አጪጭር የኢሳት ዜናዎች… የአቶ አለምነው መኮንን የግል አጃቢ ተገደለ, በኦህዴድ ውስጥ የእርስ በርስ መጠላለፍ, የባህር ዳር ስፓርት ደጋፊዎች ተቃውሞ አሰሙ

ኢሳት ዜና :- የክልሉ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ስራውን በፈቃዱ ለቋል

በአማራ ክልል ህዝብ ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠሉትና የህወሃት ቀኝ እጅ ተድርገው የሚቆጠሩት የአቶ ዓለምነው መኮንን የግል አጃቢ የሆነው አንዋር ሙሃመድ የተባለው ግለሰብ፣ ባህርዳርቀበሌ 04 በሚገኘው ግሪንላንድ ሆቴል ውስጥ በጥይት ተመትቶ ተገድሎ ከተገኘ በሁዋላ፣ የብአዴን ካድሬዎችና የአቶ ዓለምነው የቅርብ ወዳጆች ሽብር ውስጥ መግባታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።በመሆኑም ካድሬዎቹን ለማረጋጋት ሲባል የዞኑ የፖሊስ አዛዥ የሆነው ኮማንደር ዋኘው ግለሰቡ ራሱን እንዳጠፋ ተደርጎ እንዲነገር ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ለውስጥ አርበኞች አልተባበርም በማለቱ ከትናንት በስቲያ ሰኞ ምሽት ላይ እንደተገደለ የገለጹት ምንጮች፣ በእለቱ ምሽት ላይ አቶ አለምነው መኮንን በባህርዳር እንደነበርና የግድያው ኢላማም እሱ እንደነበር ገልጸዋል። አቶ አንዋር፣ የአቶ አለምነው አካባቢ ተወላጅ ሲሆን፣ አቶ አለምነውን አሳልፌ አልሰጥም በማለቱ እርምጃ እንደተወሰደበት እነዚሁ ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።
ግድያው የተፈጸመው የብአዴን ባለስልጣናት በሚዝናኑበት ግሪንላንድ ሆቴል ነው። ከዚህ ቀደምም በዚሁ ሆቴል ግቢ ውስጥ ቦንብ መፈንዳቱ ይታወሳል።
ግድያውን ተከትሎ ትናንት በክልሉ የሚገኙ ደህንነቶች የተሰበሰቡ ሲሆን፣ የክልሉ የወንጀል መከላከል ኃላፊ ኮማንደር አሰፋ ስንታየሁ “ በዚህ ሁኔታ መሥራት አልችልም” በማለት ስራውን በፈቃደኝነት ለቋል። የኮማንደሩ ከኃላፊነቱ መልቀቅ ተጨማሪ ስጋት ማሳደሩን ምንጮች ገልጸዋል።
ትናንት በነበረው ግምገማ ላይ የክልሉ የጸጥታ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባለሸ መሄዱ፣ በክልሉ ያለውን የትጥቅ ትግል መቆጣጠር አለመቻሉ፣ ለመረጃ ከፍተኛ ገንዘብ እየወጣ መረጃ መጥፋቱ ተነግሯል።
እንዲሁም ነገ በፖሊስ ኮሚሽን ላይ ጥቃት እንደማይፈጸም እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ከመድረኩ የተገለጸ ሲሆን፣ ግምገማው ወደ እርሱ ማነጣጠሩን የተረዳው ኮማንደር አሰፋ “ ዛሬ ላይ ማን ለማን እንደሚሰራ አይታወቅም” የሚልና ሌሎችንም ጠንካራ የተባሉ ትችቶችን በመሰንዘር ፣ በገዛ ፈቃዱ ስልጣኑን መልቀቁንና በስራው የመቀጠል ፍላጎት እንደሌለው ተናግሯል።
እንደውስጥ ምንጮች ገለጻ የብአዴን ባለስልጣናት ከህወሃት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ዙሪያ ከሁለት ተከፍለዋል።
አብዛኞቹ የክልሉ ፖሊሶችና ወታደሮች ብአዴን ራሱን ከህወሃት ተጽእኖ አላቅቆ የክልሉን ህዝብ መብትናማንነት እንዲያስከብር ይፈልጋሉ።እንዲሁም የደህንነትና የጸጥታ አባላቱ በክልሉ ከተሰማራው ኮማንድ ፖስት ጋር ያላቸው ግንኙነት በጣም የተደካመ ነው። ይህ ጉዳይ በፌደራል ደረጃ የተቀመጡ የህወሃት ባለስልጣናትን እያሣሰበ መምጣቱን ተከትሎ፣ በቅርቡ ሹም ሽር እንዲካሄድ ቢደረግም ነገሮች እየባሱ እንጂ እየተሻሻሉ አልመጡም።

በኦህዴድ ውስጥ የእርስ በርስ መጠላለፍና መወነጃጀል ተፈጥሯል

ኢሳት ዜና :-በኦህዴድ ውሰጥ ያሉ ታማኝ የህወሓት አገልጋዮቸ አንፃራዊ በሆነ መንገድ የራስ መተማመንንበማዳበር ላይ ያሉትን የኦህዴድ አመራር አባላትን ማደን ጀምረዋል።
የህወኃት ተላላኪዎቹ-ጓደኞቻቸውን ኦህዴድ ውስጥ ሆነው ህገመንግሥቱን በኃይል ለማፍረስ ተንቀሳቅሰዋል ሲሉ ከሰዋቸዋል። ባለፉት 2 ቀናት የምስራቅ ሸዋና የአርሲ 3 የዞን አመራሮች የታሰሩ ሲሆን፤ አምስት ሹመኞች ደግሞ ከአገር ወጥተዋል።
ውጥረቱን ተከትሎ በበርካታ በኦሮሚያ የሚገኙ የዞን አመራሮች መኖሪያ ቤት በደህንነቶች ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጓል።
ከመሣሪያ ግምጃ ቤት 78 ክላሽ መሳሪያ መጥፋቱ እየተነገረ ነው። በዚህም ምከንያት ኦህዴድ ውስጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ውጥረት መስፈኑ ታውቋል።

 

የደደቢት ተጨዋቾች በክፍያ ምክንያት ከክለቡ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። የባህር ዳር ስፓርት ደጋፊዎች ተቃውሞ አሰሙ።

ኢሳት ዜና :-ከቅርብ አመታት ወዲህ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ዋነኛ ተፎካካሪ እየሆነ የመጣውና ለየሊጉን ዋንጫ እስከማንሳት የደረሰው የትግራዩ ደደቢት እግር ኳስ ክለብበዘንድሮ አመት የውድድር ዘመን ለተጨዋቾቹ ደሞዝ ባለመክፈሉ በክለቡ ውስጥ ውዝግብ ተፈጥሯል።
ክለቡ የአምስት ወር ደሞዝ አልከፈለንም በማለት የቡድኑ ወሳኝ ተጨዋቾች የሆኑት አይናለም ኃይሌ ፣ አስራት መገርሳ ፣ ሳምሶን ጥላሁን ፣ አክሊሉ አየነው እና ዳዊትፍቃዱ ልምምድ ካቋረጡ 15 ቀናትን አስቆጥረዋል፡፡
በርካታ ተጫዋቾች ደመወዛቸውን ባላገኙበት ሁኔታ ለተወሰኑ ተጫዋቾች በተለዬ መልኩ ለብቻቸው ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ውዝግቡን ይበልጥ አባብሶታል።
ደመወዛቸውን በመነፈጋቸው ልምምድ ያቋረጡት ተጫዋቾች በተደጋጋሚ በስልክም ሆነ በአካል ቢሮ ድረስ በመሄድ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ ሊያገኙ ባለመቻላቸው በቀጥታ ለክለቡ ያቀረቡትን ቅሬታቸውን በግልባጭ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብተዋል። ይሁንና ተጫዋቾቹ ላስገቡት የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ከክለቡ የተሰጣቸው ምላሽ ደብዳቤ የክለቡን ተጨዋቾች በማሳደም ለፈፀሙት ተግባር አስፈላጊውን እርምጃእንደሚወስድባቸው የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡
እንደ ሶከር ስፖርት ዘገባ ከአምስቱ ተጫዋቾች መካከል ዘንድሮ ቡድኑን ከተቀላቀለው አስራት መገርሳ በስተቀር አራቱተጨዋቾች በዘንድሮ አመት ከደደቢት ጋር ያላቸውኮንትራት የሚፈፀም ይሆናል።
በተለይ ከሁለት ዓመት በፊት የተጫዋቾችን ክፍያ በከፍተኛ ደረጃ ያናረውና ስመጥር ተጫዋቾችን ከተለያዩ ክለቦች ከፍ ባለ ገንዘብ ሲወስድ የቆዬው ደደቢት አስራ አንድየሚሆኑ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ቢታወቅም፤ በዘንድሮ የውድድር አመት ክፉኛ የገንዘብ እጥረት እንዳጋጠመው በተለያየ ወቅት የክለቡ አመራሮችሲገልጹ ቆይተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በትርናንትናው ዕለት በባህር ዳር ከተማ ሊካሄዱ የነበሩ ሁለት የእግር ኳስ ውድድሮች የመቀሌ ከነማና የሽሬ እንደ ሥላሴ ተጫዋቾች ለደህንነታችን ዋስትና ካልተሰጠን አንጫዎትም ማለታቸውን ተከትሎ ተሰርዘዋል።
ትናንት በባህድር ዳር እንዲካሄዱ ፕሮግራም ተይዞላቸው የነበሩት ጨዋታዎች በአማራ ውሃ ሥራዎችና በመቀሌ ከነማ፣በሽሬ እንደስላሴ- እና በባህርዳር ከነማ መካከል የሚካሄዱ ነበሩ።
የትግራይ ክልል ክለብ ተጫዋቾቹ ለደህንነታቸው ዋስትና እስካልተሰጣቸው ድረስ እንደማይጫዎቱ ቢገልጹም ለዚህ ኃላፊነት የሚወስድ ባለመገኘቱ ነው ጨዋታው የቀረው።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለአማራ ክልል ወጣቶች በላከው ደብዳቤ ጨዋታዎቹ ከባህር ዳር ውጪ በአዲስ አበባ እንዲካሄዱ ከክልሉ መንግስትና አንዳንድ ቢሮዎች የቃል ጥያቄ እንደቀረበለት ሆኖም ጥያቄውን በጽሁፍ እንዳልቀረበለት በመጥቀስ፣ ፌዴሬሽኑ በራሱ ጊዜ የውድድሩን ቦታና ቀን አውጥቶ እንደሚያሳውቅ ገልጿል።
ቡድናቸውን ለመደገፍ መቀሌ ስታዲየም በተገኙ የባህር ዳር ደጋፊዎች ላይ ድብደባ መፈጸሙ ይታወቃል። ይሁንና የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጥፈተኛ በማለት ከባድ ቅጣት የጣለው በባህር ዳር ከነማ ላይ ነው።
በባለፈውም ሆነ ትናንት በተፈጠረው ሁኔታ የተበሳጩ የባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎች “የውሸት ፌዴሬሽን!” በማለት በፌዴሬሽኑ ላይ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።

 

ከ470 ብር ሺህ በላይ አጭበርብራ የታሰረች ግለሰብ በትዕዛዝ ተፈትታ ደህንነት ሥራ ላይ ተመደበች

ኢሳት ዜና :-በአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን በመረጃ ሠራተኝነት ስትሰራ የነበረችው እና “ቦታ አሰጣችኋለሁ” በማለት ከባህር ዳር ነጋዴወችና ከተለያዩ
ግለሰቦች ከ470.00ሺህ ብር በላይ ገንዘብ በመቀበል ክስ ተምስርቶባት ታስራ የነበረች ሴት በትዕዛዝ ተፈትታ አሁንም በደህንነትና ስለላ ሥራ መሰማራቷ ተጠቆመ።
በፈጸመችው የማጭበርበር ወንጀል ተይዛ በሙስና ተከሳ ከ 5 ወር በላይ በእስር ያሳለፈችው የትግራይ ተወላጇ ሰላም በሪሁ፤ በቅርቡ የአማራ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሆኖ በተሾመው በሌለኛው የትግራይ ተወላጅ ፍስሀ ወልደሰንበት ትዕዛዝ ከእስር እንድትፈታ መደረጓን ምንጮች ገልጸዋል።
የመረጃ ሠራተኛዋ ወይዘሮ ሰላም በሪሁ በፈጸመችው ወንጀል ከፖሊስነት ሥራዋ የተሰናበተች ቢሆንም አሁንም በፌዴራል መረጃና ደህንነት ቢሮ ውስጥ መመደቧ ታውቋል።
በቢሮው ውስጥ የወይዘሮ ሰላም ዋነኛ ሥራ ስለከተማው ነጋዴዎችና ወጣቶች ስለላ ማድረግና መረጃ ማቅረብ መሆኑን የጠቆሙት የቢሮው ምንጮች፤ ጉዳይ ለማስፈጸም ወደ ቢሮው የሚመጡም ሆነ የከተማው ነዋሪዎች ከእንዲህ ዓይነቶቹ ሰላዮች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሣስበዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.