ክቡር ሚንስተር

ክቡር ሚንስተር 1[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሙስና ውስጥ የተዘፈቁ ሌላ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • ኧረ እኔ ነኝ ስልኬን ረሱት እንዴ?
 • ውይ ወዳጄ አንተው ነህ እንዴ?
 • ምን ባክህ አንድ ችግር አጋጥሞኝ ነው፡፡
 • ምን ክቡር ሚኒስትር?
 • እሱን በኋላ እነግርሃለሁ፡፡
 • ለማንኛውም ምን አስደነገጠዎት?
 • እንዴት አልደነግጥም?
 • ምነው?
 • ስማ ሰሞኑን እየተፈጸመ ያለው ነገር አያሳስብህም እንዴ?
 • እኔም እኮ እሱን ብዬ ነው የደወልኩት፡፡
 • አሁን ምንድን ነው የሚውጠን?
 • ክቡር ሚኒስትር በዚህ ወቅት እኔን ባያማክሩኝ ይሻላል፡፡
 • ምን ማለት ነው ሥራውን አንድ ላይ አይደል እንዴ የሠራነው?
 • ለዚያ እኮ ነው ሥራውን መጀመሪያ ያመጡት እርስዎ ነዎት፡፡
 • ቢሆንስ ታዲያ?
 • ስለዚህ መውጫ መንገዱም እርስዎ ጋ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡
 • ለመሆኑ አንተ ጋ ዶክመንት አለ?
 • እኔ ጋ ያለውን ዶክመንት ለማጥፋት ጥረት እያደረግኩ ነው፡፡
 • ምን አደረግከው?
 • ካዝና ውስጥ ቆልፌዋለሁ፡፡
 • አሁኑኑ አውጣና አቃጥል፡፡
 • ይሻላል ክቡር ሚኒስትር?
 • በአፋጣኝ አቃጥለው አልኩህ፡፡
 • እንዳሉ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • እኔም ጋ ያሉትን አቃጥያቸዋለሁ፡፡
 • በጣም ጥሩ፡፡
 • ቅድም ስልክ ራሱ የጠፋብኝ ዶክመንት አጠፋለው ብዬ ኮንታክቶቼን በሙሉ አጥፍቻቸው ነው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር?
 • አቤት፡፡
 • ዶክመንቶቹ ግን ከእኔና ከእርስዎ ውጪ ሌሎች ሰዎች ጋም ይገኛሉ፡፡
 • እኔም የጨነቀኝ ጉዳይ እሱ ነው፡፡
 • ምን ተሻለ ታዲያ?
 • ዶክመንቱ ያላቸው ሰዎች ጋ ስልክ ልደውል ብዬ ፈራሁ፡፡
 • ምን አስፈራዎት ክቡር ሚኒስትር?
 • ስልኬ ይጠለፋል ብዬ ነዋ፡፡
 • ስልኩ ላይማ ስለልማት ምናምን ብለው ሸፋፍነው ያውሩና በአካል ተገናኝተው ያነጋግሯቸዋ?
 • ስማ እንደዚህ የማደርግበት ሞራሉም ድፍረቱም የለኝም፡፡
 • ለምን ክቡር ሚኒስትር?
 • ሌሊቱን ሳልተኛ ነው የማድረው፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር ይኼን ያህልማ አይረበሹ፡፡
 • ስማ ፊት ለፊቴ የአገር የመድኃኒት ብልቃጥ ነው የተደረደረው፡፡
 • ብዙ አይጨነቁ ስልዎት?
 • የሚጠብቀን ምን እንደሆነ ታውቃለህ?
 • ግፋ ቢል መታሰር ነው፡፡
 • እኔ የማልፈልጋት እሷን እኮ ነው፡፡
 • መታሰር ብርቅ ነው እንዴ?
 • አንደኛውን ብታሰር ይሻለኝ ነበር፡፡
 • እንዴት?
 • ይኸው አንዴ ስኳር፣ አንዴ ደም ግፊት ተጫወቱብኝ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር የበለጠ እየተጨናነቁ ራስዎን አይረብሹ፡፡
 • አሄሄ፡፡
 • ለማንኛውም አንድ ጉዳይ ስላለኝ ወደዚያ ልሂድ፡፡
 • እኔም በቃ ሻንጣዬን ላዘጋጅ፡፡
 • ከአገር ሊወጡ ነው እንዴ?
 • መግባቴ ስለማይቀር ልብሴን ከአሁኑ ላዘጋጅ ብዬ ነው፡፡
 • የት ነው የሚገቡት?
 • ቂሊንጦ!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚስታቸው ጋር እያወሩ ነው]

 • ሥራ አትሄድም?
 • እስቲ ተይኝ፡፡
 • ምንድን ነው ይኼ ሁሉ መድኃኒት?
 • አንቺ ነሽ ለዚህ ሁላ የዳረግሽኝ፡፡
 • ምን አደረግኩህ ደግሞ?
 • አንቺ አይደል እንዴ የገፋፋሽኝ፡፡
 • በል በእኔ እንዳታላክክ፡፡
 • ለነገሩ ‘ሴት የላከው ሞት አይፈራም’ አሉ፡፡
 • ተረትህን እዚያው፡፡
 • ይኸው ምክርሽን ሰምቼ ሊጠፍሩኝ ነው፡፡
 • ማን አባቱ ነው የሚጠፍርህ?
 • እንዲህ እያልሽ ነው ጉድ የሠራሽኝ፡፡
 • ነገርኩህ በእኔ አታሳብ፡፡
 • እና በማን ላሳብ?
 • አንተ ራስህ አምነህበት ነው የገባኸው፡፡
 • ምኑን?
 • ሙስናውን፡፡
 • እንዴት?
 • መንግሥት የሚከፍልህ ደመወዝ እንደማይበቃህ ታውቃለህ፡፡
 • እሱማ ይኼን ሁለት ቤት የሠራሁት እዚች እዛች ብዬ ባገኘኋት ኮሚሽን ነው፡፡
 • ታዲያ በእኔ ለምን ታሳብባለህ?
 • ይኸው ያቺ ኮሚሽን ለስኳርና ለደም ግፊት መድኃኒት ዳረገችኝ፡፡
 • ሰውዬ ተረጋጋ፡፡
 • እስር እኮ ነው የሚጠብቀኝ፡፡
 • መንግሥት የሰጠውን መግለጫ አልሰማህም እንዴ? አንተ አትታሰርም አልኩህ፡፡
 • እና ማን ነው የሚታሰረው?
 • ዳይሬክተሮቹ!

[ሰሞኑን ከታሰሩት ዳይሬክተሮች መካከል የአንደኛው ሚስት ለክቡር ሚኒስትሩ ስልክ ደወሉ]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • ‹‹ማን ልበል?›› ይሉኛል እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
 • ስላላወቅኩሽ ነው ይቅርታ?
 • እርስዎ ሳይገቡ የእኔ ባል ገባ?
 • ፓርላማ ነው?
 • እሱማ ቢሆን በምን ዕድሌ?
 • አላወቅኩሽም ይቅርታ፡፡
 • ባሌ ታስሮ እርስዎ ሊንደላቀቁ? መቼም አይሆንም፡፡
 • ይቅርታ የእኔ እመቤት፣ ባልሽ ማን ነው? አንቺ ማን ነሽ?
 • ባሌን አደፋፍረው ያንን ሁሉ እንዲሠራ ያደረጉት እርስዎ አይደሉ እንዴ?
 • ውይ ውይ የእኔው ጉድ ነሽ እንዴ?
 • ትዝ አልኩዎት አይደል?
 • በሚገባ አስታውሻለሁ፡፡
 • ክቡር ሚኒስትር በአፋጣኝ ባሌን ያስፈቱልኝ?
 • በምን አቅሜ?
 • እኔና ልጆቼ በየቀኑ እያለቀስን ነው፡፡
 • ምን ላድርጋችሁ ታዲያ?
 • ባሌን አስፈቱት አልኩዎት?
 • አልችልማ፡፡
 • ለነገሩ አንድ ነገር ገብቶኛል፡፡
 • ምን?
 • ሹመት ሹመቱን ለራሳችሁ ትወስዳላችሁ፡፡
 • እ…
 • እስር እስሩን ደግሞ…
 • እ…
 • ለበታቾቻችሁ!

[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሀቀኛ ሚኒስትር ደወሉላቸው]

 • ሄሎ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ማን ልበል?
 • ምነው ምነው? ያንን ሁላ ዘመን ተደዋውለን ዛሬ ስልኬ ጠፋዎት?
 • ውይ በሞትኩት አሁን በድምፅ አወቅኩዎት፣ እንዲያውም ስፈልግዎት ነበር፡፡
 • ለምን ፈለጉኝ ክቡር ሚኒስትር?
 • እንደ እርስዎ ሐቀኛ ብሆን ይሻለኝ ነበር፡፡
 • ይኼ ዛሬ ነው እንዴ የታየዎት?
 • መረረኝ እኮ በጣም፡፡
 • ያኔ ስኳሯን ሲልሷት ግን ጥማዎት ነበር፡፡
 • ምን ላድርግ? ወድጄ አይደለም፡፡
 • እኔ በደህናው ዘመን መክሬዎት ነበር፡፡
 • ያኔማ ጆሮዬ መቼ ይሰማ ነበር?
 • ለነገሩ ያኔ ስኳር የሚልሱበት ምላስዎ ብቻ ነበር የሚሠራው፡፡
 • ተወኝ እስቲ፡፡
 • ምን እያሰቡ ነው ታዲያ?
 • የልጆቼ ጉዳይ በጣም አሳስቦኛል፡፡
 • ያኔ ነበር ይኼንን ማሰብ፡፡
 • ወይ ጣጣ?
 • ለመሆኑ የዛሬውን ስብሰባ ለምን ቀሩ?
 • የትኛውን ስብሰባ?
 • ሂስና ግለሂስ የሚያደርጉበትን ስብሰባ ነዋ፡፡
 • አይ ቤቴ ሂስና ግለሂስ እያደረግኩ ነበር፡፡
 • ከማን ጋር?
 • ከስኳርና ከደም ግፊት!

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሰዓት በኋላ ቢሮ ገቡ አማካሪያቸውም ቢሯቸውን በርግዶ ገባ]

 • ውይ፡፡
 • ምነው ደነገጡ ክቡር ሚኒስትር?
 • ሊወስዱኝ የመጡ መስሎኝ ነው፡፡
 • ለነገሩ ምን ያለበት ዝላይ አይችልም አይደል የሚባለው?
 • አሁንማ እንደፈለግክ ስደበኝ፡፡
 • ኧረ ልሳደብ ፈልጌ አይደለም፡፡
 • አሁን ክብሬ ከእኔ ርቋል፡፡
 • ይኸው እኔ ራሴ ክቡር ሚኒስትር እያልኩዎት አይደል እንዴ?
 • ተወው ባክህ፡፡
 • ምነው?
 • ከጥቂት ጊዜ በኋላ ምን ብለህ እንደምትጠራኝ አውቀዋለሁ፡፡
 • እንደዚህማ አይጨነቁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
 • ሕዝቡ የሚለውን ስላልሰማህ ነው፡፡
 • ደግሞ ሕዝቡ ምን አለ?
 • እየተሰናበተን ነው እኮ?
 • ምን ብሎ?
 • ‹‹ደህና ሁኑ ሌቦች፣ የዛሬ ሚኒስትሮች የነገ ኢንቨስተሮች›› እያለ፡፡
 • ቀልድ ግን እስካሁን አልተውም ማለት ነው?
 • ይኸው አሁን ሊቀለድብኝ እኮ ነው?
 • ለመሆኑ ሰሙ?
 • ምን?
 • ፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን?
 • ዕረፍት ላይ አይደለን እንዴ? ምን ተፈጠረ ደግሞ?
 • ለዓርብ ስብሰባ ተጠርቷል፡፡
 • ችግር አለ እንዴ?
 • ሊነሳ ነው አሉ፡፡
 • የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ?
 • ኧረ አይደለም፡፡
 • ታዲያ ምኑ ነው የሚነሳው?
 • ያለመከሰስ መብት!

 

ምንጭ – ሪፖርተር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.