ማንኛውም የንግድም ሆነ የግድግዳ ላይ ማስታወቂያዎች በትግርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲጻፉ አስገዳጅ ህግ ወጣ

(ኢሳት ዜና –ነሐሴ 1/2009) ማንኛውም የንግድም ሆነ የግድግዳ ላይ ማስታወቂያዎች በትግርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲጻፉ አስገዳጅ ህግ ማውጣቱን የትግራይ ክልል መስተዳድር አስታወቀ።
አዲስ አድማስ የክልሉን ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጠቅሶ እንደዘገበው የንግድ ምልክቶቹ በተዘበራረቀ ቋንቋ መጻፍ የለባቸውም በሚል በትግርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲጻፉ አስገዳጅ ህግ ተደንግጓል።
ታዛቢዎች እንደሚሉት ደግሞ በትግርኛ ቋንቋ ብቻ የንግድ ምልክቶች በአስገዳጅ እንዲጻፉ በክልሉ ህግ የወጣው በራያና በወልቃይት ያሉ ነዋሪዎች በአማርኛ ብቻ ስለሚጠቀሙና በትግርኛ መናገርና መጻፍ ለምን አልቻሉም የሚለውን የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አባይ ወልዱን ዛቻ ተግባራዊ ለማድረግ ነው
በሀገር ቤት የሚታተመው አዲስ አድማስ ጋዜጣ እንደዘገበው የትግራይ ክልል መንግስት ማንኛውም የንግድ ማስታወቂያ ታፔላና የግድግዳ ላይ ማስታወቂያ መልዕክቶች በትግርኛ ቋንቋ እንዲፃፉ የሚያዝ አስገዳጅ አዋጅ ሰሞኑን አፀድቆ በስራ ላይ ማዋል ጀምሯል።
በአዋጁ መሰረት ማንኛውም የንግድ ድርጅትም ሆነ አገልግሎት ሰጪ ተቋም፤ የንግድ ማስታወቂያውን ወደ ትግርኛ እንዲለውጥ የሚያስገድድ ሲሆን አዋጁን ተግባራዊ ያላደረገ ድርጅትም ይታሸግበታል ይላል አዋጁ።
ይህ አዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን ከሳኦና ኩናማ ብሄረሰቦች በቀር በክልሉ ሙሉ በሙሉ ተፈጻሚ ይሆናል ተብሏል።
የሳኦና የኩናማ ብሄረሰቦች በከተማቸውና አካባቢያቸው፣ ማናቸውም የግድግዳ ላይ ማስታወቂያዎችና ታፔላዎች በየራሳቸው ቋንቋ እንዲጽፉ በአዋጁ ተደንግጓል።
ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ ጀምሮ የስራ ቋንቋውን በዚያው ዓመት በፍጥነት የቀየረው የትግራይ ክልል መንግስት ከ25ዓመት በኋላ ዘግይቶ በዚህ ዓመት አዋጅ ያወጣበት ምክንያት ግልጽ አይደለም።
ኢሳት በቅርቡ እንደዘገበው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አባይ ወልዱ ወደ ራያ በሄዱ ጊዜ ህዝቡን አስፈራርተው መመለሳቸው ይታወሳል።
አቶ አባይ በወቅቱ ህዝቡን በትግርኛ ሊያነጋግሩ ሲጀምሩ ተቃውሞ ገጥሟቸው እነደነበር ተገልጿል። እኛ ከአማርኛ ሌላ ቋንቋ አንችልም። በምንችለው ቋንቋ ያናግሩን የሚል ተቃውሞ ሲገጥማቸው በንዴት ‘’እንዴት እስከአሁን ትግርኛ አልቻላችሁም?’’ በሚል ህዝቡን በጅምላ ከዘለፉ በኋላ ‘’ ይህ መሬት የትግራይ ነው። ካልፈለገችሁ ለቃችሁ መሄድ ትችላላችሁ ‘’ ማለታቸው ይታወሳል። እዚያው መድረኩ ላይ በራያ የሚገኙ ንግድ ቤቶች የንግድ ማስታወቂያቸውን በትግርኛ እንዲያደርጉ አስገዳጅ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ተጠቅሷል።በተደጋጋሚ የህወሃት ባለስልጣናት ይህን ዓይነት ማስፈራራት ያደርጉ እንደነበርም ተገልጿል።
ድምጽ
አቶ አባይ ወደ መቀሌ ከመመለሳቸው በፊት እንዳስፈራሩትም ጥቂት ሳምንታት ቆይተው አዲስ አዋጅ እንዲወጣ ማድረጋቸውን ነው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢዎች የገለጹት። አዋጁን በራያ ብቻ ተግባራዊ ማድረጉ ከፖለቲካ አንጻር የሚያዋጣ አለመሆኑን በማስላት ህጉ በመላ የትግራይ ክልል እንዲሆን መደረጉን የጠቀሱት የኢሳት ምንጮች በራያ ህዝብ የተቆጡት የትግራይ ባለስልጣናት ቋንቋውን በሌላው ላይ በግድ ለመጫን ይህን መሰሉ አዋጅ ማውጣት ተገቢ ነው ከሚል ውሳኔ ላይ ደርሰዋል ሲሉም ያክላሉ።
ራያን ብቻ ነጥሎ ህግ ማውጣት የሚያስኬድ ባለመሆኑ እንጂ መነሻው በቅርቡ በራያ የተደረገው ተቃውሞ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በራያ ትግርኛ በብዛት የሚነገር ባለመሆኑ አዲሱ አዋጅ ተግባራዊ ሲደረግ ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ከወዲሁ ይነገራል።
ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ የህወሀት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ አባይ ጸሀዬ ራያዎችን ባነጋገሩበት ጊዜ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ‘’ራያ ትግሬ ነው። ለቃችሁ መሄድ ትችላላችሁ’’ ማለታቸው ይታወሳል። በንግድ ቤቶች ማስታወቂያዎች ላይ የሚጻፈውን ቋንቋ በተመለከተ ለሳኦና ኩናማ ብሄረሰቦች ህጉ በቋንቋቸው እንዲጠቀሙ ሲፈቅድላቸው ለራያ መከልከሉ ጉዳዩን አስገራሚ አድርጎታል። በተመሳሳይ በህወሀት ውሳኔ ወደትግራይ የተጠቃለለው የወልቃይት ጠለምት ጠገዴ አከባቢ ቋንቋቸውን እንዲቀይሩ የተገደዱ ሲሆን በተለይ በወልቃይት የቤተክርስቲያን ቅዳሴ በትግርኛ እንዲደረግ አስገዳጅ ውሳኔ ተላልፎ ተቃውሞ እንደገጠመው የሚታወስ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.