ጄኔራል ክንፈ ሊታሰሩ ይችላሉ የሚል ጭምጭምታ አይሏል (ዋዜማ ራድዮ እንደዘገበው)

(ዋዜማ ራድዮ እንደዘገበው) ከረፈደ የተጀመረው የኢህአዴግ የፀረ-ሙስና ዘመቻ የሜቴኩን ጄኔራል ክንፈ ዳኜን ሊነካ ይችላል የሚል ጭምጭምታ ከሜቴክ ሠራተኞች ከራሳቸው መስተጋባት ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ ከወር በፊት ታይቶ በማይታወቅ ድፍረት በተወካዮች ምክር ቤት አባላት ክፉኛ የተተቹት ጄኔራል ክንፈ ‹‹‹በግሌ የማምነው ለዚህ አገር ልማት እየወደቅንና እየተሰዋን እንደምንሠራ ነው፡፡ መጠየቅ ካለብኝ እኔ ልጠየቅ፡፡›› ካሉባት ዕለት ጀምሮ ሰውየው በደኅንነቶች ሊደፈሩ ይችላሉ የሚለው ጭምጭምታ ሲራገብ ቆይቶ ነበር፡፡

ከሰሞኑ የጸረ ሙስና ዘመቻ ጋር ተያይዞ ይኸው ጭምጭምታ እያደገ መጥቷል፡፡ በተለይም የርሳቸው ጽሕፈት ቤት የሚገኝበትና ከሜክሲኮ ወደ ሳርቤት የሚወስደው ዋና መንገድ ላይ በስተቀኝ የሚገኘው የመከላከያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ግቢ ሠራተኞች በክበባቸው ሻይ ቡና እያሉ የሚያወሩት ይህንኑ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ትልቁ አለቃቸው ከዛሬ ነገ ችግር ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ መጠርጠር የጀመሩት በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደኅንነት ሰዎች በመሥሪያ ቤቶቻቸው በስፋት ማንዣበባቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ቶቶት አካባቢና ኤምፔሪያል አሞራው ሕንጻ ዉስጥ የተጠለሉ የሜቴክ ሠራተኞችም ቢሆን ትልቁ አለቃቸው የማይደፈሩ እንደሆኑ ቢያውቁም ሊታሰሩ ይችላሉ የሚለው ሀሜት በስፋት መወራቱ አሳስቧቸዋል፡፡ ዘመቻውን በሚመራው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽኅፈት ቤትና አቶ ጌታቸው አሰፋ በሚመራው የመረጃና ደኅንነት ቢሮ መካከል የጄኔራል ክንፈ ጉዳይ አለመግባባት መፍጠር የጀመረው ዛሬ አይደለም ይላሉ፣ ነገሩን እናውቃለን የሚሉ ወገኖች፡፡

ጄኔራሉ ከፍ ያለ የአገር ፍቅር ያለው፣ ቀንተሌት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል የሚሠራ፣ በ‹‹ይቻላል›› ጥልቅ መንፈስ የተሞላ መሆኑ በስፋት በከፍተኛ አመራሩ ዘንድ ስለሚታወቅለት ብዙዎች ይሳሱለታል፡፡ በአንጻሩ ጥብቅ የመንግሥት የፋይናንስ አሠራርን ቸል ብሎ በዘፈቀደና በየዋህነት አንዳንዴም በማንአለብኝነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም በወታደራዊ አስተሳሰብ የሚታትትር መሆኑ ‹‹የዋህና ደፋር ጄኔራል ነው›› ያደርገዋል ይላል አንድ የቀድሞ የሜቴክ ባልደረባ፡፡ ይህ ባህሪው ደግሞ አገሪቷን በቢሊዮን የሚቆጠር ዋጋ እንድትከፍል አድርጓታል ሲል ሐሳቡን ይቋጫል፡፡
ዞሮ ዞሮ የርሱ በሕግ ፊት መቆምና አለመቆም ስለሕወሓትና ስለ ጠቅላላው የኢህአዴግ አሰላለፍ የሚነግረን ብዙ ነገር ይኖራል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.