በአምቦ ዳግም የህዝብ አመጽ ተቀሰቀሰ

በአምቦ ዳግም የህዝብ አመጽ ተቀሰቀሰ 1

(ኢሳት ዜና–ሐምሌ 21/2009) በአምቦ ዳግም የህዝብ አመጽ ተቀስቅሷል።የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት ተሰንዝሯል።ሰላም ባስ በተሰኘው የህወሃት ንብረት ላይም ህዝብ እርምጃ መውሰዱ ታውቋል።

በደደርና በአለም ገና በግብር ጭማሪው ምክንያት ነጋዴዎች አድማ መምታታቸው ተገልጿል።በአማራ ክልል በሞጣ አድማው ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው።በደቡብ ኢትዮጵያ የቦንጋ ነጋዴዎች መማረራቸውን ገልጸዋል።ከ1 ሺ በላይ ነጋዴዎች ፍቃዳቸውን መመለሳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አምቦ ዛሬ የነዋሪው ተቃውሞ ጠንከር ብሎ ውሎበታል።የመንግስት ተሽከርካሪዎች የተቃውሞ አድማ መተው እንደነበር የመረጃ ምንጮች ጠቅሰዋል።

አንድ የጤና ቢሮ ተሽከርካሪም በቆመበት የተቃጠለ ሲሆን የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ንብረት የሆነው ሰላም ባስ አውቶቡስ ላይም ጉዳት እንደደረሰበት ታውቋል።

አምቦ ከግብር ጭማሪና ከሰነበተው የኦሮሞ ህዝባዊ ንቅናቄ ጋር በተያያዘ የህዝብ ተቃውሞ ተለይቷት አያውቅም።

ባለፈው ሳምንት ሱቆችና መደብሮችን በመዝጋት ነጋዴው ያደረገው አድማ ግጭት እያስከተለ የቀጠለ ሲሆን ዛሬ በሁለት ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ውጥረቱ እንዲባባስ አድርጎታል።

ከአምቦ በተጨማሪ በአለም ገና ተቃውሞ እየተካሄደ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።የግብር ተመኑን በመቃወም የንግድ ቦታዎች ተዘግተው የዋሉ ሲሆን የመንግስት ታጣቂዎች በሃይል ለማስከፈት እየሞከሩ እንደሆነም ታውቋል።

በምስራቅ ሀረርጌ በደደርም እንዲሁ አድማ መመታቱን ከአካባቢው የወጡት መረጃዎች ያሳያሉ።በደደር ትላንት የአድማ ጥሪ ወረቀት ከተበተነ በኋላ ነው ዛሬ ሱቆችና መደብሮች የተዘጉት።

በአማራ ክልል ሞጣ ዛሬም የአድማ እንቅስቃሴ ላይ ናት። በአምስተኛ ቀኑም ሱቆችና መደብሮች ተዘግተው ውለዋል።

በነጋዴው አድማ የተደናገጡት የመንግስት ሃላፊዎች በየቀኑ እየተሰበሰቡ ችግሩን ለመፍታት እንሞክራለን የሚል ምላሽ ቢሰጡም ነጋዴዎች  እንዳልተቀበሉትና በአድማው እንደቀጠሉ ታውቋል።

በነጋዴው እምቢታ የተበሳጩት የመንግስት ሃላፊዎች የምታመጡትን እናያለን በሚል የግብር ተመኑን በንግድ ድርጅቶቹ በርና መስኮት ላይ ሲለጥፉ ማርፈዳቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል

ሞጣና ሌሎች አካባቢዎች ጥሪ አድርገዋል።በአንድነት እንነሳም ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።ደብረወርቅ የተባለችው የምስራቅ ጎጃም ከተማ ዛሬ የመጀመሪያ ቀን አድማዋን መምታቷ ታውቋል።

ሸበል በረንታ፣ብቸና፣ደጀን፣ያዝ ለቀቅ ባደረገ መልኩ አድማው እንደቀጠል ይነገራል።በሸበል በረንታ ህዝቡ አጠቃላይ የስርአት ለውጥ ካልመጣ የግብር ጭማሪውን ወደፊትም እንደማያገኝ እየተናገሩ ነው።

ላልመረጥንው መንግስት የዘራፊው የህወሃት መንግስት ግብር አንከፈም የሚለው አቋም ጎልቶ እየተሰማ መሆኑንም ወኪላችን ያነጋገራቸው ነዋሪዎችን በመጥቀስ ገልጿል።

በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ቦንጋ የነጋዴዎች ቅሬታ እየተሰማ ነው።ከ1 ሺ በላይ የሚሆኑ በቦንጋና ዙሪያዋ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ፍቃዳቸውን እንደመለሱ ይነገራል።

ከሌሎች የመልካም አስተዳደር እጦት የሰብአዊ መብት ጥሰት ግድያና ሙስና ጋር የግብር ጭማሪው ህዝቡን የመኖር ህልውና እንዲያጣ እያደረገው ነው የሚሉት የቦንጋ ነጋዴዎች ስር ነቀል ለውጥ ካልመጣ ወደ አጠቃላይ ሰብአዊ ቀውስ ከምንገባበት ምእራፍ ተጥግተናል ብለዋል።

ከዚሁ ከግብር ጭማሪ ጋር በተያያዘ ይርጋለም ከተማ ትላንት ምሽት የአድማ ጥሪ ወረቀት ሲበተንባት ነው ያደረው።ህወሃት/ኢህአዲግ በኢፍትሃዊ የጫነብንን ግብር አንከፍልም ላላመንበት ስርአት አንገብርም።የአፍ ማባበያዎችን አንፈልግም የሚሉና መሰል መልእክቶችን የያዙ ወረቀቶች በተለያዩ የይርጋለም አካባቢዎች ተሰራጭተዋል።በይርጋለም ፖሊስ ጣቢያ ፈት ለፊት በቶታል ነዳጅ ማደያ ቃኘው መንገድ ጀርባ፣ይርጋለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መንገድ ላይ በሚገኙ ግድግዳዎችና ምሰሶዎች ላይ ተለጥፈው መታየታቸውን በፎቶግራፍ ተደግፎ የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

አሁን በደረሰን ዜና በአዲስ አበባ በካራቆሬ መስመር ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገ ነው።ወደ አዲስ አበባ በሚገቡና በሚወጡ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የመንግስት ታጣቂ ሃይሎች እያሰለፉ ፍተሻ በማድረግ ላይ መሆናቸው የታወቀ ሲሆን ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግን አልታወቀም።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.