የጣና ሐይቅን አደጋ ላይ የጣላው አገዛዙ ነው፤ – ሙሉቀን ተስፋው

አገዛዙ በዐማራ ሕዝብ ላይ የከፈተው ጥቃት ሁሉን አቀፍና ውስብስብ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ በቀጥታ ሕዝብን ከመጨፍጨፍ ጀምሮ እስከ ተፈጥሮ ሀብት ጥፋት የማያደርሰው በደል የለም፡፡ በደርግ ዘመን መልሦ ለምቶ የነበረው የተፈጥሮ ሀብትና የደን ሽፋን ወያኔ በገባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ ተጨፍጭፎ ነው ያለቀው፤ በአንጻሩ የትግራይ ተራሮች አፈር ከሌላ ቦታ እየተወሰደ እንዲለሙ ብዙ ጥረት ተደርጓል፡፡

ክፋትን በማድረግ አቻ የሌለው ይህ አገዛዝ የጣና ሐይቅን ብዛሃ ሕይወትና ውኃ ጥፋት ማድረግ የጀመረው ሰርቀው እንደማይወስዱት በተረዱ ማግስት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በ1993 ዓ.ም የትግራይን ከተሞችና ፋብሪካዎች የኤሌክትሪክ እጥረት ለመፍታት ጢስ ዓባይ ሁለት የኤሌክትሪክ ማመንጫ ኃይልን ሲገነቡ በጣና ላይ የተደገሰውን ጥፋት አንድ ብለው የጀመሩበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ የጢስ ዓባይ ፏፏቴን ውኃ ከ50 በመቶ በላይ ቀንሰው በመውሰድ 73 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ሲያመርቱ የትግራይ የኃይል ፍላጎት በአንድ በኩል ሲፈታ በሌላ በኩል ግን የጢስ ዓባይን የቱሪስት ፍሰት መቀነስ እቅድ ውስጥ ገብቶ ነው፡፡ ይህ ፓወር ፕላንት የውኃ እጥረት ገጥሞት የትግራይ ፋብሪካዎች እንዳይቆሙ ጨረጨራ ላይ ጣናን ገደቡት፡፡ በዚህም የዓባይ የውኃ የፍሰት መጠን ያልተስተካከለ ከመሆኑም ባሻገር ደስ ባላቸው ጊዜ ያለምንም ማስጠንቀቂያ ውኃውን በመልቀቅ በርካታ ንጹሐን ሰዎች በውኃ እንዲወሰዱ ምክንያት ሆኗል፡፡
በ2002 ዓ.ም የጣና በለስ ፓወር ፕላንት የተገነባ ጊዜ በጣና ሐይቅ ላይ የተጋረጠው ሌላኛው አደጋ ሆነ፡፡ የጣና በለስ የኃይል ማመንጫ ከጣና ሐይቅ ከ29000 ሜትር ኩብ በላይ ውኃ በየሰከንዱ ይወስዳል፤ በአንጻሩ ደግሞ ወደ ጣና ሐይቅ የሚገባው የውኃ መጠን ይህን ያክል አይሆንም፡፡ እንዲያውም እንደ ግልገል ዓባይ፣ ጉማራ፣ ርብና እንፍራዝ ያሉ ወንዞች በተፈጥሮ ሀብት መመናመን ምክንያት ዓመታዊ የውኃ ፈሰታቸው በመቀነሱ ምክንያት ቀድሞ ይዘውት የሚመጣው ውኃ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ ወይም የለም ማለት ይቻላል፡፡ የርብና የጉማራ ወንዞች በበጋ ወቅት ወደ ጣና የሚያስገቡት አንድም ሊትር ውኃ ቢባል የተጋነነ አይደለም፡፡
አገዛዙ የጣና በለስ ኃይል ማመንጫን በሚጀምርበት ጊዜ ከጣና የሚወጣው ውኃ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑን ከመታ በኋላ ተመልሦ ወደ ሐይቁ እንደሚገባ ቢገልጽም በኋላ የተረዳነው ነገር ቢኖር ከጣና የሚወጣው አብዛኛው ውኃ ለትግራይና ለውጭ ባለሀብቶች ለሚቸበቸበው መሬት መስኖ እንዲውል የተረፈውም ከበለስ ወንዝ ጋር እንዲፈስ ነው የተደረገው፡፡ በዚህም የጣና ሐይቅ ተፈጥሯዊ መውጫ በር ከአንድ ወደ ሁለት ተቀየረ፤ ተፈጥሯው የዓባይ ወንዝ ቢሆንም በሌላ በኩል እንዲፈስ ሲደረግ ከሐይቁ መድረቅ በተጨማሪ በዓባይ ወንዝ የውኃ መጠን ላይም አሉታዊ ተጽእኖ አሳረፈ፡፡ የጣና በለስ አሁን ዳግማዊ ወልቃይት እየሆነች ነው (ይህን በተመለከተ የዐማራ ባለሙያዎችን ማኅበር ጥናት ያንብቡ http://www.ambapu.org/…/2016-12/Tana%20Beles%20Review__0.pdf)፡፡
ሥርዓቱ የጣና ሐይቅን አደጋ ላይ ለመጣል በዚህ ብቻም የተወሰነ አልሆነም፡፡ የጣና ሐይቅ የቅርብ ተፋሰስ አካባቢ ያሉ ለም መሬቶችን ለውጭ እና ለጥገኛ ባለሀብቶች በመስጠት የአበባ እርሻ ላይ እንዲሠማሩ አደረገ፤ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የተባሉትም ራሳቸው ወደ ንግዱ ሥራ ገቡበት፡፡ ከመራዊ እስከ ሐሙሲት፣ ከጢስ አባይ እስከ ዘጌ ተበትነው ያሉት አበባ አምራች ድርጅቶች በሚጠቀሟቸው ኬሚካሎች ላይ ከዚህ ግባ የሚባል ቁጥጥር አይደረግም፡፡ በዚህም በክረምት ወራት ከአበባ እርሻዎች የሚታጠበው መርዛማ ኬሚካል ወደ ሐይቁ ቀጥታ ይገባል፡፡ ይህም የባሕሩን የብዝሃ ሕይወት በምን መልኩ ሊጎዳው እንደሚችል ለመገመት የግድ ቦታኒስት መሆን አይጠይቅም፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለአገዛዙ ቅርብ የሆኑ ታላላቀቅ ሆቴሎች ቆሻሻቸውን ወደ ሐይቁና ወደ ዓባይ ወንዝ ሲለቁት ምንም ዓይነት ሀፍረት አይታይባቸውም፤ ሕግም አይመለከታቸውም፡፡ ለዚህም እንደማሳያ ልንወስደው የምንችለው የባሕር ዳር የቆዳ ፋብሪካ ወደ ዓባይ ወንዝ የሚለቀውን ግልጽ ኬሚካል መመልከት ይቻላል፡፡ በነገራችን ላይ የባሕር ዳር ሆቴሎች ወደ ሐይቁ የሚለቁትን ቆሻሻ በተመለከተ አንድ የምዕራባውያን ታዋቂ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘጋቢ ፊልም ከጥቂት ጊዜያት በፊት አስተላልፎ ነበር፤ ፊልሙን ከተሳካልን ተርጉመን ልናቀርበው እንችል ይሆናል፡፡
በመጨረሻ አገዛዙ የጣና ሐይቅን ለማድረቅ የዘመተውን ያክል የወባ መራቢያ የሆነውን የኡዶ ባሕር ለማድረቅ አልተጋም ብንል የተጋነነ አይደለም፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.