ከግብር ጫናና ትመና ጋር ተያይዞ እንደገና ያገረሸው ተቃውሞ በርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎችን እያዳረሰ ይገኛል

ኢሳት ዜና
በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ በተለያዩ ተሽከርካሪዎች ወደ ኦሮሚያ ተጨማሪ ወታደሮችን እየላከ መሆኑ ተነግሯል። በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው አምጽ በአምቦ ጀምሮ ጊንጪና ጀልዱ እንዲሁም ወሊሶና ቡራዩን አዳርሷል። በደቡብ ክልል ሳውላ ከተማ ከግብር ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነስቷል።በአማራ ክልልም ከግብር ጫና ጋር በተያያዘ የባህርዳር ነጋዴዎች ፈቃዳቸውን እየመለሱ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ነጋዴን በግብር፣ ገበሬን በመሬት፣
ከተሜን በቤት፣ ሾፌርን በቅጣት
ድሀን ግጦ መብላት !!!
ለወያኔ “ልማት”!!!

ሙክታር ከድር ሄዶ፣መገርሳ ቢመጣ፣
አስቴር ቁልቁል ወርዳ፣ ወርቅነህ ቢወጣ፣

ዝፍዝፍ ጉልቻዎች፣ ቦታ ቢለውጡ፣
ይብስ ጎረና እንጂ፣ አልጣፈጠም ወጡ።

የቦካ ጥያቄ፣ በጥልቀት በስፋት፣
እንዴት መልስ ያገኛል፣ጉልቻ በመግፋት? ( ደረጀ ሀ)

የሕሊና ዳኝነት እና ቀጣዩ ፈተና
ክፍል አንድ

” ችግሩ ካልተፈታ የአማራ ህዝብ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቅልን እናደርጋለን!” ይሄን የተናገረው የብአዴን ካባ የለበሰውና አማራ ክልል ተብሎ የተፈጠረውን አስተዳደር ለረጅም ጊዜ የመራው አቶ አዲሱ ለገሰ አይደለም። ” ኦቦ!” ምን ጐድሎበት ይሄን ይላል። ” ላለፋት አስር አመታት አንድም አዲስ ማከፋፈያ አልተገነባ።” ይሄንንም ያለው የኢህአዴጉ ጐብልስ በረከት ስምኦን አይደለም። እሱስ ቢሆን ምን ጐድሎበት ። ” ያሉት 25 ሐይል ማከፋፈያ (substations) አብዛኛው በደርግ ጊዜ የተሰሩ ናቸው። አርጅተዋል። ቮልታቸው አነስተኛ ነው። እነዚህን ይዞ ፋብሪካ መገንባት አይቻልም። የተገነቡትም መስራት አልቻሉም። ክልሉ ባለሃብቶችን መጥታችሁ አልሙ የማለት ሞራል የለንም።” ይሄንንም ህውሓቶች እና የፌስ ቡክ ስኳዶቻቸው የቁርጥ ቀን ልጆቻችን የሚሏቸው ታጋይ ታደሰ ጥንቅሹ፣ ታጋይ ካሳ ሸሪፎ፣ ታጋይ ህላዌ ዬሴፍ አይደሉም። ሁሉ በእጅና ደጅ ሆኖላቸው እንዴት ይሄን የሚል የሞራል ልዕልና ያገኛሉ? … ኧረ በጭራሽ!…ታዲያ ማነው ይሄን ያለው?

ተስፋዬ ጌታቸው ይባላል። የአማራ ክልል የካቢኔ ፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሐላፊ ነው። ሌላኛው ደግሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪ “ማንትሴ” ጥሩነህ ይባላል። ከይቅርታ ጋር ” ማንትሴ” ያልኩት ስሙን ማንበብ ስላልቻልኩ ነው። ከላይ የተገለጠውን እውነታ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያፍረጠረጡ ብአዴኖች ናቸው።

እነዚህ ብአዴኖች በሕውኃት እቅፍ ውስጥ ሆነው ይሄን መሬት የረገጠ እውነት ለመናገር መድፈራቸው ሊበረታታ ይገባል። እንደ እውነቱ ከሆነ ጋዜጠኛውን ጨምሮ አንዳች ሂሳብ ሳይሰሩ ግልጥልጥ አድርጐ ማሳየታቸው በአርአያነት ሊታይ የሚችል ነው።ከሩቅ ሆኖ ሊከፍሉ የተዘጋጁትን ዋጋ ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
እርግጥ የህዝቡ እምቢተኝነትና የተዳፈነ ቁጭት ተናጋሪዎቹን ወደዚህ ውሳኔ እንዳመራቸው ከጥያቄ የሚገባ አይደለም። የተዳፈነ ህዝባዊ ቁጣ በበረታ ቁጥር ህውሓት `ብአዴን` በሚባል የልጥ ገመድ ያሰራቸው አማሮች ገመዱን መበጣጠሳቸው የማይቀር ሐቅ ነው።

እነዚህ ሁለት የብአዴን ካድሬዎች ያቀረቡት ማስረጃና ምሬት በጥሞና ለተከታተለው ብዙ ምላሾችን ይሰጣል። እንድምታዎቹም ብዙ ናቸው። የበላይ ባለስልጣናት እንደመሆናቸው መጠን የፌዴራሉ መሥሪያቤቶች መረጃ ይደርሳቸዋል። ለምሳሌ የመብራት ሐይል ባለሥልጣን ባለፋት አራት አመት ብቻ 92 ማከፋፈያ በኢትየጵያ ደረጃ ሰርቷል። እ•ኤ•አ• በ2015 ብቻ የተሰሩት ሃይል ማከፋፈያዎች 45 ያህል ይሆናሉ። ይሁን እንጂ የአማራ ንግድ ቢሮ ሐላፊው እንደገለፀው ላለፋት አስር አመታት በአማራ ክልል አንድም ማከፋፈያ አልተገነባም። የገዱ አንዳርጋቸው ልዩ አማካሪ እንደገለጠው ከሆነ ደግሞ የተሰሩት ማከፋፈያዎች በደርግ ጊዜ ተገንብተው ያረጁና ከጥቅም ውጭ የወጡ ናቸው። ይሄን እውነት መስማት በጣም ያሳፍራል።

ሁለቱ የብአዴን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሚያውቁት ሌላም እውነት አለ። ህውሃት እድሜውን ለማራዘም እና የገባበትን የውጭ ምንዛሪ ማነቆ ለማስተንፈስ የአገሬውን ህዝብ በኤሌክትሪክ እጦት እያሰቃየ ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ግብፅ ከ3,300 ሜጋ ዋት በላይ ለመሸጥ ዉል ተፈራርሟል። ግብፅ ብቻ ከ2ሺህ በላይ ሜጋ ዋት ለመውሰድ አሰፍስፋ እየጠበቀች ነው። በሌላ በኩል አቶ አርከበ እቁባይን የፈረንጅ ላም ሆነው እያገለገሉ ያሉትና የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቁምሳጥኖች የኤሌክትሪክ ያለህ እያሉ ነው። የባህርዳሩ፣ የኮምቦልቻው እና የጐንደሩ ቁምሳጥኖች ከ934 ሜጋዋት በላይ እንደሚያስፈልጋቸው ለክልሉ መስተዳድርና ለኤሌክትሪክ ባለሥልጣን መስሪያቤት አቅርበዋል። እናም እነዚህ የክልል ባለስልጣናት ቢጨንቃቸው ለዘመናት ተሸክመው የኖሩትን እውነት አፍረጠረጡት። አይደለም የኢንዱስትሪ አብዬት የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን ዳቦ ጋግሮ ለማብላት የሚያስችል ኮረንቲ እንደሌለ ይፋ አደረጉ። እንጅባራ እና ወልዲያ ዩንቨርስቲ ልጆቻቸውን የሚልኩ ቤተሰቦች ልጆቻቻቸው በጠኔ ሊጐዱ እንደሚችሉ በእጅ አዙር አሳወቁ። መቼስ ለወላጆች ይሄን መርዶ ከመስማት በላይ ጭንቀት የለም። ለብአዴኖቹ ባለስልጣናትም ቢሆን ይሄን መራር ሐቅ የኢትዩጵያ ህዝብ እንዲያውቅላቸው ከማድረግ ውጭ ጊዜያዊ አማራጭ የለም።(Ermias Legesse Waqjira)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.