“ከልደት ወደ ታሪክ” በደስታ ስሜት ውስጥ የተፃፈ (ያሬድ ሹመቴ)

በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ስም የተሰየመው የደብረብርሀን ዩኒቨርሲቲ “ዳግማዊ ምኒልክ” ካምፓስ የመሰረት ድንጋይ በዛሬው እለት ከደብረ ብርሀን 7 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የእምዬ ምኒልክ የትውልድ መንደር አንጎለላ ላይ ተጥሏል።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ላለፉት 2 አስርት አመታት በስማቸው ምንም አይነት መታሰቢያ ሳይሰራላቸው ወይ ሳይሰየምላቸው የቆየ ከመሆኑ አንፃር ይህ የዛሬው ጅምር እንቅስቃሴ በታሪካችን ውስጥ ጉልህ ቦታ እንዳለው ይሰማኛል። በዚህም በእጅጉ ተደስቻለሁ። ሁላችንንም ኢትዮጵያዊያን በተለይም የጉዞ ዓድዋ አባላትና ደጋፊዎችን እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለኢትዮጵያ የለፉ ኢትዮጵያንም የሰሩ ሰው ናቸውና ስማቸው በየትኛውም ቦታ ከፍ ብሎ ሲጠራ ደስታ ይሰማኛል። ለልደታቸው መታሰቢያ ይሆን ዘንድ በስማቸው በትውልድ መንደራቸው የሚሰራውን ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ግናባታ ፍፃሜ በጉጉት እየጠበቅን ምዕራፍ አንድ በድል እንደተጠናቀቀ ይሰማኛል።

ነገር ግን ከፍተኛ ታሪክ በሰሩበት በዓድዋ ተራሮች ዙሪያ እሳቸውን የሚዘክር ሐውልት ይሁን ሌላ መዘክር ቆሞ እስካላየው ድረስ አፄ ምኒልክ ከዘመኑ የቀበሌኛ አስተሳሰብ አርቀን በኢትዮጵያ ግዝፈት ልክ ማየት ጀምረናል ብዬ ማሰብ አልችልም።

የዩኒቨርሲቲውን ዳግማዊ ምኒልክ ካምፓስ ግናባታ ለወጠናችሁ ስራውንም ከመሰረት መጣል ላደረሳችሁ ያለኝን አክብሮት እየገለጽኩ፣ ከዚህ በተጨማሪ ዳግማዊ አፄ ምንሊክ እና ሌሎችም የሀገራችን ታሪክ ሰሪ ቀደምት መሪዎች ከቀበሌኛ ከፍ ያለ ታላቂቱን ኢትዮጵያን ሊያሳይ የሚችል ውጤት እንዲመጣ ለሰሩት ውለታ ስለ ኢትዮጵያ የከፈሉትን ዋጋ ታሪክ በሰሩባቸው ቦታዎች በሙሉ መዘከር ይጀምር ዘንድ እንድንተጋ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ።

በዓድዋ ተራሮች ማህፀን ከመቶ ሀያ አመታት በኋላ የተሰባሰቡት የዘንድሮ መሪዎቻችን የፓን አፍሪካን ዩኒቨርሲቲ መሰረት ድንጋይ ሲያቆሙ በነበረበት ስነ ስርዓት ላይ የእኒህን ታላቅ ጀግና ስም አንዴም እንኳን ሳይጠሩን ማለፋቸው ትዝብት ላይ ይጥላል።

እባካችሁ ከልደት ወደ ታሪክ እንሸጋገር
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም!!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.