የአዲስ አበባ ባለቤት የአዲስ አበባ ህዝብ ነው! – አበጋዝ ወንድሙ

በቅርቡ በህወሓት የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት አዲስ አበባን አስመልክቶ ያወጣው ረቂቅ አዋጅ አነጋጋሪ ሆኗል ። ሀገር ቤት፣ የተወሰኑ ሰዎች ባለው ውሱን ሚዲያ አንዳንድ ሃሳቦችን አየሰነዘሩ ይገኛሉ። ለወትሮው ገዥው ቡድን የሚያቀርብለትን ማናቸውም ረቂቅ አዋጅ፣ ይሄ ነው የሚባል ውይይትም ሆን ክርክር ሳያካሂድ፣ ማጽደቅ ልማዱ የነበረው ፓርላማም ለእረፍት ልንወጣ ሳምንት ሲቀር እንዲህ ያለ ትልቅ አዋጅ በቶሎቶሎ የሚጽድቅ ስላይደለ ፓርላማው ሰፋ ያለ ጊዜ ሰጥቶ መወያየት ይኖርበታል ብሎ ሲያጉረመርም ፣ አፈጉባኤው አባዱላም የግድ በጥድፊያ መሆን የለበትም በሚል ለጊዜው ተላልፏል። ለጊዜው የተወሰደ እርምጃ ቢሆንም ጊዜ ፈጅቶ መወያያት ያሻል መባሉ በራሱ ጥሩ እርምጃ ነው።

 

ይሄም ሆኖ፣ህወሓት መራሹ መንግስት አዋጁ የተመሰረተበት ታሪካዊ ሃቅ አውነት ይሁን አይሁን፣ ሕጋዊ  ይሁን አይሁን፣ ፍትሃዊ ይሁን አይሁን ፣ሕዝብ ይደግፈው አይደግፈው፣ ህዝብ ለህዝብ ያጋጭ አያጋጭ፣የአዋጁ ተግባራዊ መሆን በሀገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለው የወደፊት ችግር አስከፊ ሆነ አልሆነ፣ ለስልጣኑ መቆየት አስቀጠቀመው ድረስ ተግባራዊ ሊያደርገው አንደሚችል ምንም አይነት ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም ።

 

ይሄ አንደተጠበቀ ሆኖ ግን፣ በሀገር ቤት የሚገኙትም ሆነ በውጭ ያለን ሰዎች ጉዳዩን አስመልክቶ ከስሜታዊነትና ከታሪካዊ ጥራዝ ነጠቅነት ነጻ በሆነ መንገድ፣የአንድ ብሄር ልዩ ጥቅም በሚል ሳይሆን፣ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥቅም፣ ከኢትዮጵያ የረጅምና አጭር ጊዜ ታሪክ፣ የወደፊትም ሃገራዊ ጥቅም አንጻር በመነሳት የሰከነ ውይይት በማካሄድ፣ ለመፍትሄ የሚሆን ሃሳብ ልናመነጭ አንችላለን የሚል አምነት አለኝ ።

 

ከዚህ መንፈስ በመነሳት አቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ ‘ፊንፊኔ -የኦሮሚያ ክልልና የፌደራል ዋና ከተማ፣ያስከተለው ችግርና መፍትሄው።(ለውይይት መነሻ ) በሚል ዘሃበሻ በተባለው ድረ-ገጽ በጁላይ 9 ያቀረቡትን መጣጥፍ መሰረት በማድረግ አንዳንድ አስተያየቶችን ለማቅረብ አፈልጋለሁ። በቅድሚያም አቶ ባይሳ በጽሁፋቸው የጎላ የታሪክ ስህተት ቢያደርጉምና ለውይይት መነሻ በሚል ያቀረቡት ፅሁፍ ላይ የማልስማማባችው ነገሮች ቢኖሩም፣ አጠቃላይ የፅሁፋቸው ይዘት መፍትሄ በማቅረብ ላይ ያተኮረ በመሆኑና፣ ለሰከነ ውይይት ቀስቃሽ በመሆኑ ላመሰግናቸው እወዳለሁ።

 

አቶ ባይሳ አዲስ አበባን አስመልክቶ በመጀመሪያ አስረግጠው ማለፍ የሚፈልጉት ፣ በሳቸው እምነት አንደማናቸውም በአለማችን አንደሚገኙት ከተሞች የራሷ የሆነ የአፈጣጠር ታሪክ ስላላት  ታሪኳን እንይ በሚል ፣ አንድ ክራፍና አይዝንበርግ (krapf and Isenberg) የሚባሉ ወንጌላውያን በ1840 ከጻፉት የጉዞ ማስታወሻ በመጥቀስ ‘የምንሊክ ጦር’፣ አሁን አዲስ አበባ በምንለው አካባባቢ የነበሩ የኦሮሞ ጎሳዎችን አንዴት  አንዳጠፋ ይገልጡና ፣ ‘ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አይመስለኝም ። ስለዛሬዋ የፊንፊኔ ሕጋዊ ባለቤትነት ስናወራ የጠራና ቅንነት የተሞላበት አመለካከት አንዲኖረን ይረዳናል ብዬ እገምታለሁ ።’ በሚል የውይይቱን ታሪካዊ ፋይዳ ሊዘጉት ይፈልጋሉ።  ይሄ ግን በኔ እይታ ትክክለኛ አካሄድ አይመስለኝም። ሲጀመር የክራፍ ዘገባ ስለ ሳህለ ስላሴ ዘመቻ እንጅ፣ ምኒልክ በዚህ ወቅት የሸዋ ንጉስ ስላልነበሩ ከአዲስ አበባ መቆርቆር ጋር በቀጥታ የሚያይዘው ነገር ያለ አይመስለኝም። ስለ ክራፍ ፅሁፍ ከተነሳ ዘንዳ ግን እሳቸው ከገጽ 197 ጠቅሰው በቃ ይላሉ እንጅ፣ ወደ ገጽ 211-212 ብንዘልቅ የሚቀጥለውን እናገኛለን

In the south-west we had before us the high mountains in the territory of Matisha, with their immense forests ;and on the south-west, we had before us the high mountain Entoto, where several of the Kings of Abyssinia had resided, till Gragne, the King of the Adal, destroyed the city built there…Neble Denghel is said to have been the last King who resided there. He took flight to the neighbouring mountain Ferrer, and then to the mountain Bokan, till he was compelled to retire to Tigre,when the Gallas profiting by this opportunity entered this part of Shoa after the death of Gragne.Thus Gurague was separated from Shoa. They took the most beautiful provinces….

 

ለማናቸውም እርሳቸው የጠቀሱት የሚስዮናዊው ዘገባ የሚለው፣የንጉሱ ገባር የነበሩና  ግብር ላልከፈሉ መቀጣጫ መንደሮቻቸው እንዲቃጠሉ ንጉሱ አዘዙ ሲሆን፣የንጉሱ ስርዓት ገባሩ ህብረተሰብ ላይ የሚያካሂደውን ጭካኔ አመላካች መሆኑ ጠቃሚ መረጃ ነው። እንዲህ ያለ አሳዛኝ የታሪክ ክስተት ግን በዚያና በቀደሙት ዘመናት ግብር አልገብርም ያለም ሆነ ለሌላ ህብረተሰብ መስፋፋት እሺታን ያላሳየ ወገን የሚያጋጥመው መከራና ስቃይ፣ የአንድ ህብረተስብ ልዩ ባህሪ ሳይሆን ሁሉም ተግባራዊ ያደርጉት የነበረ አስከፊ የታሪክ ሂደት እንደነበረ መቀበል ያስፈልጋል።

 

ኦሮሞውም በመስፋፋት ዘመቻ ወቅት የተከተለው አካሄድ ከዚህ ብዙም የተለየ እንዳልነበር ታሪክ ይመሰክራል። ታሪክን ለኛ በሚያመች መንገድ ብቻ ቆንጽለን ካላየን በቀር፣ ከባሌ ተነስቶ በየጁ አድርጎ ከግራኝ መሃመድ ጋር ዘምቶ ጎንደር ድረስ ዘልቆ ንግስናን የተጎናጸፈው የኦሮሞ መስፋፋት፣ የእንኳን ደህና መጣህ ዘንባባ እየተነጠፈለት እንዳልሆነ እንገነዘባለን። በበርካታ ስፍራ የተካሄዱት የኦሮሞ መስፋፋቶችም እምቢ ያለውን አንገቱን በሰይፍ እየቆረጠ፣ የገበረውን ማንነቱንና ቋንቋውን ሳይቀር ደፍጥጦ ሞጋሳ በሚሉት ስርዓት የኦሮሞ ሰብዕና በመስጠት ያጠምቅ እንደነበርም የሚታወቅ ነው።

 

ክራፍና አይስንበርግ ሚስዮናውያን እንጂ የታሪክ ምሁራን ስላልሆኑ፣ ከጻፉት ብዙ የጉዞ ማሳታወሻዎች አንዳንድ ጠቃሚ መረጃዎችን ልናገኝ ብንችልም ጥንቃቄም ማድረግ የግዴታ አስፈላጊ ነው።

 

አሁን ከዚህ ከሱ ዘገባ ተነስተን ግን፣ የተወሰነ ግዛትን የባለቤትነት ጥያቄ እንደማረጋገጫ ብንወስድ ወደ ብዙ ስህተት እንደሚከተን እሙን ነው። ታሪካችን ገና ብዙ ምርምርና ጥናት እንደሚያስፈልገው ግልጽ ቢሆንም፣ያለፉ ታሪካዊ ኩነቶችን አስመልክቶ የሚበጀው ከሌሎች ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የውጭ ሃገር የታሪክ ባለሙያዎች ምርምር በማጣቀስ ለታሪካዊ እውነቱ ቅርብ የሆነውንና የማያወላዳ ታሪክዊ እውነቶችን ያካተተውን፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለትንተና ግብአት አድርጎ መጠቀም እንጂ የፈረንጅ መንገደኛን የጉዞ ማስታወሻ እንደ ብቸኛ የታሪክ እውነታ መቀበል ለስህተት ይዳርገናል።

 

በጣም የሚያሳዝነው ግን ይሄ ከ 175 አመት በፊት ይደረግ የነበረው ህዝብ ላይ የሚካሄድ አስከፊ ጥፋት፣ ትምህርት ለመውሰድ ዝግጁ ባለመሆናችን ባለፉት ሰላሳ አመታት ዳግም ሲፈጸም ማየታችን ነው። በደርግ የመጨረሻ አመታት ኦነግና ሻዕቢያ ጣምራ ጦር ይዘው አሶሳ ላይ የተጠና፣ ግን ድንገተኛ ዘመቻ አድርገው መጤ ብለው የነጠሉት ማህበረሰብ ላይ የጅምላ ግድያና ሰውንም ከነቤቱ በእሳት እንዳጋዩት ተዘግቦ የተቀመጠ ነው።

 

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሁሉም የሃገሪቱ ግዛት የመኖር መብት አለው የሚል ድንጋጌ ያለው ህገ-መንግስት ቢኖርም በኦነግ ካድሬዎች አስፈጻሚነት በበደኖና አርባጉጉ አማራና የሌላ ብሄረሰብ አባላት ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ ከነነፍሳቸው ወደ ገደል መወርወርም ሆነ፣  በኦህዴድ ካድሬዎች አቀነባባሪነት፣ አርሲ ለረጅም ትውልድ የኖሩ የከምባታ ብሄረሰብ አባላት በመቶዎች ተገድለው፣ ሺዎች ነፍሳቸውን ለማዳን ከሃገር ውስጥ እስከ ደቡብ አፍሪካ እንዲሰደዱ መደረጉ ትኩስ ቁስል ነው። በቅርቡ ደግሞ በነሽፈራው ሽጉጤ መሪ ተዋናይነት በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ብሄረሰብ አባላት ንብረታቸው ተዘርፎ፣ ተገድለው ከጉራ ፈርዳና ሌላ አካባቢዎች እንዲሰደዱ ተደርጓል።

 

ወደ ዋናው ጉዳያችን ስንመለስ ፣አዲስ አበባና አካባቢዋ የነበረውን  የሕዝብ  አሰፋፈርን አስመልክቶ የመቶና ሁለት መቶ ሳይሆን የብዙ ሺህ አመታት ታሪክ ያለው በመሆኑ፣ የህጋዊ ባለቤትነት ጥያቄ መነሳት ካለበት፣ በመቶ ሁለት መቶና ሶስት መቶ ዓመት አጥር ውስጥ ከቶውም ሊሆን አይገባም። ታሪክን መሰረት ያደረገ የሕጋዊ ባለቤትነት ጥያቄ ከተነሳ መደረግ የሚኖርበት ከረጅሙ የስፍራው የአሰፋፈር  ታሪክ ተነስቶ አንዲሆን የግድ ይላል።  ይሄም በመሆኑ አዲስ አበባንና አካባቢውን አስመልክቶ ከደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል ተነስቶ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል የተሰራጨው ኦሮሞም ሆነ፣ ከሰሜን ተነስቶ ወደ ደቡብ ያቀናው አማራ ከረጅሙ የታሪክ ፍስት አንጻር መጤዎች መሆናቸውና፣ የብቸኛ ባለቤትነት ጥያቄ ሊያቀርቡ እንደማይችሉ አንዳችም ጥርጥር ሊገባን አይገባም። አውቁ የታሪክ ምሁር ዶክተር መሐመድ ሐሰን ‘ ኦሮሞውና የኢትዮጵያ የክርስትያን ግዛት 1300-1700 ( The Oromo and the Christian Kingdom of Ethiopia 1300-1700)የሚለውን መጽሐፍ ብናገላብጥ ከላይ ያሰፈርኩትን በሰፊው ስለሚያብራራ ታሪካዊ ባለቤትነት የሚለውን ጉዳይ በቅጡ መረዳት ስለሚቻል በዚህ አጋጣሚ ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ እንዲያነቡት እጋብዛለሁ።

 

ሌላው ከታሪካዊ ተምሳሌትነት በመነሳት ለማነጻጸር በሚል ስለ ዋሽንግተን ዲሲ  (‘ ዲሲ የተቋቋመችው በፈቃደኝነት በስጦታ በተሰጠ መሬት ላይ ሲሆን ፊንፊኔ ግን ከሕጋዊ ባለቤቶቿ በጉልበት ተነጥቃ ነው’ ብለው ሲጽፉ ከላይ አንዳልኩት የአንድን ስፍራ ታሪክ በአጭር የጊዜ ገደብ ገድቦ ማየት የሚያመጣውን ስህተት ፍንትው አድርጎ በማሳየቱ፣ ስለአንድ ስፍራ ባለቤትነት ለማውራት፣  የግዴታ የረጅም ጊዜ ታሪኩን የመመልከት  አስፈላጊነትን ያጠናክራል።

 

አርግጥ ነው ታሪክን እንዲሁ በግርድፍ ካየነው፣ ዲሲን ለመምስረት ቨርጂንያና ሜሪላንድ መሬት አዋጥተው በስጦታ መልክ መስጠታቸው አውነትነት አለው። ሆኖም የ ዲሲ ባለቤትነት ጉዳይ ከተነሳ ግን፣ ስፍራው  አሎንግኳያን (Algonquian ) ቋንቋ የሚናገሩ ባብዛኛው  የፕካታዋይ(Piscataway)ህንዶች አንደነበረና በ1604 ገደማ  ከአውሮፕውያን ጋር ግንኙነት በተጀመረ በአርባ ዓመት ውስጥ በጦርነትና በበሽታ ሶስት አራተኛውን ሕዝብ ጨርሰው፣ በሂደት ደግሞ ቀሪውን ለስደት ዳርገው፣  አዲሶቹ ባለቤቶች የተሰጣጡት እንጂ፣ እርስዎ እንደሚሉት   ’በፈቃደኝነት በስጦታ በተሰጠ መሬት’አይደለም ዲሲ የተቆረቆረችው።  ይሄን ያመጣሁት እርስዎ ዲሲን እንደልዩ ስላዪዋትና፣ አለመሆኗን ከማሳየት ውጭ በአለም ህዝቦች ታሪክ ተደጋግሞ የሆነ አካሄድ በመሆኑ የተለየ አያደርገውም ለማለትም ጭምር ነው። ሌላው ትንሽ ግንዛቤ የሚያሻውና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ፌዴራሊዝምን አስመልክቶ እኛ ሃገር ያለው ብሄርን ብቻ (ሲመቸው ብል ይሻላል ደቡብ የሚል በርካታ ብሄረሰቦችን ጠቅሎ የያዘ አለና!)ማእከል ያደረግ ፌዴራሊዝም ከአሜሪካን ሃገር ፌዴራሊዝም ሆነ በሌላ መስፈርት ከተቋቋሙ የፌዴራል ስርዓቶች ጋር ለማወዳደር መሞከር ለስህተት እንዳይዳርገን ልንጠነቀቅ ይገባል።

 

አቶ ባይሳ “የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮና ተከባብሮ ይኖር ነበር ተብሎ እንደተወራለት ሳይሆን…”ወዘተ በማለት የአቶ ሃዲስ አለማየሁን በ1953 ዓ.ም. ለንጉሱ የተጻፈ ማስታወሻ በመጥቀስ ካሉት ሶስት አይነት ቅርጫቶች  ሁላችንም የማንነት ቀውስ ካልያዘን በቀር ባንዱ ብሄርተኛ ቅርጫት ውስጥ መካተት እንዳለብን እርግጠኛ ሆነው ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ደፍጥጠው ለማለፍ የሚሞክሩበት ዘዴ የሚያስኬድ አይደለም። የጠቀሷቸው ቅርጫቶች ቢኖሩም ከሶስቱም የማይገባ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ግን ያለና የነበረ መሆኑንንም መቀበል ግዴታዎ ይመስለኛል።

 

በሃገራችን የነበረው የአጼዎች ስርዓት አድሎአዊ እንደነበር ፣የብሄረሰቦችን መብት በመደፍጠጥ ወጥ የሆነ አሃዳዊ አገዛዝ ለመምስረት የሞከረ መሆኑ እውን ቢሆንም፣ እንድማናቸውም ብሄርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት በሂደት እያደገ እንደነበር ሊያስክደን አይችልም። ከሃገራችን ረጅም የታሪክ አንጻር የቅርቡን እንኳን ብናይ፣ጉርዓ፣ ጉንደት ሰሃጢ፣መተማ ፣ አድዋ፣ ማይጨውና የአምስት አመቱ የአርበኝነት ጦርነት፣ ከሶማሌ ተስፋፊ ሃይልና፣ ኤርትራን  ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ከታገለው ከሻዕቢያ ጋር ከተለያዩ የኢትዮጵያ ብሄረሰቦች በተውጣጡ የሚሊዮኖች ደም ተገብሮ ሕይወት ያለው ኢትዮጵያዊነት እንደተገነባ ጥርጥር ሊገባን አይገባም። ይሄ ማለት ግን ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ነበር፣ ሃገራችንም ሁሉም በፍቅር ተዋዶ የሚኖርባት ማርና ወተት የሚፈስባት ለውጥ የማያስፈልጋት ሃገር ነበረች ማለት አይደለም።

 

ኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ የሆነ፣አንዱን ገዥ አንዱን ተገዥ፣ አንዱን ባለመሬት አንዱን ጭሰኛ ያደረገ፣ ፍትህና ርትእ የጎደለባት፣ሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የማይታይበት፣ እንደ ማናቸወም በሃገሪቱ የሚኖሩ ዜጎች አንዳንዶች የሚገባቸውን የዜግነት መብት የሚገፍ የአጼዎች ስርዓት ነበር። የዚህን አድሎአዊ ስርዓት አስከፊነት የተገነዘቡና፣ መለወጥም አለበት ብለው ያመኑ፣ ከሁሉም ብሄረሰብ የተውጣጡ የ60ዎቹ ወጣት ትውልድ አባላት፣በኢትዮጵያ መልክአ ምድር የሚኖሩ ዜጎችን ሁሉ በህግ ፊት እኩል የሚያደርግ፣ ፍትህና ርትእ የሰፈነባት ሃገር ለመገንባት በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወታቸውን የገበሩበት ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትና ማንነት ይዘው እንድነበር መዘንጋትም ፣ ትልቅ ስህተት ነው።

 

ስለ ታሪክ ይህን ያህል ካልን በቂ ነውና አዲስ አበባን አስመልክቶ የባለቤትነትን ጥያቄ ከተነሳ፣ አቶ ባይሳ እንዳሉት “ባገሪቷ የሚገኙት ከሰማኒያ የማያንሱ ብሄረሰብ አባላትን በኩልነት የምታስተናግድ..” በመሆኗ ባለቤቷ እኒህ በውስጧ የሚኖሩ ከአራት እስከ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ናቸው የሚል የጸና አቋም አለኝ። አዲስ አበባ በማን ስር ትተዳደር የሚለውንም፣ በነዋሪዎቿ በተመረጠ የከተማ አስተዳደር ሆኖ፣ አሁን በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት አንቀጽ 49 እንደሚደነግገው ይህም አስተዳደር “ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል”ባለው መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን መታገልን ይጠይቃል። የፌዴራል መንግስቱ መቀመጫና የፌዴራል መንግስቱ ርዕሰ ከተማ በመሆኗም ተጠሪነቷ ለፌዴራል መንግስቱ ብቻ መሆን አለባት የሚል እምነት አለኝ።

 

አቶ ባይሳ ከአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ ባሻገር  ሁለት ታላቅችግሮች ብለው ያነሷቸው፣ አንደኛ “ትልቁ ችግር ባገሪቷ የፌዴራላዊ አስተዳደር ቅርጽና ይዘት..””ሁለተኛው ትልቁ ችግር አሁንም በኔ ግምት፣ የፊንፊኔ ከተማ ድንበር በግልጽ አለመታወቅ” በሚል ያስቀምጡታል።

 

በኔ እይታ ግን በገሃድ ለሚታየው የሃገራችን የሰላም፣የዴሞክራሲና የፍትህ እጦት ትልቁ ችግርና እንቅፋት የህወሃት መራሹ መንግስት በስልጣን መቆየት ይመስለኛል። ይሄን ስል ግን የህወሃት የበላይነትን መሰረት ያደረገው መንግስት ነገ ወይንም ከነገ ወዲያ ከስልጣን ቢወርድ ችግሮቻችን ሁሉ ተነው ይጠፋሉ ለማለት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

 

የህወሃት አብዛኛው መስዋዕትነቱና ተጠሪነቱ ለትግራይ ህዝብ በሚል ብቻ ስለነበርና (ኤርትራን ለማስገንጠል ከገበራቸው በአስር ሺህ ከሚቆጠሩ የትግራይ አርሶ አደር ወጣቶች በቀር)ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የህዝብ ቁጥር አንጻር አናሳ በመሆኑም ጭምር፣ ፍትሃዊ የሆነ የፌዴራል አስተዳደር ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት፣ የበላይ የመሆን ፍላጎቱን ስለሚከለክል፣ በሃገራችን እንዲህ ያለ ስርዓትእንዲሰፍን ምንም ፋላጎት የለውም። ባለፉት ሃያ ስድስት አመታት  ያየነውም በአፍና በወረቀት አስፈላጊነቱንና እንዴት የህልውና ጥያቄ አድርጎ እንደሚመለከተው ከመለፈፍ ውጭ፣ በተግባር ግን እያንዳንዱን የፍትሃዊ ስርዓት ጥረትም ሆነ ራሱ ባጸደቀው ህገ መንግስት የተካተተውን የፌዴራል አስተዳደር እያጨናገፈ፣ ወይንም እሱን በሚጠቅም መንገድ ብቻ ተግባራዊ እያደረግ ሲሄድ በመገንዘብ፣ የሃገራችን ዋነኛ ችግር በህወሃት የበላይነት የሚመራው የኢህአዴግ መንግስት በስልጣን መቆየት ነው እንድል አስችሎኛል።

 

ኢትዮጵያ ምን አይነት የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ያስፈልጋታል በሚለው፣ እኔም እንደ አቶ ባይሳ ለሃገራችን የፌዴራል አስተዳደር ይበጃል የሚል እምነት ቢኖረኝም፣ ቋንቋን ብቻ መሰረት ያደረገ መሆን አለበት የሚል ግንዛቤግን የለኝም። በኔ እምነት የጂኦግራፊያዊ አቀማመጥን፣ የኢኮኖሚ ትስስርንና ቋንቋን መሰረት ያደረግ የፌዴራል አወቃቀር የተሻለ መስሎ ይታየኛል።

 

ሁለተኛው ትልቅ ችግር ያሉት የአዲስ አበባ ድንበር በግልጽ አለመታወቅ አምጥቶታል ያሉት ችግር ሲሆን፣ በኔ እይታ ድንበሩ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት፣በአካባቢው ከሚገኙ ትናንሽ ከተሞችም ሆነ ነዋሪው ህዝብ ጋር በሁሉም ኢኮኖሚያዊና ለሎች ጉዳዮች ፍትሃዊ ግንኙነት መኖሩ አስፈላጊ መሆኑን አምናለሁ። በሃገሪቱ ፍትሃዊና የህግ የበላይነት እስከሌለ ድረስ ግን የድንበር መኖር የዜጎችን በደልና አላግባብ መፈናቀል ያስቀራል የሚል እምነት የለኝም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ህወሃት/ኢሃዴግ በጋምቤላ ክልል ሺዎችን በግፍ ከመሬታቸው አፈናቅሎ ለስደት ከዳረገ በኋላ፣ ካራቱሪ ለተባለ ወሮበላ ቡድንና ለሌላ አረብ ከበርቴዎች እንድ መለስተኛ የአውሮፓ ሃገር የሚያህል መሬት እንደቸበቸበ ስናይ፣ ችግሩ ያለው ሌላ ስፍራ መሆኑን ይጠቁማል።

 

በመጨረሻም የአቶ ባይሳን መደምደሚያ ልዋስና “የድህረ-ወያኔዋ ኢትዮጵያ ሁሌም የምንመኛት ዲሞክራሲያዊት ሆና ህዝቦቿ በእኩልነት የሚኖሩባት በዳይና ተበዳይ የማይገኝባት የእኩዮች አገር እንድትሆን ካሁኑ መሰረቱን መጣል አለብን እላለሁ።

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.