዋቹ ሌላው በመሆኑ ነው። ቅዋሜው ይቅረብ እንጂ ነገሩ የህልውና ጥያቄ ላይ ሲደርስ፣ ወሳኙ ሕዝቡ ይሆናል። ያንጊዜ ውሳኔውን መቃወም ከማይቻልበት ደረጃ ይደርሳል።

ለአዘጋጆቹ

የተጠበቀው የጉባዔው ውጤት በገንዘብ የሚተመን ከሆነ፣ በዕርግጥ ከስሯል። በታሪካዊ ስራ ላይ ያተኮረ ከሆነ ግቡን መቷል። የሚያኮራ ስራ ነው። የተጓደለ አሰራር ካለ አዘጋጆቹ እንጂ የውጩ ጎልቶ ሊያየው የሚችል አልነበረም። ብዙ ሰው ማካተት ከግዜ አንጻር አስፈላጊ መሆኑን አለመሆኑን አሁንም አዘጋጆቹ መገምገም ይገባቸዋል። የሚጠበቀውና የተጠበቀው ውጤት ምን እንደሚሆን ምናልባት ለእንግዶቹ ግልጽ ከዚያም በላይ የተሳተፉበት አለመሆኑ ጎልቶ ታይቷል። በዚህ አርዕስት መጥተህ ተናገር ነው የተባልኩ ብለዋል። በመጨረሻ የፈለቀው ሰፊ ልዩነት ተደጋጋሚ ውይይትን እንደሚጠይቅ ያስረዳል። የስያትል ፎረም የወደፊቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ጉባዔ ድርጅት መቋቋም ኃላፊነቱ ለጉባየው አልጣለም። የተነበበውም የጉባየው መቋቋሚያ ቃል የፎረሙ እንጂ በጉባዔው የተነደፈ አይመስልም። የዚህ ጉባዔ ጥርት ሲመዘን፣ ሽነጎ የተባለ ተመሳሳይ ታላቅ ድርጅት ስላለ አንድነት የተባለው በምንና በማን እጅ ያምራል ወደ ሚያሰኘው ጥያቄ ይወስዳል። አንድነት ሲባል መንፈሱን እንጂ ምግባሩን ለመፈጸም የተዋቀረ ድርጅት ስለሌለ የጉባዔው አላማ ይህን ለማድረግ መስሏል።

ሽልማት

ለክቡር ፕ/ር መስፈን ወለደማርያም የተበረከተው ሽልማት እጅግ አስደናቂ ነው። በስያትል የኢትዮጵያኖች ሕዝባዊ ፎረም ዕንቁ ድርጊት ፈጽሟል። ፕ/ር መስፍን ለተመረጡት ወጣቶች ክብርት ወ/ሮ ርዕዮትን ጨምሮ ያስተላለፉት የቃል አደራ ታሪካዊ ነው። ሊላውን ሕግ ግን አልጣሱም። ሶስቱ ወጣቶች ርዕዮት፣ ነጻነትና እሸቱ ሊዘነጉት የማይችሉት ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በፎረሙ ፕረዚዳንት በዶ/ር አሸናፊ ጎሳየ የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ባንዲራ በአፍሪካ ዩኒቲ ህንጻና በተባበሩት መንግሥታት ጽ/ቤት ፊት ለፊት እንደገና እንዲውለበለብ ማድረጉ ከባድ ስራ ነው። ከፕረዚዳንቱ ከዶ/ር አሸናፊ ጀምሮ ሌሎችም ያሳዩት ትብብር በጉባዔው ውጤት ሊታይ ችሏል። ከዚህ የበለጠ መሆን እንደሚገባውና ሊሆን እንደሚችል ግልጽ ነው። ምን ጎደለ ማለቱና የጎደለውን ማወቁ የአዘጋጆቹ ጣጣ ነው።

መግለጫ

በዚህ ጽሑፍ የተገለጹት በተገደፈውና በተጣመመውና በማናቸውም ስህተት ጸሐፊው ኃላፊነቱን ይወስዳል። ሀሳባቸው ተጣሞ በማይፈልጉበት ሁኔታ ቀርቦ ከሆነ ታላቅ ይቅርታ እየጠየቀ አስቦና አቅዶ ያደረገው አለመሆኑን በቅን ልቦና ይገልጻል። የተባለውን አቅሙ በፈቀደለት ለማስቀመጥ ሶሞክር ለበጎ  እንጂ ለትቺት አለመሆኑን ከልቡ ይገልጻል። ያለንበት ሀገር የዲሞክራቲክ መንፈስ የተሞላበት በመሆኑ ወያኔ እንዳይደለው የሚደረጉ ነበሩ። የ2020 ፈጥኖ ደራሽ ባቡሩን ፈጥኖ አድራሽ ያርግለት።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.