የአማራ ክልል ፖሊስ የህወሃት ደጋፊ የትግራይ ተወላጆች “ ልዩ ጥበቃ” እንዲደረግላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አደረገው

(ኢሳት ዜና ነሃሴ 9 ቀን 2009 ዓም)

በባህርዳር ከተማ የሚኖሩ የህወሃት ደጋፊ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች በክልሉ ያለው የጸጥታ ሁኔታ በድጋሜ ስጋት ላይ የጣላቸው መሆኑን ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ባለስልጣናት በተወካዮቻቸው አማካኝነት ተናግረዋል። የህወሃት ደጋፊዎቹ በክልሉ የሚታየው ሁኔታ እያስፈራቸው እንደመጣ፣ ከዚህ በፊት የተከሰተው አደጋ በድጋሜ ሊከሰት የሚችልበት እድል እንዳለ በመግለጽ፣ ክልሉ እነሱን ለመጠበቅ የሚሰራው ስራ ባለመኖሩ ወቀሳ አቅርበዋል። የክልሉ የጸጥታ አካላት የተለዬ ጥበቃ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ቢያሳስቡም፣ የክልሉ ፖሊስ ግን ማሳሰቢያውን ወደ ጎን በማለት ለእነሱ የተለዬ ጥበቃ እንደማያደርግ ገልጿል። የክልሉ ፖሊስ፣ በክልሉ ማንኛውንም የጸጥታ መደፍረስ ለመቆጣጠር እየሰራ መሆኑን ገልጾ፣ ጥበቃ ከተፈቀደለት ባለስልጣን እና ከመንግስት ተቋማት ውጭ በግለሰብ ደረጃ የሚደረግ ጥበቃ እንደማይኖር ገልጿል። የክልሉ ፖሊስ የሰጠው መልስ የህወሃት ደጋፊዎችን አላስደሰተም።
ከዚህ በፊት የህገ ወጥ መሳሪያዎች ቁጥጥር ቢመደረግበት ጊዜ ለከተማ ነዋሪዎች የተከለከሉ አውቶማቲክ ጠመንጃዎች ከበርካታ ጥይቶች ጋር በእነዚሁ የህወሃት ደጋፊ ወገኖች እጅ ቢያዙም፣ በአካባቢው ከሚገኘው መኮድ እየተባለ ከሚጠራው የመከላከያ ካምፕ የሚመጡ ወታደራዊ አዛዦች የሚያዙትን ጠመንጃዎች ለስራ ተብለው የተሰጡ የመንግስት መሳሪያዎች መሆናቸውን እየገለጹ መሳሪያዎቹ ለባለቤቶቹ እንዲመለሱ ሲያደርጉ ቆይተዋል። የክልሉ ፖሊስ ይህንን ድረጊት ጠንቅቆ ቢያውቅም እርምጃ ለመውሰድ ሲደፍር አልታየም።
የአሁኑ የልዩ ጥበቃ ጥያቄ ህወሃት፣ በጸጥታ መደፍረስ ስም ከዚህ ቀደም ሲወስዳቸው የነበሩትን ሁለቱን ህዝቦች የሚጋጩ ስራዎችን ለመስራት ማቀዱን እንደሚያመለክት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ይገልጻሉ።
በተያያዘ ዜና ባለፈው እሁድ የክልሉ የመረጃ አካላት ከዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊዎች ጋር ጎንደር ላይ ባደረጉት ስብሰባ፣ በአገዛዙ ላይ ስለተቃጣው አደጋና የጸጥታ መደፍረስ ተወያይተዋል። የክልሉ የደህንነት አካላት ስራቸውን በተገቢው ሁኔታ እየሰሩ አይደለም በሚል ወቀሳ ቀርቦባቸዋል። በባህርዳር ከተማ የሚደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ ማስቆም አለመቻሉ የግምገማው ዋና አጀንዳ የሆነ ሲሆን፣ በአደባባይ እየተዛተ የሚደረገው ፍንዳታ በክልሉ ያለው ችግር ውስብስብና ሰፊ መሆኑ ተገልጿል። ኢሳት ቀደም ብሎ እንደዘገበው ፍንዳታውን አደረሱ ተብለው የተያዙ ሰዎች ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች መሆኑ በስብሰባው ላይ የተወሳ ሲሆን፣ ይህም በደህንነቱ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ክፍተት መኖሩን ያሳያል ተብሎአል።
በአዲስ መልክ የተዋቀረው የጸጥታ ስራ ምንም ለውጥ አለማምጣቱ በስብሰባው ላይ ተደጋግሞ ተነስቷል። በክልሉ ያሉት አብዛኞቹ የደህንነት ሰራተኞች እና የፖሊስ አባላት የህወሃትን የበላይነት እየተቃወሙ እንደሆኑ የሚደረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.