የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅን ለማሻሻል ፓርቲዎች ተስማሙ – ነአምን አሸናፊ

ከዋናው ድርድር አስቀድሞ በርካታ ወራትንና አሰልቺ ውይይቶችን ያለፈው የገዥው ፓርቲና የ16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርድር ባለፈው ሳምንት ተጀምሮ፣ በመጀመርያው ዙር በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ውስጥ አዳዲስ አንቀጾች ለማካተትና ያሉትን ለማሻሻል ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡

ለድርድሩ ቅድሚያ የተሰጠው አጀንዳ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2003 የተመለከተው ነው፡፡ ይህም ድርድር በሦስት ክፍሎች ተከፋፍሎ የሚከናወን ነው፡፡ በዚህም መሠረት በመጀመርያው ዙር ከክፍል አንድ እስከ ክፍል ሦስት ወይም ከአንቀጽ 1 እስከ 31 ላይ ድርድር ተካሂዶ አዲስ አንቀጾችን ለመጨመርና ያሉትንም ለማሻሻል ውሳኔ መተላለፉን፣ ከአደራዳሪዎቹ አንዱ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሠረተው 1,500 አባላት ሲኖሩት ነው የሚለው የአዋጁ አንቀጽ 5(1) ሀ ወደ 3,000 አባላት ሲኖሩት በሚል ለመተካት ተስማምተዋል፡፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተመሳሳይ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (2) ሥር የተጠቀሰው ‹‹መሥራች አባላት ድምፅ ለመስጠት መብት ያላቸው ሆነው፣ የፖለቲካ ፓርቲው አባል ለመሆናቸው ስምምነታቸውን በፊርማቸው የገለጹ መሆን አለባቸው፤›› የሚለው ንዑስ አንቀጽ ደግሞ፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ አባል ለመሆናቸው ስምምነታቸውን የሚገልጽ የተረጋገጠ ፊርማና የተረጋገጠ የነዋሪነት ማረጋገጫ ማቅረብ አለባቸው፤›› በሚል ለመተካት ተስማምተዋል፡፡

በዚህ አንቀጽ ላይ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሠረተው አገራዊ ፕሮግራም ያለው መሆኑ፣ ቢያንስ በአራት ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ፓርቲው ጽሕፈት ቤት ያለው መሆኑ ሲረጋገጥ ነው የሚል አዲስ አንቀጽ እንዲካተትም ተስማምተዋል፡፡

በተመሳሳይ የክልል የፖለቲካ ፓርቲ ምሥረታን አስመልክቶ የነበረው የመሥራች አባላት ቁጥር ገደብ ከ750 ወደ 1,500 ከፍ እንዲል ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪም ክልላዊ ፕሮግራም ያለው መሆኑና የፖለቲካ ፓርቲው በሚቋቋምበት ክልል ውስጥ ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተሞች ውስጥ ቢያንስ 25 በመቶ በሚሆኑ ቦታዎች፣ ፓርቲው ጽሕፈት ቤቶች ያሉት መሆኑ ሲረጋገጥ የሚል ንዑስ አንቀጽ እንዲጨመር ፓርቲዎቹ ይሁንታቸውን ገልጸዋል፡፡

በምዕራፍ አንድ ውስጥ እንዲጨመር ይሁንታ ያገኘው አዲስ አንቀጽ ደግሞ የፓርቲዎችን የጽሕፈት ቤት ኪራይ የተመለከተ ነው፡፡ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎች በማንኛውም ቦታ ጽሕፈት ቤት ለመከራየት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተከራይና አከራይ የሚወሰን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጽሕፈት ቤት ለመከራየት የሚያደናቅፉ ተግባራት መፈጸም የተከለከለ ነው፤›› የሚል አዲስ አንቀጽ እንዲካተትም ተስማምተዋል፡፡  

በምዕራፍ ሁለት ውስጥ ከሚገኙ አንቀጾች መካከል ስለፖለቲካ መተዳደሪያ ደንብ በሚያትተው አንቀጽ 15 ላይ አዲስ ንዑስ አንቀጾች እንዲጨመሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ አንቀጹ ሦስት ንዑስ አንቀጾች የነበሩት ሲሆን፣ አሁን ንዑስ አንቀጽ አራትና አምስት እንዲጨመሩበት በመስማማት ንዑስ አንቀጽ አራት፣ ‹‹የማንኛውም ፓርቲ መተዳደርያ ደንብ የፖለቲካ ፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ አባላት ብዛት፣ ውሳኔ አሰጣጥ፣ ጉባዔው የሚካሄድበትን አማካይ መደበኛ ጊዜ፣ የጉባዔ ዝግጅት አሰያየምና የሚከናወንበትን አሠራር በግልጽ የያዘ መሆን ይኖርበታል፤›› ይላል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ሥር እንዲካተት ስምምነት የተደረሰበት ንዑስ አንቀጽ አምስት ደግሞ፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲው የመተዳደርያ ደንብ የአባላቱን ተሳትፎ፣ የፓርቲው መሪዎች በተወሰነ ወቅት በጠቅላላ ጉባዔ የሚመረጡበትና በጠቅላላ ጉባዔው መወሰን ያለባቸውን ጉዳዮች ሥልጣን በፓርቲው ጥቂት ኃላፊዎች እጅ ተጠቅልሎ በማይገባበትና በአጠቃላይ የፓርቲውን የውስጥ ዴሞክራሲ በሚያዳብር አግባብ ስለመቀረጹ ቦርዱ ይቆጣጠራል፤›› የሚል ነው፡፡

 ሌላው በክፍል ሦስት ምዕራፍ ሁለት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ግዴታ ጋር የተያያዙ አንቀጾች ላይ ማሻሻያዎችና አዳዲስ አንቀጾች ተካተዋል፡፡

በዚህም መሠረት አንቀጽ 19 ላይ ንዑስ አንቀጽ ሠ ተካቷል፡፡ የተጨመረውም አንቀጽ፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ስብሰባ ከመካሄዱ 30 ቀናት በፊት የቦርዱ ተወካይ እንዲገኝ አስቀድሞ ያሳውቃል፤›› የሚል ነው፡፡

አሁን ባለው አዋጅ አዲስ አመራር የመረጠ ፓርቲ አዲሱን አመራር ወዲያው ለቦርዱ ያሳውቃል የሚለው በ30 ቀናት ውስጥ ያሳውቃል በሚል እንዲተካ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በተለያዩ ምክንያቶች የአመራር አባላቱ የተጓደሉ ከሆነና ቁጥሩም ከ50+1 በታች ከሆነ በ30 ቀናት ውስጥ መሟላት አለበት፡፡ ይህንንም ወዲያውኑ ለቦርዱ በጽሑፍ ማሳወቅ አለበት፤›› የሚለውም እንዲሁ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ማሳወቅ አለበት በሚል እንዲተካ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል፡፡

የፓርቲዎቹ ድርድር በሌሎች ጉዳዮች ላይም ይቀጥላል፡፡ ድርድሩ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካ፣ የእንግሊዝ፣ የጀርመን፣ የካናዳና የኔዘርላንድ ኤምባሲ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡ 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.