አፋን ኦሮሞ የሚያድገው አማርኛን እየጠሉ ሳይሆን በፍቅር ነው – ናኦሚን በጋሻው

መግቢያ

ሰሞኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም በሚል አንድ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው አቅርቧል። ይህ አዋጅ እንደ ልዩ ጥቅም ካስቀመጣቸው በርካታ ነጥቦች መካከል አንዱ “በአዲስ አበባ የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ቤት መቋቋም አለበት” የሚል ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በመቀሌ፣ በጎንደርም፣ በአፋን ኦሮሞ መማር የሚፈልጉ ካሉ፣ ቁጥራቸው በርከት ካለና የክልሉም ሆነ የዞኑ መንግስት አቅም ካለው፣ በአፋን ኦሮሞ የመማር ሙሉ መብት ሊኖራቸው ይገባል። ይሄ ልዩ ጥቅም ሳይሆን መሰረታዊ መብት ነው። ይህ መብት ደግሞ ለአፋን ኦሮሞ ተናጋሪዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም መከበር ያለበት መብት ነው። ሁሉም ዜጎች በእኩልነት መታየት አለባቸው። ለአንዱ ተሰጦ ሌላው የሚከለክልበት ምክንያት አይኖርም።

እዚህ ጋር የክልሉ መንግስታት ሆነ የአዲስ አበባ አስተዳደር አንደኛ ቋንቋቸው የተለያዩ የሆኑ፣ የተለያዩ ማህበረሰባት ካሉ ለሁሉም ትምህርት ቤቶችን ቢያዘጋጁ ጥሩና ተገቢ ቢሆንም፣ የአቅም ችግር ሊኖርባቸው እንደሚችል መዘንጋት አያስፈለግም። እንደዚያም ሆኖ ግን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ዜጎች በግል ተነሳሽነት የግል ትምህርት ቤቶች ማቋቋም ከፈለጉ ሊበረታቱና አስፈላጊው መንግስታዊ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል።

እንግዲህ በዴሞክራሲያዊና የሰብአዊ መብት መርህ አንጻር በአፋን ኦሮሞ ትምህርት መሰጠቱ በምንም መስፈርት ችግር ሆኖ ሊታይ እንደማይችል ከተግባባን በዚህ ዙሪያ ብዙ መከራከር የሚኖርብን አይመስለኝም።

  1. የኦሮሞ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው የሚማር አልተገኘም

ሌላው ብዙዎች የምንዘነጋው ነገር ቢኖር በሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቀቀው አዋጅ እንደ ልዩ መብት ከተቀመጡት መካከል አንዱ በአዲስ አበባ፣ በአፋን ኦሮሞ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ጉዳይ፣ እንደ ልዩ ጥቅም ቢቀርብም፣ ከዚህ በፊት በአቶ መለስ ዜናዊ የተፈቀደና ተግባራዊ ሆኖ የነበረ መሆኑን ነው። ከባድመ ጦርነት በኋላ በነ አቶ ግርማ ብሩና አባ ዱላ ገመዳ የሚመራው ኦህዴድ፣ አቶ መለስ ዜናዊን አስፈቅዶ፣ በአዲስ አበባ ሁሉም ወረዳዎች የአፋን ኦሮሞ ት/ቤቶች ለመክፈት ሞክሮ ነበር። የቀድሞ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር የነበረው ኤርሚያ ለገሰ እንዲህ ሲል የነበረውን ሁኔታ በግልጽ ይተነትናል፡

“እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተገንብተው እስኪያልቁ አምስቱም ዞኖች በአጣዳፊነት ነባር ትምህርት ቤቶችን በመለየት ለጐልማሶች የማታ፣ ለህጻናት እና ታዳጊዎች የቅዳሜ እና እሁድ እንዲሁም በክረምት ኢ_መደበኛ ትምህርት እንዲጀመር ጥብቅ ኦህዴዳዊ ትእዛዝ ተላለፈ። በድርጅት ቋንቋ መደብ ወረደ። መደቡን ለማስፈፀም ደግሞ የአዲሳአባ ካቢኔ የነበሩት ሊቀመንበር አሊ አብዶ ፣ ሀይሉ ደቻሳ ፣ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ( የአፈ ጉባኤ ደግፌ ቡላ ባለቤት እና በኋላ ላይ በአዜብ መስፍን ከም/ል ሚኒስትርነት የተባረረች የምንወዳት እህታችን) እና አምባሳደር ሰለሞን ተመደቡ። ተግባሩ በቁልፍ ደረጃ በመቀመጡ ስራውን ያንጠባጠበ ካድሬ በኦህዴድነት መቀጠል እንደማይችል ተገለፀ። በየቀበሌው የሚገኝ ካድሬ ቤት ለቤት እያሰሰ የኦሮሞ ዘር አለው የሚለውን አዲስአበቤ እንዲመዘግብ አደረገ። እንደ መሰረተ ትምህርት ዘመቻ ፍቃደኛ ያልሆነውን ማስገደድ ተጀመረ። በደርግ ጊዜ ዝነኛው ቆምጬ አምባው ” አስኳላ የማይሄድ ቡዳ ነው!” ያለውን በተሞክሮ በመውሰድ የአዲሳአባ ኦህዴድ ካድሬዎች ” አፋን ኦሮሞ የማይማር የነፍጠኛ ተላላኪ ነው!” የሚል ማዕከላዊ መልእክት ቀርፀው በጥቅም ላይ አዋሉ።ስራው በተጀመረ የመጀመሪያው ወር የተመረጡት አምስት ትምህርት ቤቶች በምሽቱ ክፍለ ጊዜ ከጠቅላላው አዲሳአባ በአማካይ 500 ተማሪ ተገኘ። ቅዳሜ እና እሁድ በተዘጋጀው የህጻናት፣ ታዳጊዎች እና ወጣቶች ክፍለጊዜ በአማካይ አንድ ሺህ የሚጠጋ ተገኙ። የኦህዴድ አብዮታዊ ካድሬዎች አጀማመሩ ጥሩ እንደሆነ ገመገሙ። ስራው በተጀመረ ሶስተኛው ወር የምሽቱ 60 ፣ የሰንበቱ ወደ 90 ተማሪ ብቻ ቀረ። አምስቱ ትምህርት ቤት ታጥፈው በዞን ሁለት ውስጥ ወደ ሚገኘው ተግባረ እድ ትምህርት ቤት እንዲጠቃለል ተደረገ። በአራተኛው ወር እንደ ኮንደሚኒየም ወደ 40/60 ተቀየረ። አካሄዱ አስደንጋጭ የሆነበት ኦህዴድ ” ሁሉም ዜሮ ዜሮ” መመዝገቡ በፊት ትምህርቱ ባልተገለፀ መመሪያ እንዲቀር ተወሰነ”

እንግዲህ እዚህ ላይ የምናየው የኦሮሞው ማህበረሰብ ለአፋን ኦሮሞ ክብር ቢኖረዉም፣ በዋናነት ግን ልጆቹ በአማርኛና በእንግሊዘኛ እንዲማሩለት እንደሚፈለግ ነው። ልጆቹን ወደ ኦፋን ኦሮሞ ትምህርት ቤት ለመላክ ፍቃደኛ አልነበረም።

ከሁሉም የሚገርመው ኤርሚያስ እንደ ገለጸው አዲስ አበባ የሚኖር አንድም የኦህዴድ ባለሥልጣን ልጆቹን አፋን ኦሮሞ እንዲማሩለት አልሰደደም። በክረምቱ ክፍለ ጊዜም ሆነ በሰንበት ባለሥልጣናት ልጆቻቸውን የሚልኩት የእንግሊዘኛ እውቀታቸውን የሚያሳድጉበት ከ3ሺህ ብር በላይ የሚከፈልባቸው ውድ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ትምህርት ቤቶች ነበር። ለምሳሌ ግርማ ብሩ ልጆቹን ሳንፈርድ የእንግሊዝ ትምህርት ቤት፣ አባ ዱላ ደግሞ በቅድስ ዩሴፍ የግል ትምህርት ቤት ነው ያስተማሩት። የእነዚህ የኦህዴድ አመራሮች ልጆች አማርኛና እንግሊዘኛ በደንብ የሚጽፉና የሚናገሩ ናችው። ይሄ ቁቤ የሚባለው ላቲን እንኳን ሊጽፉ አፋን ኦሮሞን መናገራቸዉንም እግዜር ይወቀው።

እንግዲህ አስቡት፣ በኦሮሞ ስም እየነገዱ ያሉ የኦህዴድ ሆነ ሌሎች ለኦሮሞ ቆመናል የሚሉ ግለሰቦች የሚሰብኩትንና የሚለፍፉትን በራሳቸው ሕይወት፣ በልጆቻቸው ተግባራዊ ሳያደርጉ ነው በሌላው ድሃ የኦሮሞ ልጅ እየቀለዱ ያሉት። አማርኛን እና እንግሊዘኛን የማወቅ ጥቅሙን ያውቃሉ። ለዚህም ነው ልጆቻቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ ያሉት። ሆኖም ግን የስንቱን ድሃ ሕይወት ግን አጨለሙ።

  1. የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥያቄ

በአሁኑ ጊዜ የኦሮሞ ማህበረሰብ ጥያቄ የስራ፣ የመብት፣ የፍትህ ጥያቄ ነው። የኦሮሞ ወጣት የሚያስፈልገው አማርኛን ማወቅና መማር ነው። በፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮች፣ በአማራው፣ በደቡብና በቤኔሻንጉል ክልሎች ፣ በተለያያዩ የግል መስሪያ ቤቶች የመቀጠር እድላቸው እንዲሰፋ፣ በኦሮሚያ ልማት እንዲስፋፋ ነው የሚፈልጉት። በርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ወድቀዋል። ያ እንዲለወጥ ይፈልጋሉ።

ሕወሃቶች ቆመንለታል የሚሉትን የትግራይ ሕዝብ በሁሉም መስክ ቀዳሚ እንዲሆን፣ የትግራይም ክልል ከሁሉ ቀድማ እንድታድግ እያደረጉ ነው። የትግራይ ልጆች ከአራተኛ ክፍል ጀመሮ አማርኛ ማንበብና መጻፍ ይችላሉ። (ከትግሪኛ በተጨማሪ)። ከዚህም የተነሳ በፌዴራል መንግስት ይሁን አማርኛ የሥራ ቋንቋ በሆነባቸው አብዛኛው ክልሎች የመስራት እድላቸው የሰፋ ነው። ሆኖም ግን ለኦሮሞው ቆመናል የሚሉት የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄ ላይ አይደለም ትኩረታቸው። የሕዝቡን ኑሮ የሚያሻሽለው ላይ ከማተኮር፣ ጠባብ ሆነው፣ ኦሮሞው ከአማራው፣ ከጉራጌው፣ ከሶማሌው፣ ከጉሙዙ ..ጋር እንዲቃቃር እያደረጉት ነው። ሌላውን ማህበረሰብ የሚያስቀየሙ፣ ኦሮሞው በሌሎች እንዲፈራና እንደ ጠላት እንዲታይ የሚያደረጉ ጊጂና የኋላ ቀር ፖለቲካን ነው የሚያራመዱት። ሕወሃቶች የመኪና መገጣጠሚያ በትግራይ ሲገነቡ፣ ኦህዴዶችና የኦሮሞ ፖለቲከኞች የጥላቻ ሃዉልት ነው የሚገነቡት።

  1. አፋን ኦሮሞ እንዲያድግና እንዲስፋፋ የሚያስፈለገው

አሁን የአፋን ኦሮሞ ትምህርት ቤት ቢቋቋም የሚለውጠው ነገር አይኖርም። ከዚህ በፊት ተሞክሮ ከሽፏል። አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ ቢሆን አብዛኛው የመንግስት ሰራተኛ አፋን ኦሮሞ የማይናገር በመሆኑ አብዛኛው ሰው መናገር እስኪጀመር ድረስ የሚለወጥ ነገር አይኖርም። ሌላው አፋን ኦሮሞ እንዲያውቅና እንዲማር ከተፈለገ ደግሞ፣ አፋን ኦሮሞ ከኦሮሞው አልፎ በሌላው ማህበረሰ ተቀባይነቱ ፣ ተወዳጅነቱ መጨመር አለበት። ለዚህም የኦሮሞ አክቲቪስቶች ከሕወሃት ጋር ታንጎ እየደነሱ በሃይልና በግርግር በግዳጅ ሕዝቡ ላይ ለመጫን መሞከር ሳይሆን ሌላውን ማሳመንና ማግባባት ይጠበቅባቸዋል። በፍቅር ነው ሁሉም ነገር ሊሆን የሚችለው።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅን ተከትሎ አንዳንድ በፓርላማ የኦህዴድ ተወካዮች፣ በአዲስ አበባ በሁሉም ትምህርት ቤቶች በግዳጅ አፋን ኦሮሞ ትምህርት መሰጠት አለበት የሚልም አስቂኝ አስተያየት አቅርበዋል። እነዚህ ሰዎች ያልተረዱት ነገር ቢኖር አንደኛ ሕዝብን በማስገደድ የሚሆን ነገር አይኖርም። ሁለተኛ አዲስ አበባ ራሷን በራሷ የማስተዳደር መብቷ በህግ የተረጋገጠላት መሆኑ ነው።
ለዚህም ነው የፓርላማ የኦህዴድ አባላት፣ በዘረኝነት ሰክረው እንዲህ አይነት አስተያየት ከመስጠታቸው በፊት ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ቢገመግሙ ጥሩ ይሆን ነበር የምለው።

ይሄን ስል በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች በአፋን ኦሮሞ ትምህርት መሰጠቱትን በመቃወም አይደለም። ከአማርኛና ከእንግሊዘኛ ቀጥሎ ዜጎች መርጠው ሌላ ሶስተኛ ቋንቋ ቢማሩ ጠቃሚ ነው። ሶስተኛው ቋንቋ አፋን ኦሮሞ ቢሆን ችግር አይኖረዉም። ግን ጥቅሙን በማስረዳት፣ በአዲስ አበባ አስተዳደር በማስወሰን እንጂ በአዋጅ፣ ከሕዝብ ፍቃድ ውጭ በማድረግ አይደለም። ህዝብን ለማሳመን ደግሞ አሳማኝ ነጥቦች መቀመጥ አለባቸው፡

በዋናነት አፋን ኦሮሞ የሚጻፍበት ፊደል እንደገና መጠናት አለበት። ማንም ላቲኑን በፍቃደኝነት የሚማር አይኖርም። በላቲን የተጻፈ የመማሪያ መጽሀፍ የእሳት ማገዶ ነው የሚሆነው። ላቲኑ ሮምን እንጅ ኦሮሞን አይወክልም። እነ ሃይሌ ፊዳ ናቸው ከአዉሮፓ ያመጡት። መጤ ፊደል ነው። በመሆኑም አፋን ኦሮሞ በሳባ ፊደል እንዲጻፍ ማድረግ ቢቻል አንደኛ በቀላሉ አፋን ኦሮሞ የበለጠ ተቀባይነቱና ተወዳጅነቱን ይጨምራል፤ ሁለተኛ  አማርኛ ተናጋሪዎችም በቀላሉ ሊማሩት ይችላሉ።

“አይ ፊደሉ የኦሮሞዎች ጉዳይ ነው፣ እኛ ኦሮሞዎች ብቻ ነው የምንወስነው” የሚል ፉሊሽና ጠባብ አስተያየት ከተሰጠ ደግሞ “ ታዲያ እዚያው ነጆና ዶዶላ እናንተው ለምን አትማሩት ? ለምን ወደኛ ወደ አዲስ አበባ ታመጡታላችሁ? “  የሚለው ጥያቄያችን ይሆናል። በርግጠኝነት የምነግራቸው ላቲኑ ፊደል የአፋን ኦሮሞ ጠላት ነው የሚሆነው።

ሌላው የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይሄ ፊንፊኔ፣ ሸዋ፣ ያ መሬት፣ ይሄ መሬት የኦሮሞ ነው የሚሉትን አጉል ፈሊጥ ማቆም አለባቸው። ኦሮሞዎች የሚኖሩባቸው አብዛኛው ቦታዎች በወረራ የተያዙ ናቸው። ኦሮሞዎች ራሳቸው ወራሪዎችና መጤዎች ሆነው ሌላው መጤ የማለት መብት የላቸውም። ከዚህ አጉል ቅዠታቸው ቢነቁና ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳት ለኦሮሞ የሚጠቅም አቅጣጫ ቢይዙ ጥሩ ነው። ያኔ ከሌላው ጋር የሚያስተሳስራቸው ገመድ ያጠብቃሉ። ያኔ የኦሮሞ ጥያቄ የሌላው የሌላውም ጥያቄ የኦሮሞ ጥያቄ ይሆናል። ያኔ አፋን ኦሮሞ የኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ቋንቋ ይሆናል። ያኔ ከፍቅርና ከአንድነት የተነሳ የተለያዩ ባህሎቻችን፣ ቅርሶቻችን፣ ቋንቋዎቻችን የሁሉም ሃብቶች ይሆናሉ።

(ከዚህ በታች ያለው፣ የነቀምቴን፣ የአሰላን የመቀሌን ከተሞች የሚያሳይ ምስል ነው። መቀሌ የትግራይ ክፍል ሃገር ነበረች። ነቀምቴ የሃብታሟ የወለጋ ክፍለ ሃገር፣ አሰላ ደግሞ የአርሲ ክፍለ ሃገር ዋና ከተሞች ነበሩ። ከ25 አመታት የሕወሃት/ኦሃዴድ ዘመን በኋላ ከተሞቹ ይሄን ይመስላሉ። ያለፉትን ቁርሾ በማንሳት ፣ አላስፈላጊ፣ ጥቃቅን፣ የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚጎዱ አጀንዳዎችን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ከሕወሃት ጋር እያራገቡ፣ የዘር ፖለቲካን እያራመዱ፣ በሌላ በኩል ግን የኦሮሞ ከተሞች በዚህ መልክ የወዳደቁ ሆነዋል። የኦሮሞ አካራሪዎች ኦሮሞ በብዛት የሚኖርባቸውን  ከተሞች ለማሳደግ ከመስራት፣ ሌሎች ማህበረሰቦች በብዛት የሚኖሩባቸውን እንደ አዳማ፣ አዲስ አበባ፣ ቢሾፍቱ ያሉትን ኦሮሞያዝድ ለማድረግ ነው እየደከሙ ያሉት።ከንቱ ድካም።)

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.