ሱዳን ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተባበሩት መንግስታት የሥደተኞች ጉዳይ መ/ቤት (UNHCR) የሚደርስባቸው ግፍ እና መድሎ ( ከአየሁባይኔ ወገኔ )

ሱዳን ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተባበሩት መንግስታት የሥደተኞች ጉዳይ መ/ቤት (UNHCR) የሚደርስባቸው ግፍ እና መድሎ የተሞላበትን የተወላገደ ስራ በሚመለከት የተጻፈ።

የዚህ የብሦትና የምሬት ፁሁፍ መነሻ መጋቢት 3/2017 በሱዳን ካርቱም የ UNHCR ቅርጫፍ መ/ቤት ፕሮቴክሽን ኦፊሠር የሆነው ሚስተር ሮን የተባለ በ2000 ዓ.ም ሥክሪኔንግ አድርገው የነበሩና ሥደተኝነታቸው የተረጋገጠላቸው ሥደተኞችን በመ/ቤቱ ሥብሠባ ጠርቶ ባነጋገረበት ወቅት ኢትዮጵያዊ ሥደተኞችን አስመልክቶ የተናገራቸውን ጉዳዮች መነሻ በማድረግ ነው።

UNHCR ቀደም ሲል ለተመሰረተበት ሰብአዊ አላማ ሲል ራሳቸውን ሊሰው የሚችሉ መድሎን የሚጠየፉ፣ በሙስና የማይታሙ፣ ስራቸውን እና የቆሙለትን የተቀደሰ አላማ ባአግባቡ የሚተገብሩና እራሳቸውን አስከብርው ያንን ግዙፍ እና ስመ ጥር ድርጅት በስራቸው የሚያስከብሩ ነበሩ። አሁን አሁን ግን የምናየው ይህንን ታላቅ አለማቀፋዊ መ/ቤት ሊመጥኑ የማይችሉ ሠብአዊነት የማይሰማቸው፣ የስራ ልምድ የሊላቸው፣ በሙስና የተጨማለቁ ተመርጠው የሚሰሩበት ሆኗል።

ይህ ካርቱም ሱዳን የሚገኘው ቅርጫፍ መ/ቤት ላለፉት 20 ዓመታት በፕሮቴክሽን ክፍሉ ውስጥ የሚመደቡት ኦፊሰሮች አብላጫዎቹ የወያኔ መንግስት የቀጠራቸው የሚመስሉ ለሱም የሚያገለግሉ ሆነው ተገኝተዋል። በተለይ ውሳኔ መስጠት በሚያስችሉ ቦታዎች ላይ የሚመደቡት ወዲያውኑ በኢትዮጵያ መንግስት ተጠልፈው በጥቅም ተደለልው ለኢትዮጵያ መንግስት ፍላጎት ተገዥ እንዲሆኑ ይደረጋሉ ይህ እንግዲህ ላለፉት 20 ዓመታት ሲሰራበት የኖረ አሁንም እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው።

ይህንን ያልነበት ደግሞ ኦፊሰሮቹ አብላጫውን ጊዜ የኢትዮጵያን ህገ መንግስት በመጠቀስ በኢትዮጵያ ሰላምና ዲሞክራሲ መስፈኑን በመስበክ ሥደተኛው ወደ ሃገሩ ቢመለስ ምንም ችግር እንደማይገጥመው አስረግጠው የሚነግሩን የመንግስት ቃል አቀባይ የሚመስሉ ሠራተኞችን ማየት ጉዳይ ለማስፈጸም የሄደ ስደተኛ ያየውና ያረጋገጠው ጉዳይ በመሆኑ ነው። ይህንን የሚሉን በዓለማችን ላይ በህገ መንግስት ሳይሆን በማያፈናፍን አዋጅና አሁን ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የምትገዛ ሐገር መሆኗን እያወቁ ነው።

በተወሰነ ደረጃ ከምርጫ 2005 በኋላ የተለያዩ ሰብአዊ ድርጅቶች ባደረጉት ተጽኖ መ/ቤቱ ትንሽም ቢሆን በሩን የከፈተ በሚስልም እንኳ ውሳኔ በመስጠት ላይ ያተኮረ ሥራ ከመሥራት ይልቅ በቀጠሮ በማመላለስ ተስፋ በማስቆረጥ ሥደተኛው ተማሮ ክትትሉን ሲያቆም ደላላ አስማርተው አንድ ኬዝ ከ3 ሽ ተነስቶ ዛሪ ላይ ዕስከ 10 ሽ ዶላር መሸጥ የተለመደ አሠራር እየሆነ መጥቷል። በዚህም የተነሳ መ/ቤቱ ሠብዓዊ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ ባቋራጭ የሚከበርበት የቢዝነስ ማዕከል ሆኗል።

መ/ቤቱ በመመሪያ ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን አንቀበልም አይልም ነገር ግን ” እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” አይነት የግፍ አስራር እየሠራ ነው። ከላይ እንደተገለፀው የመ/ቤቱ ከፍተኛ የፕሮቴክሽን ሃላፊ ለኢትዮጵያውያን ሥደተኞች ብዙ እድል እንደሊለና ባአብላጫው የሚሠራው ለኤርትራውያን ስደተኞች መሆኑን ያረጋገጠልን ቢሆንም ይህ ሲባል ግን ኢትዮጵያዊ ሆነ ኤርትራዊ ሥደተኛ ጠቀም ያለ ገንዘብ ከከፈሉ ያለምንም ውጣ ውረድ ያለምንም መመላለስ ጉዳያቸው ተፈጽሞ ወደ ሦስተኛ ሃገር እንደሚላኩ እኛ የበደሉ ገፈት ቀማሾች ምስክር ነን። ይህ ብቻ አይደለም እንደ ኦፊሰሩ ገለጻ ለኢትዮጵያውያን ዕድሉ የጠበበው በኢትዮጵያ የተሻለ ሥራዓት ስላለ መሆኑን ጠቅሶ ኦነግ እና ኢሕአፓም ሽብርተኛ ድርጅቶች ተብለው መፈረጃቸውን በመግለጽ ነው።

ለተጠየቀው ጥያቄ ተገቢ መልስ መሥጠት ያልቻለ ሲሆን በተለይ ሥለ ቄስ ተገኝ ጥያቄ ሲቀርብለት የሰጠው መልስ አጠያያቄ ሆኗል ኦፊሰሩ ሲመልስ ሥለዚህ ሠው አትጠይቁ ዕሱ አላርፍ ብሎ ነው ፖለቲካ ውስጥ ምን አገባው? አርፎ አይቀመጥም በቅርቡ ወደ ሦስተኛ ሃገር ልንሰደው እየሰራን ነው ብሎ እንደተናገረ ሳምንት ሳይሞላው ነበር ቄስ ተገኝ ወደ ኢትዮጵያ ተላልፈው የተሰጡት። (ሥለ ቄሱ ወደ ኋላ ላይ እመለሳለሁ)።

አንደ የተረዳነው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊ መሆን በራሱ ወንጀለኝነት እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለው። እርግጥ ነው የኤርትራ መንግስት ማለት ኢሳያስ አፎርቂ ነው። ኢሳያስ አፎርቂ በኤርትራ አድራጊ ፈጣሪ ነው። መግደል የሚፈልገውን በአደባባይ ይገድላል፣ መናገር የሚገባውን በአደባባይ ይናገራል፣ ማሰር ያለበትን ማጎሪያ ውስጥ በማስገባት ዕስረኛው ከማንም ጋር እንዳይገናኝ አድርጎ ያሰቃያል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ሃገሪቱን ሊያጠፉ መሃላ በገቡ በጥቂት የ ህውሃት ጨካኞች እንደምትገዛ እነዚህ አረመኔዎች ደግሞ አይደለም በጓዳ በአደባባይ በሽዎች የሚቆጠሩ ሲገደሉ በየተራ በጅምላ ጭፍጨፋ ሲያደርጉ ምዕራባውያን መንግስትን ጉዳዩ አሳስቦናል ከማለት ውጭ ጠንከር ያለ በኤርትራ ፣ በሱዳንና ዝምባቡየ ላይ ያደረጉትን እርምጃ ሲውስዱ አላየነም።

ዕውነት ለመናገር ወየኔ እየፈጸመ ያለውን የአደባባይ ግድያ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መንግሥታት ፈጽመውት ቢሆን ኖሮ ከማዕቀብ በላይ የጉዞ መከልከል እና የሃብት ዝውውር እገዳ ምናልባትም ጦር እናዝምት እስከ ማለት ያደርሳቸው ነበር። ግን ምን ያደርጋል ህውሃት ሆነባቸውና አንጀታቸው አልቆርጥ ብሎ ዕንደ ህፃን ልጅ በቁጣ ብቻ አልፈውታል። ይህ የሆነበት ምክንያት በአፍሪካ ውስጥ ካሉት መንግስታት ለምዕራባውያን እንደ ወያኔ ያለ አሽከርና በፀረ ሽብር ሥም የሚማገድ ወታደር የሚያቀርብ የሌላ ሃገር መንግስት ስለሌለ ነው።

ዜጎች በአደባባይ ወጥተው መብታቸውን ስለጠየቁ ብቻ በመግደል መልስ ሲሠጥ የምዕራቡ ዓለም መንግስታት ለዜጎቻቸው ተጨንቀው ጥንቃቄ እንዲያደርጉና ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ የሚያስቡ ካሉ የጉዞ ፕሮግራማቸውን እንዲሠርዙ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ይህንኑ ጭፍጨፋ ፈርተው ኢትዮጵያውያኑ ወደ ሃገሮቻቸው ሲሰደዱ አንቀበልም የሚለውን መልስ ሲሠጡ መስማት ምን ያህል እንደሚያም አለመረዳታቸው ነው ክፋቱ። የመራቡ ዓለም በአንድ ጉዳይ ላይ ሁለት አይነት ፍርድ ሲሰጥ ማይት በጣም የሚያሳዝን ነው። ውይም ደግሞ እንሱ እንደሚሉት (double standards) እውነት ለመናገር ምድራዊ ኃይሎች ኢትዮጵያ የሚባል ስምና ኢትዮጵያዊ የሚባል ዜጋ መስማት የሚፈልጉ አይመስሉም። በመዕራቡ ዓለም የሚዘወረው UNHCR የጌቶቹን መመሪያ በማክበር ኢትዮጵያዊ ስደተኞችን ባለመስተናገድ ግፍ በመፈጸም ላይ ይገኛል።

አንድን ስደተኛ ከአስር ዓመት በላይ ያለ ውሳኔ በቀጠሮ እያመላለሱ ማጉላላት ምን የሚሉት የስራ መመሪያ ነው? ከሌሎች ስደተኞች አንፃር ተመሣሣይ ወይም የበለጠ ችግር ገጥሟቸው ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ ጉዳያቸው እልባት እንዳያገኝ ለምን ይደረጋል? የሱዳን መንግስት ስደተኞችን እያፈነ ለወያኔ መንግስት ሲያስረክብ ተቃውሞ አለማሰማቱ ንቀት ወይም ጥላቻን አያሣይም? ለምሳሌ በ2007 ታፍነው ከተወሠዱት ኢትዮጵያውያን መኅል በአዲስ አበባ ማዕከላዊ ዕስር ቤት ሥቃይ ሲቀበሉ አንዱ በህመም ሲሞት አንዱ ደግሞ በወያኔው ፍርደ ቤት የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል። ሁሉም የታፈኑት ችግር እንዳለባቸውና ሊታፈኑ እንደሚችሉ ለUNHCR ሄደው ሪፖርት ቢያደርጉም ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ብቻ ተቀባይነት አጥተው ነው ለዚሁ አደጋ የተጋለጡት። በዚህ ጉዳይ ይህ ቅርንጫፍ መ/ቤት መጠየቅ ይገባው ነበር።

ባለፈው ዓመት ቄስ ተገኝ እና አንድ ሊላ ሥደተኛ ታፍነው ተወሠዱ ለ8 ወር ያህል በአዲስ አበባ በማዕከላዊ ሲሰቃዩ ኖረው እንደተፈቱ ተመልሰው ካርቱም በመግባት ለ UNHCR ሪፓርት አድርገዋል ይሁንና ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ማጉላላቱ ቀጠለ አንዳንዴም ለማነጋገር ፈቃደኛ የማይሆኑበት ሁኔታ ተፈጠረ ወያኔም ከውስጥ ባለው መረጃው አማካኝነት ቄስ ተገኝ የሠጡት ቃለ ሥላሳሰበው አሁንም በፖለቲካ ሥራ ላይ ናቸው የሚል የሃሠት መረጃ አቅርቦ በሱዳን መንግስት እንዲታፈኑ ያደርጋል።

ቤተሠቦቻቸው ሄደው ለ UNHCR ሪፖርት ያደርጋሉ ቤተሰቦቻቸው መረጃ የሚያገኙት በ UNHCR በኩል ብቻ ስለሆነ እየተመላለሱ ሲጠይቁ ከመ/ቤቱ የሚሰጣቸው መልስ ደህና እንደሆኑና በጭራሽ ወደ ኢትዮጵያ እንደማይመለሱ እና ሦስተኛ ሃገር ለመስደድ በሂደት ላይ እንዳሉ ነበር የሚነገራቸው ለ7 ወር ያህል በሱዳን እስርቤት ከቆዩ በኋላ በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ ለወያኔ መንግስት ተላልፈው እንደተሰጡ ተነገራቸው። እንግዲህ ካርቱም የሚገኘው የ UNHCR ቅርንጫፍ መ/ቤት ይህን ያክል ግፍ የሚሰራበት ብቻ ሳይሆን እንደ ወያኔ ባለሥልጣናት ለመዋሸት በአደባባይ የሚቆሙ ሃላፊዎችን የያዘ በዚህም አስነዋሪ እና ሞራል የለሽ ስራው ፈጽሞ የሚኮራ ሆኗል።

ሌላው ይህ መ/ቤት ስደተኛው ወደ ሊቢያ እንዳይሄድ ስደተኛውን በመሰብሰብ ውይይት አድርጓል። አሳዛኙ ነገር የስደቱ ዋና መንሲኤ ግን ይሄው መ/ቤት መሆኑ ነው። እራሱን ሳያጸዳ ሠራተኞችን ያለሙስና እንዳይሰሩ ሳያደርግ ሥብሰባ በመጥራት የውሎ አበል በስደተኛ ስም መገሽለጥ ምንኛ ፀያፍ ተግባር እንደሆነ እያወቁ እንደ አላዋቂ መስለው መስራታቸው ነው የሚያሳዝነው። በዚህ በስደተኛው መ/ቤት አድሎ የተሞላበትና ህገ ወጥ አሠራር የተማረሩ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ስደተኞች ተቃውሞቸውን ሲያቀርቡ ፖሊስ እየጠሩ ማስበርገግ መጀመራቸው ደግሞ የ2017 የመ/ቤቱ የአሰራር ደንብ ሆኗል።

አቶ ብርሃነ የሚባል ካርቱም በሚገኘው መ/ቤት በፕሮቴክሽን ኦፊሰርነት ተመድቦ ከመጣ ሁለት ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል ይህ ሠው ተወልዶ ያደገው ሱዳን ሲሆን ቤተሰቦቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ግለሰቡ በአፍላ የስራ ዘመኑ ለስደተኛው ተስፋ ሆኖ ታይቶ ነበር ዳሩ ምን ያደርጋል በዚሁ መ/ቤት የወያኔ ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኗል። አቶ ብርሃነ ካርቱም በሚገኘው የወያኔ ኢምባሲ መመሪያ በመቀበልና ወያኔም በዚሁ ሰው አማካኝነት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ በሱዳን ቅርንጫፍ መ/ቤት በኩል በህጋዊ መንገድ የትግራይ ተወላጆችን ወደ ሦስተኛ ሃገር እንዲሄዱ ዕያደረገ ነው።

ለዚህም ሥራው ይረዳው ዘንድ በቅርንጫፍ መ/ቤቱ በፕሮቴክሽንና በሪሰትልመንት ክፍል ውስጥ የሚሰሩ ሃላፊዎችን ከወያኔ መንግስት በተለቀቀለት በጀት ክፍያ በመክፈል ዕሱ በሚፈልገው መንግድ ሥራውን እያስኬደው ይገኛል። አቶ ብርሃነ ሰራተኞችን እንዳሳመነና በወያኔ እቅድ መሰረት እንደሚሰራ ለማረጋገጥ ሦስት ነጥቦችን ማንሳት ይቻላል።

1ኛ. ለኢንተርቪ የገቡት የኦነግ ፣ የግንቦት 7 እና የኢህአፓ አባላትን አሸባሪ ድርጅት ናቸው በሚል ተቀባይነት እንዳያገኙ ማድረግ በቅንጅት ወቅት የወጡ የቅንጅት አባላትን ወያኔ ምን ያህል ቂመኛ ድርጅት እንደሆነ እየታወቀ ቅንጅት የሚባል ድርጅት ፈርሷል በሚል ተቀባይነት አግኘተው የነበሩትን ሁሉ ተቀባይነት አጥተው በራሡ ፊርማ የሪጀክት ደብዳቤ በመስጠት ማሰናበቱ።

2ኛ. ሊላው አዲስ እየመጡ ላሉ የትራይ ተወላጆች ኮታውን ለመሙላት ሲባል የቆዩ ፋይሎችን ተራ የሚጠብቁትን እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ። ይህ በፕሮቴክሽን ሆነ በርሰትልመንት ዕየተሰራበት ያለ መሆኑ ጥቂቱ ሲሆን በአደባባይ ግን የተጋለጠው በመጋቤት በተደረገው ስብሰባ ላይ የአቶ ብርሃነ አለቃ የሆነ ሰው አቶ ሮን ሣያፍርና ሳይፈራ የወያኔ ምክር ቤት አሸባሪ ያላቸውን ድርጅቶች በስም ጠርቶ አሸባሪ ተብለው መፈረጃቸውን መጥቀሱ

3ኛ. እነዚህ ድርጅቶች የአሜሪካና የከናዳ መንግስትም በአሸባሪነት ፈርጀዋቸዋል በማለት አፉን ሞልቶ እንዲናገር ማድረጉ የአቶ ብርሃነ ጽያፍ ድርጊት ያገሩን ልጆች ደላላ አስማርቶ ከፍተኛ ገንዘብም በመቀበል ሙስና ውስጥ መግባቱ ብቻ ሳይሆን በነዚሁ ደላሎች ጀሮ ጠቢዎች አማካኝነት ሥለርሱ ምን እንደሚባል ወሬ በመቃረም ክፉ ያወሩትን ስም ዕየለቀመና በሞባይል ፎቶ እያስነሳ ችግር የሚፈጥር ሆኖል። ኢትዮጵያ ባሉ ኤርትራያን ሥደተኞች ስም በየአቅጣጫው የትግራይ ተወላጆች እንደሚላኩ ሁሉ እዚህም በዚሁ ግለሰብ አማካኝነት የወያኔ ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች የኤርትራዊ መታወቂያ እንዲያወጡ በማድረግና ያልቻሉት ፎርጅድ በማሰራት ኤርትራዊ ተብለው እንዲቀርቡ አድርጎ ወደ ሶስተኛ ሃገር እንዲሄዱ እያደረገ ይገኛል። በመሆኑም የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በሰለጠነው ዓለም ያላችሁ ወገኖች ማድረግ ያለባችሁን ለወገኖቻችሁ እንድታደርጉ ለመጠየቅም ነው። ይህን ጹሁፍ ለማቅረብ የተገደድኩት በውጭ የሚገኙ ኤርትራውያን ሥለወገኖቻቸው በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ለመንግስታትና ለ NGO ደብዳሜ በመፃፍ አቤት ይሉላቸዋል። የሚያሳዝነው ብዙ ተደማጭነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንደአሉ እየታወቀ ሱዳን ሥለሚገኘው ስደተኛ ምንም ድምጽ አለማሰማታቸው ነው።

ድርጅቶች ስለ ሃገር የምትሰሩት የፖለቲካ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ እሲኪ ሰብአዊ ጉዳዮችንም አብራችሁ ለማየት ሞክሩ። ለዚህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ እንደ ድርጅትና እንዲሁም የዚሁ ድርጅት መሪ የተከበሩ አቶ ኦባንግ ሜቶ በዓለም ዙሪያ በሚባለ መልኩ በስደተኛው ዙሪያ ከፍተኛ ትግል አድርግዋል ተቀሳቅሰዋል። አሁንም ሱዳን ስለምንገኘው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እንዲንቀሳቀሱልንና የተቻለወትን ያደርጉ ዘንድ ስጠይቅ ከታላቅ አክብሮት ጋር ነው። እንዲሁም ሌሎች ድርጅቶች ድምጻችሁን አሰሙሉን።

ከግለሰቦችም የተከበሩ ፕሮፊሰር አለማየሁ ገ/ማርያም የተከበሩ ዶክተር አክሎግ ቢራራም በስደተኛው ዙሪያ በመጻፍም ሆነ በማንኛውም መንገድ ስራ ብትሰሩልን በማለት በአክብሮት እጠይቃለሁ። የአቶ ኦባንግ ሚቶን ድርጅትና ዕነዚህን የተከበሩ ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሙሁራኖች ምርጫ ውስጥ ያስገባሁት ያለመሰልቸት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚጽፉ በመሆናቸው ብቻ ነው።

ይህንን ስል አቅሙ ያለው ሁሉ በሱዳን ስለሚገኘው ስደተኛ በምትችሉት መንገድ ሁሉ ለሚመለከታቸው ሁሉ አቤት ትልሉን ዘንድ የምር የሆነ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንደምታደርጉልን በመተማመን ነው።

ከአየሁባይኔ ወገኔ

ሱዳን ካርቱም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.