የማለዳ ወግ …ዝክረ ሰማዕት ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ! – ነቢዩ ሲራክ 

* ዛሬም ክብር ለብጹዕ አባታችን

ኢትዮጵያ ከሀዲ ብቻ ሳይሆን ስለ እውነት ፣ ለእውነት አድረው ፣ የዛሬ ኢትዮጵያን በደማቸው ዋጅተው ፣ በሰማአዕትነት ዝንተ አለም የማይረሳ ኩሩ ታሪክ ያወረሱን ልጆች እናት ናት ። የኢትዮጵያ ማሕጸን ካፈራቸው መካከል ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ይጠቀሳሉ። ሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ በ1875 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ አገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ። በበቂ የቤት ክህነት ትምህርት ታንጸው ከዲቁና እስከ ጵጵስና ከፍተኛ ማዕረግ የደረሱት ብፁዕነታቸው ጣሊያን በስሩ እንዲያድሩ በጥቅምና ስልጣን ሊገዛቸው ሲሞክር አሻፈረኝ አሉ፡፡ አቡነ ጴጥሮስ ለጣሊያን ፍርፋሪ ሳይንበረከኩ ፣ ለአድርባዮች የማሸርገድ ሽምግልናእንቢ እንዳሉ ምድሪቱና ህዝቡ ለጣሊያን እንዳይገዙ በእግዚአብሔር ስም ግዝት አስተላለፉ ! እናም ልክ የዛሬ 81 ዓመት ሐምሌ 22, 1928 ስለ ኢትዮጵያና ህዝቧ ክብር በጥይት ተደብድበው በግፍ ተገደሉ ! እናም ኢትዮጵያን የምንወድ እነሆ ለትውልድ ትውልድ በክብር ኩራት ሰማዕቱን አባት ሳምሰለች እናዘክራቸዋለን !

ጸሃፌ ተውኔት ሌሬት ጸጋየ ገብረ መድህን ለብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ልዩ ፍቅር ነበራቸው ። አንድ ጀንራሬ በሰማዕቱ መታሰቢያ ሃውልት ላይ በንቀት ሽንቱን ሲሸና ያገኙባት ቀን ልዩ ቀን ነበረኝ ። ሎሬት ጀብራሬውን ገፍተው ብቻ አልቀሩም ። ያችን ቀን ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲማለዳት “ሰቆቃዎ ጴጥሮስ ” ሲሉ ታላቁ ሊቅ ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ በተማጽኖ ቅኔ ዘረፉ ! ውጋት ቁስላችን የሚያነሳሳበት ዘመን ተሻጋሪ የግጥም ቋጠሯቸው ” ምነው እመብርሃን ኢትዮጵያን ጨከንለሽባት ? ምነው ቀኝሽን ረሳሻት ?” እያለ የሎሬት ቅኔ ዛሬም ዛሬን ያጠይቃል !

እኔም ታላቁን ሰማዕት የብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ሙት አመት መታሰቢያ ቀን በባለቅኔው አባት በሌሬት ጸጋየ ገብረ መድህን ጴጥሮስ ያችን ሰዓት ዛሬን ማዘከሩን መርጫለሁ ! ዛሬ የብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ የምናስታሳውቸው በኩራት ነው ! ለኢትዮጵያና ህዝቧ ክብር ሰማዕትነትን ከፍለዋልና !

ክብር ለሚገባው ክብር እሰጣለሁ !

ነቢዩ ሲራክ
ሀምሌ 22 ቀን 2009 ዓም

Watch “Laureate Tsegaye Gebremedhin : ጴጥሮስ ያችን ሰዓት” on YouTube

ሰቆቃ ወ – ጴጥሮስ … !
===============
አየ ምነው እመ ብርሀን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከ መቼ ድረስ እንዲሁ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን ሰቀቀንዋን ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንደሁ ትናጋዋን በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ ተምሳ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን እንደ ኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ስልጡን ብኩን መጻጉዕ ናት፤…
እና ፈርቼ እንዳልባክን ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋጋን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ በርታ በይኝ እመብርሀን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን::
አወን ብቻየን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያ መንፈሴ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሰጋሁ::

ተጻፈ በብላቴን ጌታ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህን
ቀበና ላይ …1961 ዓም

ማስታወሻ
======== በህይዎት ዘመኔ ሁሉ ይህንን የከበረ የአባት ስጦታ ፣ የሚያመራምር ፣ የሚነሽጥ የስንኝ ቅኔ ቋጠሮ ሰምቸ አልጠግበውም። በእርግጥ ሀገሬ ታላቁን ባለ ቅኔ ሊቅ አጣለች ፣ ትውዴ ጀግና ሊቁን በክብር ማዕረግ አልሸኘውምና አፍራለሁ ፣ አዝናለሁ  … ነፍስ ይማር አባታለም 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.