ዜና ለፈገግታ….. በምዕራብ አርሲ “ያፈቀርኳት ልጅ እሺ እስክትለኝ ከዛፍ ላይ አልወርድም” ያለው ወጣት ተሳክቶለታል – ይታዎቅ ባለምላይ ከበደ

በምዕራብ አርሲ ዞን ሻላ ወረዳ አዋረ ጋማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር የ23 ዓመት ወጣት የሆነና የ7ኛ ክፍል ተማሪ ሮንዲ ነጌሶ በሚኖርበት ቀበሌ በአንዲት ወጣት ፍቅር ይወድቃል።

በፍቅር የወደቀው ወጣት ሮንዲ ፍቅሩን ወደ ቁምነገር ለመቀየር በማሰብም በአካባቢው ባህል ለልጅቷ ጋብቻ ጥያቄ ያቀርባል፡፡

ወጣት ሮንዲ ነጌሶ የጋብቻ ጥያቄ ቢያቀርብም ተፈቃሪዋ ወጣትና ቤተሰቦቿ ፍቃደኛ ሳይሆኑ ያቀራሉ፡፡

ታዲያ ይህ ወጣት ያፈቀራትን ልጅ ለማግኘት አንድ ነገር ያስባል፡፡

በዚህም ቤተሰቦቿ እሺ ብለው ያፈቀራትን ልጅ ካላመጡ እና ልጅቷን ከማጣ በማለት ሀምሌ 30 2009 ዓ.ም ከጠዋቱ 2 ሰዓት በአካባቢው የሚገኝ ትልቅ የዋርካ ዛፍ ጫፍ ላይ ይወጣል፡፡

የዚህ ወጣት አላማ ግራ ያጋባቸዉ የአካባቢው ሽማግሌዎች እና ቤተሰቦቹ ከዛፉ ላይ ውረድ ሲሉት ሲሉት ይለምኑታል፤ እምቢ አሻፈረኝ ያለው ሮንዲ ግን ያፈቀርኳትን ልጅ ካላመጣችሁ ከዚህ ዛፍ ላይ ዘልዬ እራሴን አጠፋለሁ የሚል መልስ ይሰጣቸዋል።

በሁኔታው ግራ የተጋቡት የአካባቢው ሽማግሌዎችም ይህን የወጣት ሮንዲን የፍቅር ጉዳይ ይዘው ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ይሄዳሉ።

የልጅቷ ቤተሰቦችም ሮንዲ ከዛፉ ላይ እንዲወርድ ለማድረግ 10 ሺህ ብር ይዘው ሄደው ከዛፉ ላይ ውረድና ይህንን ብር እንስጥህ ይሉታል።

ሮንዲ ግን ፍቅር ነው ያሸነፈውና ከልጅቷ በስተቀር ምንም አይነት ነግር ብታመጡ ከዛፉ ላይ አልወርድም የሚል ምላሽ ይሰጣቸዋል።

የሻላ ወረዳ ፍትህ ፅህፈት ቤት ዓቃቤ ህግ አቶ ላዕከምህረት መኮንን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ የልጁን አቋም መቀየር ያልቻሉት የልጅቷ ቤተሰቦች ውስጣቸው ባይወድም ልጁ ያፈቀራትን ልጅ ለሀገር ሽማግሌዎች አሳልፈው ሰጥተዋል።

የአካባቢው ሽማግሌዎችም ሮንዲ ያፈቀራትን ልጅ ይዘው ሄደው ልጁ ከዛፉ እንዲወርድ አድርገዋል።

ልጁ ከዛፉ ላይ ከወረደ ብኋላ የሀገር ሽማግሌዎቹ ቃል በገቡለት መሰረት ከዛፉ ከወረደ ከሁለት ቀን ብኋላ የልጅቷ ቤተሰቦች ከልጁ ተስማምተው ሮንዲ እና ያፈቀራት ልጅ እንዲግባቡ በማድረግ መርቀው ሰጥተውታል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.