አቶ ካሳ ተክለማሪያም እዚያው ጓዶቻቸው ጋር ያልቅሱ #ግርማ_ካሳ

“በትግራይ እና በአማራው ክልል የሚኖሩ፣ ማን እንደወከላቸው የማይታወቁ ሰዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች ነን በሚል፣ የሁለቱም ክልሎች ፕሬዘዳንቶች፣ አቶ ገድ አንዳርጋቸውና አቶ አባይ ወልዱ፣ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሕወሃትና የብአዴን አመራሮች በተገኙበት አንድ ጉብዬ በመቀሌ አድርገዋል። ህዝብን ከሕዝብ ለማቀራረብ በሚል። በዚህ ስብሰባ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና አቶ ካሳ ተክለማሪያም ተናገሩት የተባለው፣ በአንዳንድ ማእዘናት ውይይቶችን ጭሯል። በመርህ ደረጃ ህዝብን ሊያቀራረብ የሚችል ማናቸውም አይነት ድርጊት ሆነ ስብሰባ የሚደገፍና ሊበረታታ የሚገባ ቢሆንም፣ ይህ የመቀሌው ስብሰባ ግን እንኳን የተባለለትን አላማ ሊያሳክ ቀርቶ ጭራሹን በሕዝብ መሳቂያና የጥቂት ጊዜ ወሬ ነው የሆነው።

ከስብሰባው ጋር በተዛመደ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ፡

አማራ በሚባለውና ትግሬ በሚባለው ማህበረሰብ መካከል ምን ችግር ተፈጠረና ነው አሁን የማቀራረብ እንቅስቃሴ በጎላ መልኩ የሚደረገው ? ችግር አለ ከተባለስ ችግሮቹ ምንድን ናቸው ? የችግሮቹ መንስኤ ወይም ዋናው ነቀርሳው ላይ ሳይተኮር ላይ ላዩን ማውራት ችግሩን ይፈታል ወይ ? ላለፉት 25 አመታት በኦሮሚያ በኦህዴድና በኦነግ ፣ በደቡብ ክልል በነ አቶ መለስ ዜናዊ ትእዛዝና በነአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ተላላኪነት፣ እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ ኢትዮጵያዉን “አማራ ፣ ነፍጠኛ ..ናችሁ” በሚል በጅምላ ሲገደሉ፣ ከቅያቸው ሲፈናቀሉ፣ በባዶ እግራቸው ኪሎሜትሮች አቋርጠው እንዲሰደዱ ሲደረጉ፣ አገራችሁ አይደለም ተብለው ሲባረሩና ቤቶቻቸው ሲቃጠሉ፣ መቼ አይተን እናውቃለን የህዝብ ለሕዝብ መቀራረብ ጉባዬ ? መቼ ነው የኦሮሚያ ክልል ሽማግሌዎች በባህር ዳር መጥተው፣ በአማራ ክልል ካሉ ሽማግሌዎች ጋር እንዲነጋገሩ የተደረገው? የኦህዴድ ባለስልጣናትስ፣ እንኳን በአማራ ክልል ካለው ሕዝብ ጋር ሊነጋገሩ ቀርቶ፣ በኦሮሚያ አፋን ኦሮሞ ከማይናገሩ፣ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ወገኖች ጋር እንኳን መነጋገርና የነርሱን ጥያቄ ማስተናገድ የተሳናቸው አይደለም ወይ ?

እነዚህንና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ስናነሳ በመቀሌ የተደረገው መቃወማችን አይደለም። ነገር ግን ከፈረሱ በፊት ጋሪው ከቀደመ ጉንጭ ከማልፋት ዉጭ አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ እንደማንችል ለማሳየት እንጅ።

የሕወሃት ባለስልጣናት ችግር መኖሩን መረዳታቸው ተገቢ ነው። መፍትሄ የሚፈለገው ችግር እንዳለ መረዳት ሲጀመር ነው። አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በመቀሌው ስብሰባ እያለቀሱ መናገራቸውን ስምተናል። “አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን በመቀሌው ጉባኤ ላይ አለቀሱ የሚል ነገር ሰማሁ፡፡አቶ ካሳ ለወደፊቱ ሽንኩርት እየከተፉ ስብሰባ ላይ አይሳተፉ” እያለ እንደቀለደው ጦማሪ ስዩም ተሾመ፣ ለእኝህ ባለስልጣን እምባ ቦታ የሚሰጥ ዜጋ ይኖራል ብዬ አላስብም። ለማስመሰል ይሁን ከልብ ከተናገሯቸው አባባሎች መካከል የተወሰኑቱን በጣም የምጋራው መሆኔን ግን ሳልገልጽ ማለፍ አልፈልግም። “አማራና ትግራይ በጎንደር ተጣልተው ሽምግልና ተቀመጡ ሲባል በእውነት ያማል። ጎንደር የአቢሲንያ ርእሰ ከተማ ነው። የጎንደር መነሻ አክሱም ነው። በአክሱምና ጎንደር መካከል ልዩነት መፈጠር የአቢሲንያ ጉድ ነው። ውድቀት ነው። እናም ያማል “ ነበር ያሉት፣ የጎንደርና የትግራይ ህዝብን ትስስር ሲገልጹ። ትክክል ናቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ጎንደሬ ሆኖ ትግሬነት የሌለበት ይኖራል ብዬ አላስብም። ይሄ ሰሜን ጎንደር የሚኖር በአማራነት ስም ጸረ-ትግሬ ጦማር የሚለቀልቀው ሁልአ ወረድ ሲል አያት ቅድመ አያቶቹን ቢመረመምምር፣ ጎይቶሞችንና ትብለጾች ያገኛል።

አቶ ካሳ እተፈጠረ ነገር መታመማቸው ማለፊያ ነው። ግን አንድ ነግር መረሳት የለበትም። አቶ ካሳ አሁን ነው ያመማቸው፤ እኛ ግን ላለፉት 25 አመታት ነበር ሲያመን የነበረው። ለስልጣን እንዲያመቸው አገሪቷን በዘር በመሸንሸን፣ “ይሄ መሬት የአማራ፣ ያ መሬት የኦሮሞ፣ እዚያ ማዶ የትግሬ” እያለ ፣ ዜጎች በሚያስተሳስራቸው ነገር ላይ ሳይሆን በሚከፋፍላቸው ጉዳዮች ላይ እንዲያተኮሩ፣ እርስ እርስ እንዳይተማመኑ፣ እንዲከፋፈሉ ሲያደርግ የነበረውና አሁንምም እያደረገ ያለው፣ እርሳቸው “ያማል” ላሉት ነገር ተጠያቂ የሆነው፣ እርሳቸው አመራር አባል የሆኑበት አገዛዝ አይደለም እንዴ ? በዚሁ በመቀሌ ስብሰባ “የጥላቻ ዘርን በመዝራት የፍቅር አዝመራን መሰብሰብ አይቻልም” እንዳሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይህ አሁን የሚታየው ከዘር ጋር የተገናኘውን፣ የጥላቻና እና የዘረኝነትን ዘር እራሱ ሕወሃታ እነ አቶ ካሳ ያሉ አገልጋዮቹ ዘርተው አሁን እንዴት ፍቅር እንዲሰበሰብ ይጠብቃሉ ?

እስቲ የወልቃይት ጉዳይን እንመልከት። ወልቃይት ጠገዴ የሚኖረው ህዝብ አማራ፣ ትግሬ ሳይባባል ለዘመናት በጎንደር ጠቅላይ ግዛት ሥር እንደ ወልቃይቴ ሲኖር የነበረ ሕዝብ ነው። ትግሬው፣ ከአማራው ተዋልዶ፣ ተደባልቋል። አብዛኛው ሕዝብ አማርኛም ትግሪኛም ይናገራል። ሲያሻው ሽሬ፣ ሲያሻው ጎንደርና ደባርቅ ሄዶ ይነግዳል። ወልቃይት ጠገዴ የፍቅር፣ የትስስር ተምሳሌት ነበረች። ሆኖም አንድነት፣ ፍቅርን ከማጠናከር ይልቅ ሕወሃት የትግሬነት ማንነት በወልቃት ህዝብ ላይ ለመጫን ተሞክረ (የኦነግ ጠባብ ፖለቲክ ያሰከራቸው አክራሪዎች የኦሮሞ ማንነት የሚሉትን አዲስ አበባና ሌሎች የኦሮሚያ ትላልቅ ከተሞች በሚኖርው ህዝብ ላይ ለመጫን እንደሚሞክሩት)። በግድ ትግሬ ነህ ሲባል፣ ህዝቡ ተፈጥሯዊ ነውና ተቃወመ። ህወሃቶች የዘር ካርድ መዘው በዘር ጨዋታ ሲንቀሳቀሡ ሌላዉም ሳይወድ በግዱ የዘር ጨዋት ካርድ ለመምዘዝ ተገደደ። ከሁለተኛ አለም ጦርነት በኋላ የበርሊን ከተማ ለሁለት ተከፍላ ነበር። ያ የሆነበት ምክንያት በራሺያና በአሜሪካ መካከል የርዮት አለም ልዩነት ስለነበረ ነው። በራሺያ እነ ጎርባሾቭ ሲመጡ በበርሊን የነበረው ግንብ ፈረሰ። ከተማዋ እንደጋና አንድ ሆነች። አሁንም ህወሃት ያመጣው የዘር ፖለቲካ ለምሳሌ አንድ የነበረውን የጠገዴ ህዝብ፣ ለሁለት ከፍሎታል። ጠገዴና ጸገዴ በሚል። እንደ ሞያሌ፣ ዲላ ያሉ ከተሞችን ለሁለት ክፍሏል።

የበርሊን ግንብ እንደፈረሰው፣ በጠገዴ/ጸገዴ በሞያሌ፣ በዲላ … ያለውም የዘር መከፋፈል ግንብ ካልተደረመሰ አሥር ሺህ ጉብዬ ቢደረግ የሚለወጥ ነገር አይኖርም። የትግራይ ክልል መንግስት፣ ሕወሃት፣ በሃይልና በጉልበት፣ ያለ ሕዝቡ ፍላጎት፣ በዚያ የሚኖረውን ህዝብ አፈናቅሎና ለስደት ዳርጎ ፣በግድ ትግሬ ነህ እየተባለ፣ በአማርኛ እንዳይማርና በአማርኛ የመንግስት አገልግሎት እንዳያገኝ ተከልክሎ ፣ በወልቃይት ጉዳይ ህዝብ ወክሏቸው ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ዜጎች በግፍና በጭካኔ እየተሰቃዩ፣ በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች የሕወሃት የበላይነት ገኖ፣ እንዴት ነው እርቅ ሊመጣ የሚችለው ? አቶ ካሳ መቀሌ ሄደው ከሚያለቅሱ ለምን በሚኒስትሮች ምክር ይሁን በአሕአዴግ ፖሊት ቢሮ ስብሰባ ላይ ወልቃይትን ጨምሮ፣ በጎንደር በጎጃም..የሚኖረው ሕዝብ የጠየቃቸውን መሰረታዊ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ ለምን አይተጉም? እዚያው ጓዶቻቸው መካከል ለምምን አያለቅሱም ?

ከፈሩሱ በፊት ጋሪው አይቀደም ያልኩት እንግዲህ ይሄንን ነው። እንደውም ጉባዬ፣ ስብሰባ አያስፈለግም። በሕዝብና በሕዝብ መካከል ችግር የለም፣ ኖሮም አያውቅም። ችግር ፈጣሪዎቹ ፖለቲከኞችና ስልጣን ላይ የተቀመጡት ናቸው። እነርሱ ባመጡት ጣጣና የዘር ፖለቲካ ነው አገር እየታመሰች ያለችው። ስለዚህ የዘር ጨዋታ ካርዶች ወደ ገደል እየተጣሉ አዲስ ፣ ጤናማ፣ ህዝብን የሚጠቅም፣ በሰብአዊነት ላይ ያተኮረ ጨዋታ መጀመር አለበት። እነ አቶ ካሳ በርግጥም እየተፈጠረ ባለው ነገር ሕመም ከተሰማቸው፣ ፍቱን መድሃኒት እንዲመጣ ማድረግ አለባቸው። እርሱም ከናካቴው ከዘር ፖለቲክ በመውጣት፣ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ መባባሉና ሁሉንም፣ ነገር በዘር ሂሳብ ማስላቱ ቆሞ፣ ዜጎች በሁሉም የአገሪቷ ግዛት፣ ባህላቸው፣ ቋንቋቸው ተከብሮ፣ ሁሉም የአገሪቷ ግዛት አገራቸው መሆኑን አምነውና ተረድተው፣ ያም በሕግ በማያሻማ መንገድ ተረጋግጦ፣ እንዲኖሩ መደረግ አለበት። አሁን ያለው ፌዴራል አወቃቀር ተሰርዞ ወይም ተሻሽሎ፣ አዲስ ዘመናዊ፣ በቋንቋ ላይ ብቻ ሳይሆን በባህል፣ በታሪክ፣ በሕዝብ አሰፋፈር በኢኮኖሚ፣ በጂዮግራፊ፣ በሕዝብ ፍላጎትና በአስተዳደር አመችነት ላይ የተመሰረተ የዘመኑን ትዉልድ የሚመጥን አወቃቀር ያስፈልገናል።

አንድ ሰው መጥበብ፣ ጎሰኛና መንደርተኛ መሆን ከፈለገ፣ ትግሬነትን፣ ኦሮሞነትን፣ አማራነትንን ..ማቀንቀን ይችላል። ያ መብት ነው። ሆኖም ግን በመንግስት ደረጃ አጼ ቴዎድሮስ “ሃይማኖት የግል አገር የጋራ” እንዳሉት፣ እኔም ዘርን ጨምሬ “ሃይማኖትና ዘር የግል አገር የጋራ” ይሁን እላለሁ። በዚህ ረገድ ገዢዎች መሰረታዊ የአካሄድ ለውጥ በቶሎ እንዲያደርጉ እመክራለሁ።

(ከዚህ በታች የምታይዋቸው በግፍና በጭካኔ ፣ “አማራ ናችሁ” ተብለው የተፈናቀሉ ናቸው። በጎንደር የነበሩ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች፣ ጎንደር በነበረው እንቅስቃሴ ስለፈሩ በፍቃዳቸው ጎንደርን መልቀቅ በፈለጉ ጊዜ በቦይንግ ነው ወደ መቀሌ እንደሄት፣ እነዚህ ወገኖች ቦይንግ አይደለም የፈረሰ ጋሪ አልቀረበላቸውም። ሳይፈልጉ በግድ ነው፣ ኪሎሜትሮች በማቋረጥ በእግር የተፈናቀሉት። በተለይ በአርባ ጉጉና በበደኖ ብዙዎች በጭካኔ ተግድለዋል። ከመተማ አካባቢ ወደ ሱዳን ተሰደው ለነበሩ የትግራይ ተወላጆች መልሶ ማቋቋሚያ በሚል በአሥር ሚሊዮኖችች የሚቆጠር ገንዘብ በክልሉ መንግስትና እንደ ሶማሌ ክልል ባሉ ሌሎች የክልል መንግስታት ሲሰበሰብ፣ የመንግስት ሜዲያ የነዚህ የትግራይ ወንድሞቻችንን መፈናቀል በስፋት ሲዘግብ፣ እዚህ ፎቶ ላይ ያሉ ወገኖቻችን ግን ዞር ብሎ የተመለከታቸውም የለም። በነርሱምም ጉዳይ የተጠራ ጉባዬ የለም)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.